“በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሐረርን ውሀ እጥረት አባብሶታል” አቶ ዲኒ ረመዳን  -የሐረሪ ክልል ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ

የሐረር ከተማ በከፍተኛ ቦታ ላይ መገኘቷ፤ በተራሮች እና ኮረብታዎች መታጀቧ ካሏት ቅርሶች ጋር ተደምሮ ውብትን አጎናጽፈዋታል። ይሁን እንጂ የሐረር ተራሮች ሐረር በፈለገችው ልክ ውሃ ጠጥታ እንዳታድር እክል ፈጥረውባታል። ተራሮቿ የፈጠሩባት እክል ሳያንስ የመብራት ኃይል እየፈጠረ ያለው ችግር የሐረርን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት አባብሶታል።

ተራሮች እና መብራት ኃይል የፈጠሩትን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ምን እያደረጋችሁ ነው? ስንል ከሐረሪ ክልል ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ዲኒ ረመዳን ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን:- በ2016 የበጀት ዓመት ምን አቅዳችሁ ምን ፈጸማችሁ? ምን አይነት ችግሮች አጋጠማችሁ?

አቶ ዲኒ፡– ከተማችን ከፍተኛ የሆነ የመጠጥ ውሃ ችግር ያለባት ከተማ ናት። ይህን ችግር ለመቅረፍ በረጅም፣ በመካከለኛ እና በአጭር ጊዜ የሚሰሩ ስራዎችን ለማከናወን አቅደን እየሰራን ነው። ከተማችን ውሃ የምታገኘው ከሁለት ቦታዎች ነው። አንደኛው ከሐረር ከተማ 72 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከድሬደዋ አካባቢ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ 26 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ኤረር ተብላ ከምትጠራው የክልሉ የገጠራማ አካባቢ ነው ።

የሐረር መልካምድራዊ አቀማመጥ ከፍተኛ ቦታ ላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በከተማዋ አቅራቢያ የከርሰ ምድርም ሆነ የገጸ ምድር የውሃ አማራጮችን ማግኘት አልተቻለም። በመሆኑም የክልሉ መንግስት እና ውሃ ቢሮ የሐረር ከተማን እና የአካባቢዋን ሕዝብ ውሃ ለማጠጣት በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ከድሬደዋ እና ከኤረር ጉድጓዶችን በመቆፈር ወደከተማችን ውሃ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል። ይሁን እንጂ አሁንም ከተማዋ ላይ በቂ የሆነ የውሃ ምርት የለም።

ይህን ችግር ለመቅረፍ ሲባል የአጭር ጊዜ እቅድ እና ጥናት በማካሄድ ከ72 ኪሎ ሜትር ላይ ውሃ በማውጣት የሐረርን ሕዝብ ለማጠጣት ጥረት እየተደረገ ነው። ውሃ የተገኘበት ቦታ በጣም ሩቅ በመሆኑ የተመረተውን ውሃ ወደ ሐረር መግፋት በራሱ ከፍተኛ የሆነ ጉልበት ይፈልጋል። ከ72 ኪሎ ሜትር ላይ የሚመጣው ውሃ በራሱ ከ1000 ሜትር ጥልቀት ካለው ጉድጓድ የተገኘ በመሆኑ ውሃውን ከምንጩ ወደ ላይ ለመግፋት እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ የኤሌክትሮ መካኒካል እቃዎች ማሟላት ግድ ነው። አሁን ላይ የውሃ ፕሮጀክቱ የአገልግሎት ዘመኑ ያለቀ በመሆኑ ምክንያት የኤሌክትሮ መካኒካል እቃዎች ከፍተኛ የሆነ የጥገና ስራዎች ያስፈልጋቸዋል። በዚህም ከአጭር ጊዜ እቅድ አንጻር ውሃ የማቅረብ ሂደት ሳይቆም አሁን እየሰጠ ያለውን አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረጉን ስራ እያከናወን ነው።

