ዘለንስኪ ከፍተኛ የፀጥታ ባለሥልጣንን ከኃላፊነት አባረሩ።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ እያካሄዱት ባለው የአመራር ለውጥ ዘመቻ ከትናንት በስትያ የዩክሬንን የብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት ጸሐፊ ማባረራቸውን እና በእሳቸው ቦታ የውጭ ደኅንነት ኤጀንሲ ኃላፊ የነበሩትን መሾማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ወር ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት ቁልፍ ሚና ነበራቸው የተባሉትን ዋና የጦር አዛዥ ከኃላፊነት ማንሳታቸው ይታወሳል።
የፀጥታ ኃላፊው መባረራቸውን ይፋ ያደረገው የፕሬዚዳንቱ ድረ-ገጽ የተባረሩበትን ምክንያት ግን ግልጽ አላደረገም።
የተሰናበቱት የብሔራዊ ደኅንነት እና የመከላከያ ምክርቤት ፀጥታ ኃላፊው ኦሌክሲ ዳኒሎቭ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ሥልጣን ከመያዛቸው ከአንድ ወር በፊት ከ2019 ጀምሮ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ዘለንስኪ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ዳኒሎቭ አዲስ ኃላፊነት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።
ዘለንስኪ ዳኒሎቭን ያነሱበትን ምክንያት አላብራሩም፤ ነገርግን የብሔራዊ ደኅንነታችንን ለመጠበቅ አስተማማኝ የትንበያ አቅም ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።
“ዩክሬንን የማጠናከር እና በሁሉም ዘርፎች ያሉ አሠራሮችን የማደስ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል ዘለንስኪ።
ዘለንስኪ በግልጽ የማይታወቁትን የውጭ ደኅንነት ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑትን የ51 ዓመቱን ኦሌክሳንደር ሊቲቪንኮን ምክርቤቱን እንዲመሩት ሹመት ሰጥቸዋል።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ አዲሱ ተሿሚ ዩክሬን የምትፈልገውን የደኅንነት እና የፀጥታ ልምድ ያካበቱ ናቸው ብለዋል።
ተጠሪነቱ ለፕሬዚዳንቱ የሆነው ምክር ቤቱ የዩክሬንን ከፍተኛ የፖለቲካ፣ የፀጥታ እና የመከላከያ ኃላፊዎች ያካተተ እና የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮችን የሚያስተባብር ነው።
ፕሬዚዳንቱ ምክትል የወታደራዊ ስለላ ምክትል ኃላፊ የነበሩትን ኦሌህ ኢቫስቸንኮን የውጭ ደኅንነት ኃላፊ አድርገው ሾመዋቸዋል።
የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ሁለት ዓመት ያለፈው ሲሆን ሩሲያ በቅርቡ በምሥራቅ ዩክሬን አቭዲቪካን ጨምሮ በርካታ መንደሮችን ተቆጣጠራለች።
ዩክሬን ቦታዎቹን የለቀቀችው የምዕራባውያን ወታደራዊ እርዳታ በፍጥነት ባለመድረሱ እና ወታደሮቿን ከከበባ ለማውጣት መሆኑን መግለጿ ይታወሳል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም