አብሮነት

ጠዋት አንዱ ቤት፣ ማታ ደግሞ ሌላኛው ቤት ከጎረቤት ጋር ቡና መጠራራት በኢትዮጵያውያን የተለመደ:: እንደ ባህልም ተደርጎ የሚወሰድ ነው ብሎ መናገርም:: ጎረቤቱ ብዙ ከሆነም ቡና መጠራራቱ ከሁለት ቤት ያልፋል:: በቡና መጠራራት ወንዶችም አብረው የሚሳተፉ ቢሆንም እናቶች ወይንም ሴቶች ግን ዋነኛ ተሳታፊዎች ናቸው::

የቡና ስነስርዓት፣ የቡና ቁርስ ስላለው በቤት ውስጥ ቁርስ የማይቀመስበት ጊዜ መኖሩ የተለመደ ነው:: አንዳንዶችም በቡና ጠጡ ላይ የሚነሳውን ጨዋታና ሳቅ እንደሚናፍቁ ይናገራሉ::

ከጎረቤት ጋር ቡና መጠራራቱ አብሮነት ያጠናክራል:: ማህበራዊ ትስስሩ ቡና ጠጡ ብሎ ጎረቤት ከሚላኩት ልጆች ይጀምራል:: የሚላኩት ልጆች የነማን እንደሆኑ በጎረቤትም ስለሚታወቁ ልጆቹ ክፉም ደግም ነገር እንኳን ቢያጋጥማቸው የእከሌ ልጅ ነው ወይንም ናት ብሎ ጎረቤቱ ይደርስላቸዋል:: ልጆች ሲላኩ የሚበሉት ነገር ስለሚሰጣቸውም ለመላክ ይሽቀዳደማሉ::

ቡና ጠጡ ብለው ጎረቤት እንዲጠሩ የሚላኩት ልጆችም የተለያየ ሰው ባህሪን ከልጅነታቸው ለማወቅ ዕድል ይሰጣቸዋል:: በዚህ መካከል ልጆች አብሮነትን፣ ማክበርን፣ መተሳሰብን እያዩ ያድጋሉ:: በዚህ መልኩ ከጎረቤት ጋር በሚፈጠር ግንኙነት አብሮነቱ ስለሚጠነክር ልጆች ከሥነምግባር ውጭ እንዳይሆኑ ድርሻው የጎረቤትም ጭምር ይሆናል::

መጥፎ ነገር አይቶ ልጆቹን አያልፋቸውም:: ከመጥፎ ሥነምግባራቸው እንዲመለሱም ጎረቤት ይገስፃል፤ ይቀጣል:: ልጆች በወላጆች ብቻ ሳይሆን በጎረቤትም ጭምር ነው የሚያድጉት:: ልጆቹም አድገው እራሳቸውን ሲችሉ የልጅነታቸውን ጊዜ በጥሩ ትውስታ ነው የሚያነሱት:: የጎረቤቶቻቸውን ውለታ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉም ይስተዋላል:: አንዳንዶችም የድሮውን ጉርብትና በማስታወስ ይጠይቋቸዋል:: በሚችሉት ሁሉ ለማገዝ ጥረት የሚያደርጉ ጥቂት አይደሉም::

እንዲህ ያሉ ማኅበራዊ ትስስሮች አሁን ላይ እንዴት ናቸው? ጭርሱ ነው የጠፋ ነው ባይባልም፤ ግን ደብዝዟል የሚለው ያስማማናል:: አሁን ላይ እንደ ሀገር የገጠመን አለመግባባት፣ ችግሮችንም ተቀራርቦ ለመፍታት ፍላጎት የማጣት ጉዳይ አብሮነትን የሚሸረሽሩ ነገሮች በመፈጠራቸው ምክንያት ነው::

በጉርብትና፣ በጋብቻ፣ በክርስትና፣ በአበልጅነት እየተሳሰርን አዳብረናቸው የነበሩ መልካም እሴቶች ቦታ አለማግኘታቸው፣ አለመግባባቱ፣ አንዱ ለሌላው አለማሰቡ፣ አለመከባበሩ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ ቃታ እስከመሳብ የመድረሱ ጉዳይ የማኅበራዊ ግንኙነት እየላላ መምጣትን ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል::

