የካራማራ ድል እና የመተማ ጦርነት

በየካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት እንደገለጽነው፤ የካቲት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያለው ወር ነው፡፡ ይህን የየካቲት ታሪካዊ ወርነት ባለፈው ሳምንት በብዙ መገናኛ ብዙኃን ሲደጋገም ሰማሁት፡፡ የካቲት በኢትዮጵያ ታሪካዊ ክስተቶች የታጨቀ መሆኑን ብዙዎች ልብ ብለውታል ማለት ነው፡፡ በአጭሩ የካቲት የኢትዮጵያውያን ወር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዓለም አቀፍ ድሎችም ሆኑ የሀገር ውስጥ አብዮቶች የተከናወኑበት ነው፡፡

የካቲትን ስናጠቃልለው፤ ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት ለማስወገድ አብዮት የተቀጣጠለበት፣ ለ17 ዓመታት የኖረውን የደርግ መንግሥት ለማስወገድ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የትጥቅ ትግል የጀመረበት(የካቲት 11)፣ ለ27 ዓመታት ያህል የቆየው የኢህአዴግ መንግሥት በመሪው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኩል ‹‹በቃኝ›› ብሎ ይፋ ያደረገበት… በአጠቃላይ ብዙ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ሁነቶች ጭምር የታጨቁበት ነው፡፡

ወደ ዓለም አቀፉ ስንሄድ የየካቲት 12 ሰማዕታትን አስታውሰናል፤ የዓድዋን ድል አክብረናል፡፡ እነሆ ዛሬ ደግሞ የየካቲት ወር የመጨረሻ ክስተት የሆነውን የካራማራን ድል እናስታውሳለን፡፡ በመቀጠልም የመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ክስተት የሆነውን የመተማ ጦርነት እናስታውሳለን፡፡ ከዚያ በፊት እንደተለመደው የዚህ ሳምንት ሌሎች ክስተቶችን እናስታውሳለን፡፡

ከ78 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 25 ቀን 1938 ዓ.ም አንጋፋው የፊልም ባለሙያ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ተወለዱ፡፡ ኃይሌ ገሪማ ዓድዋን ጨምሮ የኢትዮጵያን ታሪክ በፊልም ለዓለም በማስተዋወቅና በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ አርዓያ በመሆን ይታወቃል፡፡

ከ9 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዘመናዊ የባንክ አሠራር ሥርዓት አባት የሚባሉት ተፈራ ደግፌ አረፉ፡፡

ወደ ካራማራ የድል

ታሪክ እንመለስ፡፡

የካራማራ ድል ልክ እንደ ዓድዋ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከወራሪ ራሳቸውን የተከላከሉበትና ነፃነታቸውን ያስጠበቁበት የድል በዓል ነው፡፡ ልዩነቱ፤ ዓድዋ ለጥቁር ንቀት ያለው የነጭ እብሪተኛ የተዋረደበት ሲሆን ካራማራ ግን የግዛት ማስፋፋት ፍላጎት የነበረው ጎረቤት ኃይል የተሸነፈበት ነው፡፡

በወቅቱ በዚያድ ባሬ ይመራ የነበረው ተስፋፊው የሶማሊያ መንግሥት ‹‹ታላቋን ሶማሊያ እገነባለሁ›› በሚል ህልም የኢትዮጵያን መሬት ለመውረር አስቦ እሱም ልክ እንደ ጌቶቹ አውሮፓውያን ሽንፈትን ተከናንቦ የተመለሰ ነው፡፡

ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን ቅጽ ፩›› መጽሐፍ እና የካራማራ ድል በተከበረባቸው ዓመታት ከተሰሩ ዘገባዎችንና ከተለያዩ ድረ ገጾች መረጃዎችን አሰባስበን በየዓመቱ የካቲት 26 የሚከበረውን የካራማራ ድል እናስታውሳለን፡፡

