የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ታሪክ መስካሪው

ዋለልኝ አየለ እርሳቸው የ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ክስተት ናቸው፡፡ 20ኛው ክፍለ ዘመን ሲገባ (1901 ዓ.ም) የ10 ዓመት ታዳጊ ናቸው፡፡ ከዚህ ዕድሜ በኋላ ትምህርት የጀመሩበትና ነገሮችን በመኖር እና ማስታወሻ በመያዝ የሰነዷቸው ናቸው። 20ኛው ክፍለ ዘመንን እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ ኖረውበታል፡፡

መስርዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ! በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ125 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 17 ቀን 1891 ዓ.ም የተወለዱትን መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስን በዝርዝር እናስታውሳለን፡፡ ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት የታሪክ ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውስ፡፡

ከ146 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 18 ቀን 1870 ዓ.ም ንጉስ ምኒሊክ (ገና የሸዋ ንጉሥ ሳሉ) የንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ 4ኛን የበላይነት (ንጉሠ ነገሥትነት) የተቀበሉበትና አፄ ዮሐንስ 4ኛም የምኒሊክን የሸዋ ንጉሥነት የተቀበሉበት (ያፀኑበት) የልቼ ስምምነት ተፈረመ፡፡

ከ116 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 19 ቀን 1900 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ እንስሳት የታመመበት ሰው ሁሉ እንስሳውን እንዲያሳክምና እንስሳው ከሞተም በሽታው ወደ ሌሎች ነፍስ ያላቸው አካላት እንዳይዛመት የሞተው እንስሳ በአግባቡ እንዲቀበር ትዕዛዝ የሚያስተላልፍ አዋጅ አስነገሩ፡፡

ከ63 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 21 ቀን 1953 ዓ.ም ከታኅሣሥ 1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጠንሳሾችና መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ በስቅላት ተገደሉ፡፡ ከ43 ዓመታት በፊት መጋቢት 21 ቀን 1973 ዓ.ም በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበረው ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ አረፈ፡፡

ከ94 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ልክ በዛሬዋ ቀን መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም የአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን የንጉሠ ነገሥትነት መንገድን የጠረገው (ያመቻቸው) እና ራስ ተፈሪ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር ካደረጓቸው ታላላቅ ጦርነቶች መካከል የመጨረሻው ውጊያ የነበረው የአንችም (ደብረ ዘቢጥ) ጦርነት ተካሄደ። ከ88 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ ሽንፈትን ያስተናገደችበትና ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ የወረራ ሙከራ ያደረገበትና ለአምስት ዓመታት ያህል በከፊል እንዲቆጣጠር ያስቻለው የማይጨው ጦርነት ተካሄደ፡፡

በዝርዝር ወደምናየው የመርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ ታሪክ እንሂድ፡፡ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መጋቢት 17 ቀን 1891 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ አባታቸው አለቃ ወልደ ቂርቆስ አልታመን በደብረ ሊባኖስና በእንጦጦ ማርያም የቤተልሔምን መዝገበ ድጓ ሲያስተምሩ የነበሩና በዜማ መምህርነት የታወቁ ሰው ነበሩ፡፡ የአባታቸው አጎት አለቃ ገብረ ክርስቶስ የብሉይና የሐዲስ ሊቅ እንዲሁምና የቅኔ መምህር የነበሩና በንጉሥ ኃይለ መለኮት፣ በአጼ ዮሐንስ 4ኛ እና በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት እጅግ የተከበሩ ሰው ነበሩ፡፡

