ዝክረ ሴቶች

አንዳንድ ሚስቶች ጫንቃ ላይ እንዳረፈ ከባድ ሸክም አስጎንባሾች ናቸው። አንዳንድ ሚስቶች ራስ ላይ እንደተደፋ ዘውድ ክብርና ቀና ማያ ናቸው።

በምትሆነው መሆን ሚስቴ የአዕምሮ ውስኑነት እንዳለባት መጠራጠር ከጀመርኩ ሰንበትበት ብያለው። ከእኔና ከበፊቷ ፍቅረኛህ ሲለብስ ማነው የሚያምርበት? ማንኛችን ነን ቆንጆ? ፍቅር መሥራት ላይ የጣመህ ማነው? ስትል ትጠይቀኛለች። በማይጠየቅ ጥያቄዋ ትንሽ ቅሬታን አሳይቼ እንድናልፈው ብገፋፋትም አትተወኝም። አጠገቤ ከሆነች እየነካካች፣ መኝታ ቤት አልጋ ላይ ከሆንን ደረቴ ላይ ተሳፍራ በል ንገረኝ ስትል ወጥራ ትይዘኛለች። ሁሉም ባይሆኑም አንዳንድ ትላንቶች በዛሬ ፊት ላይ አይዘከሩም። በተለይ ፍቅር ላይ አደገኛዎች ናቸው።

ሚስቴ ግን ይሄንን አትረዳም..ከእሷ በፊት የኖርኩትን ሕይወት እንዳለ ዘርዝሬ እንድነግራት ትፈልጋለች። አይጠቅምሽ ብላት ‹ምን የተደበቀ ታሪክ አለህ እንዴ ምነው ፈራህ? ስትል ራሷ በፈጠረችው ጥርጣሬ ቀን ሙሉ ታኮርፈኛለች። ሚስቴን በተመለከተ ቀጣይ እቅዴ ከቻልኩ ብቻዬን ካልሆነ የሰፈር ሰው አሰባስቤ አማኑኤል ማስገባት ነው።

ሰው የሕይወት ዘካሪ ነው። ከዛ እዚህ ባመጣውና ከዚህ ወደዛ በሚወስደው ዝክረ ወጉ ውስጥ እንደቦይ የሚፈስ ነው። ሕይወት ወደኋላ ቢኖራት..ካለፈው መርጠን ለዳግም ሕይወት የምንከጅለው በኖረ ነበር። እረ እንዳውም በዛሬ እና በመጪው ቀይረን ባለፍንበት ሰርጥ ላይ ለማግደም አይናችንን የማናሽ አንድ መዓት ነን። በእዬዬ እንጂ ትላንትን ደግመን እንድንኖረው ባልተፈቀደ ተፈጥሮ ውስጥ መቆማችን የሁላችንም ቁጭት ይመስለኛል።

መነሻዬ ፍቅር ነው..መድረሻዬ ደግሞ አንዲት ስንጥር..! በላመ እንቅልፍ ስር ከተባዕት ጉያ ስለበቀለች ነፍስ። በፍቅር ላይ ሳልንጠራራ የነካሁት ክብር የለም። መንጠራሪያዬ ፍቅር ነው። አልደርስ ያልኩባቸው ሩቅ ምኞቶች እነሱ ካለፍቅር የሄድኩባቸው እንደሆኑም የማምን ነኝ።

ሰው እቃ ቤት ነው። የሕይወት ገሰስ ማከማቻ። ባደፈ መጋረጃ ከለል እንዳለ ዝርክርክ ታዛ ማንም እየመጣ ነውሩን የሚደብቅበት። በእኔም ውስጥ በዘመን የተደበቀ ስንት ጉድ አለ መሰላችሁ! ለማንም እንዳይታዩ አርቀን በደበቅናቸው ጋፍና እንዲታዩ በገለጥናቸው ሸጋ ታሪኮች ስር ዝብናኔ የጎበኘን ነን። ጋፍን ማውጋት ስለማንወድ እንጂ ከሰውነት የሚፍቁን ስንት ጉዶች ነበሩን።

