የሀገር ውስጥ ባንኮችን ተፎካካሪነት ለማሳደግ

በወርሃ ሰኔ 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት እንዲሆን የሚያስችል ተስፋ ሰጪ ርምጃ ተጀምሯል። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራው የባንክ ሥራ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ በመንግሥት የተላለፈውን የፖሊሲ ውሳኔ ወደ ተግባር ለማሸጋገር ያለመ ነው። አዋጁን ተከትሎ የውጭ ሀገር ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ሥራ ሲጀምሩ ለዜጎች ጥሩ የባንክ አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ ፤ አዳዲስ አማራጮችንና ቴክሎጂዎችን እንድንጠቀም በር ይከፍታል። መንግሥት የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ “አገልግሎቶች በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር የበለጠ እንዲተሳሰር ለማድረግ ያስችላል “የሚል እምነት አለው።

ሃሳቡ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አዲስ የሚባል ቢሆነም ከኢትዮጵያ ያነሰ ምጣኔ ሀብት ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ከውጭ ባንኮች ጋር መሥራት ከጀምሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ኬንያ ፣ ሱዳን ፣ ጋና ፣ ናጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ የውጭ ባንኮችን በሀገር ውስጥ በማሳተፍ ጥሩ የሚባል ተሞክሮ ያላቸው ናቸው ። ይህን ተከትሎም የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መግባት በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይስማማሉ።

የውጭ ሀገር ባንኮቹ የሚመጡት ከበለፀገ ሀገር በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ይዘው ይገባሉ። የውጭ ባንኮቹ ደንበኛው በቤት ውስጥ ሆኖ ሁሉንም የባንክ አገልግሎቶች የሚያገኝበትን አሠራር ይዘው እንደሚመጡ ይጠበቃል። በባንኮች መካከል ፉክክር በማሳደግ ተጠቃሚው የተሻለ አማራጭ እንዲያገኝ ዕድል እንደሚፈጥር ይታመናል።

ባንኮቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ እንደማንኛውም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በውጭ ምንዛሪ ኢንቨስት የሚያደርጉ በመሆኑ እንዲሁም የሥራ ፈቃዳቸውንና ሌሎች ወጪዎቻቸውን በውጭ ምንዛሪ የሚከፍሉ በመሆኑ ያለውን የምንዛሪ ችግር ያቃልላል። ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ እነሱን ተከትለው የሚገቡ የውጭ ኢንቨስተሮች እና ተቋማት ይኖራሉ።

ይህ ኢኮኖሚው ላይ የውጭ ምንዛሪ በማምጣትና የሀገሪቷን ምርት በማሳደግ እንዲሁም የሥራ ዕድል በመፍጠር የራሱ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። በሌላ በኩል የውጭ ባንኮች መግባት ወደ ሥራ ለመሠማራት ለተዘጋጁ ወጣቶች የብድር አማራጭ በመሆን ለሥራ ፈጣሪዎች ጥሩ ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው።

ባንኮቹ የራሳቸውን ትልቅ ካፒታል ይዘው የሚመጡ በመሆኑ የነበሩ የአነስተኛ ብድር እጥረቶችን እና ያለዋስትና ብድር የማግኘት ችግሮችን እንደሚቀርፉም ይታመናል። የውጭ ባንኮቹ መግባት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማደግ ትልቅ ፋይዳ ቢኖረውም ፤ አዋጁን ተከትለው በሚወጡ መመሪያዎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ባለሙያዎቹ ይመክራሉ። መንግሥት የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረጉና የውጭ ባንኮቹ መግባት የሀገር ውስጥ ባንኮችን ባለአክሲዮኖችን ሕልውናን እስከመፈታተን ሊደርስ ይችላል።

የሀገራችን ባንኮች ለተወሰኑ አቅም ላላቸው ጥቂት ባለሀብቶች ከማበደር ባለፈ፤ ድሃውን እና በገጠር የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በአግባቡ እያገለገሉ ናቸው ለማለት አያስደፍርም። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ዋነኛ ምሰሶው ግብርናው በሆነበት ሁኔታ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ገበሬው ከባንኮች መበደር የሚችልበት አማራጭ አልነበረውም ።

ከብት የሚያረቡም፣ ቡና፣ የቅባት እህል ፣ አዝዕርትና አትክልት አምርተው የሚሸጡ ገበሬዎችን ባንኮቻችን ሊደግፉ የቻሉበት መንገድ ብዙም አይታይም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወጣ መመሪያ ገበሬው የሚያርስበትን መሬት አስይዞ ብድር ሊያገኝና ሊሠራ የሚችልበትን እየተመቻቸ ነው።

