“ባለሥልጣኑ – በዓለም አቀፍ ደረጃ ድርሻውን መወጣት የሚያስችለው አደረጃጀት ቢፈጠርለት ጥሩ ነው”- አቶ አስራት መኩሪያ የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል የቡና ሻይ ቢሮ ኃላፊ፤

የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል ገበያ ተኮር በሆኑ ምርቶችን በማምረት ይታወቃል:: እነዚህ ምርቶች ደግሞ ለሀገራችን ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኙ፣ ለወጪ ንግዱም ከፍ ያለ አበርክቶ ያላቸው ናቸው:: በዚህም እንደ ቡናና ሻይ ያሉ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ምርቶች በምርት፣ በግብይት ሥርዓቱም የተሻለ ነገርን ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራባቸው ይገኛል::

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶች የቅሬታ ምንጭ እየሆኑ፤ የግብይት ሥርዓቱንም እየፈተኑ ይገኛል:: በዚህ ረገድ በተለይም በቡና ግብይት ሥርዓቱ ላይ በተፈጠረ አሰራር አምራቾች እና ነጋዴዎች ከፍተኛ ችግር እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ:: ይሄ ችግር ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ሲሆን፤ እኛም ለዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል የቡና ሻይ ቢሮ ኃላፊ አቶ አስራት መኩሪያን ጠይቀን ያገኘነውን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል:: መልካም ንባብ::

 አዲስ ዘመን፡- ቢሯችሁ የተሰጠውን ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ በዘርፉ ክልሉ ያለውን አቅም ምን ያህል አውቆ ነው ወደሥራ የገባው?

አቶ አስራት፡– የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ሰብሎችን፤ በተለይም ቡና እና በቅመማ ቅመም እንዲሁም የሻይ ቅጠልን የመሰሉ የግብርና ምርቶችን በማምረት ይታወቃል::

የቡና ምርትን በተመለከት ክልሉ በሽፋንም ሆነ በአቅርቦት ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ ከ560 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ማሳ መሸፈን የቻለ ነው:: ከዚህ ባሻገር በክልሉ ከ513 ሺህ በላይ ቡና አምራች አርሶአደሮች ያሉ ሲሆን፤ ቡናን በአራት አይነት የአመራረት ዘዴዎች (ከጫካ፣ ከፊል ጫካ፣ በዘመናዊ የተከላና እና ከጓሮ) ያመርታሉ::

ከቅመማ ቅመም ምርት ጋር በተያያዘ በክልሉ ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ ዓመታዊ እና ‹‹ሰንባች›› ቅመማ ቅመሞች ይለማሉ:: በተጨማሪም በሻይ እርሻ በክልላችን ኢስት አፍሪካ እና ኢትዮ አግሮሴፍ ውሽውሽ በተባሉ ሁለት ትላልቅ ኩባንያዎች እንዲሁም በኮንትራክት የታቀፉ አርሶ አደሮች ከ2ሺህ 282 ሄክታር በላይ ማሳ እየለማ ነው:: ከዚህ ውስጥ 446 ሄክታሩ በኮንትራክት እርሻ በታቀፉ አርሶ አደሮች የለማ ነው:: በዚህም 512 የሚሆኑ አርሶ አደሮችን በህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጀት ተችሏል::

አዲስ ዘመን፡- ቢሮው በ2016 ዓመት በጀት ዓመት ምን አቅዶ ምን አከናወነ? ከእቅድ አንጻር አፈጻጸማችሁ ምን ይመስላል?

