አዲስ ዘመን ድሮ

በትምህርትና በእውቀት የተደገፈ አልቃሽነት ያስፈልጋል በማለት አዲስ የለቅሶ ዜማ ተደርሶ በለቅሶ ላይ ሊውል ነው። የማስለቀስ ልምዳችሁን በስልጠና አዳብሩ የተባሉት የመንደር አልቃሾቹም፤ ገሚሱ አሻፈረኝ በማለት ተቃውሟል፤ ገሚሱ ደግሞ ተማሩ ካላችሁን የምንማረው እየተከፈለን ካልሆነ በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። አዲስ ዘመን ድሮ ወደ 1963ዓ.ም መልሶ ይህን ያስነብበናል። አውቶቡሱ ተገልብጦ ሰዎችና 58 በጎች ተዳጡ። ከሁለቱ የመረጃ ትውስታዎች ጋር “አንድ ጥያቄ አለኝ” ከተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ ደብዳቤዎች፤ በምልሰት ብዙ ጉዳዮችን እንመለከታለን።

አውቶቡስ ተገልብጦ ሁለት ሰዎች ሞቱ 58 በጎች ተዳጡ

የአንበሳ አውቶቡስ ከዛፍና ከገደል ተጋጭቶ፤ 4 ቤት ጥሶ ገብቶ በተፈጠረው አደጋ፤ ሁለት ሰዎች ወዲያውኑ ሞተዋል። እንዲሁም በደረሰው አደጋ 22 ሰዎች በጠና ሲቆስሉ፤ 58 በጎች አልቀዋል።

አደጋው የተፈጠረው ከእንጦጦ ተራራ ላይ የሚሽቆለቆል ቁጥር 15 ሺህ 125 የሆነ የአንበሳ አውቶቡስ ከሹፌሩ ቁጥጥር ውጪ በመሆኑ፤ በአደጋ ላይ እንዳለ በ1 ሺህ ሜትር ርቀት ተጉዞ ከገደል፤ ከጉድጓድና ከቤት ጋር እየተጋጨ አሳዛኝ ድርጊት ከተፈጠረ በኋላ መሆኑን ከስፍራው የነበሩት ሰዎች አመልክተዋል።

(አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 1966ዓ.ም)

አዲሱን የለቅሶ ዜማ የመንደር አልቃሾች ተቃወሙ

የቤተሰብን ጤንነትና አካል እንዲጠብቅ ተብሎ በፀሎት መልክ የቀረበውን አዲሱን የሀዘን ዜማ አንዳንድ የመንደር አልቃሾች መቃወማቸውን አቶ አብረሃም መኮንን በኢትዮጵያ መንበረ ፓትሪያርክ፤ የወጣቶች አንድነት ማዕከላዊ ፅ/ቤት ዋና ፀሐፊ አስረዱ።

አዲሱን የለቅሶ ዜማ የመንደር አልቃሾች ኮርስ ወስደው እንዲያጠኑ ተጠይቀው ፍቃደኞች አለመሆናቸውን ዜና ሰጪው ተናግረዋል።

አዲሱ ዜማ አንድ ሰው ሲሞት በህብረት ዝማሬ እየተዜመ ሙታንን ለመሸኘት የሚያስችል ነው።

በተለይ አንድ ሰው በሞተ ጊዜ የሟች ቤተሰቦች ደረት በመደለቅ፣ ከመሬት በመፈጥፈጥ፣ ፊት በመንጨት የሚደርስባቸውን ከባድ ጉዳት የሚያስወግድና ስርአትና መልክ ያለው መሆኑን አቶ አብረሃም ገልጠዋል።

በዚህ መሰረት ሰባት ዓይነት ልዩልዩ በህብረት የሚዜሙ የለቅሶ ዜማዎች ተዘጋጅተውና ተፈልስፈው ይገኛሉ።

ዜማዎቹን የደረሱት አቶ አብረሃም ሲሆኑ እነዚህኑ ዜማዎች በኮርስ መልክ የመንደር አልቃሾች እንዲያጠኑ 8 ያህል አልቃሾች ማነጋገራቸውን ዜና ሰጪው ተናግረዋል።

ከስምንቱ አልቃሾች ሁለቱ ወንዶች ሲሆኑ ጥቂቶቹ አልቃሾች ዜማውን ለማጥናት ኮርስ ከገባን ዜማውን እስክናጠናቅቀው ድረስ በወር 25 ብር ክፈሉን በማለት አቶ አብረሃምን የጠየቁ መሆናቸውን ዜና ሰጪው አስረድተዋል።