እኔ ግን ሌላ ነኝ..በምድር አዲስ ነገር የለም ብዬ የማምን፣ ለሆነው እየሆነ ላለውና ለሚሆነው ራሴን ያሰናዳሁ፣ ሊሰማኝ ለፈለገ የመጣሁበትን አንድ ሳላስቀር የምናገር። ለምን አስመስላለሁ..? በሰሚ ማጣትም ይሁን ንግግር ባለመቻል ብዙ ያልተነገሩ ታሪኮች አሉን። የሚሰማንን እንደማግኘት እኩያ እድላምነት እንደሌለ ለብዙ ዘመን በሠራሁት ጥናት አረጋግጫለሁ። ሰው ድሉና ዕድሉ የሚጀምረው እህ ብሎ ከሚሰማው ሰው በኩል ነው። በሰው ልጅ ታሪክ ከጥላቻ ቀጥሎ አድማጭ ማጣት ሁለተኛው ገዳይ በሽታ ነው። በፅሞናና በሰከነ መንፈስ፣ ዓይኑን ዓይናችሁ ላይ ሰክቶ..አንዳንዴም ጭንቅላቱን እየነቀነቀ የሚያደምጣችሁ ካለ በምርጥ ዕድል ጊነስ ቡክ ላይ ለመስፈር ብትወዳደሩ ያዋጣችኋል ባይ ነኝ።

በሰሚ ማጣት ታሪኮቻችን አልተነገሩም። በቦታ ማጣት ሕልሞቻችን አልተመነዘሩም። በተሸረፈና በተገመሰ ሕይወት ውስጥ ነን። የጀመርንውን ሳንጨርስ አድማጭ ልቦች ይሸሹናል። ተስፋ ባደረግናቸው ማግስት ቅርንጫፋቸውን ሰብረው ጥላና ማረፊያ ያሳጡናል። ለመስጠት በደሀ ዓለም ውስጥ ፍቅር የማያውቀው ሀገር ሄዶ ቦታ እንዳጣ ሀገረ ገዢ ነው። በመጠበቅ ውስጥ ፍቅር ግማሽ ያህሉ የለም። አንዳንዴ በብዙ ሰው መሐል ብቸኝነትና ባይተዋርነት ይሰማናል። ሌላ ጊዜ በአንድ ሰው ጎን ቆመን በዓለም ላይ ምርጡን እኛን እናገኘዋለን። ሰው ልቡን ካልሰጠ..ከእምነቱ ካልከፈለ፣ ከሕልሙ ካላጋራ፣ ከእውነቱ ካልቆረሰ፣ ከስኬቱ ካልገመሰ፣ ከመንገዱ ካልቸረ አንካሳ ነው። በእንዲህ አይነት ሰዎች መሐል መብቀል በጭንጫ ውስጥ እንደወደቀ ፍሬ ነው። አንድ ሆነው ብዙ ሰዎች አሉ። ብዙ ሆነው የአንድ ሰው ያክል ዋጋ የሌላቸውም አሉ።

አድማጭ መሆኔን አንድም ቀን አስቤው አላውቅም። በቻልኩት ሁሉ የሰዎችን ንግግር፣ ስሜት ለመረዳት እሞክራለሁ። አድማጭነቴ የተረጋገጠው በሴቶች ነው። በፍቅሬ ከሚወድቁበት ነገር አንዱ ስሰማቸው ሁሉ ነገሬን ሰጥቼ መሆኑ ነው። ምኔን ወደድሽው ብዬ ጥያቄ ያቀረብኩላት ሴት አድማጭነትህን አለማለት አትችልም። ማድመጥ በሴቶች ዘንድ የፍቅር መውደቂያ ከመሆኑም በተጨማሪ የጠቅላላ እውቀታችን መለኪያ መስፈርትም ነው። እናም በሴቶች ዘንድ እጸሙናለሁ። በዝክረ ሴቶች ታሪኬ የማልዘነጋው እውነት በሴቶች ዘንድ በአድማጭነቴ ያገኘሁትን ሙገሳ ነው። በቆንጆ ሴት እንደመወደስ ለወንድ ልጅ እኩያ ጀብድ የለውም።

በሁሉም ወንዶች ልብ ውስጥ ያልደበዘዘች አንድ ሴት አለች። እንደንስር ራሷን እያደሰች ከዘመን ዘመን የምትበረታ። ልጅ ሆኜ የምሰማው አንድ አባባል አለ..በሁሉም ወንድ ታሪክ ውስጥ ከደመቁት ደምቃ የምታበራ አንድ አብሪ ነፍስ አለች የሚል። ይሄን አባባል አላምን ብዬ የመጀመሪያ ፍቅረኛዬን እስከተዋወኩበት ጊዜ ድረስ በእንቢተኝነቴ ቀጥዬ ነበር። ከአፍላነቴ ውስጥ ደማቅ ታሪክ ለማግኘት ወደነገ የሚሻገር ትዝታዋን ስበረብር ነበር። ካለ ደማቅ እስከ አፍላነቴ ማብቂያ ድረስ ተምዘገዘኩ። ባምን እንኳን አልረሳ ብላ በሕይወቴ ሁሉ የምትከተለኝን ሴት ሁናቴ ባላደኩበት የልጅነቴ ደብር ውስጥ እርቃኝ ነበር።

