የዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት

ኢትዮጵያ ከአንድ መንግሥት ወደ ሌላ መንግሥት ለውጥ ስታደርግ ጦርነቶች እንደነበሩ የቆዩ ታሪኮችን የታሪክ ድርሳናት፣ የቅርቦችን ደግሞ በሕይወት ያሉ ሰዎች ይመሰክራሉ። ለ27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የቆየው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ሞቅ ቀዝቀዝ ሲሉ የቆዩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሲደረጉበት ቆይቷል። ከ2008 ዓ.ም አካባቢ ጀምሮ ግን በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልል አካባቢዎች ጠንከር ያሉ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች አጋጠሙት። በግንባሩ ሁለት ድርጅቶች (ኦህዴድ እና ብአዴን) አመራሮች የኢህአዴግን ጥፋት በግልጽ የመናገር ምልክቶች ታዩ፤ ይህኔ ሕዝብ ወኔ አገኘ። በመጨረሻም ኢህአዴግ ለ17 ቀናት ያህል በር ዘግቶ መከረ። አራቱ የግንባሩ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ አሉ። ‹‹በስብሰናል፣ አጥፍተናል›› እያሉ ተናገሩ። በመጨረሻም ለውጥ መምጣት እንዳለበት ታመነ!

እነሆ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ! ‹‹ፖለቲካና ኤሌክትሪክን በሩቁ›› ይባል የነበረው የፖለቲካ ባህል ተቀየረ። መንግሥትን ለመቃወም ሰልፍ ይወጣባቸው የነበሩ አደባባዮች መንግሥትን ለመደገፍ በሚወጣ ሰልፈኛ ተጥለቀለቁ።

ዶክተር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ማግስት ጀምሮ በተለያየ ዘርፍ ውስጥ የሚገኘውን የማህበረሰብ ክፍል ማወያየት ጀመሩ። መምህራንን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎችን፣ ባለሀብቶችን… በየደረጃው ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል አወያይተዋል። በተለያዩ አካባቢዎች እየሄዱም ነዋሪውን አወያይተዋል።

እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉዞ እዚህ ደርሶ እነሆ ዛሬ እየታወሰ ነው። ለአሥርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት፣ እስር ቤት ተረስተው የነበሩ የፖለቲካ አመራሮችና ጋዜጠኞች መፈታት፣ በተቃውሞ ጎራ የነበሩ አካላት ወደ ፍትሕ ተቋማትና ወደ ካቤኔ መግባት፣ ለዓመታት ተረስቶ የነበረው የወደብ ጉዳይ መነሳት፣ አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ ከተማ መሆኗን የሚመሰክሩ ትልልቅ ውብ ፕሮጀክቶች መሠራታቸው… የለውጡን መንግሥት በዚች ስድስት ዓመት ውስጥ ብቻ በታሪክ ሰነድ ውስጥ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርጉ ናቸው። የተጀመሩት ሲያልቁ ደግሞ የሺህ ዘመናት ደማቅ ታሪክ እንዲኖረው የሚያደርጉ ናቸው።

ያም ሆኖ ግን ባለፉት ዓመታት እጅግ ነውር የሆኑ ክስተቶችም ታይተዋል። አውዳሚ የእርስ በእርስ ጦርነት ተካሂዷል፤ አሁንም እየተካሄደ ነው። ሀገር አቋራጭ አውራ ጎዳናዎች በተደጋጋሚ ተዘግተዋል። የጋዜጠኞች መታሰር እና የፖለቲከኞች ‹‹ፍትሕ የለም›› ወቀሳ አሁንም አለ።

በጎ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን ጥፋቶችንም ታሪክ ያስቀምጣልና አኩሪ ታሪክ ደምቆ እንዲጻፍ ጥረት ይደረግ እንላለን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You