የአባታቸውና አጎታቸው ሊቅነት መርስዔ ኀዘንም የእነርሱን ፈለግ ተከትለው እንዲጓዙ አስተዋፅዖው ቀላል አልነበረም፡፡ ሕፃኑ መርስዔ ኀዘን አራት ዓመት ሲሞላው ፊደል መቁጠር ጀመረ፡፡ በ1896 ዓ.ም ወደ እንጦጦ መጥቶ ንባብ ተማረና ዳዊት ደገመ፡፡ ቀጥሎም የዜማ ትምህርት በመጀመር ጾመ ድጓና ድጓን አጠናቀቀ። ከ1901 እስከ 1904 ዓ.ም በጅሩና በአዲስ አበባ ከታላላቅ የዘመኑ ሊቃውንት የቅኔ ትምህርት ተማረ፡፡

በ1906 ዓ.ም በቀኛዝማች ናቄ ዘንድ የጸሐፊነት ሥራ ተቀጥሮ ለአንድ ዓመት ከአራት ወራት ያህል ካገለገለ በኋላ በአባቱ ወዳጅ በአቶ ሕለተ ወርቅ እሸቴ ምክር የጸሐፊነቱን ሥራ ትቶ በነሐሴ ወር 1907 ዓ. ም ወደ ትምህርት ገበታው ተመለሰ። ከዚህ በኋላ የመጻሕፍት ሐዲሳትንና የዮሐንስ አፈ ወርቅ ትርጓሜዎችን ከታላላቅ መምህራን ተማረ፡፡ ወጣቱ መርስዔ ኀዘን በ1912 ዓ.ም በስመ ጥሩው ሊቅ በአለቃ ገብረ መድኅን አማካኝነት የመንግሥት ሥራ ጀመረ። ሥራውም የትርጓሜ ሥራ መሥራትና የትርጓሜውን ንባብ ከነትርጉሙ ለኅትመት ማዘጋጀት ነበር።

በወቅቱም ‹‹አረጋዊ መንፈሳዊ›› ከተባለውና አልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን በ1920 ዓ.ም ድሬዳዋ ላይ ካሳተሙት ሥራ በተጨማሪ ሌሎችን የትርጓሜ ሥራዎችንም አዘጋጅቶ አቅርቧል። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመማር ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ ይሁን እንጂ ከሦስት ወር በኋላም የትርጓሜ ሥራውን ብቻ እንዲሠራ ስለታዘዘ የቋንቋ ትምህርቱን አቋረጠ። የቋንቋ ትምህርቱ ስለመቋረጡ ‹‹ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው›› በሚል ርዕስ በ2005 ዓ.ም ላይ ታትሞ በወጣው የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የግለ ታሪክ መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው ተገልጿል።

‹‹… የቋንቋ ትምህርት መጀመሬንም እንዳይሰሙብኝ ለማድረግ ተጣጣርሁ። ዳሩ ግን ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለሌለ ወሬውን ሰምተው ጠሩኝና እያዘኑ ክፉኛ ገሠጹኝ። ‹ዳግመኛ ወደዚያ ስፍራ እንዳትመለስ› ብለውም አስጠነቀቁኝ። እንግዲህ የተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት እስከተከፈተ ድረስ የቋንቋ ትምህርቴን አቋርጬ ተቀመጥሁ። ጌታ አለቃ ገብረ መድኅን ይህን ማድረጋቸው በእርሳቸው አስተያየት እኔን ለመጥቀም እንጂ ለክፋት እንዳላደረጉት ሕሊናዬ ስላወቀ አላዘንሁባቸውም … ›› ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም በአልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን አማካኝነት ‹‹ብርሃንና ሰላም›› የተባለ ጋዜጣ ሲመሠረት ወጣቱ መርስዔ ኀዘን ወደ ጋዜጠኛነት ተዛውሮ በዋና ጸሐፊነት መሥራት ጀመረ። ከአራት ወር በኋላም ሚያዝያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርቆ ሲከፈት የግዕዝና የአማርኛ አስተማሪ ሆኖ ወደ ትምህርት ቤቱ ተዛወረ። በዚህ ጊዜ ያሰናዳት ‹‹ትምሕርተ ሕፃናት›› የተባለች መጽሐፍ ግንቦት 1 ቀን 1917 ዓ. ም ታትማ ወጣች፤ የግብረ ገብ ትምህርት ማስተማሪያም ሆነች።

