ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ መዳን ይችላል ወይስ ይዳፈናል?

የመጨረሻ ክፍል

በዚህ ጽሑፉ የመጀመሪያ እትም፣ የአዋቂዎች የስኳር በሽታ (Type II Diabetes Mellitus) ምንነት ፣ ሙሉ በሙሉ ይድናል ፣ አይድንም የሚለውን ሳይንሳዊ መረጃዎች በማጣቀስ ለማየት ተሞክሯል። እስካሁን ባለው ሳይንሳዊ መረጃ፣ አንድ ሰው በወሰዳቸው ርምጃዎች ከምልክቶቹ ነፃ ሆነ ማለት ዳነ ማለት እንዳልሆነ፣ ይሁን እንጂ “የማይመለስና” እየጨመረ የሚመጣ (irreversible and progressive) የሚለውን የቀደመ አስተሳሰብ የለወጡ እጅግ ብዙ መረጃዎች መውጣት መጀመራቸውን ፤ በተግባርም ከሰዎች እና ከሥራ ልምድ ማየት መቻሉን አይተናል። በዛሬ እትማችን ደግሞ የስኳር በሽታ ለማዳፈንም ሆነ ቀድሞ ለመከላከል ሰዎች ምን ሊያደርጉ ይገባል የሚለውን ይዘን ቀርበናል።

  1. የመጀመሪያውና ከሁሉም ቀዳሚው በቂና ዘላቂነት ያለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ነው።

የቀደመውን ባላገኘውም በሁለተኛው ውይይት ላይ ስለአካል ብቃት እንቅስቃሴ አስፈላጊነት ብዙ ትኩረት ስላልተሰጠው በሌላ መድረክ ትንሽ ዘርዘር ተደርጎ ቢቀርብ መልካም ነው። ኦፕሬሽን የሚሰራው፣ ክብደት ቀንሱ የሚባለው፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲዘወተር የሚመከረው እና ካርቦሃይድሬት ምግቦችን አታብዙ የሚባለው ሁሉ በደም ውስጥ የስኳር መጠን እንዳይበዛ ሲሆን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ግን ብዙ ተጨማሪ ጥቅሞች አሉት።

ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ የተገኘባቸው ሰዎች ሊያደርጉ የሚችሉት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በእድሜ እና በሰውነት ክብደት መጠን ይወሰናል። በብዙ ጽሑፎች እና መጽሐፎች ላይ በሳምንት ለአምስት ቀን (በእያንዳንዱ ቀን ለ30 ደቂቃ) ቀላል ኤሮቢክ እንቅስቃሴ (Aerobic exercise) ወይም ጫና ያልበዛበት ተብሎ ለሁሉም የሚመከረው በተወሰነ ደረጃ ጉድለት አለበት። ጫና ያልበዛበት የሚባለው አካላዊ ስትረስ እንዳያመጣ ነው። እሱም ቢሆን እንደ ሥነ ልቦናዊ ስትረስ ቀጣይ ሳይሆን እረፍት ሲያደርጉ የሚጠፋ ስለሆነ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል፤ በ24 ሰዓት ለአንድ ሰዓት በሚሰራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አካላዊ ስትረስ ተፈጥሮ የስኳር መጠን የመጨመር እድሉ ዝቅተኛ ነው።

ስለሆነም እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ላሉ ሰዎች፣ ከበድ ያለ የጤና ችግር ላለባቸው እና የውፍረታቸው መጠን ከፍተኛ (BMI>35 kg/m2) ወይም ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ (BMI <25 kg/m2) ከሆነ ኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በቂና ትክክል ሊሆን ይችላል። (BMI የሚለካው ክብደትን እርስ በርሱ ለተባዛ ቁመት በማካፈል ነው)። ነገር ግን BMI ከ25- 35 kg/m2 ከሆነ ከሁሉ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባና ሁለተኛውን ዓይነት የስኳር በሽታ ለማዳፈን ብሎም እጅግ መጥፎ የሆነውን የጉበት እና የቆሽት የስብ ክምችት በመቀነስ እጅግ ውጤታማ የሆነው ክብደት መቀነስ ስለሆነ፣ ከበድ ያለ ኤሮቢክ (ሶምሶማ ሩጫን ጨምሮ) በሳምንት ቢያንስ ሶስት ቀን ለአንድ ሰዓት መሥራት ያስፈልጋል።

ሰውነት እስኪለማመድ ድረስ ሁለተኛውን ዓይነት የስኳር በሽታ የተገኘባቸው ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረጋቸው በፊት ቀለል ያለ ምግብ መውሰድ አለባቸው። ለረጅም ጊዜ ግሉኮስ መቀበል ቀንሰው የነበሩ የጡንቻ ህዋሳት እና የስብ ቅንጣትን በኃይል ምንጭነት ሲጠቀሙ የነበሩ የበለጠ ይነቃቁና (Hypertrophy) ብዙ ስብ እና ግሉኮስ ወደ ኃይል እየቀየሩ ያቃጥላሉ፤ የደም ስሮች ቁጥርና መጠን ይጨምራል (በዚያውም ለደም ግፊት በሽታ መጋለጥ ይቀንሳል)፤ አዕምሮ ንቁ ይሆናል፤ የበሉት ምግብ ይዋሃዳል፤ ቅዤት የሌለው እንቅልፍ ይወስዳል፤ የሥነ ልቦና ስትረስ ይቀንሳል። የእንቅልፍ መረበሽና የሥነ ልቦና ስትረስ በአብዛኛው የደም የስኳር መጠንን እንደሚጨምሩ ይታወቃል።