አቶ አስራት፡– በክልሉ ያለውን አቅም፣ እንዲሁም የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸማችንን ማዕከል በማድረግ ነው ለ2016 በጀት ዓመት እቅድ ያስቀመጥነው:: በዚህም በ2015 በጀት ዓመት የነበሩን ጥንካሬዎች እና ጉድለቶች በመገምገም በ2016 በጀት ዓመት ምርታማነትን ማሻሻል፤ እንዲሁም የምርት ዝግጅትና አቅርቦት ላይ ያለ የግብይት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎችን አቅደን ሰርተናል::

በአመቱ አጠቃላይ ከሰራናቸው ስራዎች መካከል የቡና ማሳን ማስፋት እና የቡና ምርጥ ዘር ማዘጋጀት የሚሉት በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሾች ናቸው:: ከዚህ አኳያ 54 ሺህ አንድ መቶ ኪሎ ግራም የቡና ምርጥ ዘር እናዘጋጃለን ብለን አቅደን፤ ከእቅድ በላይ ከ59 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የቡና ምርጥ ዘር ማዘጋጀት ችለናል::

የምናዘጋጀው ምርጥ ዘር ለእኛ ክልል ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሦስት ክልሎችም የሚሰራጭ ነው:: 16 ሺህ ኪሎ ግራም የሚሆን የቡና ምርጥ ዘር በሲዳማ፣ ማዕከላዊና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተሰራጭቷል:: ከክልሎች በተጨማሪም ቦንጋ፤ ዋቻሞ እና ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች ምርጥ ዘር ወስደዋል:: በነገራችን ላይ ይህን ምርጥ ዘር ከቢሮው በተጨማሪ የብቃት ማረጋገጫ ‹‹ሲኦሲ›› ያላቸው አርሶአደሮች ጭምር ያመረታሉ::

እነዚህ አርሶአደሮች በከፋ ዞን በአራት ህብረት ሥራ ማህበራት የተደራጁና ‹‹በኳራንታይን›› ማእከል ወይም በእጽዋት ዘር ጥራት ማዕከል የብቃት ማረጋገጫ ‹‹ሲኦሲ›› የተሰጣቸው ናቸው:: አርሶ አደሮቹ በየአመቱ ስልጠና ይሰጣቸዋል::

በዚህ ዓመት ሶስቱም ዩኒቨርሲቲዎች ከእኛ ምርጥ ዘር ወስደዋል:: እነዚህን ጨምሮ በእኛ ክልልም ልማቱ ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች በፕሮጀክቶች እና በተለያዩ ድጋፎች በዞኖች እና በወረዳዎችም ዘር የማሰራጨት ሥራዎች እየተሰሩ ነው:: ከዚህ አኳያ በክልሉ የቡና ዘር በሁለት ወቅት ነው የሚፈሰው:: የመጀመሪያው ዙር ከመስከረም እስከ ህዳር ሲሆን፤ ሁለተኛው ዙር ደግሞ ከሚያዝያ ጀምሮ ክረምቱን የሚፈስ ነው:: በመጀመሪያው ዙር ወደ 13 ሺህ ኪሎ ግራም ምርጥ ዘር ቡና በክልሉ ለማፍሰስ አቅደን በዘጠኝ ወር ውስጥ 11 ሺህ ኪሎ ግራም የሚሆን ማፍሰስ ችለናል::

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከበልግ ተከላ ጀምሮ እና በክረምቱን 72 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በተለያየ ደረጃ የሚገኝን የቡና ችግኝ ለመትክል አቅደን በዘጠኝ ወር ውስጥ 71 ሚሊዮን የሚጠጋ የቡና ችግኝ ለተከላ ተለይቷል:: ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ተከላውም ተጀምሯል:: እስከ ሰኔ 30 ድረስም 42 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ይተከላል:: ለዚህ ይረዳ ዘንድ 31 ሚሊዮን የሚሆን የቡና መትከያ ጉድጓድም ተዘጋጅቷል::

በቅመማ ቅመም ከእቅድ በላይ ተከላ ማካሄድ ችለናል:: በበጀት አመቱ 38 ሄክታር አመታዊና ሰንባች ቅመማ ቅመም አይነቶች ተከላ ለማካሄድ፤ እስከ ዘጠኝ ወር ደግሞ 24 ሺህ በላይ ችግኝ ተከላ እናከናውናለን ብለን አቅድን 25 ሺህ ችግኝ በመትክል ከእቅድ በላይ ማሳካት ችለናል::

በሻይ 35 ሄክታር በአርሶ አደሩ እናለማለን ተብሎ ታቅዶ በዘጠኝ ወር ውስጥ 10 ሄክታር ማልማት ተችሏል:: የሻይ ግብርና ሥራ በዋናነት በክረምት ስለሚከናወን እቅዱን ለማሳካት ክረምት ላይ ቀሪ ስራዎች ይከናወናሉ:: በኮንትራክት ፋርሚንግ ደግሞ 10 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ 12 ሄክታር ሻይ ማልማት ተችሏል::

የቡና ምርቱን ለማሳደግ ያረጀና ምርት ያቆመ የቡና ግንድ በጉንደላ እና በነቀላ ማደስ ያፈልጋል:: ከዚህ አኳያ 4ሺ ሄክታር በላይ እናድሳለን ብለን አቅደን ነበር:: በዘጠኝ ወራት ብቻ የእቅዳችንን 77 በመቶ ወይም ሦስት ሺህ 600 ሄክታር የቡና እደሳ ስራዎችን ሰርተናል::

እንደሚታወቀው ቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም በእጅጉ ስትራቴጂክ ምርቶች ናቸው:: እነዚህ የግብርና ምርቶች እንደሌሎች ምርቶች ለቤት ፍጆታ በማዋል መጨረስ ስለማይቻል ወደ ገበያ የሚወጡ ናቸው:: ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ናቸው:: በተለይም ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኙ ናቸው:: ከዚህ አንጻር በበጀት አመቱ ወደ 67 ሺህ 348 ቶን የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እናቀርባለን ብለን አቅደን ነበር:: ከዚህ አንጻር በዘጠኝ ወራት ውስጥ 38 ሺህ 40 ወይም 87 በመቶ ማሳካት ችለናል::

በቅመማ ቅመም ዘርፍ በበጀት ዓመቱ 54 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እናቀርባለን ብለን በዘጠኝ ወር 32ሺ ቶን ማቅረብ ችለናል:: በሻይ ምርትም ከሁለቱ ካምፓኒዎች ሰባት ሺህ 26 ቶን እናቀርባለን ብለን አቅደን በዘጠኝ ወር ብቻ አራት ሺህ 500 ማሳካት ችለናል::

በእነዚህ ዘርፎች የተገኘው ውጤት ከእቅድ አንጻር ጥሩ ነው:: ከአምናው ጋርም ሲነጻጸር እድገት አለው:: ለምሳሌ፣ የቡና የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ከአምና ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር 15ነጥብ ሰባት በመቶ እድገት አለው:: በቅመማ ቅመም ዘርፍ ከአምና ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር ሁለት እጥፍ ነው:: በሻይ ምርትም ከአምና ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር ሁለት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እድገት አለው:: በቀሪው ጊዜ ትኩረት አድርገን ካልሰራን እቅዱን ለማሳካት ስለምንቸገር የ90 ቀን እቅድ አዘጋጅተን ሥራ ጀምረናል::

አዲስ ዘመን፡- በዘጠኝ ወሩ ውስጥ ምን ተግዳሮት አጋጠማችሁ? ችግሮቹን ከመሻገር አኳያስ በምን መልኩ ሰራችሁ?

አቶ አስራት፡- ከላይ የተጠቀሱትን ስራዎች ስናከናውን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ነበር ማለት አይደለም:: በርካታ ተግዳሮቶች ነበሩ:: በተለይም ሶስቱን ስትራቴጂክ ምርቶች በተሳካ ሁኔታ በማምረት እና ወደ ገበያ እስከ ማቅረብ ባለው ሂደት በርካታ ችግሮች አጋጥመውናል::

ከእነዚህ መካከል የኤክሴሽን ስርአቱን ማጠናከር አንደኛው ነው:: ከዚህ አንጻር ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለውን መዋቅር የተጠናከረ ባለመሆኑ በተለይም ቀበሌና ወረዳ ላይ የተጠናከረ መዋቅር ባለመኖሩ ምርቶቹን በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር አስቸጋሪ አድርጎታል:: መዋቅሩ በሎጅስቲክ የተደራጀ አለመሆኑ ሌላኛው ተግዳሮት ነው::