በዚህ ጊዜ መርስዔ ኀዘን ቀደም ሲል አቋርጦት የነበረውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ለመማር በትጋት ጥረት ማድረግ ጀመረ። ከአንድ ዓመት በኋላ ጽፎ ያቀረበው ‹‹በአዲስ ሥርዓት የተሰናዳ የአማርኛ ሰዋስው›› የተሰኘው ሥራ በደብተር እየተገለበጠ የተማሪዎች መማሪያ ሆኖ በአገልግሎት ላይ ዋለ። ይህ ሰዋስው በኋላ ከፋሺስት ኢጣሊያ ጦር መባረር በኋላ በ1935 ዓ.ም ታትሞ የወጣው ነው።

ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ለኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የሰዋሰው ማስተማሪያ ሆኖ አገልግሏል። ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ከሕክምና ሙያቸው በተጨማሪ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ‹‹የዓለም ጂኦግራፊ›› መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ ጽፈው ነበር፡፡ ሐኪም ወርቅነህ መጽሐፉን እንደገና ባረሙበትና ለሕትመት ባዘጋጁበት ወቅት መርስዔ ኀዘን ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡ ሐኪም ወርቅነህም በ1920 ዓ.ም በታተመው በዚሁ መጽሐፋቸው መቅድም ላይ ‹‹ይህንም ለማረም ምሑር የሆነ ወዳጄ አቶ መርስዔ ኀዘን በትዕግሥትና በልበ ፈቃድ ከእኔ ጋር በማረም ረዳኝ፤ ቀጥሎ መጽሐፉ ሲታተም ግድፈቱን እያረመ አሳተመልኝ፤ ይህን የመሰለ እርዳታ ባላገኝ ኖሮ ይህ የጂኦግራፊ ትርጉም ወደ ፍጻሜ ባልደረሰም ነበር›› በማለት ምስጋና አቅርበውለታል።

በ1922 ዓ.ም ወደ ጂግጂጋ በመዛወር በዚያ ለተከፈተው ራስ መኮንን ትምህርት ቤት ዋና ሹም በመሆን ለአምስት ዓመታት አገልግሏል። ከትምህርት ቤቱ ዋና ሹምነት በተጨማሪም በወሰን አከላለል ሥራ ላይ ኃላፊነት ተሰጥቶት ሠርቷል፡፡ መርስዔ ኀዘን በታኅሣሥ ወር 1924 ዓ.ም በተጀመረው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሱማሌላንድ የወሰን አከላለል ሥራ እስከተጠናቀቀበት እስከ የካቲት ወር 1927 ዓ.ም ድረስ በዋና ጸሐፊነት አገልግሏል።

ወራሪው የፋሺስት ኢጣልያ ጦር ኦጋዴን ውስጥ ወልወል በተባለው ስፍራ ላይ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ላይ አደጋ ባደረሱበት ጊዜ መርስዔ ኀዘን በስፍራው ተገኝቶ አደጋውን በመከላከል ሥራው ላይ ተሳትፏል። በፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ዓመታት በጅሩ፣ በአድአና በሌሎች አካባቢዎች እየተዘዋወረ በነፃነት ተጋድሎው ላይ ተሳትፎ አድርጓል። መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ ወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ በተለያዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል፡፡