ከራት በኋላ ቢያንስ አንድ ሰዓት ቆይቶ ለ10 ደቂቃ ቀለል ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዘወትር ማድረግ ይመከራል። አንድ ሰው በእንቅልፍ ላይ በአማካይ ለ8 ሰዓት ስለሚቆይ በዚያን ጊዜ ከBasal metabolism ያለፈ ህዋሳቶች የኃይል ምንጭ የሆኑ ምግቦችን ስለማያቃጥሉ እና የደም የስኳር መጠንን ስለሚጨምር የስኳር ምንጭ የሆነውን ቀድሞ መቀነሱ መልካም ነው። ስለሆነም ከተበላው ላይ የተወሰነውን አቃጥሎ (ወደ ኃይል ምንጭነት ተጠቅሞ) መተኛት ለህዋሳት እረፍት ከመስጠቱም በላይ ሰላማዊ እንቅልፍ ለመተኛት ያስችላል። ከዚሁ ጋር የተያያዘው ራት ላይ ከበድ ያሉ ምግቦችን አለመውሰድ ነው።

እጠቅሳለሁ ነፍሳቸውን በገነት ያኑረውና አንድ ኢትዮጵያዊ የስኳር በሽታ ፕሮፌሰር ሲያስተምሩን “በልተህ ተንቀሳቀስ እንበለው እንጂ ይህን ይህን ምግብ አትብላ አንበለው” ይሉ ነበር (ምክራቸው ስኳር በሽታ ላለበት ሳይሆን ቀድሞ ለመከላከል ነው)። በርግጥም ምግብ መርጠን ይህን ብላ ይህን አትብላ የምንለው ሰውነቱ ካልተስማማው ወይም ካልተንቀሳቀሰ የበላውን (ካርቦሃይድሬት) የሚያስቀምጥበት ስለሌለ (ስለማይቃጠል ወይም ስብ ሆኖ ስለማይከማች) እንጂ ካለበለዚያማ ከተጠቀመበት እና ለሰውነቱ ከተስማማው ሁሉም ምግብ ነዳጅ ወይም ገምቢ ወይም በሽታ ተከላካይ ነው። እዚህ ጋ ነው አንዱ የዶ/ር ደምሴ ነጥብ ሚዛን የሚደፋው። ሰውነታችን የበላነውን ምግብ በራሱ ጊዜ እንዲቀበል ሳናደርገው በመድኃኒት እገዛ (ሳይፈልግ በግድ እንደማለት) እንዲቀበል እናደርገዋለን። ይሄ ደግሞ “የታመሙ” ህዋሳቶች አልታከሙም ወይም በመደበኛው መንገድ ምግብን እንዲያዋህዱ ስላላደረግናቸው ችግሩ እየባሰ ይሄዳል እንጂ መፍትሔ አይሆንም። ህዋሳቶቻችን ከመድኃኒት በተጨማሪ የማይመቻቸውን ምግብ በመተው እና እንዲሰሩ በማድረግ አላገዝናቸውም።

ያልተኛ ልጅ እረፍ ቢሉት እሺ እንደማይለው ሁሉ ደጋግመን ስንቀመጥ ለጡንቻችን ተፈጥሯዊ ያልሆነ ነገር እያደረግን ነው (ጡንቻዎቻችን ይደክማሉ)። የአእምሮም ሆነ የሰውነት ምቾት በመቀመጥ ወይም በመተኛት ብቻ ሳይሆን በእንቅስቃሴ ጭምር ሲደገፍ ጤናም፣ ጥንካሬም፣ እድሜም ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ልማድ ማድረግ ከስኳር በሽታ ብቻ ሳይሆን ከብዙ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ይከላከላል እና እኛ እየሰራን ልጆቻችን እንዲለምዱት እናድርግ የሚለው ዋናው መልዕክት ነው።

ሲጠቃለል አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር ሲጀመር የደም ስኳር ስለሚቀንስ፣ እንደበፊቱ ብዙ መጠን ያለው መድኃኒት ማስፈለጉ ይቀንሳል። ከዚያም አልፎ በሂደት መድኃኒት እስከማቆም መድረስ ይቻል ይሆናል። ነገር ግን በሽታው ዳነ ማለት አይደለም። ምልክቱ እንጂ መንስኤው ስላልጠፋ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና ሌሎች ርምጃዎችን ስናቆም ተመልሶ ይጨምራል፤ ለዚያም ነው Remission ማለት የተዳፈነ ነው የተባለው። የተዳፈነ እሳት ውሉ አድሮ ሲገለጥ ሳይጠፋ ይገኛል።