ጎረቤታሞች በአንድ ተሰባስበው ቡና ሲጠጡ በአጋጣሚው የሚያነሷቸው ሀሳቦችም ሆኑ ማኅበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት መንገድ እንደዋዛ የሚታይ እንዳልሆነ የነ ወይዘሮ ፋጤና ይመናሹ ግንኙነትም አንዱ ማሳያ ነው:: በሁዳዴ እና በረመዳን አጽዋማት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ቡና መጠራራቱ በቀጠለ ጊዜ ነበር በቡና ሰበብ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ይጋሩት የነበረው ሀሳብ፣ ሳቅና ጨዋታ እንደቀረባቸው ያስተዋሉት:: በግል ጉዳያቸው የገጠማቸውን ችግር እንኳን ተገናኝተው ሲወያዩበት ትልቅ የሆነ እፎይታን ነው የሚያገኙት:: ከጾም በኋላ እንደቀደመው ቡና እየተጠራሩ የቡና ዋጋቸውን ቀጥለዋል::

ወይዘሮ ፋጤና ይመናሹ ስለ እለት ተእለት ኑሮአቸው መጉደልና መሙላት ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳትንም እያነሱ ይጨዋወታሉ፤ ሀሳብ ይለዋወጣሉ:: ጎረቤታሞቹ በሀገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱትን ፖለቲካዊ ሁኔታዎችና ሌሎችንም እንቅስቃሴዎች ከመገናኛ ብዙሃን በመከታተል አንዳቻው ለሌላኛቸው ሀሳብ በማጋራት የሚያደርጉት ውይይት ጥሩ መረጃ ሰብሳቢዎች መሆናቸውን ያሳያል::

ቡና እየጠጡ ቢጫወቱም ቴሌቪዥን ወይንም ሬዲዮ ስለሚከፍቱ ጆሮአቸውን ጣል ያደርጋሉ:: አንድ ጆሮ የሚስብ ነገር ከገጠማቸው ጨዋታቸውን አቁመው መረጃውን ይሰማሉ:: የሰሙትንም ርዕስ አድርገው ይነጋገሩበታል:: እነ ወይዘሮ ፋጤንና ይመናሹን ለየት የሚያደርጋቸው ለመረጃ የሚሰጡት ትኩረት ነው::

ወይዘሮ ፋጤ ማልደው በመነሳታቸው የጠዋት ቡና ቀድመው ነበር ያፈሉት:: ወይዘሮ ይመናሹም ቡናው ቁርስ ስላለው ቁርስም ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ አላሉም:: ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ እንደተለመደው የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮችን አንስተው እያወጉ ነው:: ግን ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ሲጨዋወቱ የነበረው አሁን ላይ ‹‹ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!!›› በሚለው መሪ ቃል ላይ ነበር::

ሁለቱ ጎረቤታሞች በጋራ የተረዱት ነገር ቢኖር በተለያዩ አካባቢዎች ሰሞኑን የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር መድረክ የሁሉንም ዜጎች ሀሳብ በማሰባሰብ አንድ መፍትሄ ላይ ለመድረስ መሆኑን ነው:: በኢትዮጵያ በዚህ ወቅት እየታዩ ያሉ አለመግባበባቶች ይፈታል ተብሎ ተስፋ የጣለበት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በርካታ ሂደቶችን አልፎ አሁን አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር ውስጥ መግባቱን ተረድተዋል::

ወይዘሮ ፋጤ ይህን ርእሰ ጉዳይ ሲያነሱ ወይዘሮ ይመናሹ እጃቸውን ወደላይ በማድረግ ፈጣሪያቸውን ነበር የተማፀኑት:: ምክክሩ ውጤት እንዲያመጣ ነበር የተመኙት:: ኢትዮጵያን በትንሽ በትልቁ ወደ ግጭትና ወደ ጦርነት መግባታቸውና ይህም ለዓመታት መዝለቁ ምን ያህል ሀገርን ያስጨነቀ ጉዳይ እንደሆነም ሀሳብ ሰጡ::