መርስዔ ኀዘን በ1936 ዓ.ም የ‹‹ብላታ››ነት ማዕረግን አግኝተዋል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ኃላፊነቶቻቸው በተጨማሪ (በመደበኛ ሥራቸው ላይ ደርበው) የአንጋፋው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሹም ሆነው ለ14 ዓመታት፤ የሕዝብ ጤና ሚኒስቴር ተጠባባቂ ሹም ሆነው ደግሞ ለአንድ ዓመት ሠርተዋል። በብዙ ድርጅቶች የሥራ አስፈፀሚ ቦርዶችም በአባልነትና በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል። ከእነዚህም መካከል ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ቦርድ ሊቀ መንበር (1946-54 ዓ.ም)፣ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ቦርድ አባል (1940-54 ዓ.ም)፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ቦርድ አባልና ምክትል ሊቀ መንበር (1942-66 ዓ.ም)፣ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ) ቦርድ አባልና ምክትል ፕሬዚዳንት (1941-1966 ዓ.ም) ይጠቀሳሉ፡፡

ከብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ ሥራዎች ሁሉ ጎላ ብለው የሚጠቀሱላቸው የድርሰት ሥራዎቻቸው ናቸው። በተርጓሚነት፣ በአዘጋጅነት እና በደራሲነት ባገለገሉበት ጊዜ ከ35 በላይ የሚሆኑ መጽሐፍትን ለሕትመት እንዲበቁ አድርገዋል፡፡ ከድርሰት ሥራዎቻቸው (የትርጉሞቹን ጨምሮ) እነዚህ ይጠቀሳሉ፡፡ ትምህርተ ሕፃናት፣ የአማርኛ ሰዋስው፣ የአማርኛ ሰዋስው መክፈቻ፣ የአማርኛ ሰዋስው አንደኛ ክፍል፣ የአማርኛ ሰዋስው ሁለተኛ ክፍል፣ የትዕምርተ መንግሥት ታሪክ፣ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጎንደርን የመጎብኘታቸው ታሪክ፣ ዐውደ መዋዕል፣ የኢትዮጵያ መዝገበ ዕለታት፣ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፡ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ፡ ካየሁትና ከማስታውሰው (1896-1922)፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (1922-1927)፣ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት፣ የንጉሥ ሣሕለ ሥላሴ ዕረፍት መታሰቢያ፣ ጥበብን መፈለግ፣ ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ 1ኛ መጽሐፍ፣ ጥበብን መፈለግ፣ ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ 2ኛ መጽሐፍ፣ ጥበብን መፈለግ፣ ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ 3ኛ መጽሐፍ፣ ፍሬ ከናፍር፣ ሔሮዶቱስ፣ 1ኛ መጽሐፍ – የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው፣ ሔሮዶቱስ፣ 2ኛ መጽሐፍ – የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው፣ ሔሮዶቱስ፣ 3ኛ መጽሐፍ የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው … የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ ከተዘጋጁ ሃይማኖታዊ መጻሕፍት መካከል ደግሞ ‹‹አረጋዊ መንፈሳዊ››፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ጸሎት››፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ዜና››፣ ‹‹መጽሐፈ ቅዳሴ በግዕዝና በአማርኛ››፣ ‹‹ሢመተ ሊቀ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ››፣ ‹‹የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ›› እና ‹‹ቅዳሴ በእንግሊዝኛ (ትርጉም)›› ይጠቀሳሉ፡፡ ከነዚህ ሥራዎቻቸው በተጨማሪም ከስድስት በላይ ያልታተሙ ሥራዎች እንዳሏቸው ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

በሃይማኖታዊ ጉዳዮችና ጽሑፎች ላይ የጎላ ተሳትፎ የነበራቸው ብላታ መርስዔ ኀዘን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ እንድትሾም በኢትዮጵያና በእስክንድርያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በሚደረገው ድርድር ተካፋይ እንዲሆኑ ተመርጠው እስከድርድሩ ፍጻሜና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ የአቡነ ባስልዮስ ሲመት እስከሚፈጸም ድረስ ተሳታፊ ሆነው አገልግለዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ አራሚ ኮሚቴ እንዲሁም በ1942 ዓ.ም የወጣው መጽሐፈ ቅዳሴ አዘጋጅ ሆነው ሠርተዋል፡፡