  1. አመጋገብን ማስተካከልና የሚያብስብንን ምግብ ሁሉ ለይቶ መተው ያስፈልጋል።

ለግንዛቤ እንዲሆን፣ በተለምዶ ካርቦሃይድሬት ምግቦችን “ኃይል ሰጭ”፣ ፕሮቲን የሆኑትን “ገንቢ” የሚለው ቃል ገላጭ ስላልሆነ (ከላይ እንደተጠቆመው በማወፈር ደረጃ ትርፍ ካርቦሃይድሬት ቀዳሚ ስለሆነ)፣ ቃሉን እንዳለ መጠቀሙ የተሻለ ነው። በየትኛውም ዓይነት ቢዘጋጁ የእህል ዘሮች ከሆኑት ከስንዴ፣ ከገብስ፣ ከበቆሎ እና ከሩዝ የሚዘጋጁ ምግቦች ከፍተኛ የካርቦሃይድሬት መጠን የያዙ ናቸው። እህል ያልሆኑ ማር፣ ድንች፣ ቆጮ እና ሸንኮራ አገዳ (ስኳር) ተጠቃሽ ናቸው። ነገር ግን ካርቦሃይድሬት መጠኑ ያንሳል እንጂ በብዙ ምግቦች ውስጥ (አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ) ይገኛል። የካሎሪ መጠናቸው ከፍ ያሉ (በግራም ከ7 እስከ 9 ካሎሪ) ከሚባሉት መካከል የቅባት ምግቦች (የሥጋ ውጤቶች፣ የወተት ውጤቶች፣ አሳ፣ ዘይትና የቅባት እህሎች) እና አልኮል መጠጦች ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ብዙ ጊዜ ካርቦሃይድሬት ምግቦችን ብቻ ሳይሆን ሥጋም ሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ ላለባቸው ሰዎች ሲከለከል መስማት የተለመደ ነው። ምናልባት የሪህ በሽታ ካለባቸው፣ የኮሌስትሮል መጠናቸው ከፍ ያለ ከሆነ፣ የሰውነታቸው ክብደት ከፍ ያለ ከሆነ ወይም ለሰውነት ክብደት መጨመር የተጋለጡ ከሆነ ትክክል ነው። ነገር ግን የተመጣጠነ ወይም ዝቅተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸው ከሆኑ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያዘወትሩ ከሆነ ሥጋ መብላት (ከፍተኛ ካሎሪ ሰጭ ከሚባሉት ቢመደብም) የስኳር መጠን ከፍ እንዲል የማድረግ እድሉ እንደ ካርቦሃይድሬት ምግቦች ከፍ ያለ ላይሆን ይችላል። ግን እንደሰው ይለያያል።

በተሻለ የሚገልጸው ከሆነ ሁሉም የሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ህዋሳቶቻቸው ለካርቦሃይድሬት ምግቦች “አለርጂክ” ናቸው። በሕክምናው ቋንቋ “Carbohydrate intolerance” ከብዙ ዓመታት በፊት ያጋጠማቸው ሰዎች ለህዋሳቶቻቸው ካርቦሃይድሬት ምግቦች አለርጂክ የሆኑባቸው ናቸው እንደማለት ነው። ስለዚህ የሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ እንዳለበት ያወቀ ሰው በአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና በሌሎቹም መንገዶች የስኳሩ መጠን ቢቀንስም መቼም ቢሆን ከፍተኛ መጠን ወደ አላቸው የካርቦሃይድሬት ምግቦች ዳግም መመለስ የለበትም። የብዙ ሰው ስህተት ይሄ ነው።

የሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ እንደ ቁስል በጠባሳ አይድንም። ሁሉንም ዓይነት የማዳፈኛ ዘዴዎች ብንተገብር እንኳን ህዋሳቶቻችን ከሌሎች ምግቦች የሚገኘውን ግሉኮስ እንዲጠቀሙ እና የደም ስኳር እንዳይጨምር ማስቻል ይቻላል እንጂ፣ አንድ ጊዜ ህዋሳቶቻችን ለካርቦሃይድሬት አለርጂክ ከሆኑ በኋላ ይህን ምግብ ወዳጅ ሊያደርጉት አይችሉም። ስንበላው የሚጣፍጠን ካርቦሃይድሬት ህዋሳቶቻችን እንደ “ሬት” መሯቸው የተፉት ስለሆነ ሊቀበሉት አይችሉም።

በሚገርም ሁኔታ ህዋሳቶች ካርቦሃይድሬት እንደመረራቸው ለንቁ አዕምሯችን በግልፅ ይናገራሉ። አንድ የሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ ያለበት ሰው ካርቦሃይድሬት ምግቦችን ሲበላ እንደማንኛውም ሰው አፉ ላይ ይጣፍጡታል። አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ (ካርቦሃይድሬት ምግቦች ወደ ግሉኮስ ተቀይረው ህዋሳቶች ዘንድ ሲደርሱ) ባዶ የሆነው አፉ እንደ ሬት ይመረዋል፤ ከዚያም አልፎ አፉና ጉረሮው ይደርቃል (ብዙ የሰውነት ፈሳሽ ወደ ደም ስር ስለሚመጠጥ)። የህዋሳቶቹ መልዕክት ግልፅ ነው። ይህን ምግብ መቼም ቢሆን አንፈልግም ነው። ጣፋጭ ምግብ የሚወደው እና ምንጊዜም ምግቡ ግሉኮስ የሆነው አንጎል (ንቁ አአምሮ) ደግሞ ካርቦሃይድሬት ምግብ ለመብላት ይጓጓል (የውስጣችን ጥልፍልፎሽ)።

ስለሆነም በየትኛውም ጊዜ ወደ ከፍተኛ የካርቦሃይድሬት ምንጭ ወደሆኑት ምግቦች መመለስ ተገቢ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች ቀድሞ የሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ የነበረባቸው እና መድኃኒት ሲወስዱ የነበሩ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስለምሰራ ምግብ አልመርጥም” ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ምናልባት የጊዜ ጉዳይ ነው ወይም ከስኳር በሽታ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ለረጅም ጊዜ የተዳፈነላቸው ናቸው።