በእርግጥ ለአርምሞ ጥላኝ አልደበዝዝ ያለች ሴት እስካሁን በእኔ ውስጥ የለችም። ከሰውነቴ ለእኔ ብቻ በዝቶ እንደተሰጠ የማስበው የትዝታ ተጠቂነት አለ። ሁሉም ትላንት..ሁሉም ዛሬ፣ ሁሉም ነገ ለእኔ ናፍቆት ነው። በዚህ እውነታ ውስጥ የተዋሓድኳቸው ሁሉም ሴቶች በሆነ በጎ ነገራቸው በኩል በናፍቆት የሚፈነግሉኝ ናቸው። አንዳቸውን ከአንዳቸው አስበልጬ እንደእሷ አይነት ሴት አላየሁም የምላትን አይነት ከታሪኬ ውስጥ መዝዤ ለማውጣት ብዙ ደክሜ አልተሳካልኝም።

በእኩል የተከረከሙ የእኩያ ታሪክና ናፍቆት ባለቤት ነኝ። አጠገቤ ላለችው ሚስቴ ይሄን ብነግራት ሰማኒያችንን ቀዳ ፍቺ እንደምታስገባ የማውቅ እኔ ብቻ ነኝ። በእያንዳንዱ ወሬዬ ውስጥ ስሟ እንዲኖር፣ ሚስትነቷ እንዲጎላ ትፈልጋለች ይሄ ባልከፋ ነበር ጉዳዬ ከአሜሪካው የስለላ ተቋም ከኤስ አይ ኤስ ጋር ቢሆን እንኳን ስሟን ጠርቼ እንድጀምር እና በስሟ እንድጨርስ የምትመኝ ናት። ሁልጊዜ ምርጥ እንደሆነች በመናገር ግዴታ የተጣለብኝ ባሏ ነኝ። እንደዛም ሆኖ አፈቅራታለሁ። የእኔን ያህል ቻይ ባል የእሷን ያክል ጠያቂ ሚስት ታሪክ አላጣመረም።

ዛሬ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳና አብሬያት ቁርስ ስበላ የሆነ ነገር በመናገር ቀኗን አሳምሬው ነበር። የዛሬው ማለዳ ሳልጠየቅ ያወራሁበት የመጀመሪያ ቀኔ ነው። ‹እስከዛሬ ድረስ ወደሕይወቴ ከመጡት ደማቋን ነሽ። በእኔ ሰማይ ላይ ብዙ ደማቅ ከዋክብቶችን ተመልክቻለሁ። አንቺ ግን ከስንት አንድ ጊዜ የምትወጣውን ከሁሉም ደማቋን ኮከብ ነሽ› ስላት የተሰማትን ስሜት ደግሜ ማስታወስ አልቻልኩም። በሚገርም ፈገግታ ለብዙ ሰዓት ስትስቅ አየኋት..ማብቂያዋ እኔ ሆኜ ለሰባት ዓመታት ባላቀፈችኝ አስተቃቀፍ፣ ባልሳመችኝ አሳሳም ሰውነቴ ላይ ተጣበቀች።

‹የጀመርኩት ባንቺ አይደለም የማበቃው ግን ባንቺ ነው። መላ ታሪኬ አንቺ ያለሽበትን አሁንና ነገ አያክልም። ደምቄ አውቃለሁ..ከውበት ጋር የፈካሁት ግን ካንቺ ጎን ካንቺ ጋር ነው። እንደእኔ ጥቂቶች ካልሆኑ ሕይወት ማብቂያዋ ምን ጋ እንደሆነ ሳይገባን የምንኖር ነኝ..ባንቺ ያለፈውን ጨምሮ የሚመጣውን የማውቅ ከእግዜር ቀጥሎ ሆኛለሁ። ሳከብርሽ፣ ሳፈቅርሽ፣ ስጠነቀቅልሽ ያዩኝ ሰዎች እንደእኔ መሆንን በሚያስመኝ ምኞት ውስጥ ባልሽ ልሆን ልብሽ ላይ ወድቄአለሁ› ይሄን ብዬ በእሷና በእኔ መሐል ሳሎን ቤት ምን እንደተፈጠረ ለማሰብ ብዙ ዝም ማለቴን አስታውሳለሁ። እንባ በቀላቀለ የደስታ ስሜት ፊቴ ሳገኛት ሳላምነው ከኖርኩት ደማቅ ዝክረ ታሪኬ ጋር የተገናኘሁ መስሎኝ ነበር።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You