ስፖርትን በጥናትና ምርምር መምራት ፈጣንና ዘላቂ ለሆነ ውጤት

ዓለም በቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ግኝቶች ተደግፋ በምትሽከረከርበት በዚህ ዘመን ልማዳዊ አሠራሮችና አካሄዶች ኋላ ቀርነትን እያስከትሉ ዋጋ ማስከፈላቸው እውን ነው:: ይህ ሁኔታ በየትኛውም ዘርፍ ላይ የሚስተዋል ሲሆን፤ ስፖርትም ከወቅቱ ጋር መራመድ ካልቻለ ውጤታማነት የማይታሰብ ነው:: ሳንሳዊ የስፖርት ጥናትና ምርምር ውጤቶች ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትና ስኬትን ለመጎናጸፍ ቁልፍ መሣሪያ በመሆናቸውም ዘመናዊው ዓለም ይህንኑ መንገድ በመከተል ላይ ይገኛል::

በልማዳዊ የስፖርት ሥልጠና እንዲሁም በስፖርተኞች የግል ጥረት ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ስፖርትም በሳይንሳዊ አሠራር ተተክቶ ከጊዜው ጋር ራሱን ባለማሻሻሉ ከውጤታማነት እየራቀ መሆኑ እየታየ ነው:: በመሆኑም የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎችና የጥናትና ምርምር ውጤቶች በጥቂቱም ቢሆን መነቃቃት ላይ ናቸው:: በዚህ ረገድ ከሚሠሩ አካላት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲሆን፤ ታዳጊ ስፖርተኞችን በዘመናዊ ሥልጠና ወደ ብቁ ስፖርተኝነት ከማሸጋገር ባለፈ የስፖርት ጥናትና ምርምር ማከናወን ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከለ ይጠቀሳል::

በኢትዮጵያ በብቸኝበት በተደራጀ ሁኔታ አግልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውና በርካታ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎችን ያቀፈው አካዳሚው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባዔ ያዘጋጃል:: ባለፉት ዓመታት 207 የሚሆኑ የጥናት ውጤቶችን ያሠራጨ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በባለሙያና በቁሳቁስ (ቤተሙከራ) ይበልጥ ተደራጅቶ እየሠራ ይገኛል:: ትኩረቱንም ሀገራዊ የስፖርት ችግሮችን የሚፈታ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ማድረጉን በአካዳሚው የጥናትና ምርምር ማማከር ምክትል ዳይሬክተር አመንሲሳ ከበደ (ዶ/ር) ይናገራሉ:: ይኸውም በአካዳሚው ብቻ ሳይሆን የምርምር ውጤቱን ሊጠቀሙበት የሚችሉ ስፖርታዊ ተቋማትን በማካተት፤ ጥልቀት ያላቸውና መፍትሄዎችን ማመላከት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ የተመሠረቱ ናቸው::

ለአብነት ያህል ከሰሞኑ በተካሄደው የአካዳሚው 9ኛ የጥናትና ምርምር ጉባዔ ላይ ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል እና 5ሺ ሜትር ርቀት የሥልጠና ሞዴል ነው:: አካዳሚው በሠልጣኞቹ ላይ ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ የሆነበትን መንገድ ከአትሌቶች አመላመል እስከ ምዘና ያለውን ሂደት ያካተተ ሞዴል ይፋ አድርጓል:: ይኸውም በሀገር አቀፍ ደረጃ የአትሌቲክስ ስፖርትን በእጅጉ ሊጠቅምና ለስኬታማነትም ጉልህ ድርሻን ሊያበረክት እንደሚችል ታምኖበታል:: ሌላኛው በመድረኩ ላይ የቀረበው ለኢትዮጵያ ስፖርት በእጅጉ ስጋት የሆነው የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት ጉዳይን የሚመለከት ጥናት ሲሆን፤ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን የተሠራ ነው:: በሀገሪቷ ያለውን ተጠቃሚነት በግልጽ ከማመላከት ባለፈ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚጠቁም ጥልቅ የምርምር ውጤት በመሆኑ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልም ነው::

አካዳሚው በራሱ አቅምና ሌሎች ባለሙያዎች ከሚሠሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ባለፈ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሠሩ ጥናቶችን ማሰራጨት አንዱ እንደመሆኑ ሀገር አቀፍ የስፖርት ጆርናልን ሥራ ላይ ማዋሉ ይታወቃል:: ጆርናሉ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘና የአህጉር አቀፍ መሰል ተቋማት ጋር የሚሠራ በመሆኑም ምሁራኑ ጥናቶቻቸውን የሚያሳትሙበትን እድል ማመቻቸት ችሏል:: በጉባዔው ላይ ተሳታፊ ከሆኑ አካላት መካከል 9 የሚሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥናቶቻቸውን ማቅረባቸውም ተደራሽነቱን ከማስፋት አንጻር የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል የማይባል መሆኑንም ምክትል ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ::

ይሁንና በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥናታዊ ውጤቶችን ወደ ተግባር ከመቀየር አንጻር ሰፊ ክፍተት አለ:: በስፖርቱም ችግር ፈቺ ሊባሉ የሚችሉ ጥናቶችን መሬት ማድረስ አለመቻሉ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል:: ለክፍተቱ በምክንያትነት ጥናቶቹ በቀጥታ ተጠቃሚው ጋር አለመድረሳቸው እንዲሁም የመሠረተ ልማት ችግር መኖሩ ከጉባዔው ተሳታፊዎችም ጭምር አስተያየት ተሰጥቶበታል:: ምክትል ዳይሬክተሩም ለዚህ ከሚያነሷቸው ሃሳቦች መካከል አንዱ ጥናቶች ሲሠሩ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያላገናዘቡ እንዲሁም ሥራ ላይ በሚውሉበት ቋንቋና ሁኔታ ያልተዘጋጁ መሆናቸውን ነው:: በሌላ በኩል እንደዘርፍ ጥናቱ የሚያመጣው ለውጥ ስጋት የሚሆንባቸው አካላት መኖራቸው ቁርጠኛ አፈጻጸም አስፈላጊ ነው::

የስፖርት ኢንዱስትሪው ለምርምርና ቴክኖሎጂ በሩን መዝጋቱ ዋጋ የሚያስከፍልም ነው:: ክለቦች ለአንድ ስፖርተኛ ከፍተኛ ገንዘብ ከማውጣት ይልቅ ለቴክኖሎጂ፣ ለታዳጊዎች ልማት፣ … ትኩረት መስጠት ቢቻል ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ውጤት ሊመጣ እንደሚችልም ምክትል ዳይሬክተሩ ያስገነዝባሉ::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You