በአጓጊ ፉክክር የተጠናቀቀው የሠራተኛው የበጋ ወራት ውድድር

በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበር ኮንፌዴሬሽን(ኢሠማኮ) አዘጋጅነት ከጥር ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የሠራተኞች የበጋ ወራት ውድድር ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ፍፃሜ አግኝተዋል። በአስር የስፖርት አይነቶች ፉክክሮችን ሲያስተናግድ በቆየው ውድድር አብዛኞቹ የስፖርት አይነቶች ቀደም ብለው አሸናፊዎቻቸውን አውቀዋል። ጠንካራ ፉክክር በሚታይበት እግር ካስ በሁለት ዲቪዚዮን የሚደረገው ፉክክር ግን እስከ ውድድሩ ማጠቃለያ እለት ድረስ አሸናፊው ያልተለየበት በጉጉትም ሲጠበቅ የነበረ ነው።

ዘጠኝ ክለቦች ሲፋለሙበት በቆዩት በአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር የተለያዩ ቡድኖች ተቀራራቢ ነጥብ መሰብሰባቸው የፉክክሩን መጨረሻ በጉጉት እንዲጠበቅ ያደረገው ምክንያት ነው። የውድድር ዓመቱን ዋንጫ ለማንሳት ተመሳሳይ ነጥብ ይዘው የመጨረሻውን ጨዋታ ሲጠብቁ የነበሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር በተመሳሳይ ሰዓት በሁለት ሜዳዎች ላይ ተፋልመዋል።

በ19 ነጥብና 13 ግብ ዋንጫውን ለማንሳት የተሻለ እድል የነበረው ንግድ ባንክ የመጨረሻውን ወሳኝ ጨዋታ ዮሐንስ ቢፍ ኢን ውሃን ማሸነፍ ብቻ በቂው ነበረ። ይሁን እንጂ ንግድ ባንክ በወሳኙ ጨዋታ 3ለ2 ተሸንፎ ዋንጫውን ለማንሳት በእጁ የነበረውን እድል በአግባቡ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በተመሳሳይ አንድ ጨዋታ እየቀረው በ16 ነጥብና 18 ግብ ሁለተኛ ላይ ተቀምጦ የነበረው የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች የንግድ ባንክን ነጥብ መጣል እየጠበቀ የመጨረሻውን ፍልሚያ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያደረገ ሲሆን 2ለ1 ማሸነፍ ችላል። ይህም ከንግድ ባንክ ጋር ነጥቡን እኩል 19 በማድረስ በግብ ክፍያ በልጦ በመጨረሻ ሰዓት የአጓጊውን ፉክክር ዋንጫ ለማንሳት አብቅቶታል።

እንደ አንደኛ ዲቪዚዮን ሁሉ የሁለተኛ ዲቪዚዮን የእግር ካስ ፉክክርም እስከ መጨረሻው አጓጊ ሆኖ ተጠናቋል። በዚህ ዲቪዚዮን የፍፃሜ ተፋላሚ የሆኑ ሁለት ክለቦች በግማሽ ፍፃሜ ጨዋታቸውን አሸንፈው ቀደም ሲል የተለዩ ነበሩ። ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ አዋሽ ወይን ፋብሪካን በግማሽ ፍፃሜው ፍልሚያ 3ለ1 በመርታት የዋንጫ ተፋላሚ መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኮካ ኮላ ሞኤንኮ ኩባንያ ጋር በመለያ ምት 10 ለ 9 አሸንፎ ወደ ዋንጫ ያለፈ ቡድን ነበር። በውድድሩ ፍፃሜ ዋንጫውን ለማንሳት አጓጊውን ጨዋታ ያደረጉት ቃሊቲ ብረታ ብረትና ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አስደናቂ ፉክክር በማድረግ በመጨረሻም ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ 3ለ2 አሸንፎ የዋንጫው ባለቤት ለመሆን በቅቷል።

በሠራተኞች ስፖርት የፍፃሜ መርሐግብር ላይ በአዝናኝነቱ በሚጠበቀው የገመድ ጉተታ ውድድርም በሁለቱም ፆታ ፍፃሜ ተደርጓል። በዚህም በወንዶች ኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ፋፋ ምግብን 2ለ0 ሲረታ፣ በሴቶች ደግሞ ብራና ማተሚያ በተመሳሳይ ፋፋ ምግብን 2ለ0 አሸንፎ የውድድር ዓመቱ ሻምፒዮን ሆነዋል።

ከጥር 19 ጀምሮ ጥሩ ፉክክር ሲደረግባቸው የቆዩ ሌሎች የስፖርት አይነቶች ቀደም ሲል አሸናፊዎቻቸው እንደታወቁ ይታወሳል። ጠንካራ ፉክክር በሚታይበት የቮሊቦል ውድድር በወንዶች አንደኛ ዲቪዚዮን ከስድስት ጨዋታዎች አራቱን ድል ማድረግ የቻለው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በአስራ ሦስት ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ በሁለተኛ ዲቪዚዮን የወንዶች ቮሊቦል ፋፋ ምግብ አክሲዮን ማኅበር ስድስቱንም ጨዋታ አሸንፎ በአስራ ስምንት ነጥብ ቀዳሚ የሆነ ቡድን ነው። በሴቶች ቮሊቦል ከአስር ጨዋታ በአንዱ ብቻ ሽንፈት የገጠመው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በሃያ ሰባት ነጥብ አንደኛ ሆኖ መጨረሱም ይታወቃል።

በአንደኛ ዲቪዚዮን ጠረጴዛ ቴኒስ ወንዶች ውድድር ኢትዮ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። በሁለተኛ ዲቪዚዮን የወንዶች ጠረጴዛ ቴኒስ ፉክክር በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች ስድስቱን በድል የተወጣው ፋፋ ምግብ አክሲዮን ማኅበር በአስራ አራት ነጥብ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል። በሴቶች ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ስምንቱንም ጨዋታ ማሸነፍ የቻለው አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት በአስራ ስድስት ነጥብ ቀዳሚውን ደረጃ በመያዝ አጠናቋል።

በወንዶች የዳርት ውድድር ከአስር ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት ያልገጠመው አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ በሃያ ነጥብ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጣል። የወንዶች ከረንቦላ ውድድር አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ከስድስት ጨዋታ ሦስቱን አሸንፎ በቀሪዎቹ ቢሸነፍም በዘጠኝ ነጥብ የግብ ክፍያ ሳይኖርበት ቀዳሚ ሆኖ አጠናቀቋል። በወንዶች የዳማ ውድድር በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች አራቱን ያሸነፈው የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ በአስራ ሁለት ነጥብ አንደኛ ሆኖ የጨረሰ ቡድን ነው።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You