ሦስተኛ ተግዳሮት ደግሞ፣ የምርታማነት ፓኬጅ ትግበራ ላይ በተለይ በጉንደላ ያረጀ ቡናን አለማደስ፣ የኮምፖስት ዝግጅት እና ኮምፖስት አጠቃቀም ላይ የሚስተዋሉ አንዳንድ የአመለካከት ችግሮች አሉ:: በተጨማሪም የምርት ዝግጅትና ግብይት አካባቢ ላይ የሚስተዋሉ በተለይ የምርት ጥራትን አስጠብቆ ከመሄድ አንጻር፤ ህገ ወጥ የምርት ዝውውርን መግታት አለመቻል፤ ከግብይት ሥርዓቱ አንጻር የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ::

ከቡና አንጻር መሰረታዊ የሆኑ ችግሮችን የውስጥ እና የውጭ ብለን የለየናቸው አሉ:: የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ መዋዥቅ ጋር ተያይዞ 2015 ዓ.ም የምርት ዘመን የነበረው እስከ 2016 ድረስ መዝለቁ በራሱ ያሳደረው ተጽእኖ አለ:: በኒዮርክ ገበያ የቡና ዋጋ በወረደ ቁጥር የእያንዳንዱን አርሶአደርና ነጋዴን ቤት እያንኳኳ ነው::ይህ አንዱ መሰረታዊ ችግር ሆኖ ቀጥሏል::

ሌላው ገበያ ከማግኘት አንጻር በተለይ አልሚ እና ላኪ አርሶ አደሮች ገዥ ከማግኘት አንጻር በወቅቱ ገዥ አለማግኘት፤ ከዋጋም አንጻር አንዳንዴ ዋጋን ከፍ አድርጎ ገዝቶ የዓለም ዋጋ በሚወርድበት ጊዜ በወረደ ዋጋ ለመሸጥ ስለሚቸገሩ ምርቱን የመያዝ እና በህገ ወጥ መንገድ ለመሸጥ ሙከራ ሲደረግ ይስተዋላል:: እንደ ክልል ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን እነዚህን እና መሰል ችግሮች በየጊዜው እየተከታተሉ መቅረፍ በሚል ገምግመን የተለያዩ ስራዎችን እያከናወንን ነው::

በተጨማሪም በፌዴራል ደረጃ ለውጡን ተከትሎ ቡና ላይ ያሉ ችግሮችን ለማስቀረት በቡናና ሻይ ባለስልጣን አጠቃላይ ሪፎርሞችን አድርጓል:: ሪፎርም ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል የግብይት ሥርዓቱ አንዱ ነው::

አዲስ ዘመን፡- የግብይት ሥርዓቱ ላይ ያለውን ችግር ከማቃለል አኳያ ለውጡን ተከትሎ የተፈጠረው የቀጥታ ግብይት ሥርዓት ምን ምን ውጤት አስገኘ?

አቶ አስራት፡– ከዚህ በፊት ቡና ይሸጥ የነበረው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ኢሴክስ) ነበር:: ቡና ኢሴክስ ውስጥ ገባ ማለት በገበያው ገዥ እስከሚገኝ ድረስ ቡናው መጋዘን ውስጥ ይቆያል:: ይህ ደግሞ ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው በሚል ተገምግሟል:: ለውጡን ተከትሎ ከቡና የግብይት ሥርዓት ጋር ተያይዞ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ተለይተዋል::

ከተለዩት ችግሮች አንዱ ሀገራችን ከፍተኛ ምርት ያላት ሆና ወደ ውጭ ልካ በምንዛሬ የምታገኘው ገንዘብ ግን ትንሽ ነው የሚል ነው:: በሁለተኝነት የተለየው ችግር ደግሞ በንግዱ ያሉ ተዋንያንን የሚፈጥሯቸው ቢሮክራሲዎች ናቸው::