የሐረርን ከተማ የውሃ ችግር ለመቅረፍ በመካከለኛ ጊዜ ከሚሰሩ ስራዎች አንጻር 2015 ዓ.ም አካባቢ የጀመርነው ፕሮጀክት አለ። በዚህም በሁለቱም ሳይቶች ላይ ተጨማሪ ውሃ የማምረት አቅም እንዲኖረን የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወን ነው። ከዚህ አኳያ ድሬደዋ ላይ ተጨማሪ ሁለት ጉድጓዶችን ወደ ስራ ማስገባቱን የሲቪል እና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች የተጠናቀቁ ሲሆን የኤሌክትሪክ ኃይል የማቀናጀት ስራዎችንም ሰርተን ጨርሰናል። አሁን የሚጠበቅብን ወደ ስራ መግባት ነው። በተመሳሰይ ኤረር ላይም እንደዚያው ተጨማሪ ጉድጓችን ቆፍረን ወደ ስራ የማስገባቱን የሲቪል እና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች የተጠናቀቁ ሲሆን የኤሌክትሪክ ኃይል የማቀናጀት ስራዎችንም ሰርተን ጨርሰናል።

አሁን ያለን ውሃ ምርት ካለው ከአጠቃላይ የውሃ ፍላጎታችን አንጻር 20 በመቶውን ብቻ ነው እያሟላን ያለነው። ያለንን ውሃ በፍትሃዊነት ለማዳረስ ማኅበረሰባችን የ15 ቀን ወረፋ ይጠብቃል። በመካከለኛ እቅድ በተሰሩ ስራዎች ይህን ፍለጎታችንን እስከ 50 በመቶ ለማድረስ አቅደን እየሰራን ነው። በመካለኛ ጊዜ ለመስራት የተቃደው ፕሮጀክት 2016 ዓ.ም ግንቦት መጨረሻ ሰኔ መጀመሪያ ላይ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል።

በረጅም ጊዜ የተያዘው እቅድ ደግሞ ለቀጣይ 50 እና 60 ዓመታት የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት የሚፈታ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሁለት ሳይቶች ላይ ጥናት ተደርጎ ተጠናቋል። የዲዛይን ስራውም እንዲሁ ተጠናቋል። ወደፊት ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ስራ ስንጀምር የሐረር ከተማን የንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት መቅረፍ ያስችለናል።

አዲስ ዘመን ፡- ከ72 ኪሎ ሜትር ውሃ የሚያጓጉዙ እና ከ1000 ሜትር ጉድጓድ ውሃ ወደላይ ማውጣት የሚያስችሉ ማሽነሪዎች እና የሌሎች ወጭዎችን ገንዘብ እንዴት እና በማን ይሸፈናል? የስራው ክብደት እንዴት ይገለጻል?

አቶ ዲኒ፡– በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች የሐረርን ያህል የተወሳሰበ የኤሌክትሮ መካኒካል እቃዎች ያለበት የውሃ አገልግሎቶች ሰጪ ቢሮዎች አሉ ብየ አላስብም። አንድ ሺህ ሜትር ወደላይ ውሃ ስትገፋ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታውም በጣም ከፍተኛ ነው። ከአንድ ሺህ ሜትር ጉድጓድ ውሃው ወደ ላይ የሚወጣው በአራት ቅብብሎሽ ነው። ይህም በገንዘብ እና በጉልበት ሲሰላ በጣም ውድ ነው። ነገር ግን ወደ ሐረር ከተማ በቂ ውሃ እየገባ ባለመሆኑ ምክንያት በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ጫና እንዳይደርስ በማሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ክፍያው ሙሉ በሙሉ የሚሸፍነው በክልላችን መንግስት ነው።

