ከድል በላይ የደመቀው ታሪክ ሲታወስ

ክስተቱ ከተፈጠረ ሁለት አስር ዓመታትን ቢያስቆጥርም ዛሬም ድረስ ደምን እንዳሞቀ ቀጥሏል። በአረንጓዴ መለያ የቀረቡት ሦስቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መም ላይ ያሳዩት የሃገርና የወገን ፍቅር በእርግጥም በስታዲየም የታደመውን የአትሌቲክስ ቤተሰብ ቆሞ እንዲያጨበጭብ አድርጓል። ‹‹ታሪክ ተሠራ›› በሚል ቃል በተደመደመው ሩጫ መዋደድ፣ መከባበር እና አብሮነት በግልጽ ታይተዋል። እአአ በ2004 የሆነው ይኸው ክስተት ዓመታትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ የሚወሳ ለወጣት አትሌቶችም ተምሳሌት ሲሆን የሚኖር ነው።

የኦሊምፒክ ጨዋታዎች መነሻ የሆነችው አቴንስ ባሰናዳችው በዚህ ኦሊምፒክ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ እና ስለሺ ስህን ኢትዮጵያን በ10ሺ ሜትር ሊወክሉ ተሰለፈዋል። ከሩጫው መጀመር አስቀድሞ የሕመም ስሜት በእግሩ ላይ የነበረበት ታላቁ አትሌት ኃይሌ በዓለም ሻምፒዮናው እንደተመዘገበው ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ከወርቅ እስከ ነሐስ ያለውን ሜዳሊያ ወደ ሃገሩ ለመመለስም ነበር በሩጫው የተካፈለው። ርቀቱ እየጨመረ ሲመጣም አምስት አትሌቶች ብቻቸውን ቢቀሩም እንደታሰበው ግን ሶስቱም ኢትዮጵያውያን ወደፊት መውጣት አልቻሉም።

የመጨረሻዎቹ የርቀቱ ዙሮች ላይ ቀድሞ በሚታወቅበት ሁኔታ መውጣት አቅቶት ከመሪዎቹ ወጣት አትሌቶች ቀነኒሳ እና ስለሺ የተነጠለውን ኃይሌን እንዲመጣ ጠበቁ። በሩጫቸው መካከል ዘወር እያሉ በተደጋጋሚ አሯሯጡን ሲቃኙ ቆዩ፤ የእሱ ሃሳብ ግን የሃገርና የሕዝብን አደራን ተቀብለዋልና ሁለቱ እንዲወጡ ነበር። በመጨረሻም ወሰኑ፤ ተከታትለውም ተወነጨፉ። በውድድሩ ማብቂያም ኢትዮጵያ የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በኃይሌ ዲፕሎማን አስመዘገበች። ፈጣኑ ቀነኒሳ የገባበት 27 ደቂቃ ከ05 ሰከንድ ከ10 ማይክሮ ሰከንድ የሆነ ሰዓትም የርቀቱ የኦሊምፒክ ክብረወሰን ሆኖ ተመዘገበ።

ልብ የሚነካውን የሃገርና የወገን ፍቅር የተመለከቱት በስታዲየሙ የሚገኙ ታዳሚዎችም በአድናቆት ቆመው ለማጨብጨብ ተገደዱ። የወጣቱ አትሌት ድንቅ አሯሯጥም ‹‹ቀነኒሳ አንበሳ›› ተብሎ እንዲዘፈንለት አደረገ። ይህ ሁኔታ ዓመታትን ቢያስቆጥርም እነሆ ዛሬም ድረስ ግን ከአትሌቲክስ ቤተሰቡ ሕሊና ሳይፋቅ እንደታተመ ይኖራል። የያኔው ወጣት አትሌት የመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ይህን መሰል ታሪክ የጻፈው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፤ ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ችሎታውን ለዓለም የገለጠበትም ነበር።

ኃይሌ የመም ሩጫዎች ማምሻው ላይ በነበረበት ወቅት የተገኘው የ21 ዓመቱ ቀነኒሳ በአቴንስ ምድር ካንጸባረቁ እጅግ ድንቅና ጀግና አትሌቶች ተርታም ሊሰለፍ ችሏል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከታዩ ምርጥ የዓለም አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ቀነኒሳ ከ20 ዓመታት በኋላም እነሆ ሃገሩን በዚህ የውድድር መድረክ ከመወከል ወደኋላ አላለም። በ3 የኦሊምፒክ ተሳትፎ ባስቆጠራቸው 4 የኦሊምፒክ ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያውያንን አስፈንጥዟል።

ቀነኒሳ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባጠለቀ የ5 ቀናት ልዩነት ሁለተኛው ውድድር ላይ ተሰለፈ። እንደ ታላላቆቹ አትሌቶች ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር እና ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በሁለቱም ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያስመዘግባል በሚል ይጠበቅ ነበር። ይሁንና በ5ሺ ሜትር ድንገት በተፈጠረ የቴክኒክ ስህተት የብር ሜዳሊያ ለማጥለቅ በቃ።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም

Recommended For You