መጋቢት 17 ቀን 1946 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ የፍትሐ ነገሥት ኮሚሲዮን (የኮዲፊኬሽን ኮሚሽን) ሲቋቋም የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሆነው የተሾሙት የፍርድ ምክትል ሚኒስትሩ ብላታ መርስዔ ኀዘን ነበሩ። የኮሚሽኑ አባላት ሦስት የታወቁ የአውሮፓ የሕግ ፕሮፌሰሮችና የካበተ የባሕልና የሕግ ዕውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ነበሩ። የኮሚሽኑ ዓላማ በፍትሐ ነገሥትና በኢትዮጵያ የነበሩትን ልማዶችና ባሕሎችን መሠረት በማድረግ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር፣ የንግድና የባሕር ሕጎችን ማዘጋጀት ነበር። የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በ1949 ዓ.ም፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ በ1952 ዓ.ም እንዲሁም የንግድና የባሕር ሕጎች ደግሞ በ1953 ዓ.ም. በፓርላማ ተቀባይነትን አግኝተውና በንጉሠ ነገሥቱ ፀጽቀው ሕግ ሆነው ወጥተዋል። በእነዚህ ሕጎች ዝግጅት ሂደት ውስጥ የብላታ መርስዔ ኀዘን አበርክቶ ትልቅ ነበር፡፡

ከእነዚህ ሕግጋት መካከል ብዙዎቹ አሁንም ድረስ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በ1960 ዓ.ም የፍትሐ ነገሥት ንባብና ትርጓሜ የሚሠራ ኮሚቴ በተቋቋመበት ወቅት የኮሚቴው ሰብሳቢ የነበሩት ብላታ መርስዔ ኀዘን ሲሆኑ፤ የፍትሐ ነገሥት ንባብና ትርጓሜ ሥራው በ1962 ዓ.ም ተጠናቆ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጥቷል። ከ1964 እስከ 1966 ዓ.ም ደግሞ የአማርኛ ቋንቋን ማዳበርና የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እንዲስፋፋ ማበረታታትን ዓላማው አድርጎ የተቋቋመው የአማርኛ መርሐ ልሳን (አካዳሚ) አባል ሆነው ሠርተዋል፡፡

በርካታ የአማርኛ ቋንቋ ባለሙያዎች ‹‹ብላታ መርስዔ ኀዘን አንዱ የአማርኛ ቋንቋ አባት ተብለው ቢወደሱ ማጋነን አይሆንም›› ብለው ይመሰክሩላቸዋል። ይህ የተባለበት ምክንያትም የአማርኛ ሰዋስውን አስመልክቶ ባደረጓቸው ጥልቅ ምርምሮች እና በተቀናጀ መልክ የተዘጋጁ የአማርኛ ሰዋስው መማሪያ መጸሐፍትን በመጻፋቸው ነው። የአማርኛን ቋንቋ ከዘመናዊ እና ከኪነታዊ አነጋገር በማስማማት ያሳደጉ ታላቅ ባለሙያ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡

ብላታ መርስዔ ኀዘን በተለይ በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፅዖ በ1964 ዓ.ም የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሽልማትን አሸንፈዋል፡፡ አንጋፋው የታሪክና የቋንቋ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ስለብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ እንዲህ በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል … ‹‹ … ክቡር ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ለኢትዮጵያ የሰጡትን ልባዊ አገልግሎትና እሳቸውንም በአካል የሚያውቅ ሰው በየምዕት ዓመት አንድ ጊዜ የሚታዩ የዕውቀትና የጥበብ ሰዎች ካሉ ክቡርነታቸው አንዱ መሆናቸውን አይጠራጠርም።›› ጡረታ እስከወጡበት እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ በአጠቃላይ ለ50 ዓመታት ያህል አገራቸውን በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉት አንጋፋው ባለሙያ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ጥቅምት 19 ቀን 1971 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ እነሆ ሥራዎቻቸውም እርሳቸውንና ታሪክን ሲዘክሩ ይኖራሉ፡፡

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You