ይህን ተከትሎ በለውጡ አማራጭ የግብይት ሥርዓቶች መኖር አለባቸው የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሶ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ኢሲኤክስ) አንደኛው አማራጭ የሚሆንበትን እና የቀጥታ የገበያ ትስስር ደግሞ ሌላኛው አማራጭ እንዲሆን ውሳኔ ላይ ተደርሷል:: ነገር ግን በቀጥታ ትስስር ቡናን ማገበያየት የሚቻልበትን እና አምራቾችን ከላኪዎች በማገናኘት ያለ ምንም ቢሮክራሲ በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ መጋዘን ይገባል:: ወደ ውጭም ይላካል::

በዚህ አሰራር በተለይም በ2013 ዓ.ም የምርት ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ መላክ አስችሏል:: ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ከግብርና ምርቶች በተለይም ከቡና ያገኘችበት ወቅት ነበር:: ይህም አንድ የለውጡ ውጤት ተደርጎ የሚወሰድ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በቀጥታ ትስስር በሚደረገው ግብይት የቡና ላኪዎች ለአምራቾች እና ነጋዴዎች በወቅቱ ገንዘባቸውን እየከፈሉ አለመሆናቸው ይነገራል:: በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

አቶ አስራት፡– በቀጥታ ትስስሩ አንዱ የሚስተዋለው ችግር አምራቹ እና ላኪው ውል ገብተው ቡናውን ከተረካከቡ በኋላ ላኪው በወቅቱ ለአምራቹ ገንዘብ ያለመክፈል ይስተዋላል:: ይህ ደግሞ በአምራቹ ላይ ከፍተኛ ችግር የፈጠረ እና ነጋዴዎችንም ከገበያ እያስወጣ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በቀጥታ ትስስሩ የሚሸጥ ቡና ደረጃ እና ሰርተፍኬት ይሰጠዋል:: ነገር ግን እነዚህን ስራዎች ለማከናወን እንደ ሀገር ያሉ ማዕከላት ትንሽ በመሆናቸው በግብይት ሥርዓቱ ላይ ችግር እየተፈጠረ መሆኑ ይነገራል:: በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

አቶ አስራት፡– በቀጥታ ትስስር ቡና የሚሸጠው ተቀምሶ እና ደረጃ ወጥቶለት ነው:: ደረጃ ማውጣት እንዲቻል የቡናና ሻይ ባለስልጣን ቀደም ሲል በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከነበሩት ላቦራቶሪዎቹ በተጨማሪ በጅማ እና ሀዋሳ ሌሎች ማዕከላትን ከፍቷል:: ይሁን እንጂ እነዚህ ማዕከላት አሁንም በቂ ባለመሆናቸው ቡና ጭነው የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች የጫኑት ቡና ደረጃ እስከሚወጣለት ድረስ ለበርካታ ቀናት እና ሳምንታት ወረፋ እንዲጠብቁ ተገድደዋል:: ይህም ነጋዴዎችን ላልተገባ ወጪ ዳርጓቸዋል::

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ በኩል በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል:: ከነዚህም ውስጥ አሁን ላይ በቦንጋ የደረጃ እና ሰርተፍኬሽን ማዕከል ስራዎችን ለመጀመር ቅድመ ሁኔታዎች ተጠናቅቀዋል:: በቅርቡ ሥራ ጀምራል:: ቦንጋ ላይ ያለው ማዕከል ሥራ ሲጀምር ለደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል ቡና አምራቾችን እና ነጋዴዎችን ከከፍተኛ እንግልት እና የገንዘብ ወጪ የሚታደግ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ሊለማ ከሚችለው መሬት እስካሁን ምን ያህል ለምቷል?