ለወረራ አሰፍስፎ በመጣው የዚያድ ባሬ ጦር ከሐምሌ 1969 ዓ.ም እስከ የካቲት 1970 ዓ.ም ድረስ ምሥራቃዊዋ የኢትዮጵያ ክፍል ኦጋዴን ጦርነት ተካሄደባት፡፡ ሶማሊያን ለ21 ዓመታት የመሩት ጄኔራል ዚያድ ባሬ ኦጋዴንን በመጠቅለል ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት የቆየ ራዕይ ነበረው፡፡ ጊዜ አይቶ ወቅትን ገምቶ ኢትዮጵያ በገንጣይ አስገንጣዮች ትግል የተዳከመች ሲመስለው እቅዱን ለማሳካት ጊዜው አሁን ነው አለ፡፡

ዚያድ ባሬ ያሰበውን ዳር ለማድረስ የኢትዮጵያን ጠላቶች ተጠቀመ፡፡ ያዋጣኛል ያለውን የሴራ መንገድ ሁሉ ተከተለ፡፡ ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ወረራ ከመፈፀሟ በፊት በህቡዕ በተደራጀ ቡድን ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል ማዳከም የሴራው አካል ነበር፡፡ ጦርነቱ በግልጽ በታወጀበት በሐምሌ ወር 1969 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሳምንታት የሶማሊያ ጦር ባልታሰበ መልኩ ጅግጅጋ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ድረስ ዘልቆ ገባ፡፡

በመጀመሪያ በሶቭየት ህብረት እና በመቀጠልም በአሜሪካ ድጋፍ የነበረው የፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ጦር ለድል የተቃረበ መሰለ፡፡ የኋላ ኋላ የውጭ ድጋፍ እየቀነሰበት የመጣው የሶማሊያ ጦር የኢትዮጵያ የውስጥ ተገንጣይ ኃይሎች የውስጥ ለውስጥ ድጋፍ ስላልተለየው ጦርነቱን ከመግፋት አልተቆጠበም ነበር፡፡

ልክ እንደ ዓድዋው በዚህን ጊዜም የኢትዮጵያው መሪ ለጀግና ሕዝባቸው የክተት ጥሪ አቀረቡ፡፡ ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም በብሔራዊ ቴሌቭዥን ቀርበው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚከተለውን የክተት ጥሪ አቀረቡ፡፡

‹‹… ታፍራና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ተደፍራለች፡፡ ለብዙ ሺህ ዓመታት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም፡፡ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊት! የኢትዮጵያ ሕዝብ! ለክብርህንና ነፃነትህን ለመድፈር ሀገርህን ለመቁረስ የተጀመረው ጣልቃ ገብነትና ወረራ ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሰልፈህ ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ተነስ! ታጠቅ! እናሸንፋለን!››

በተደረገለት ጥሪ የኢትዮጵያ ሕዝብም የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ቀፎው እንደተነካ ንብ በቁጣ ወጣ። የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጦር ወደ ፍፁማዊ ማጥቃት እና እልህ አስጨራሽ ጦርነት መግባቱን የሚያመላክቱ ርምጃዎች መታየት ጀመሩ። ከኦጋዴን ሞቃታማ ቦታዎች በአንዱ ‹‹ካራማራ›› ከሚባለው ተራራ ከምድርም ከሰማይም እሳት የሚተፉ የኢትዮጵያ ወታደር የጦር አረሮች ምድሪቱን ዘነቡባት፡፡

ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት ህልም አንግቦ የነበረው የዚያድ ባሬ ጦር አይቀጡ ቅጣት ተቀጣ። ኢትዮጵያ በታሪክ እንደለመደችው አሁንም ድል አደረገች፡፡

የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር፣ የእናት ሀገር ወዶ ዘማቾች እና 16 ሺህ የሚደርሱ የፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮዋ ኩባ አጋር ወታደሮች ይህን ታሪካዊ ጦር ተቀላቅለው የዚያድ ባሬን ጦር ድባቅ መትተው የኢትዮጵያን አሸናፊነት ታወጀ፡፡