በተጨማሪም ከውሃ ጋር ተያይዞ የሚወጣ ማንኛውም ወጭ የሚሸፈነው እና የሚደጎመው በክልላችን መንግስት ነው። ለምሳሌ እንደክልል አንድ ሜትሪክ ኪውቢክ ውሃ ከድሬደዋ ለማምጣት ከ104 ብር በላይ ይፈጃል። ነገር ግን የክልሉ መንግስት ከ104 ብር በላይ ወጭ ያደረገበትን አንድ ሜትሪክ ኪውቢክ ውሃ በ15 ብር ብቻ ለነዋሪዎች ይሸጣል። ቀሪውን ገንዘብ የሚደጉመው የክልሉ መንግስት ነው።

ከዚህ ውጭ የውሃ አገልግሎቱን የተሳለጠ ለማድረግ ዘመናዊ እና ትልልቅ ኤሌክትሮ መካኒካል የሚባሉ ማሽኖችን፣ ፓምፖችን እና ሞተሮችን ማሟላት ግድ ነው። አሁን የምንጠቀምባቸው ማሽነሪዎች ደግሞ ዲዛይን ጊዜያቸው ያለቀ በመሆኑ የግድ መቀየር አለባቸው። እሱንም እየቀየርን ነው። ይህ ሁሉ ወጭ የሚሸፈነው በክልላችን መንግስት ነው።

አሁን ላይ የውሃ አገልግሎት እየሰጠን ያለነው ለከተማችን ብቻ ሳይሆን ከድሬደዋ ሐረር መስመር ለሚገኙ አራት ከተሞች ጭምር ነው። የሐረር ከተማን ውሃ የምናጠጣው ደንገጎ፣ አዲሌ፣ ሀሮማያ እና አወዳይ ከተሞች ውሃ ካገኙ በኋላ ነው።

በእነዚህ ከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ በመምጣቱ ምክንያት የከተሞቹ የውሃ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። ይህ ደግሞ ወደ ሐረር የሚገባውን ውሃ በእጅጉ ይቀንሰዋል። በዚህም ከፍተኛ የገንዘብ እና የጉልበት ወጭ አድርጋ ፕሮጀክቶችን ያስገነባቸውን ሐረር በእጅጉ እየጎዳት ይገኛል። ከተሞች የሚወስዱትን ውሃ ለመተካት ስንል በከፍተኛ ወጭ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እየሰራን ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ ሶስት ጉድጓችን ወደ ስራ እያስገባን ነው። ስለሆነ የውሃ ምርት ላይ ብዙ ችግር የለብንም። ነገር ግን የተመረተውን የውሃ ምርት ለማሕበረሰባችን ማድረስ እንዳንችል የኤሌክትሪክ መቆራረጡ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ችግር እየፈጠረበን ነው። በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሐረርን ውሀ እጥረት አባብሶታል። መብራት ከሌለ ንጹህ ውሃ አይኖርም። አንድ ሺ ሜትር ወደ ላይ ገፍትህ የወሰድከው ውሃ መብራት በጠፋ ጊዜ ወደኋላ ይመለሳል። ይህ ደግሞ በርካታ ችግሮች ያመጣል። አንደኛ የኃይል ብክነት ነው። ሁለተኛ ውሃው ሲመለስ በውድ ዋጋ የተገዙ ማሽነሪዎችን ለብልሽት ይዳርጋል። በመሆኑም የመብራት መቆራረጡ በምንፈልገው ልክ ውሃ አምርተን ከተማ ውስጥ ማስገባት እንዳንችል ትልቅ እክል ፈጥሮብናል።

ይህ ችግር ዛሬ ብቻ የተከሰተ ሳይሆን ባለፈውም ዓመትም በተደጋጋሚ ሲከሰት የነበረ ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ ለ104 ቀናት መብራት አልነበረም። ይህም በ2015 የበጀት ዓመት 104 ቀናት ውሃ ማምረት እንዳልቻልን አድርጎናል። ይህም ከተማዋ ውስጥ ያለውን የውሃ ችግር በከፍተኛ ደረጃ አባብሷል።