ብዙ ሳይንሳዊ መረጃዎች የሚያሳዩት ለአብዛኞቹ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነት የሚጀምረው ልጅ ገና ማህፀን ውስጥ እያለ ነው። ሌላው ቀደም ብሎ የአንጀት ውስጥ “ጎጂ ያልሆኑ” ይባሉ የነበሩ ተህዋስያን አለመመጣጠን ወይም አንዱ ዓይነት ከመብዛቱ የተነሳ ጎጂ (Gut microbiota dysbiosis) መሆን ሌላው ለብዙ የጤና ችግሮች ምክንያት እንደሆነ መረጃዎች መውጣት ከጀመሩ ቆይቷል። ሁለቱም ከአመጋገብ ባህርይ ጋር ይገናኛሉ። የአንጀት ማይክሮባዮታ (Gut microbiota) የሚባሉት ተህዋስያን (በዋናነት ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች እና ፈንገሶች) በመቶ ትሪሊዮን የሚገመቱ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ የሰው ህዋሳት 10 እጥፍ እንደማለት ነው። የሰው ልጅ እነዚህን ተህዋስያን የሚያገኘው ሲወለድ ጀምሮ ነው። ከአንጀት ማይክሮባዮታ መካከል ባክቴሪያዎቹ በአራት ይመደባሉ (Bacteroidetes, Firmicutes, Actinobacteria, Proteobacteria)። እነዚህ ባክቴሪያዎች ምግብን በማዋሃድ፣ የተለያዩ ቫይታሚኖችን (ቫይታሚን ቢ እና ኬ) በማምረት እና ሁልጊዜም ጎጂ ተህዋስያን (Pathogens) እንዳይራቡ በማድረግ ለሰው ጠቃሚዎች ናቸው።

ለጤና ጎጂ የሚሆኑት አንዱ ዓይነት በዝቶ የሌላው ዓይነት ባክቴሪያ ዝርያዎች ሲያንሱ ነው። የእነዚህ ተህዋስያን አለመመጣጠን በሰው ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እጅግ ብዙ እንደሆነ እየታወቀ ሲመጣ የተመራማሪዎችን ቀልብ በከፍተኛ ደረጃ መሳብ ጀመረ። በተለይ እንዳለፉት አስር ዓመታት የሆነበት ጊዜ አልነበረም፤ እጅግ በጣም ብዙ የምርምር ውጤቶች የወጡት ባለፉት አምስት ዓመታት ነው። የእነዚህ ተህዋስያን በሰው ጤና ላይ የሚያደርሱት ተፅዕኖ ከአንጀት አልፎ አንጎል (Gut-brain axis) እና ሳንባ (Gut-lung axis) እና ሌሎች አካላት ጭምር ድረስ መሆኑን ለማሳየት ተመራማሪዎች እንደዚህ ዓይነት አገላለፆችን ይጠቀማሉ።

የእነዚህ ተህዋስያን ምንጭ ምግብ እንደሆነው ሁሉ መዛባት የሚያስከትለው የምንበላው ምግብ ጭምር ነው። ብዙ የስኳር በሽታ ታማሚዎች በተደጋጋሚ የሚገልፁት ምግብ ከበሉ በኋላ የሆድ መረበሽ (በአብዛኛው የሆድ መነፋት፣ ግሳት እና ጋዝ መብዛት) ምክንያቱ የእነዚህ ተህዋስያን አለመመጣጠን ነው። እነሱም የምንበላውን ምግብ ስለሚመገቡ (የላመ እና በቀላሉ በባክቴሪያ የሚበላ ከሆነ) ከምግብ በኋላ ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል (በየ20 ደቂቃው ይራባሉ)፤ ከፍተኛ ጋዝ (በዋናነት CO2) ያመርታሉ (Fermentation)። የተህዋስያኑ ቁጥር የተመጣጠነ እንዲሆን ፋይበር ያላቸው ምግቦች (በቀላሉ በተህዋስያኑ የማይበሉትን እንደ ቆጮ ዓይነት) ተመራጭ ናቸው። በተለይ የስኳር በሽታ ባለባቸው ሰዎች ላይ የማይክሮባዮታ ብዝሀነትን ከሚቀንሱ ምግቦች መካከል ቀዳሚዎቹ ከፍተኛ መጠን ካሎሪ የያዙ የቅባት እና ከፍተኛ ፕሮቲን የያዙ ምግቦች ናቸው (ለአንዳንድ ሰዎች በተለይ ዘይት እና የቅባት እህሎች)።