ከልጅነት እስከ እውቀት መልካም ነገር አይተው መኖራቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ይመናሹ፤ ‹‹አንተ ዘርህ ምንድነው፣ ከየት መጣህ ሳንባባል የሰው ልጅ በመሆኑ ነው አብረን የኖርነው:: የነበረው አብሮነታችን ቀርቶ መከፋፈልን ምርጫችን ያደረግነው ለምንድነው›› በማለት በቁጭት ለጎረቤታቸው ሲናገሩ በአንድ አዳራሽ ውስጥ ብዙ ሰው ተሰብስቦ የሚናገሩ ነበር የሚመስሉት::

ሀገራዊ ለውጦች ሲኖሩ አለመረጋጋት፣ ለውጡን ላለመቀበል ማንገራገር የተለመደና ተፈጥሮአዊ ነገር አድርገው ቢቀበሉትም አሁን ላይ የሚስተዋለው ዘርን ማዕከል ያደረገ ነገር የእርስበርስ ግጭት፣ አልፎ ተርፎ ጦርነት ውስጥ እስከመግባት መድረሱ ጥያቄ ፈጥሮባቸዋል::

ወይዘሮ ይመናሹ ንግግራቸውን በመቀጠል እንዲህ ላለው ችግር ምክንያት ነው ያሉትንም ለጎረቤታቸው እንዲህ አጫወቷቸው፤ ‹‹አዎ ዛሬ ሰው እንደድሮ ቡና አብሮ መጠጣቱን እየቀነሰ ነው:: በበዓላት ጊዜም እየተጠራራ አብሮ መብላት፣ መጠጣትና ማሳለፉን ትቶታል:: ይህ ደግሞ ጉርብትናን እያስቀረ በመሆኑ ሰው ለጎረቤቱ ደንታ እንዳይሰጠው እያደረገው ነው›› አሉ::

በተለያየ መንገድ የሚደረገው ማኅበራዊ ትስስር ለአብሮነት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ነበር ያነሱት:: እርሳቸው ይህን ሲሉ ወይዘሮ ፋጤም አከሉበት::‹‹ ልክነሽ ዛሬ ለጎረቤቱ መልእክት የሚላክ ልጅ እንኳን እንደሌለ እያስተዋልን ነው:: በልጆቹም አይፈረድም:: ጎረቤት ሲላኩ፣ ጎረቤቱም ሲያዛቸው ነው በእድሜ የገፉትንም ሆነ ለታላላቆቻቸው መታዘዝና መከባበር ምን እንደሆነ የሚማሩት›› በማለት ሀሳባቸውን አጠናከሩ:: የሁለቱ እናቶች ወግ እንዲሁ ቡና ጠጡ ላይ የተነሳ ተራ ነገር ተደርጎ የሚወሰድ እንዳልሆነ ካነሱት ሀሳብ መረዳት ይቻላል::

ተራ ፀብ ቀርቶ ከባድ የተባለ ችግር በሰዎች መካከል ሲፈጠር እንኳን በአካባቢና በሀገር ሽማግሌዎች፣ ከፍ ካለም የኃይማኖት አባቶች ጣልቃ ገብተው ሰዎች ቁርሾአቸውን እንዲረሱ የሚደረግበትንም ጊዜ በእድሜያቸው ማየታቸውን ያነሱት ወይዘሮ ፋጤ ጉዳዩ በሀገር ሽማግሌ ወይንም በኃይማኖት አባት ሲያዝም ማኅበረሰቡ ትልቅ ቦታ በመስጠት ታዛዥ እንደሚሆንም ነው የገለጹት::

‹‹የአባት ገዳይ እንኳን ታርቆ ቂሙን ያነሳል›› በማለት ከደመኛው ጋር ቂሙን ባይረሳ እንኳን የአባቶችን ትእዛዝ አክብሮ የተባለውን ይፈጽማል እንጂ ለፀብ አይነሳሳም በማለት ነበር በጨዋታቸው ያነሱት:: እንዲህ ያለ መልካም የሆነ እሴት እያለ እዚህም እዚያም ብጥብጥ ተፈጥሮ አንዱ ወደሌላ አካባቢ ለመሄድ እስኪቸገር ድረስ ነገሩ ሥር መስደዱንም እግረመንገዳቸውን አነሱ::

