በርካታ የማሠልጠኛ ማዕከላት አትሌቶች በክለቦች ተመልምለዋል

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት ውድድር በአሰላ አረንጓዴ ስቴድየም ተካሂዷል። ከሰባት የማሰልጠኛ ማዕከላት የተውጣጡ ታዳጊ አትሌቶች በውድድሩ ተሳትፈዋል፡፡ እነዚህ ታዳጊ አትሌቶች የወሰዱትን ሥልጠና በውድድር መለካት ችለዋል፡፡ በክለቦችና በሌሎች መልማዮች ዓይን ውስጥ የገቡትም እድል አግኝተዋል። በዚህም ክለቦችና ማናጀሮች በውድድሩ ሥፍራ ታድመው ብቃት ያላቸውን ታዳጊ አትሌቶች ማስፈረም ችለዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዓመታዊው የውድድር መርሃ ግብሩ መሠረት ከሚያካሂዳቸው የአትሌቲክስ ውድድሮች ይህ የሥልጠና ማዕከላት ውድድር አንዱ ነው፡፡ በፌዴሬሽኑ ስር የሚተዳደሩትና የተለያዩ ድጋፎች ተደርጎላቸው፤ ታዳጊና ሀገርን የሚወክሉ አትሌቶችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለአትሌቶች ዘመናዊና እውቀትን የዋጀ ሥልጠናን ይሰጣሉ። የሰጡትን ሥልጠና የሚመዝኑበትና አትሌቶች ቀጣይ ዕድላቸውን የሚወስኑበት እንዲሁም አቅጣጫቸውን የሚለዩበት ደግሞ ይህ የውድድር መድረክን ነው። ለአራተኛ ጊዜ በአሰላ አረንጓዴ ስቴድየም የተካሄደው የማሠልጠኛ ማዕከላት ውድድርም ይሄንኑ የሚያጠናክር ሲሆን በዚህም መሠረት ለአትሌቶች የውድድር ዕድልን መፍጠር፣ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት እና በክለቦችና ማናጀሮች ዓይን ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ ዓላማን አንግቦ ተከናውኗል።

ውድድሩ ግንቦት 15/2016 ዓ.ም ጀምሮ በአትሌቲክስ (በአጭር፣ መካከለኛ፣ ረጅም ርቀትና የሜዳ ተግባራት) የተካሄደ ሲሆን ጠንካራና ተስፋ ሰጪ የሆኑ ፉክክሮች ተስተናግደውበታል። ከተጀመረበት አንስቶ በርካታ የፍጻሜ እና የማጣርያ ውድድሮች ተከናውነዋል። ይህም አትሌቶች በሥልጠና ማዕከላት የተከታተሉትን ሥልጠና በውድድር በመለካት የሚገኙበትን አቋም ለመለየትና የመመረጥ እድሎችን ማግኘት ችለዋል። በዚህም መሠረት በርካታ ታዳጊ አትሌቶች የክለቦችን እና የማናጀሮችን ቀልብ በመግዛት ቀጣዩን ምዕራፍ ተቀላቅለዋል።

የሥልጠና ማዕከላት ውድድር በክለቦችና ማናጀሮች የመታየት እድልን እንደፈጠረላቸውም ታዳጊ አትሌቶች ተናግረዋል። ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ክፍቶች ቢኖሩም ከሌላው ጊዜ የተሻለ እና ጠንካራ ፉክክርም ታይቶበታል። አትሌቶቹ በሁሉም ተግባራት እራሳቸውን ለማሳየት እና ለመመረጥ የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታና ተስፋን የሚሰጥ እንቅስቃሴን አስመልክቷል። አሠልጣኞችም አትሌቶቹ የወሰዱትን ሥልጠና በውድድሩ በተገቢው መልኩ እየተገበሩ ለመመረጥ ያላቸውን እድል ማስፋተቸውን ገልጸዋል።