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በማሰብ የድሬደዋ ዲስትሪክ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን ለውሃ ስራው ብቻ የሚሆን መስመር እንዲዘረጉልን ጠይቀን ነበር። ጥያቄ ስናቀርብ ፋብሪካ እንዳለው ማንኛውም ሰው ገንዘብ እንክፈል እና የኃይል መስመር ዘርጉልን ብለን ነበር። ጥያቄውን ስናቀርብ ከእኛ የሚጠበቅብን ሁሉ አሟልተን ነበር። ነገር ግን የዲስትሪክቱ ኃላፊ ጥያቄያችንን ለመመለስ ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም።

በመሆኑም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ሁሉ ችግሩ እንዲቀረፍ ቢጠይቁም እስከዛሬ ድረስ በድሬዳዋው ዲስትሪክት ኃላፊ ስራ ማጓተት ምክንያት ችግሩ ባለበት እንዳለ ነው። በመሆኑም አሁንም የሐረር ከተማ ለከፍተኛ ውሃ ችግር ተጋልጣ ትገኛለች።

አዲስ ዘመን፡- አሁን የተጠናቀቀው ፕሮጀክት ከ50 በላይ የሚሆነውን የሕዝብ ፍላጎት ማሟላት እንደሚችል ይገለጻል። ለዚህ ፕሮጀክት የወጣው ወጭ ምን ያህል ነው?

አቶ ዲኒ፡– የሐረርን የውሃ ችግር ለመቅረፍ በአጭር እና በመካከለኛ ጊዜ የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ስንሰራ ቆይተናል። በመካከለኛ ጊዜ ሁለት ፕሮጀክቶች በእቅድ ተይዘው ነበር። አንደኛው የኤረር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሲሆን ሌላኛ ደግሞ ድሬደዋ ነው። ኤረር ላይ ለተከናወነው ፕሮጀክት ተጨማሪ ጉድጓዶችን ወደ

ስራ ለማስገባት ተጨማሪ ኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች ተከናውነዋል። ለዚህም 224 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበታል። የድሬደዋው ድግሞ ተጨማሪ ሁለት ጉድጓችን ወደስራ የማስገባት እና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች ተከናውነዋል። በዚህም 100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበታል። ጠቅለል ባለ መልኩ በመካከለኛ ጊዜ ታቅደው ለተከናወኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በዘንድሮው ዓመት ብቻ ከሶስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ አድርገናል።

አዲስ ዘመን፡- በውሃ ፕሮጀክቶች ላይ ሕዝብ ተሳታፊ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ምን አደረጋችሁ?

አቶ ዲኒ ፡- ከተማችን ላይ ያለው የውሃ ፍላጎት እና አቅርቦት በጣም ያልተጣጣመ በመሆኑ ምክንያት በተቻለ መልኩ ሕብረተሰቡ በራሱ በየአካባቢው ላይ በሚችለው የራሱን ጉድጓድ መቆፈር ይኖርበታል። ከዚህ አንጻር እንደክልለ ሕብረተሰቡን በማሳተፋ በርካታ ስራዎችን አከናውነናል። ማህበረሰቡ የጉድጓድ ቁፋሮ በሚያከናውንበት ወቅት እኛ እንደ ቢሮ የቴክኒክ እና የማቴሪያል ድጋፍ እንዳርጋለን። ይህ ደግሞ የሐረርን የውሃ ችግር ከመቅረፋ አንጻር ትልቅ አስተዋጾ ይኖረዋል።

ወደከተማችን ውሃ የሚመጣው በ15 ቀን አንድ ጊዜ ነው። አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ እስከ አንድ ወር የሚቆይበት ወቅት አለ። ብዙ ጊዜ ውሃ መቼ ይመጣል? የሚለውን የሚወስነው የኤሌክትሪክ መቆራረጡ ነው። ይህ በሚሆንበት ሰዓት ጉድጓድ ቆፍረው ውሃ ከሚጠቀሙ ሰዎች ማሕበረሰቡ ውሃ እዲያገኝ የማድረጉን ስራ ለመስራት ሕብረተሰቡ በራሱ ለማገዝ ጉድጓድ በየዓመቱ ፕሮጀክቶችን እየቀረጽን ድጋፍ የማድረጉን ስራ እንቀጥልበታለን።