መንግሥት መፍትሄ ያለውን ሀገራዊ ምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ማድረጉን ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ በእጅጉ ደግፈውታል:: ወይዘሮ ፋጤ እንደሚሉት ከሀገራዊ ለውጥ ጀምሮ በፊት ኢትዮጵያ ሰላም ርቋት ነው የቆየችው:: በጦርነትም አሸናፊና ተሸናፊ አልታየም:: ይልቁንም የሰው ሕይወት ነው የተቀጠፈው:: ሀብት ንብረት ነው የወደመው:: የሀገር ኢኮኖሚ ወደኋላ አሽቆለቆለ እንጂ እድገት አይደለም የተመዘገበው:: በሰዎች መካከልም ቁርሾና ቂም እንጂ መልካም የሆነ ነገር አልተዘራም:: አንዱ ሌላውን እንደጠላቱ እንጂ እንደወገኑ እንዲያየው አልሆነም::

ይሄ ክፉ የሆነ መንፈስ በመሆኑ ሊቆም ይገባል:: ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ሰዎች በችግሮቻቸው ዙሪያ መክረውና ዘክረው የጋራ የሆነ መፍትሄ ማምጣት ሲችሉ ነው:: መመካከር ከግለሰብ አልፎ ለሀገር ፍቱን መድሃኒት ነው::

ወይዘሮ ይመናሹም በሀሳባቸው ይስማማሉ:: እርሳቸውም የተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ ሳያገኙ መራዘመቻው በእነርሱ የእለት ተእለት ኑሮ ላይ እንኳን ያሳደረውን ጫና በቀላሉ በምሳሌነት አንስተዋል:: ኢትዮጵያ ካላት የሰው ኃይል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣት ዛሬ ስራ ይፈልጋል:: ከእራሱ አልፎ ቤሰተቡን መርዳት ይሻል:: ይህ የሚሆነው ደግሞ ሰላም ሲኖር ነው:: ወጣቱ ከጥንት ጀምሮ ቦጦርነት ውስጥ ማሳለፉ በእውቀቱና በጉልበቱ ለሀገር ሊያበርክት የሚችለውን መልካም ነገር እንዳያሳልፍ አድርጎታል::

ሀገራዊ ምክክሩ ይህን ዘመን የተሻገረ ችግር ለመቅረፍ እንደሚያስችልም ሁለቱም እምነት ጨብጠዋል:: በተለይም ወጣቱ ነገን በተሻለ እንዲመለከት እንደሚያስችለው ተስፋ ሰንቀዋል::

ሆኖም አንዳንድ ወገኖች ከራሳቸው ጥቅም በመነሳት የሀገራዊ ምክክሩ እንዳይሰምር ሲጣጣሩ መመልከታቸው ስጋት ፈጥሮባቸዋል:: ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ ለችግሩ ከቀወዲሁ መፍትሄ ማበጀት ካልተቻለ ሀገር ተረካቢ፣ ለሀገር እድገት የሚያስብና የሚቆረቆር ትውልድ እንዳይኖር የሚያደርግ ነገር እንዳይፈጠር ነው ስጋታቸውን የገለጹት::

ወይዘሮ ፋጤና ይመናሹ በውይታቸው ያነሱት የነበረው ሀሳብ ጠንከር ያለ ነበር:: እነዚህ እናቶች በሀገራዊ ምክክር መድረክ ላይ የመሳተፍ እድል ቢያገኙ ብዙ ሀሳብ እንዳላቸውም ከውይይታቸው መረዳት ይቻላል:: ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ ያነሱትን ሀሳብ በፀሎት ነበር የደመደሙት::ሀገራዊ ምክክሩ ውጤት እንዲያመጣ ትልቁ ምኞታቸው ነው::

ሰዎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰባስበው የሚያደርጉት ውይይት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ያምናሉ:: ሁሉም በየእምነቱ ፀሎት በማድረግ የተጀመረው በጎ ነገር እንዲሳካ ማሰብ እንዳለበት ነው የሚስማሙት:: እነርሱም መልካም ምኞታቸውን ተመኝተው ወደ የእለት ተግባራቸው ተመለሱ::

 ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You