የአንጀት ማይክሮባዮታ ብዝሀነትን ጠብቆ ጤናማ ለመሆን ትልቅ ተስፋ የተደረገበት ምርምር (እስካሁን ከ100 በላይ ጥናቶች በቅርቡ የወጡበት) የልየታ ሥራ እየተሰራ ነው። ዋና ዋናዎቹን ለመጠቆም ያክል ሕይወት ያላቸውን ተህዋስያን በመስጠት (Probiotics)፣ አንጀት ውስጥ ላሉት ተህዋስያን የሚስማማ ምግብ በማዘጋጀት (Prebiotics)፣ ሁለቱንም ቀላቅሎ በመስጠት (Synbiotics) እና ከጤናም አንጀት የተወሰዱ ተህዋስያንን በመስጠት (Fecal microbiota transplantation) ማከም እጅግ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተገኘበት ነው። ለጊዜው ማስተላለፍ የፈለግኩት መልዕክት፣ ለአንጀት መረበሽ ምክንያት የሆኑ ምግቦችን በመተው ከዚህ ችግር ጋር ትስስር እንዳላቸው የታወቁ በሽታዎችን እንከላከል። የሆድ መረበሽ ካለ የወሰድነው ምግብ አንዱን ወይም ሁለቱን ዓይነት ባክቴሪያዎች አብዝቶ ሌላውን የቀነሰው ስለሆን ይህን የሚያስከትሉ ምግቦችን ጨርሶ መተው የስኳር በሽታን ለማዳፈንም ሆነ ለመከላከል ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። እዚህ ጋም የአንጀት ህዋሳቶች አልተመቸንም ብለው እየነገሩን አናስገድዳቸው።

ለዘመናት ሳትታወቅ ጤፍ በፈረንጆቹ “የእህል ንጉስ” እንደተባለችው ሁሉ ቆጮም አንድ ቀን ሰው ሠራሽ ሳይሆን ተፈጥሯዊ Prebiotics መሆኑ በሳይንስ ይረጋገጥ ይሆናል። ለማንኛውም ቆጮን ያልተስተካከለ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሁሉ ያዘውትሩት ማለቴ ሳይሆን ሌሎች ቢለምዱት እጅግ ብዙ ዓይነት ከሆኑ የአንጀት በሽታዎች መከላከል ይቻላል። አትክልትና ግልፋፊያቸው ያልተጣሉ ምግቦች ከፍተኛ የቫይታሚን (ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ በሽታ ተከላካይ Antioxidant) ክምችት ስላላቸው እንደዚሁ ማዘውተሩ መልካም ነው። ከፍተኛ ካሎሪ ምግብ ከመሆኑ በተጨማሪ ምናልባት በእሳት ሲጠበስ ብዙ ጤናማ ያልሆኑ ኬሚካሎች ስለሚፈጠሩ ዘይት በብዙ ሰዎች ላይ ስኳር እንዲጨምር ያደርጋል፤ አልፎም የሆድ መረበሽ ስለሚያስከትል የማይስማማዎት ከሆነ ቢተውት መልካም ነው። እዚህ ጋ ነው ለሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ታካሚ ዶክተር እራሱ ነው የሚባለው። የተወሰኑ የቅባት ምግቦች/አሳን ጨምሮ (Omega-3 fatty acids) ሳይበዛ (አንጀት ውስጥ ያሉ ባክቴሪያዎች ቁጥር የተመጠነ እንዲሆን፣ insulin resistance እንዲቀንስ፣ ለሰውነትና ለጉበት ብግነት መጋለጥ እንዳንጋለጥ እና የግሉኮስ በጡንቻ ህዋሳት መጠቀም እንዲጨምር ስለሚያደርጉ) የሚስማማውን (የስኳር መጠን የማይጨምረውን) መርጦ መጠቀሙ መልካም ነው።

እየረዘመ ስለሆነ ለማጠቃለል፣ የመጀመሪያው ስኳር በሽታ ሲጨምርም ሆነ ሲቀንስ ወይም ሲስተካከል በጣም ረጅም ጊዜ ወስዶ ነው። እንዲያም ሆኖ አንድ ችግሩ ያለበት ጎልማሳ ለሳምንታት ጠንከር ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቢያደርግ ስኳር ከደሙ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ይህ ማለት ግን ተዳፈነ ማለት አይደለም፤ እንቅስቃሴውን ካቆመ ወደነበረበት ይመለሳል። ስለዚህ ከጅምሩ በአጭር ጊዜ የስኳር መጠኔን አስተካክዬ ከመድኃኒት ነፃ እወጣለሁ ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም። ትዕግስት ይፈልጋል። እያንዳንዷ ህዋስ በነባራዊው ዓለም ከምናየው በላይ እጅግ ውስብስብ ሂደት ያለበት ስለሆነ ለመስተካከል (ወደ ቀድሞ ተግባር ለመመለስ) ጊዜ ይፈልጋል። በቂ እንቅስቃሴ እያደረግን ጭምር ግሉኮሳችን ከፍ እንዳለ ከሆነ መድኃኒት መውሰድ አለብን። መድኃኒቱ ግሉኮስን ከሰውነታችን ጋር አዋሃጅ ስለሆነ በአንድ ጊዜ መቋረጥ የለበትም። ርምጃዎቻችን ሁሉ ቅንጅታዊ መሆን አለባቸው (ቢያንስ እዚህ የተጠቀሱትን ስድስቱንም መፈፀም ያስፈልጋል)።

ከሰማናቸው ምክሮች መሃል ሌሎችም ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡ አሉ።

  1. ዶ/ርደምሴለሁለተኛውዓይነትስኳርበሽታዋናመንስኤዎች (causes) ብለው የጠቀሷቸው፡

1) የቆየ ስትረስ (Chronic stress)

2) በሰውነት ሁሉ የተሰራጨ ብግነት (chronic systemic inflammation)

3) የኢንሱሊን መጠን በከፍተኛ ደረጃ መጨመር (Hyperinsulinemia)