አሁን ላይ በግል ከሚቆፈሩ ጉድጓዶች በተጨማሪም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ተግባራትን አከናውነናል። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የሐረር ሕዝብ ውሃ የሚያገኘው በ15 ቀን አንድ ጊዜ ነው። አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ እስከ አንድ ወር የሚቆይበት ወቅት በመሆኑም አቅም ያለው የማሕበረሰብ ክፍል ውሃው በታንከር ሰብስቦ በመያዝ ይጠቀማል። በአንጻሩ አቅም የሌለው የማሕበረሰባችን ክፍል ደግሞ ለችግር ሲጋለጥ ይስተዋላል። ይህን ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር አቅም ደካማ ለሆኑ የክልልላችን ነዋሪዎች ውሃ መያዝ የሚያስችሉ “ሮቶዎች” እና በርሜሎችን ድጋፍ እያደረገ ነው። ባለፈውም ዓመት በዚህ ላይ በርካታ ስራዎችን ሰርተናል። ይህ ጥሩ ተሞክሮ ነው። በሚቀጥለው ዓመት ይህን አማራጭ አጠናክረን የምንሰራው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- የውሃ ጉድጓችን ከመቆፈር ባለ ወንዞችን እና ምንጮችን ገድቦ ከመጠቀም አንጻር ምን የታሰበ ነገር አለ?

አቶ ዲኒ፡- እንደክልል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን በየዓመቱ እናከናውናለን። ይህ የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ በተለይ እንደ ሐረሪ ክልል ከፍተኛ የሆኑ በጎ ተጽኖዎችን እያስገኘ ነው። ይህ የአካበቢ ጥበቃ ስራ በገጠርም ሆነ በከተማ የውሃ ጉድጓድ ለሚቆፍሩ ሰዎች ከሕልውናቸው ጋር የተገናኘ ነው ። በመሆኑም የአካባቢ ጥበቃ ስራውን ከሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን አጠናክረን እንቀጥላለን።

እነዚህ ስራዎች በተሰሩባቸው አካባቢዎች በተጨባጭ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ መጥቷል። በዚህም ከፍተኛ የሆነ የጉድጓድ ወሃ ተገኝቷል። የበርካታ ሰዎችን የውሀ ችግር መቅረፍ ተችሏል።

ወንዞችን እና ምንጮችን እንደ አማራጭ ከመጠቀም አንጸር ክልሉ በረጅም ጊዜ ለማከናወን በእቅድ ከያዛቸው ፕሮጀክቶች አንደኛው ነው። ከዚህ አኳያ በአካባቢያችን ኤረር የሚባልን ወንዝ ለመገደብ ጥናቶች እና የዲዛይን ስራዎች ተጠናቀዋል። አሁን ስራው በይፋ ባለመጀመሩ ምክንያት ይህ ነው ብሎ መናገር አይቻለም። ነገር ግን ፕሮጀክቱ በዘላቂነት ከተማችንን ለሚቀጥሉት 50 እና 60 ዓመታት የመጠጥ ውሃ ችግር የሚቀርፍ ነው። ይህ ስራ ተጀምሮ ሲጠናቀቅ አሁን የሚነሳውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ይፈታል። ክልሉ ከገጸ ምድር የሚያገኘውን የንጹህ መጠጥ ውሃ የሚጨምር ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- የውሃ እጥረቱ በከተማዋ ውበት፣ ቱሪዝም እና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች የሚያሳድረውን ጫና እንዴት ይግልጹታል?