የካራማራን ድል በመጽሐፋቸው ላይ ባስቀመጡት በአንዲት የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ገጠመኝ እንቋጨው፡፡ በኩባ እና በሌሎች ወዳጅ ሀገራት አማካኝነት ኮሎኔል መንግሥቱ እና ዚያድ ባሬ ለውይይት ተጠርተው በየመን ይገናኛሉ፡፡ ዚያድ ባሬ እብሪተኛ ስለሆነ ኮሎኔል መንግሥቱ የእብሪት መልስ እንዳይመልሱ በወዳጆቻቸው ተመክረዋል፡፡

የተፈራው አልቀረም በውይይቱ ላይ ዚያድ ባሬ ኮሎኔል መንግሥቱን ‹‹ጦርነት የት ታውቃለህና ነው! ጦርነት እንዴት እንደሆነ አሳይሃለሁ›› ብሎ ፎከረ። ዳሩ ግን ኮሎኔል መንግሥቱም እብሪተኛ ነበሩና (መታገስ አልቻልኩም ነው የሚሉ እርሳቸው) ምክሩን ጥሰው ‹‹ማን ጦርነት እንደሚችል እንተያያለን! እዚያው እንገናኝ!›› ብለው ፎከሩ፡፡ ውይይቱም ያለ ስምምነት ተቋጨ፡፡

እነሆ ጦርነት ማን እንደሚችል ታየ! ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም አሸናፊ ናቸው!

ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት፤ ከ135 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ልክ በዛሬዋ ቀን መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም የተከሰተው የመተማ ጦርነት ነው፡፡

በመጀመሪያ ‹‹አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት›› የተሰኘውን የተክለጻድቅ መኩሪያ መጽሐፍ ዋቢ አድርገን ታሪኩን በአጭሩ እናስታውስ፡፡

ከጣሊያን ጋር ጦርነት ላይ የነበሩት አፄ ዮሐንስ አራተኛ ደርቡሾች ኢትዮጵያ ላይ ያደረሱትን ጥፋት ለመበቀልና የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር የደርቡሾችን ጦር ለሚመራው ዘኪ ቱማል ‹‹መጣሁ ጠብቀኝ! እንደ ሌባ አዘናግቶ ወጋኝ እንዳትል!›› የሚል መልዕክት ላኩበት፡፡ አፄ ዮሐንስ አራተኛ ይህን መልዕክት ልከው ጦራቸውን ይዘው ወደ መተማ ሄዱ፡፡

በዕለተ ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም ረፋድ አካባቢ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ አፄ ዮሐንስ ልክ እንደ ተራው ወታደር መሐል ገብተው ሲዋጉ ዋሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ጠንክረው እየተዋጉና ምርኮኛ እየያዙ ሳሉ አንዲት ተባራሪ ጥይት የንጉሠ ነገሥቱ አፄ ዮሐንስ አራተኛ ደረት ላይ አረፈች፡፡ የንጉሡን መቁሰል ያየው ሠራዊታቸውም መደናገጥና መሸሽ ጀመረ፡፡

የአፄ ዮሐንስ አራተኛ መልዕክት፤ ለዘኪ ቱማል እንደደረሰ በደርቡሾች ዘንድ ሽብር ተፈጥሮ ነበር። ዘኪ ቱልማ ወታደሮቹን ሰብስቦ ‹‹ምን ይሻለናል? ውጭ ወጥተን ሜዳ ላይ እንጠብቃቸው ወይስ እዚህ በቅጽሩ ውስጥ ምሽግ ውስጥ እንጠብቃቸው?›› ብሎ ሲጠይቅ፤ አሕመድ አሊ የሚባለው (የእስላሞች ቃዲ ይሉታል የታሪክ ፀሐፊው ተክለጻድቅ መኩሪያ) ‹‹አይ! ሜዳ ላይ ከወጣን አበሾች ፈረሰኞች ናቸው፤ በፈረስ አጎዳ ይጥሉናል፣ ስለዚህ እዚሁ አጥራችን ውስጥ ሆነን ብንጠብቃቸው ይሻለናል›› ብሎ እንደነበር የታሪክ መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡

አፄ ዮሐንስን ለመግጠም የተመደበው የዘኪ ጥምር ጦር 80 ሺህ ደርሷል። ከቁጥሩ በላይ ጦሩ ምሽጉን አጥብቆ በመያዝ የመጣበትን ጦር ለመመከት ቁርጠኛ ነበር። አዋጅ ነጋሪዎች በገጠር በከተማው እየዞሩ ሱዳናዊ ሁሉ የዕለት ተግባሩን ትቶ ጠመንጃውን አንግቶ፣ ጎራዴውን ታጥቆ ሀገሩን እንዲከላከል የመሪያቸውን ትዕዛዝ አሰሙ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የዘመቻ ዝግጅት ከተነገረው በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን የድርቡሽ ወታደራዊ ምንጮች ገለፁ። እነዚህ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት መረጃዎችን ያሰባሰቡ የነበሩ ሰላዮች የኢትዮጵያን ሠራዊት እንቅስቃሴ በሚከተለው መልክ አቀረቡት።

‹‹የሀበሻ ሠራዊት እንደሰማይ ከዋክብት እንደባሕር አሸዋ ህልቆ መስፈርት የለውም። ሠራዊቱ ሲርመሰመስ ለዓይን እይታ የሚታክት፣ መጨረሻው ከአድማስ ባሻገር የሆነ፣ የዘመቻው ንቅናቄ በሚያስነሳው ምድራዊ ደመና ፀሐይን ያጠቆረ አስፈሪ ኃይል ነው››

ይህ ደማቅ ወታደራዊ ዘገባ የድርቡሾች ዋና ከተማ የነበረችውን አምድሩማንን ከወዲህ ወዲያ በሽብር አናወጣት። ከዕለታት አንድ ቀን ሱዳን በሀበሻ እንደምትተፋ፣ የንጉሡ ፈረስም ኮቴው በፈሰሰው ደም ተውጦ፣ እንደ ወሬ ነጋሪ ከጥፋት በተረፈችው አንዲት ዛፍ ጥግ ታስሮ እንደሚታይ እንደ ትንቢት የሚነገረው አፈ ታሪክ ጊዜው መድረሱና ትንቢት የተነገረለት የሀበሻ ንጉሥ ዮሐንስ እንደሆነ ትንቢት ተናጋሪዎች አስረዱ።

በ1881 ዓ.ም ወርሃ የካቲት መጨረሻ ላይ ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ዮሐንስ 4ኛ ጎንደር ከተማን ለቅቀው በመውጣት ሕዝብን ለማጥፋት የተነሳውን ቁርጠኛ ጠላት ለመደምሰስ ሠራዊታቸውን በረድፍ በረድፍ አስከትለው ወደ ገላባት ተመሙ። ከከተማዋ አቅራቢያ እንደደረሱ አፄ ዮሐንስ እንዲህ አሉ፡፡

‹‹እንደ ሌባ ተሽሎክልኮ መጣ እንዳትለኝ፤ ለፍልሚያው ተነስቻለሁና ተነስ!›› ብለው ለድርቡሹ አዋጊና የጦር አዛዥ መልዕክት ሰደዱለት፡፡ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ከወንዶቹ ሌላ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወይዛዝርት አብረው ተሰልፈዋል። እነዚህ ሴት ዘማቾች የትዳር ጓደኞቻቸውን፣ የእጮኞቻቸውን፣ የወንድሞቻቸውንና የአባቶቻቸውን የሞትና የመከራ ጽዋ ለመቅመስ ኑሯቸውን በትነው፣ ጎጇቸውን ዘግተው ወደ ጦር ሜዳ የዘመቱ ናቸው።