የቆየ ስትረስ ስትረስ ሆርሞን የሚባሉት ለወራትና ለዓመታት እንዲጨምሩ የሚያደርግ፣ እነዚህ ሆርሞኖች ደግሞ ኢንሱሊን በትክክል እንዳይሰራ የሚያደርጉ ከመሆኑም በላይ ለሁለተኛውና ለሶስተኛው ችግር ጭምር እንደሚያጋልጡ ይታወቃል። ይሁን እንጂ አንድ እና ሁለት ለብዙ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች (ሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታን ጨምሮ) ዶ/ር ይሁን እንዳሉት አጋላጭ (factor) ተደርገው የተወሰዱ እንጂ መንስኤ (causes) ናቸው ተብለው እስካሁን በሳይንስ አልተረጋገጡም። አንደኛው ለሁለተኛው፣ ሁለተኛው ለውፍረት ሳይቀር ለብዙ የጤና ችግሮች እንደ አጋላጭ ምክንያት ተደርጎ ሲጠቀስ ቆይቷል። ሶስተኛውም ቢሆን እንዲከሰት ያደረገው በቀዳሚነት በደም ውስጥ የስኳር መጠን መብዛት ቢሆንም በተወሰነ ደረጃ የአንደኛውና የሁለተኛው ችግሮች ጭምር የሚያስከትሉት ነው ተብሎ በስፋት ይገለፃል። ለHyperinsulinemia የዳረገው በህዋሳት ደረጃ ግሉኮስን መጠቀም አለመቻል እንደሆነ እሳቸውም ገልፀዋል። ይህ ደግሞ ምክንያቱ ከመላምት ያለፈ በትክክል አይታወቅም።

ስለዚህ ሶስቱ መንስኤ ናቸው (“Primary causes”) ተብሎ የተገለፀው ሳይንሳዊ መሠረት የለውም። ምክንያቱም አንድ እና ሁለት ያላቸው ሰዎች ሁሉ የእነዚህ በሽታዎች ተጠቂ አይደሉም። መሠረታዊ ሳይንስ (animal model) ላይ በተሠሩ ጥናቶች ልዩነት እንጂ መንስኤ እና በሽታ (cause and effect relationship) ማምጣት እስካሁን አልተቻለም። ከዚህ በተጨማሪ ካርቦሃይድሬት ምግብ ለብዙዎች ጤናማ ነው። በሌላ ምክንያት Hyperinsulinemia ያላቸው ሁሉ የስኳር በሽታ ሳይሆን ለተቃራኒው የስኳር መቀነስ (Hypoglycemia) የተጋለጡ ናቸው። ስለሆነም ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ላለባቸው Hyperinsulinemia መንስኤ ሳይሆን በinsulin resistance (ሰውነታችን የማይፈልገውን ምግብ በማብዛት ወይም ባለማቃጠል የሚከሰት) ምክንያት የሚመጣ (secondary complication) እንጂ ከጅምሩ መንስኤ ተደርጎ እንዲወሰድ የሚያሳይ መረጃ የለም። ምክንያቱም ከሱ ቀድሞ የተፈጠረ ችግር አለና።

  1. “ምልክቱንእንጂበሽታውእየታከመአይደለም” የተባለውምበሕዝብዘንድትልቅብዥታየሚፈጥርነው

በመጀመሪያ ደረጃ የአንድ በሽታ መነሻ መንስኤው በግልፅ ሲታወቅ ነው እንዲህ ዓይነት አስተያየት ተገቢነት የሚኖረው። ብዙ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (የስኳር በሽታን ጨምሮ) መንስኤቸው ስለማይታወቅ ሁልጊዜም የሚታከመው ምልክቱ ነው። መንስኤው ቢታወቅማ በአንድ ጊዜ እንደ ተህዋስያን በሽታ አክሞ ማዳን ይቻል ነበር። ብዙ ሳይዘረዘር ልክ እንደ ስኳር በሽታ ሕዝቡ በስፋት የሚያውቃቸው የደም ግፊት፣ ካንሰር፣ የሚጥል በሽታ፣ ሪህ፣ አስማ ዓይነቶቹ የሚታከመው ምልክቶቹን ነው፤ እንዳይጨምሩ ወይም እንዳይብሱ ማድረግ ነው። ለእነዚህና ሌሎች መሰል በሽታዎች እስካሁን በሽታውን የሚያጠፋ መድኃኒት አልተገኘም (ተስፋ የሚደረግበት ግንደ-ህዋስ ምርምር/Stemcell research እንኳን ገና ወደ ተግባር አልተቀየረም)።

ስለሆነም የስኳር በሽታ በመድኃኒት ሲታከም በቅድሚያ የሚታከመው ቀጣይ ቀውስ (Secondary complication) የሆነው የደም ስኳር መጨመር (Hyperglycemia) ነው። ይህ ደግሞ በበዛው የስኳር መጠን ሊከተሉ የሚችሉ እጅግ ከባድ ቀውሶችን (Tertiary complications) ለመከላከል ያስችላል። ስለዚህ ሕዝቡ ልብ ሊል የሚገባው የሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ ሕክምናም ሆነ ከላይ የተጠቀሱት ስድስቱ የመፍትሔ ሃሳቦች ተመሳሳይ እና ዋና አላማቸው የበሽታውን ግስጋሴ መግታት ነው (Disease progression arrest)። የበሽታው መንስኤ ስለማይታወቅ እና ስለማይድን በደም ውስጥ ስኳር እንዳይበዛ በማድረግ ጤናማ ሕይወት መምራት ነው የሁለቱም መንገዶች ዘላቂ አላማ።