አቶ ዲኒ፡– የውሃ መኖር እና አለመኖር በሁሉም መስሪያ ቤቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽኖ ቀላል የሚባል አይደለም። ውሃ በማይኖርበት ጊዜ በየትኛውም ኢንዱስትሪ ላይ ጉዳት ይደርሳል። በተለይም ሰርቪስ ሴክተሩ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ያድርሳል። በቱሪዝሙ፣ በጤና እና በሌሎች ላይ በተመሳሳይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል።

አሁን ላይ በከተማችን ውስጥ በቂ የውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ምክንያት ከተማችን ማደግ ባለባት ደረጃ አላደገችም። ለከተማችን አለማደግ አንዱ ምክንያት ሆኖ ሊጠቀስ የሚችለው የውሀ እጥረት ነው።

ይህን ችግር በመቅረፍ ከተማችንን እንደ ድሮው በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ከተማ ለማድረግ እየሰራን ነው። አሁን በተለይም በቱሪዝም ሴክተሩ የተጀመረውን መነቃቃት በታሰበው ልክ ለማስቀጠል በርካታ ስራዎችን እያከናወን ነው።

አዲስ ዘመን፡- በውሃ ውስጥ የሚገኙ ማዕድናት መጠን መብዛት ለውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች ፈተና ነው። ከዚህ አንጻር የሐረሪ ክልል ምን ገጠመው?

አቶ ዲኒ፡– ከድሬደዋ የምናመጣው ውሃ የካልሸም ይዘቱ ከፍተኛ ነው። ከኤረር የሚመጣው ደግሞ ለመጠጥ ለማዋል የሚከለክል ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ የብረት እና ማንጋናይዝ ማዕድን ይዘቱ ከፍ ያለ ነው። እንደክልል እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ ስራዎችን አጠናቀናል። ይህም ማዕድናት በማሽኖቻችን ላይ ሲያደርሱት የነበረውን ጉዳት ይቀንሰዋል። ነገር ግን እንደሌሎች አካባቢዎች ከፍ ያለ በጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችሉ የማዕድናት ብዛት የለም።

አዲስ ዘመን፡- ከውሃ እና ማዕድን ሚኒስቴር፣ ከክልሉ መንግስት እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ እና ተናቦ ከመስራት አኳያ ምን እየሰራችሁ ነው?

አቶ ዲኒ፡- የውሃ ችግር በአንድ መስሪያ ቤት ብቻ የሚፈታ አይደለም። የበርካታ መስሪያ ቤቶችን ትብብር እና መደጋገፍ የሚጠይቅ ነው። ለምሳሌ ለሐረር ከተማ ውሃ የምናመጣው ከድሬደዋ ነው። በድሬደዋ እና በሐረር ከተማ መካከል የኦሮሚያ ክልል አለ። እንደ ኢትዮጵያ ሶስት ክልሎችን አቋርጦ የመጠጥ ውሃ መውሰድ ብዙ አልተለመደም ። ይህም ሐረር ላይ ለሚመጣው ውሃ በርካታ አካላት ተሳታፊ እና ተባባሪ መሆናቸውን ያሳይል።

የሐረርን የውሀ ችግር በሚደረጉ የተለያዩ ክንውኖች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥናቶችን በማካሄድ እገዛ እያደረገልን ነው። ኤረር ላይ ሊሰራ የታቀደውን ደግሞ የቆላማ አካባቢ እና መስኖ ሚኒስቴር ነው። በነገራችን ላይ የሐረርን የውሃ ችግር የማያውቅ በየደረጃው የሚገኝ የመንግስት አካል የለም። የክልሉ መንግስት ደግሞ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራበት ነው። ከዚህ አንጻር ከበርካታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ቢሮዎች ጋር በትብብር እየሰራን ነው። ወደፊትም አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል።