በክለብ ዓይን ውስጥ ገብታ የመመረጥ እድል ማግኘት ከቻሉት አትሌቶች አንዷ የሆነች አልማዝ ዮሃንስ በ3ሺ እና 3ሺ ሜትር መሰናክል ሁለት የወርቅ ሜዳሊዎችን መውሰድ ችላለች። አትሌቷ በሲዳማ ክልል የሚገኘውን ሀገረሰላም ማሠልጠኛ ማዕልን በመወከል አስደናቂ በሆነ አሯሯጥ ውድድሩን በበላይነት አጠናቃለች። በማዕከሉ የወሰደችውን ሥልጠና በውድድር ለመለካትና ለመመረጥ ትልቅ እድልን እንደፈጠረላት ትናገራለች። አትሌቷ ከዚህ ቀደም በአህጉር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ሀገር አቋራጭ፣ ቱኒዚያ ላይ በወጣቶች 6 ኪሎ ሜትር ተሳትፋ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች። በሶስተኛ የማዕከላት ውድድር ላይም የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃ የነበረ ቢሆንም እንደ ዘንድሮ የመመረጥ እድልን ማግኘት አልቻለችም ነበር። አሁን ግን በሳየችው አስደናቂ እንቅስቃሴና ውጤት ሲዳማ ቡና አትሌቲክስ ክለብን መቀላቀል ችላለች። በቀጣይ ጠንክራ በመሥራት እንደሌሎች ጀግኖች አትሌቶች ሀገሯን በዓለም አደባባይ ለማስጠራት እቅድ እንዳላትም ተናግራለች።

ከደብረብርሃን ማሠልጠኛ ማዕከል በ3 ሺ ሜትር ተወዳድራ ሁለተኛ የወጣችው አልማዝ ገንዬ፤ ከዚህ በፊት ምንም ውድድር አለማካሄዷን ገልጻ፣ እንደ መጀመርያ ውድድር ጥሩ እንደነበረ አስተያየት ሰጥታለች። እንደዚህ ዓይነት ውድድር ልምድ ለማግኘትና በክለብና ማናጀሮች የመታየትን ዕድልን እንደሚፈጥር ጠቁማለች።

የአልማዝ አሠልጣኝ የሆነው አዱላ ቱሉቃ፣ መድረኩ የታዳጊዎች መታያ ውድድር ሆኖ እንዳገኘውና በርካታ አትሌቶችን እያስመረጠ መሆኑን ተናግሯል። ጥሩ ብቃት ያላቸውና ተስፋ የሚደረግባቸው አትሌቶችን ማፍራት የሚያስችል እና ብዙ ክለቦች አትሌቶችን ለማስፈረም ፉክክር ያደረጉበት የውድድር መድረክ እንደሆነም አክሏል፡፡

የሀገረሰላም ማሠልጠኛ ማዕከል ሥራ አኪያጅ አቶ ደሳለኝ አማቶ፣ ውድድሩ ለአትሌቶች የመታየት እድልን የሚፈጥርና ሥልጠና ጨርሰው የሚወጡ አትሌቶች ወደ ክለብ ሽግግር የሚያደርጉበት መድረክ እንደሆነ ያስረዳሉ። ማዕከሉ በዘንድሮ ዓመት ሃያ አንድ አትሌቶችን እንደሚያስመርቅ ገልፀው፤ አትሌቶቹ ጥሩ ውጤትን በማስመዝገብ ክለብ የማገኘት እድላቸውን እንዳሰፉ ተናግረዋል፡፡ ክለቦች አትሌቶችን ለማስፈረም በሚያደርጉት ጥረት በርከት ያሉ ታዳጊዎች ተመርጠዋል። ማዕከላት ተመሳሳይ የእድሜ ደረጃ እንዲኖር አበክሮ መስራት እንደሚኖርባቸውና ፌዴሬሽኑም ክትትልና ድጋፍ አድርጎ ማጣራት ከተሠራ ተፎካካሪና ውጤታማ አትሌቶችን ለክለቦች ማበርከት እንደሚቻል አክለዋል። በዚህ ውድድር ከ21 ተመራቂ የማዕከሉ አትሌቶች 18ቱ ለክለቦች ፊርማቸውን አኑረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ የውድድር ባለሙያና የአራተኛው የማሠልጠኛ ማዕከላት ቻምፒዮና የውድድር ዳይሬክተር አቶ ብስራት ለጥበሉ፣ ማዕከላት በተለያዩ ተግባራት ብዙ አትሌቶችን በማፍራት ዉጤታማ ግምገማ ማሳየታቸዉንና የተሰጣቸዉን ግብና ዓላማ በአግባቡ እያሰኬዱ መሆኑን ጠቁመዋል። በዘንድሮም በሁሉም ተግባራት ጥሩ ፉክክርና ውጤታማ የሆኑ ታዳጊዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። አትሌቶችን ለመምረጥ ብዙ የክለብ አሰልጣኞች ተገኝተው አትሌቶችን እየመረጡ በመሆኑ ጥሩ እድል መፈጠሩን አስረድተዋል።

በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙ 7 ማሠልጠኛ ማዕከላት የተውጣጡ 158 ወንድ እና 137 ሴት በድምሩ 295 ታዳጊ አትሌቶች ውድድራቸውን ማካሄድ ችለዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You