አፄ ዮሐንስ በቀጥታ ወደ ውጊያው ሲገቡ፤ ሠራዊታቸው መሪውን እየተከተለ ከምሽጉ ውስጥ በፉከራና በቀረርቶ እየዘለለ ገባ። ከጦር አውድማው የሚነሳውን አቧራ አውሎ ነፋሱ ሲያነሳው እሽክርክሪት እየሠራ በውጊያው መሀል ሰይጣናዊ ጭፈራውን አቀለጠው። ከወዲያም ከወዲህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለዘመን ፍጻሜ የሚዋደቁ የሚመስሉ ወታደሮች አንዱ ሌላውን ለመለየት በማይቻልበት ሁኔታ የሞትና ሽረት ትግሉ የቀኑን ብርሃን ጽልመት አለበሰው።

ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ ጦርነቱ መሐል ገብተው ሲዋጉ ያየው የኢትዮጵያ ወታደር መንፈሱ በአንዳች ወኔ እየተፈነቀለ ግስጋሴውን ቀጠለ። የደርቡሾች ጠንካራ ምሽግ መላላትና መሳሳት ጀመረ።

ከደርቡሾች ሰይፍና የጥይት አረር ይልቅ የኢትዮጵያ ጦር የከበደው ነገር በሀገር ምድሩ የበቀለው እሾህማ ጥቅጥቅ የቆላ ግራር ነበር። ለድርቡሾች ተደራቢ ምሽግ ሆነላቸው። ሀበሾቹ ግራሩን ግራ ቀኝ ረግጠው እየዘለሉ፣ አንዳንድ ጊዜም እያቃጠሉ ወደ ዋናው የድርቡሽ ማዘዣ ጣቢያ ዘልቀው ለመግባት ሲዋጉ የድርቡሽ ሠራዊት አጋጣሚውን በመጠቀም ጥይቱን አርከፈከፈው። በዚህ የትንቅንቅ ሰዓት ነበር ከማህዲ ሰፈር አምልጠው ለኢትዮጵያ ሠራዊት እጃቸውን የሰጡ ትኹሪሮች (ደቡብ ሱዳናውያን) ጠቃሚ መረጃ የሰጡት።

በድርቡሾች የጦር ሰፈር ደካማው የውጊያ ግንባር ያለበትን ምርኮኞቹ ተናገሩ። የኢትዮጵያ ሠራዊት ለመጨረሻው የሞት ሽረት ድል ወጊያውን አፋፋመ፡፡

በሁለቱም ወገን ከተከፈለ ከባድ የሕይወት መስዋዕትነት በኋላ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደ ውቅያኖስ ማዕበል እያስገመገመ ከፊት ለፊቱ የቆመውን ሁሉ እየደመሰሰ የደርቡሾችን ወታደራዊ እምብርት ዘልቆ በመግባት የበላይነቱን ተቀዳጀ። ድልን ጨብጦ በመገስገስ ላይ የነበረውን ኃይል በተመለከቱ ጊዜ ከኋላ ሆነው ግፋ በለው እያሉ እልል ሲሉ የዋሉት በሺዎች የሚቆጠሩ የድርቡሽ ሴቶች ልብ የሚነካ እዬዬና ዋይታ ያሰሙ ጀመር።

የኢትዮጵያ ጦር አሁንም ማጥቃቱን በመቀጠልና ያገኘውን ድል በማጠናከር የድርቡሾችን ምሽግ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ። ይህ ግስጋሴ ሀበሾችን ወደ ፍፁም ድል በር የሚያደርሰው ወሳኝ ርምጃ ነበር።