አዲስ ዘመን ፡- ሐረር ቀደምት እና ባለታሪክ ከተማ ሆና ሳለ ይህን ያህል ዘመን የመጠጥ ውሃ ችግሯ ሳይፈታ እንዲቆይ ያደረገው አብይ ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ዲኒ፡– እንደሚታወቀው የሐረር ከተማ በጣም ትልቀ ታሪክ ያላት ታሪካዊት ከተማ ናት። ከእንጦጦ ቀጥሎ የቧንቧ አገልግሎት የነበራት ከተማ ናት። የሐረር አቀማመጥ ከፍ ያለ ቦታ ላይ በመሆኗ በቂ የሆነ የገጸ ምድርም ሆነ የከርሰ ምድር ውሃ የላትም። ይሁን እንጂ ይህን ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን የውሀ እጥረት ለመቅረፍ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ለምሳሌ የድሬደዋው ፕሮጀክት የ10 ዓመት የአገልግሎት ጊዜውን ጨርሷል። ይህ ፕሮጀክቱ ከማለቁ በፊት ሌሎች ጥናቶች ተጠንተው ሌሎች ስራዎችን መስራት ነበረብን። ይህን አለማድረጋችን አንዱ የራሳችን ክፍተት አድርገን መውሰድ አለብን።

አሁን ለአጋጠመን የውሀ እጥረት አንዱ ምክንያት ዝግጅት አለማድረጋችን ነው ። ይህ ሲባል አመራሩ ከፍተኛ ጥረቶች አላደረገም ለማለት አይደለም። ለምሳሌ በድሬደዋ 14 ጉድጓዶችን ቆፍረን ስራ በጀመሩ በ11 ወራት የደረቁ አሉ። በመሆኑም ሌላ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ተገደናል። ይህ በተቋሙ አቅም ሙሉ በሙሉ የተሰራ ነበር ።

በነገራችን ላይ ድሬደዋ አካባቢ የምናስቆፍራቸው ጉድጓዶች በጣም ጥልቅ ናቸው። በትንሹ እስከ 500 ሜትር ውሃ እንቆፍራለን። የድሬደዋውን የውሃ ፕሮጀክት ለመቆጣጠር ከ130 በላይ ሰራተኛ አለን ። ይህም የክልሉ መንግስት በተቻለ መልኩ የሐረርን ሕዝብ ውሃ ለማጠጣት ማድረግ ያለበትን አማራጮች ሁሉ እያደረገ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።

ከአመራሩ በተጨማሪ የሐረር ከተማ ነዋሪዎችን ማመስገን እፈልጋለሁ። የሐረር ከተማ ነዋሪዎች እንደማንኛውም የከተማ ሕዝብ በቂ ውሃ አግኝቶ መጠጣት እና ንጽህናውን መጠበቅ ይፈልጋል። ነገር ግን በፈለገው ልክ ሳይቀርብለት በከፍተኛ የውሀ ችግር ውስጥ ቢገኝም ላሳየን ሆደ ሰፊነት እና ትዕግስት እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ሐረማያ አሁን ላይ ውሃ እየያዘ ነው። በሚቀጥሉት ዓመታት ከሀይቁ ውሃ ለመጠቀም የታያዘ እቅድ አለ?

አቶ ዲኒ፡– የሐረማያ ሐይቅ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሀይቅነት የተመለሰው አሁን ነው። አሁን ላይ የሀይቁን ውሃ መጠቀም ሳይሆን የሃይቁ ኢኮሎጂ እንዲጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል።

በእርግጥ ከ30 ዓመት በፊት የሐረር፣ የሀሮማያ እና የአወዳይ ከተሞች ውሃ ያገኙ የነበረው ከሃይቁ ነበር። ሐይቁ ከደረቀ ወዲህ ግን አማራጭ መፈለግ ስለነበረብን ወደ ድሬዳዋ እና የኤረር ፕሮጀክቶችን ገንብተናል። ነገር ግን አሁን ተመልሰን የውሃ አገልግሎት ከሃይቁ ለማግኘት እቅድ የለንም። ሀይቁ ኢኮሎጂውን ጠብቆ እንዲሄድ ለማድረግ በሚሰሩ ስራዎች እኛም የምንችለውን እናግዛለን።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

አቶ ዲኒ ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You