ቀጥለውም ‹‹ካነጋገርኳቸው ጥቂቶቹ የመንደር አልቃሾች ዘንድ ብዙ ወቀሳ ደርሶብኛል። ብላችሁ ብላችሁ በእንጀራችን ገባችሁ አሉኝ። ቄሶች በአንድ በኩል ያወግዛሉ። እኛ ስራችን ነው በማለት ተቃውሟቸውን ገለጡ። ኮርስ ግቡና በወር 5 ብር ልክፈላችሁ አልኳቸው 25 ብር ካልሆነ ብለው ሀሳቤን ሳይቀበሉ ቀሩ›› ሲሉ አቶ አብረሃም ተናግረዋል።

አዲሱ የልቅሶ ዜማ ሙታንን እንዴት መሸኘት እንደሚገባ ትምህርትና ምክር የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል። ይህም ዜማ ካሁን በፊት በደብረ ገሊላ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ዜማውን ባጠኑ ተማሪዎች በቴያትር መልክ ተዘምሮ ታይቷል። በሁለቱም ቀኖች የተገኘው ህዝብ በብዛት የሚቆጠር መሆኑንና በተመለከተው ህዝብ መደገፉን አቶ አብረሃም ተናግረዋል። አሁን የመንደር አልቃሾች ዜማ ግን ሥርዓት የሌለው ነው ሲሉ ነቅፈዋል።

አቶ አብረሃም የመጨረሻ ማብራሪያቸውን ሲሰጡ ‹‹ያሁኑ የአልቃሾች ዜማ ወንዱና ሴቱ ተለይቶ አይነገርበትም። የሞተችው ሴት የሆነች እንደሆነ ለወንድ ያለቅሱበታል፤ ሟች አርበኛ የሆነ እንደሆነም አቶ እገሌ እህል ሲያመርት፤ እርፍ ሲይዝ እንዲህ አልነበረም ተብሎ ሙሾ ይቆምበታል። በጠቅላላ ዜማው ሥርዓት የሌለው ነው። ነገር ግን በህብረት እየተዘመረ የሚዜመውን አዲሱን የለቅሶ ዜማ በአልቃሾች ቢጠና ጥቅሙ እንደሚያመዝን አንጠራጠርም›› ብለዋል።

(አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 7 ቀን 1963 ዓ.ም)

አንድ ጥያቄ አለኝ

-አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ

*የአዲስ አበባ ትራፊክ ክፍል ከባድ ቁጥጥር ጀምረናል ሲሉ በራዲዮ የተናገሩትን ሰምቼ ነበር። ቁጥጥሩ ግን ምን እንደሆነ አላየሁም። ለመሆኑ አንተ አይተሃል?

-ኸረ እኔም አላየሁም። ሲሉ ግን ሰምቻለሁ።

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 10 ቀን 1966ዓ.ም)

*የሩጫ ስሜት አድሮብኝ የቸገረኝ ነገር ጫማና ቱታ ነው። የምገዛበትም የለኝምና ምን ይሻለኛል?

(መለሰ ጌታቸው)

-ያለ ጫማና ቱታ መሮጥ ይቻላል። እንዲያው አበበ ቢቂላ ሮም ላይ ያሸነፈው ያለጫማ ሩጦ ነውና ሰበብ ሳታበዛ ትሮጥ እንደሆን ሩጥ።

*ድሮ እሷ እወድሃለሁ ስትለኝ እኔ አልወዳትም ነበር። አሁን እኔን ፍቅር ብን ሲያደርገኝ እሷ ደግሞ ገሸሽ ታደርገኝ ጀመር። ጀነንም ያደርጋታል። እንዴት ወደነበረችበት ልመልሳት እችላለሁ?

( ከበደ ለማ)

-“የሷ ፍቅር አልቆ የኔ ሲጀመር፤

ሐዲዲም ፋዲዲም ያደርገኝ ጀመር” ይል ነበር የድሮ አዝማሪ። አንተም የያዘህ አባዜ እስኪለቅህ ድረስ እንዲያው ዝም ብለህ ኑር እንጂ አንዴ የጠላችህን ልጅ እንደድሮው ለመመለስ አትችልም።

*ወንድ ለምን ጡት አያወጣም?

(ወርቅነሽ አስፋው)

-እንደ እናንተ ትልቅ አይሆንም እንጂ ማውጣቱንስ ያወጣል። ያንዳንዱማ የተበደለች ልጃገረድ ጡት የሚያህል ያለው አለ።

*ከዚህ በፊት ስለ አልአዛር ጠይቄህ ስለየቱ አልአዛር ብለኸኝ ነበር። ከሀብታሙ ከነዌ ደጃፍ ወድቆ ይለምን ስለነበረው አልአዛር ንገረኝ።

( ፋንታሁን ቱሉ)

-ስለሱማ አዲስ ኪዳን ውስጥ አንብብ። ከዚያ የተለየ እኔም የማውቀው የለም።

(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 12 ቀን 1966ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

 አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You