ሌላው አንባቢያን ልብ ሊሉት የሚገባው፣ ባለሙያዎችም አበክረው የሚመክሩት፣ ከላይ የተዘረዘሩት ስድስቱ ርምጃዎች ከመድኃኒት፣ መድኃኒትን ከእነሱ ለይተው አይደለም። አንዱ ለአንዱ ተደጋጋፊ (Synergistic) የሆነ ውጤት ነው ያላቸው፤ መድኃኒትም ሆነ ስድስቱ ምክሮች አላማቸው ስኳር ደም ውስጥ እንዳይበዛ ነው። የዚህ ጽሑፍም ትልቁ መልዕክት በስድስቱ ምክሮች ስኳር ከደም ውስጥ እስኪስተካከል ድረስ መድኃኒት እንዲቀጥሉ ነው። የስድስቱ ምክሮች የመጀመሪያው ውጤት የሚባለው የሚወሰደውን መድኃኒት ከመቀነስ እስከማቆም መድረስ ነው። መንስኤው ስላልጠፋ (ተጋላጭነት ወይም ህዋሳት ከካርቦሃይድሬት ምግብ ጋር ያላቸውን “ፀብ” አይረሱምና) ሕክምናው ወይም መከላከያው ሲቋረጥ ተመልሶ ይጨምራል። ስለዚህ ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ አይድንምና ተዳፍኖ እንዲቆይ ለማድረግ (Maintaining remission) ስኳር ከደም ውስጥ እስኪስተካከል ድረስ መድኃኒትን ጨምሮ ሁሉንም የመከላከያ ዘዴዎች መተግበር፣ ስኳሩ በአስተማማኝ ሁኔታ ቀንሶ ሳለ ስድስቱን የመከላከያ ዘዴዎች እድሜ ልክ መተግበር ግድ ይላል።

በተሻለ ለመረዳት አንድ ሰው የካንሰር በሽታ ሲገኝበት በመድኃኒት፣ በቀዶ ህክምና፣ በጨረር እና ኢሙኖቴራፒ በሚባል የሚታከመው ምልክቱ ነው (የካንሰር ህዋሳት ቁጥር እንዲቀንስ ለማድረግ/Remission ለማሳካት ነው)። ካለበለዚያማ ከጥቂት የካንሰር ዓይነቶች (መዳን ከሚችሉት) ውጭ ያሉት የጊዜ ጉዳይ እንጂ ተመልሶ ይስፋፋል። የስኳር በሽታ ከካንሰር የሚለየው መስፋፋቱን (ቀውስ እንዳያመጣ) ለረጅም ጊዜ መቆጣጠር መቻሉ ነው። “መድኃኒቱ እድሜ ማራዘሚያ እንጂ አያድንም” የተባለውም አዎ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለሆኑት ሁሉ የሕክምናው አላማ እድሜ ማራዘም እንጂ ማዳን (Cure) አይደለም። ግን ምን ያክል ያራዝማል የሚለው ነው ቁምነገሩ።

  1. “የሁለተኛውዓይነትየስኳርበሽታመመርመሪያዘዴመንስኤውንቀድሞለማወቅሳይሆንዘግይቶምልክቱንለማወቅነው” መባሉምያለውንነባራዊሁኔታከግምትያስገባአይደለም።

እንደተባለው ቢቻልና ቅድመ ስኳር በሽታ ልየታ የሚደረግበት አቅም ቢገነባ መልካም ነበር። ቢያንስ ቀድሞ ለመጠንቀቅ ከማገዙም በላይ አብዛኛውን ጊዜ የሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ ብዙ ጉዳት ካደረሰ በኋላ (ዘግይቶ) ከመታወቅ ይታደግ ነበር። ነገር ግን እስካሁን በዓለም ላይ በህዋሳት ወይም በሆርሞን ደረጃ ያለን ችግር (ለምሳሌ Insulin resistance, hyperinsulinemia, Beta-cell susceptibility) በምርምር ላቦራቶሪ (በሪሰርች ደረጃ) እንጂ ለሕዝብ አገልግሎት አልዋለም። ምናልባት ወደፊት አንድ ጠቋሚ የህዋስ ኬሚካል (Biomarker) ሲገኝ ለቀድሞ ልየታ (Screening) ይውል ይሆናል። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ባሉት የምልክት መመርመሪያዎች ሕዝቡ እንዲጠቀም ማበረታታት እንጂ ማጣጣሉ የበለጠ እንዳያሳንፍ ጥንቃቄ ማድረጉ መልካም ነው።

  1. ሌላውአልፎአልፎ (እስከሶስትቀንጭምር) መፆምንአበረታተዋል።

ርግጥ ነው መፆም ለሰውነት መልካም እንደሆነ በሳይንስ ይታወቃል፤ የአንጀት ማይክሮባዮታ የተመጣጠነ እንዲሆን እና ብዙ ዓይነት በሽታዎችን (በተለይ ከምግብ መወሃድ እና በህዋሳት መጠቀም ድክመት ጋር የተያያዙትን ለመከላከል እና ለማከም) ጠቀሜታው ከፍ ያለ እንደሆነ ብዙ ሳይንሳዊ መረጃዎች ወጥተዋል። የሰውነት ክብደትን መቆጣጠሪያ አንዱ መንገድ ነው። ህዋሳትን ለተወሰነ ጊዜ ማስራብ ከዚያው ከሰውነታችን ህዋሳት ውስጥ በስብ መልክ የተከማቸውን መቀነሻ መንገድ ስለሆነ መድኃኒት የማይወስዱ ሁሉ ሶስት ቀን ቀርቶ ግማሽ ቀንም አልፎ አልፎ ቢያዘወትሩት መልካም ነው። ነገር ግን የስኳር መድኃኒት ለሚወስድ ሰው እጅግ አደገኛ ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ይደረግበት ተብሎ መመከር አለበት። ሐኪሞቻቸው ከሚመክሯቸው (መድኃኒት ከወሰዱ ከአንድ ሰዓት በኋላ ምግብ እንዲወስዱ) ጋር የሚጋጭ ስለሚሆን ውዥንብር ውስጥ እንዳይገቡ ምክሩ ተለይቶ መሰጠት አለበት። መጾም ደረጃ ያለው ሲሆን ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ከሆነ ክብደት ለመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ስለሆነ ጠንከር ካለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር ተመሳሳይ ውጤት አለው። ነገር ግን የተመጠነ እና በሂደት ካልሆነ ለበሽታና ለከፍተኛ ስኳር መቀነስ እንዳይዳርግ በባለሙያ የተደገፈ እና ከተመጠነ አመጋገብ ጋር መሆን አለበት።

  1. “ፍሩክቶስመርዝነው” መባሉከባድአስተያየት ነው።

ይህን ለሚሰማው ሰው የሚያስደነግጥ ነው (ያውም ብዙ ዓይነት ፍራፍሬ እንዲጠቀም የተመከረ እና ሲጠቀም የኖረ፤ ማር ሲመገብ ለኖረ ሕዝብ)። ሕዝባችን በዚህ ደረጃም አይገነዘቡትም (ጉበት ላይ የስብ ክምችት ያመጣል በሚለው)። የምግብ ምንጮቹን መጥቀስ እንደዚሁ ብዙ ሰውን የሚያሳስት ሊሆን ይችላል። በሆነ ጊዜ “ቀይ ስር እና ጤፍ ምንም ምግብነት የላቸውም” መባሉ ፍፁም ስህተት እንደነበረው ሁሉ ፍሩክቶስም ለሁሉም እንዳልሆነ (ለምሳሌ ላክቶስ እማይስማማው እንዳለ) ግንዛቤ መያዝ አለበት። ምክሩ የሁለተኛውን የስኳር በሽታ መቆጣጠር አቅቶት ወይም በሌላ ምክንያት በአልትራሳውንድ በጉበቱ ላይ የስብ ክምችት ለታየበት ሰው ቢሆን ባልከፋ ነበር። ፍሩክቶስ በመድኃኒት መልክ ይሰጥ ይመስል ከፍራፍሬ በትንሽ መጠን የሚገኘውን ለሁሉም በዚህ ደረጃ ባይፈረጅ መልካም ነው።

ለማንኛውም ጅምሩ እጅግ የሚበረታት ስለሆነ ማህበር መቋቋም አለበት እላለሁ።

ብዙዎች እንዲማሩበት እና እንዲበረታቱ ሁለተኛውን ዓይነት የስኳር በሽታ ያዳፈኑ ማህበር ማቋቋም ጠቀሜታው እጅግ ብዙ ይሆናል። መጀመሪያ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላት ሊኖሩት ይችላሉ። በሂደት በሺህ የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ አባላት ይኖሩታል። ይህ ደግሞ ትልቅ ድርጅት ሆኖ መጭውን ትውልድ የሚታደግ ይሆናል። ስለዚህ ዶ/ር ደምሴ እና አዘጋጆቹ ያነሱት ሃሳብ ሊደገፍ ይገባል። ከመነጋገር እና ልምድን ከመለዋወጥ ብዙ መማር ይቻላል። ስለሆነም እነ ዶ/ር ደምሴን ከጅምሩ ሳንነቅፍ በሳይንሳዊ መረጃ እንሞግታቸው። ትክክለኛውን አካሄድ የሚከተሉ ተከታዮችን እናብዛላቸው። ማጠቃለያው ህዋሳቶቻችን ሲናገሩ ንቁ አዕምሯችን ያዳምጥ የሚል ነው። በመሰል ርዕስ እስክንገናኝ ሰላም እንሰንብት፡፡

ከዚህም ሰፋ አድርገው ማንበብ ለሚፈልጉ፡ chronic/ oxidative stress “systemic inflammation “insulin resistance/unresponsivecells ” hyperglycemia ” hyperinsulinemia” liver & pancreasfat deposition” hypoinsulinemia” worsen hyperglycemia & fat deposition”systemic complications (የደም ስር፣ የኩላሊት፣ የነርቭ፣ የዓይን እና የሌሎችም ችግሮች)፡፡

የአንጀት ተህዋስያን አለመመጣጠን ለአጠቃላይ ሰውነት ብግነት (chronic systemic inflammation), inflammatory bowel syndrome, irritable bowel syndrome, metabolic diseases (including type II diabetes and obesity), different psychiatric disorders, autoimmune diseases, የአንጀት ካንሰር ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡

ይፍሩ ብርሃን (ፕ/ር)

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You