የሰውነት ቅርጽን ለተሻለ አለባበስ

ሰዎች አለባበሳቸው ውበት እንዲኖረው ፣ በእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ምቾት እንዲሰማቸው ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የመረጡትን አለባበስ መከተላቸውና ምርጫቸው ትክክል ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆናቸው በሚያሳልፉት ቀን ላይ የራሱ አዎንታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ይታወቃል። ለእዚህም የልብስ ምርጫቸውንና እና የሰውነት ቅርጻቸውን በሚገባ ማወቅ እንዳለባቸው ይመከራል።

በፋሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ደግሞ አንድ ሰው በልብስ መሸጫ ሱቆች ውስጥ ያየውን ልብስ ከመግዛቱ በፊት የሰውነት ቅርጹን ማወቅ ይኖርበታል፤ ይህም የሚገዛውን በሚገባ እንዲያውቅና አለባበሱን የተሻለ ለማድረግ እንደሚጠቅም ይናገራሉ፡፡

በየጊዜው የተለያዩ የፋሽን ዲዛይን ልብሶች በገበያው ላይ ቢተዋወቁም፣ ልብሶቹ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ቢያገኙም እውቅናና ተቀባይነትን ስላገኙ ብቻ ግን ሁሉም ሰው ላይ ያምራሉ ማለት አይደለም።

የራሳቸውን የአለባበስ ስታይል ወይንም የሚከተሉትን የአለባበስ ፋሽን ከመምረጣቸው በፊት የሰውነት ቅርጻቸውን ማወቃቸው የሚጠቅመውም አለባበስ ሰዎች ራሳቸውን የሚገልጹበት አንዱ መንገድ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ ነው፡፡ የሰውነት ቅርጽ አይነትን ማወቅ ሰዎች የሚኖራቸውን በራስ መተማመን ከፍ እንደሚያደርግም ይነገራል፡፡

በዛሬው የፋሽን ገጻችን ሰዎች የሰውነት ቅርጻቸውን እንዴት ማወቅና ባላቸው ተክለሰውነት መሠረት አለባበሳቸውን እንዴት አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ ይችላሉ የሚለውን ለማሳየት የተለያዩ ድረ ገጾችን በመቃኘት ያጠናከርነውን ጽሁፍ ይዘን ቀርበናል፡፡

በተለመደው መንገድ አንዳንድ ሰዎች የሰዎችን ውበት ለማድነቅ ቀጭን የሚባለው የሰውነት ቅርጽ ላላቸው ሰዎች እውቅና ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ሰዎች የሚኖራቸው የሰውነት ቅርጽ ከወላጆቻቸው አልያም ከቤተሰቦቻቸው በዘር የወሰዱት ሊሆን ይችላል፤ አኗኗራቸውን ተከትሎ ክብደት ሲጨምሩ አልያም ሲቀንሱ የሚኖራቸው የሰውነት ቅርጽም እንዲሁ የሚቀያየር ሊሆን ይችላል ፡፡

የፋሽን ዘርፉ ባለሙያዎች የሰውነትን ቅርጽ የወንዶችና የሴቶች በማለት ከፍለው ይገልጸሉ፡፡ እነሱ እንደሚገልጹት የወንዶች የሰውነት ቅርጽ በሶስት፣ የሴቶች የሰውነት ቅርጽ ደግሞ በአራት ተከፍሎ ይታያል ፡፡

ስለሴቶች የሰውነት ቅርጽ ሲነሳ በተለምዶ በሴቶች ላይ የሚስተዋለው ስምንት ቁጥር የሚባለው የሰውነት ቅርጽ ይጠቀሳል፡፡ ይህን አይነቱ የሰውነት ቅርጽ አብዛኛዎቹ እንስቶች እንዲኖራቸው ይመኛሉ። ይህ የሰውነት ቅርጽ ያላት ሴት መገለጫዋ ቀጠን ያለ ወገብ ፣ እና የትከሻዋና ከወገብ በታች የሚኖራት የተመጣጠነ የሰውነት ቅርጽ ነው፡፡

ይህ የሰውነት ቅርጽ ያላቸው ሴቶች የትኛውንም አይነት አለባበስ ቢከተሉ እንደሚያምርባቸው ይገለጻል፡፡ ቀበቶ ቢጠቀሙ ፣ የሰውነት ቅርጻቸውን ተከትለው የተሠሩ ልብሶችን ቢያዘወትሩ ደግሞ የተሻለ እንደሚያምርባቸው የሚገልጹ ወገኖች አሉ። እነዚህ ሴቶች ቅርጽ የሌላቸው የልብስ አይነቶችን እንዲለብሱ አይመከርም ፡፡

ሌላኛው የሰውነት ቅርጽ አራት ማዕዘን አልያም ደግሞ ተመሳሳይ የሆነ የትከሻ እና የወገብ ቅርጽ ባላቸው ሰዎች ላይ የሚታየው ነው፡፡ ይህ የሰውነት ቅርጽ ያላቸው ሰዎች የወገብ ቅርጻቸው ከትከሻቸው ጋር ተመሳሳይ እና ያን ያህል ወፍራም የማይባሉ ናቸው፡፡ ሰፋ ያለ የአጥንት ቅርጽ ያላቸው ተደርገው ግን ይገለጻሉ፡፡