የገላባት (መተማ) ጦርነት ከዚያም ከዚህም የሰው ልጅ እንደ ቅጠል ቢረግፍበትም ድል ፊቷን ወደ ዮሐንስ ማዞሯ አጠራጣሪ አልነበረም። ሐበሾች የድርቡሽን የትጥቅና የስንቅ ማከፋፈያ ማዕከልን ተቆጣጠሩ። የጦር አዛዡ አቡ አንጋ ጦርነቱን ይመራ የነበረው ከዚሁ ሠፈር ሆኖ ነበርና የዮሐንስ ወታደሮች የማዘዣ ጣቢያው መደምሰስን ተከትሎ የድርቡሾችን የሬሳና የቁስለኛ ክምር በማገላበጥ የራሱን የአቡ አንጋን አስክሬን ለማግኘት ፍለጋ ጀመሩ።

ከማዘዣ ጣቢያቸው ሙሉ በሙሉ መደምሰስና ትጥቅና ስንቃቸው በኢትዮጵያ ሠራዊት መማረክ በኋላ የድርቡሾች ወኔ ሟሸሸ። የድርቡሽ ጦር በእጁ የያዘው ጥይትና ሌላ አስፈላጊ የውጊያ መሣሪያ አልቆ መዋጋት በማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የዮሐንስ ዘማች ኃይል አሸናፊነት ርግጥ ሆነ።

ድርቡሾች ተሸንፈው እግሬ አውጭኝ እያሉ በሚሸሹበት ሰዓት ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ በአንዲት ጥይት ተመትተው መውደቃቸው በኢትዮጵያውያን ሰፈር ተሰማ። ወሬው እየተቀጣጠለ ጦሩን ግራ አጋባው፡፡ በድርቡሽ ቆራጥነት ያልተፈቱት ሀበሾች በድል አፋፍ ላይ ቆመው የድርቡሽን ሽሽት አሻግረው በሚመለከቱበት ሰዓት በንጉሠ ነገሥታቸው መመታት ድንጋጤ ጥርጣሬና ተስፋ መቁረጥ ወረራቸው። ከድል በኋላ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ በተተኮሰችው ጥይት ምክንያት የኢትዮጵያውያኑ ሠፈር ተስፋ መቁረጥና ትካዜ ገባበት። ካለ መሪ ካለ አስተባባሪ የቀረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ፊቱን ወደ ሀገሩ በማዞር ጉዞ ጀመረ። ድል ፊቷን ወደ ኢትዮጵያውያን ብታዞርም እንደገና ወደ ድርቡሽ ዞረች፡፡

የተበታተኑት የድርቡሽ ሠራዊቶች እየተሰበሰቡ ወደ ተደመሰሰው ምሽጋቸው መመለስ ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ ድል የቀናው የድርቡሽ ሠራዊት የአፄ ዮሐንስ አራተኛን ራስ ቆርጦ ለመውሰድ ዕድል አገኘ፡፡

የአፄ ዮሐንስ ራስ በአምድሩማን አደባባይ ለዕይታ ቀርቦ እንደበቃ በቆዳ ተለብዶ ወደ ደንጎላ (ዳርፉር ግዛት) ከዚያም አልፎ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ በግመል ተጭኖ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ እነሆ ዛሬ ድረስ ይህ ታሪክ በጠላትም ሆነ በወዳጅ ወገን ይነገራል፡፡

አፄ ዮሐንስ 4ኛ ከነገሥታቱ ለየት የሚያደርጋቸውም ይህ ታሪካቸው ነው፡፡ ንጉሥ ሆነው ልክ እንደ ተራ ወታደር ሲዋጉ ነው የሞቱት፡፡ እንደ ሀገር ባላቸው ታሪክ ደግሞ ኢትዮጵያ ሀገራቸውን የማያስደፍሩ ጀግኖች ሀገር መሆኗን አሳይተዋል፡፡ የጀግኖችን ታሪክ የምናስታውሰውም ለዚህ ነው፡፡

ዋለልኝ አየለ

 

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You