አሁንም ቢሆን በገጠር እየኖሩ ገንዘባቸውን በባንክ ማስቀመጥ እንዳለባቸው የማይገነዘቡ ዜጎች ሞልተዋል። ለገበሬው ግንዛቤ ሰጥተው ተበድረው በመስኖ ምርት ማምረት የሚችሉበትን ሁኔታ አልተፈጠረም። እነዚህ እና መሰል ውስንነቶች የሚስተዋሉባቸው የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር መፎካከር ይችላሉ ለማለት አያስደፍርም።

በጥቅሉ የሀገር ውስጥ የባንኮቻችን የወለድ ምጣኔ፣ ማስያዣ እና ሌሎችም የብድር አሠራሮች ለተገልጋዩ የተመቸ አይደለም። ከባለ አክሲዮኖች በተሰበሰበ ገንዘብ፣ ከቁጠባ፣ ከብድር ወለድ እንዲሁም ከአገልግሎት ክፍያ በሚያገኙት ገንዘብ የሚንቀሳቀሱት የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር በካፒታል የመፎካከር አቅም አይኖራቸውም።

የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጪ ባንኮች በውድድር ወቅት የሚጠብቃቸውን ስጋት ለመቋቋም መሰባሰብ ይጠበቅባቸዋል። ይህም በሰው ሃይል እና በገንዘብ አቅማቸውን በማቀናጀት የተሻለ ቁመና እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን ከውጪ ከሚገቡ ባንኮች ካፒታል መበደርና አብሮ በመሥራት ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል። አሁን ባለው ሁኔታ የሀገር ውስጥ ባንኮች በቴክኖሎጂ፣ በአሠራር ፣ በደንበኛ አያያዝ፣ በአገልግሎት እና በፋይናንስ አሳታፊነት ክፍተት አለባቸው።

በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ባንኮቻችን መጪውን የውድድር ጊዜ ለመቋቋም አሠራራቸውን ከወዲሁ መለወጥ ይጠበቅባቸዋል። ትላልቅ ባለሀብቶች ወይም ተበዳሪዎች ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ አዋጭ ለሆኑ ጥቃቅን ቢዝነሶች ብድሮችን በመስጠት የራሳቸውን ደንበኛ መፍጠር ላይ ሊሠሩ ይገባል። በተጨማሪም እንደ ግብርና እና አገልግሎት ዘርፍ ያሉ ግዙፍ የኢኮኖሚ ምንጮች ላይ በተለየ መንገድ ኢንቨስት በማድረግ የካፒታል አቅማቸውንም ማሳደግ ይኖርባቸዋል።

እዚህ ጋር ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያውን ተግባራዊ ማድረግ ተከትሎ ከባለድርሻ አካላት ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ ላይ ያነሱትን ምክረ ሃሳብ ማየት ተገቢ ይሆናል። እንደ እርሳቸው ሃሳብ የውጪ ሀገር ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሠሩ ለመፍቀድ እየተደረገ ያለው ዝግጅት የሀገር ውስጥ ባንኮችን የሚያነቃቃ እንጂ ስጋት የሚሆን አይደለም። ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት ኢትዮቴሌኮምን ነው። ሳፋሪ ኮም የቴሌኮም ዘርፉን ሲቀላቀል በሚያስገርም ፍጥነት ኢትዮቴሌኮምም የማይጠበቅና ፈጣን የሆነ እድገት አሳይቷል። ይህ ሊሆን የቻለው በገበያው ላይ የውድድር ስሜት መፈጠሩና አዳዲስ የአሠራር ሥርዓቶችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች በመደረጋቸው እንደሆነ በማብራሪያቸው ላይ ገልፀዋል።

ይህ ሃሳብ በባንኮች ላይ እንደሚሠራም ጠቁመው የመጣ ያለውን እድል እንዲጠቀሙበት አሳስበው ነበር። በተለይ በአንድነት አቅማቸውን ቢያሰባስቡና ቢዋሃዱም የሚመጣውን ውድድር ማሸነፍ እና ህልውናቸውን ማስጠበቅ እንደሚያስቸላቸው መክረው ነበር። ከዚህ መረዳት እምንችለው የፋይናንስ ዘርፉ ግልፅ በሆነ ፖሊሲ እና ሕግን የተከተለ ውድድር እንደሚመራ ነው። ሥርዓቱ ተዘርግቶ ተግባር ላይ ሲውል ደግሞ የሀገር ጥቅል ኢኮኖሚ፣ የባለሀብቶችና የነጋዴዎች እንዲሁም የእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ቀጥተኛ አዎንታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረው ነው። በመሆኑም የፋይናንስ ዘርፉ ለውጪ ኢንቨስተሮች ክፍት በመሆኑ ለኢትዮጵያ አያሌ በረከቶችን የዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል።

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You