ይህን የመሰለ የሰውነት ቅርጽ ያላቸው ሰዎች የወገብ ቅርጻቸውን አጉልተው ሊያሳዩ የሚችሉ ልብሶችን እግራቸው አካባቢ ሰፊ የሆኑ የጅንስም ሆነ የጨርቅ ሱሪዎችን ቢለብሱ የተሻለ ተውበው ሊታዩ እንደሚችሉም በድረ ገጾቹ ሃሳባቸውን የሰጡ የፋሽን ባለሙያዎች ይገልጻሉ ፡፡

በተጨማሪም በሚመርጧቸው ልብሶች ውስጥ ተመጣጣኝ የሆነ የልብስ ስፋት ያላቸውን ልብሶች ማለትም ከላይ ሰፊ የሆነ የልብስ አይነት ጠበብ ካለ ሱሪ ጋር በአማራጭነት ሊለብሱ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ ፡፡ ይህን አይነት የሰውነት ቅርጽ ያላቸው ሰዎች እጅግ ሰፊ የሆነውን የሰውነት ቅርጻቸውን መግለጽ የማይችሉ የአለባበስ አይነቶችን እንዲለብሱ አይመከርም ፡፡

ሌላኛው የሰውነት ቅርጽ አይነት በፒራሚድ ቅርጽ የሚመሰለው ነው፡፡ ይህም ጠባብ ትከሻና ሰፊ የሚባለው የሆድ አካባቢ የሰውነት ቅርጽ ነው፡፡ ይህ አይነት ቅርጽ ያላቸው ሰዎች ከላይ ያላቸው የሰውነት ቅርጽ ጎልቶ እንዲወጣ የሚያደርግ አለባበስን መምረጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ሰፊ የሆኑ የልብስ አይነቶች እንዲሁም የትከሻቸውን ቅርጽ የሚያጎሉ አለባበሶች ለእነሱ የሚመረጡ ሲሆኑ፣ ጠበብ ያለ አለባበስን መምረጥ የለባቸውም፡፡

የዚህ ተቃራኒ የሆነው የሰውነት ቅርጽ የፒራሚድ ቅርጽ ግልባጭ የሚባለው አይነት ነው፡፡ ከላይ የሚኖራቸው የሰውነት ቅርጽ ሰፊ ፣ ጠባብ ወገብ እና ከወገብ በታች የሚኖራቸው ቅርጽ ቀጭን የሚባል አይነት የሰውነት ቅርጽ ያላቸው ሰዎች ይለዩበታል፡፡

በተለምዶ ሰዎች ቀጭን ፣ ወፍራም ፣ ረጅም

አልያም አጭር ሊባሉ ቢችሉም፣ ከወገብ በላይ እና ከወገባቸው በታች የሚኖራቸው የሰውነት ቅርጽ ግን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የሰውነት ቅርጽ ያላቸው ሰዎች ወጥ የሆኑ አልያም ከላይ እስከታች ሰፊ የሆኑ የጨርቅ ሱሪዎች፣ የጅንስ ሱሪ አማራጮችን እንዲሁም ተመሳሳይ ቀለም ያላቸውን ልብሶች ተመራጭ ቢያደርጉ የተሻለ አለባበስ ይኖራቸዋል፡፡

የመጨረሻው የሰውነት ቅርጽ አይነት በሰዎች እይታ ወፍራም የሚባለው መሆኑን ድረገጾቹ ይጠቁማሉ። እነዚህ ሰዎች ክብደት በሚጨምሩበት ወቅትም በወገባቸው አካባቢ ላይ ጎልቶ የሚታይ የክብደት መጨመር ሊያስተውሉ ይችላሉ፡፡

ይህ አይነት የሰውነት ቅርጽ ያላት እንስት በወገቧ ላይ ቀበቶ ባታደርግ ይመረጣል፤ ሰውነትን ያዝ የሚያደርጉ የቀሚስ አይነቶች እንዲሁም ፍጹም ሰፊ የሆኑ ልብሶችን ባታደርግም እንዲሁ ይመከራል ፤ በአንጻሩ ረዘም ያለ ጃኬት ፣ ከላይ የምትለብሳቸው ልብሶች ላይ በተለምዶው ቪ ቅርጽ ያላቸው ልብሶች ብትጠቀም ይመረጣል፡፡ እንስቶች የሰውነት ቅርጻቸውን በቀላሉ ለማወቅ የትከሻቸውን ፣ የደረታቸውን እና የወገብ ልኬታቸውን በመለየት ማወቅ ይችላሉ ፡፡

ሰዎች የሰውነት ቅርጻቸውን ተከትለው መልበሳቸው የራሳቸውን የአለባበስ መንገድ እና ምቾት የሚሰጣቸውን ልብስ ለመምረጥ ያስችላቸዋል። ነገር ግን ልብሶቻቸው የራሳቸውን ምቾትና ምርጫ ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ መሆናቸውን ነው መመልከት ያለባቸውም ፡፡

እነዚህ የአለባበስ መንገዶች በፋሽን ኢንዱስትሪ ላይ ሰዎች የሚኖራቸውን የአለባበስ መንገድ የተሻለ ለማድረግ እንደ አማራጭ የተቀመጡ እንጂ ሕግ ተደርገው የተቀመጡ እንዳይደሉም ለማስገንዘብ እንወዳለን ፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You