አቶ አስራት፡- ቅመማ ቅመምን ስንመለከት በአነስተኛ ደረጃ ሴቶች በጓሮ ከሚያለሙት ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ ተደራጅተው የሚያመርቱ አሉ:: በስድስት ዞን ውስጥ 41 የገጠር ወረዳዎች ላይ ቡናና ቅመማ ቅመም ይመረታል::

ሻይ በከፋና በሸካ ዞኖች እየለማ ነው:: ከቆላ እስከ ደጋ ድረስ ለአካባቢው የሚስማማ ዘር በማዘጋጀት ከ489 ሺህ ሄክታር በላይ ሊለማ የሚችል መሬት አለ:: ሆኖም እስካሁን በቡና እና በቅመማ ቅመም ዘርፍ ሊያለማ የገባው 237 ባለሀብት ነው:: በዚህም 59 ሺህ ሄክታር ለምቷል:: አሁንም ተጨማሪ ባለሀብት ገብቶ ሊያለማ የሚችልበት ቦታ አለ::

አዲስ ዘመን፡- ከቡና በተጨማሪ የቡናን ቅጠል ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ሀገራት አሉ:: ከዚህ አንጻር ክልሉ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?

አቶ አስራት፡– በቡና ሽያጭ አዋጁ 1051 መሰረት ወደ ገበያ ሊቀርቡ ከሚችሉ የቡና ምርቶች ውስጥ አንዱ ቡናው ቅጠል ነው:: ቅጠሉን ወደ ገበያ ማስገባት እንደሚቻል በአዋጁ ተቀምጧል:: ነገር ግን የቡና ቅጠል ንግድ ያልተለመደ በርካታ ፈተናዎች ይኖሩታል::

ቡና አረንጓዴ ተክል ነው:: በመሆኑም ምግቡን የሚያዘጋጀው በቅጠሉ ነው:: ቅጠሉን ወደዛ ሽያጭ ከተገባ ምናልባት ወደ ፍሬው የሚሄደውን ነገር በመግታት ወደ አልታሰበ ነገር ይወስዳል የሚል ስጋት አለ:: ይሄንን እንዴት እናድርግ የሚለውን መመካከር ይፈልጋል:: በሌላ በኩል ቡና ሲያረጅ እና ምርት ሲያቆም ቅጠሉ ቢሸጥ ከፍተኛ ጥቅም ማስገኘት የሚችል ነው::

አዲስ ዘመን፡- ቡናና ሻይ ባስልጣን ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር በመሆኑ እና የሚተዳደረው በሲቪል ሰርቪስ ህግ በመሆኑ ምን ተግዳሮት እየገጠመው ነው?

አቶ አስራት፡– በሲቪል ሰርቪስ ህግ በመተዳደሩ ከሰራተኛ ጋር በሚገናኝ የራሱ ተጽእኖ ይኖረዋል:: ለቡናና ሻይ ባለስልጣን የተሰጡት ምርቶች ለየት ያለ ባህሪ ያላቸው ናቸው:: አንደኛ ከሌሎች ሰብሎች በባህሪያቸው የተለዩ ናቸው:: ምርቶቹ በስፋት የሚመረቱ በመሆናቸው ለገበያ ካልሆነ በስተቀር ለቤት ፍጆታነት ተጠቅምን የምንጨርሳቸው አይደሉም:: ገበያ ተኮር ናቸው:: የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሳንባም ናቸው:: ለምሳሌ፣ ሻይ ሌሎች እንስሳቶች እንኳን አይጠቀሙትም::

ሻይ እስከ 70 አመት የሚቆይ ሲሆን፤ ቡና ደግሞ ከ30 እስከ 40 አመት መቆየት የሚችል ነው:: እነዚህ ምርቶች እሴት እየጨመሩ ገበያ ለማምጣት ፕሮፌሽናል የሆኑ ሰዎችን እና ሎጅስቲክስ ይፈልጋል:: ህግና ደንብ ሲወጣም ቢሮክራሲ ያልበዛበት መሆን አለበት:: ምክንያቱም ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ነው የሚወዳደሩት:: ስለሆነም ከቡና እና ሻይ ጋር ተያይዞ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል::

ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መዋቅሩ ራሱን የቻለ ሆኖ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚኒስቴር የሚመራ ቢሆን ይመረጣል:: ነገር ግን ተጠሪነቱ ለግብርና ከሆነ ብዙ ጉዳዮችን አልፈህ መወሰን አትችልም:: ከዚህ አኳያ ከምርቶቹ ባህሪ እና አስተዋጽኦ አንጻር ማየት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ድርሻውን መወጣት የሚያስችል አደረጃጀት ቢፈጠርለት ጥሩ ነው ብለን እናምናለን:: ነገር ግን በሲቪል ሰርቪስ መመራቱ አይደለም ችግሩ ተጠሪ ተቋም በመሆኑ ውሳኔ ሰጪው አካል ሌላ መሆኑ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በምርምር የተደገፉ ስራዎችን በማከናወን ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተባብሮ ከመስራት አንጻር ያላችሁ ተሞክሮ ምን ይመስላል?

አቶ አስራት፡- ከበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በጋራ እንሰራለን:: ነገር ግን እስካሁን ቅንጅት ከመፍጠር አንጻር ገና ብዙ የተጠናከረ ነገር የለም:: ወደፊት በምርምር የተደገፉ ስራዎችን በማከናወን ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተባብሮ ለመስራት የሚያስችሉ አሰራሮችን እየዘረጋን ነው::

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ከቡና እና ሻይ እንዲሁም ከቅመማ ቅመም ምን ያህል ገቢ አገኘ? የገበያ መዳረሻዎቹስ የት ነው?

አቶ አስራት፡– ምርቶቹ የት ነው የሚላኩት? የሚለውን መረጃ ማግኘት የሚቻለው ከፌዴራል የቡናና ሻይ ባለስልጣን ነው:: ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የክልሉ ቡና የሚላከው ወደ አሜሪካ፣ ጀርመን እና አረብ ሀገራት መሆኑን የተለያዩ ሰነዶች ያሳያሉ:: ከገቢ ጋር ተያይዞ በዚህ ዓመት ከ192 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል::

አዲስ ዘመን፡- ህገ ወጥ የቡና ነጋዴን ለመቆጠጣር በተጨባጭ ምን እየተሰራ ነው?

አቶ አስራት፡– በብዛት ህገ ወጥ ንግድ የሚበዛው ቡና ላይ ነው:: ለዚህም የዓለም ገበያ መዋዠቅ ዋነኛ ምክንያት ነው:: ከቡና ንግድ ጋር ተያይዞ በርካታ ፈተናዎች ያሉበት ነው:: እነዚህን ችግሮች ለማቃለል እንደ ክልል ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል::

ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ቡና አምራች ከሆኑ ዞኖች ጋር በመሆን ከፍተኛ የንቅናቄ ሥራ ተሰርቷል:: እንዲሁም የቡና ምርት አዘገጃጀት እና ግብይት ሥርዓት ላይ የቡና ኢንዱስትሪዎችን ማዕከል አድርገን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ሰተናል:: ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ የሚመሩበት አደረጃጀት አለ:: ይሄንን ከማደራጀት አንጻር 130 የሚሆኑ ሰዎች ያሳተፈ የንቅናቄ መድረክ አካሂደናል:: በዚህም ውጤት ተገኝቷል::

ለምሳሌ፦ እንጭጭ ቡና ሸምጥጠው በሚሸጡ ህገወጦች እስከማቃጠል የደረሰ እርምጃዎችን ወስደናል:: ለማሳያ ያህልም፣ በሸካ ዞን የኪ ወረዳ ላይ እንጭጭ ቡና ሸምጥጦ ለመሸጥ በሞከሩ አርሶአደር እና ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃዎችን ወስደናል:: ህገወጦች የሚያዘዋውሩትን ቡና ሸጠን ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ገቢ አድርገናል:: በቀጣይ እርምጃዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን::

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ቃለ መጠይቅ እናመሰግናለን::

አቶ አስራት፡-እኔም አመሰግናለሁ::

መክሊት ወንድወሰን፣ ሞገስ ተስፋ እና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You