‹‹የእግርኳስ ዳኝነት የሙያ እና የአቅም ጉዳይ ነው››  ሊዲያ ታፈሰ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ዳኛ

በሀገራችን እግር ኳስ ስፖርት ውስጥ ስማቸው በጉልህ ከሚነሱ ሴቶች ውስጥ ናት ። እሱም ደግሞ በዳኝነት የሙያ ዘርፍ በብዛት የወንዶችን የእግር ኳስ ጨዋታ የዳኘች ሴት ዳኛ በመሆኗም በቀዳሚነት ትነሳለች ። ለብዙ ሴቶችም ኩራትና ተምሳሌት መሆን የቻለችውን ዓለምአቀፍ የእግርኳስ ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የዛሬው የአዲስ ዘመን ልዩ እትም እንግዳችን አድርገናታል ።

ተወልዳ ያደገችው በጅማ ከተማ ነው ። ለቤተሰቦቿም የመጨረሻ ልጅ ናት። አብዛኛውን የልጅነት ጊዜዋን በመንፈሳዊው ውስጥ በማገልገል እንዳሳለፈችው ትናገራለች ። የስፖርት እና የእርሷ ግንኙነትም የሚጀምረው ከትምህርት ቤት ነው። በተማሪነት ጊዜዋ የቅርጫት ኳስ ትጫወት ነበር። በስፖርት ውስጥ በንቃት መሳተፍ የጀመረችው ከልጅነቷ ቢሆንም በዚህ ሥራዋም ሆነ በምታደርገው እንቅስቃሴ የተቃወማት የቤተሰብ አካል አልነበረም ። በትምህርት ቤት ውስጥ ሳለች የቅርጫት ኳስን ጅማ ከተማን ወክላ ትጫወት ነበር። ታዲያ በአንድ ወቅት ወደ ጅማ የመጣው ኢንስትራክተር ሽፈራው፣ ለአራት ሴቶች የእግር ኳስ ዳኝነት ሥልጠናን ለመስጠት እድልን ፈጠረ።

ታዲያ ሊዲያም ከአራት ሴቶች ውስጥ አንዷ ሆና ሥልጠናውን ከሌሎች ወንዶች ጋር በጋራ ለመውሰድ ቻሉ ። ይህ አጋጣሚም ለሊዲያ የዳኝነት ሕይወትን ‹‹ሀ›› ብላ እንድትጀምር አድርጓታል። ሥልጠናውን ከወሰደች በኋላም ከ17 ዓመት በታች ያለን ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ የመዳኘት እድሉን አግኝታለች። ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በፋርማሲ ቢሆንም ልቧ ግን በአብዛኛው ወደ ዳኝነቱ አድልቶ በትምህርትቤት በአጋጣሚ የወሰደችው ሥልጠና ከ15 ዓመት በላይ ያገለገለችበት ሙያ ለመሆን ችሏል። ሊዲያ የዳኝነት ሥልጠናዋን ካጠናቀቀች በኋላ ለሙያው ያላትን መረዳት እያሳደገች የተለያዩ ጨዋታዎች በረዳት ዳኝነት ከዚያም ደግሞ በመሀል ዳኝነት ማጫወቷን ቀጠለች።

የእግር ኳስ ዳኝነት እንኳን ለሴት ለወንዶችም ቢሆን ከባድ እንደሆነ የምትናገረው ሊዲያ ለዚህ እንደምክንያትነት የሚነሳው ደግሞ በሜዳው ውስጥ ያሉ ተጫዋቾችም ሆኑ ደጋፊዎች ዓላማቸው ማሸነፍ ነውና አንዳንዴም ከእውቀት ማነስ አንዳንዴም ደግሞ ለማሸነፍ ከመፈለግ ሜዳ ውስጥ ግጭት አለመግባባት ዳኞች ላይ ጉዳት የማድረስ ነገር ይኖራል ። ‹‹በሜዳ ውስጥ እንዲህ ነው የምለው በጣም የተጋነነ ጉዳት አልደረሰብኝም ›› ትላለች ።

ሊዲያ የዳኝነት ሥልጠናዋን ካጠናቀቀች በኋላ የተለያዩ ጨዋታዎችን የዳኘች ሲሆን፣ ዓለምአቀፍ ሥራዋን የጀመረችው በ (ኦል አፍሪካን ጌም) ከዚያም የሀገር ውስጥ ሥልጠናዎችን እና ፊፋ የሚያዘጋጃቸውን ሥልጠናዎች በመውሰድ ዓለምአቀፍ ጨዋታዎችን በተደጋጋሚ የመዳኘት እድሉንም አገኘች።

ሁለት ጨዋታዎችን በኦል አፍሪካን ጌም፣ አምስት የአፍሪካ ዋንጫዎችን ፣ በአውሮፓ ፊፋ በሚያዘጋጃቸው አንዳንድ ውድድሮች ላይ ፣ በዓለም ዋንጫ ላይ አንድ ከ20 ዓመት በታች እና ሁለት ከ17 ዓመት በታች እንዲሁም የዓለም ዋንጫ ላይ በዳኝነት ተሳትፋለች። በአፍሪካ ደረጃ የወንዶችን የቻን ውድድር ያጫወተች የመጀመሪያዋ ሴት ዳኛ ናት የቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የመጨረሻ ጨዋታውን ጭምር ዳኝታለች።

‹‹ወንድም ሆነ ሴት ዳኝነት የሚፈልገው ሜዳ ውስጥ የጥንካሬ እና የአቅም ጉዳይ ነው ። ›› የምትለው ሊዲያ በጾታ ልዩነት ሳይሆን ሙያው የሚጠይቀውን እውቀት ፣ ክህሎት እና ጥንካሬ መያዝ እና መወዳደር የምታምንበት ሃሳብ ነው ። በሌላው ዓለም ልክ እንደ ኢትዮጵያ ብዙም ፈተና ላይኖረው ይችላል። በሀገራችን ዳኝነት ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እና ለመሳተፍ እድሉን ሲያገኙ የሚታይባቸውን የቋንቋ ችግር ፣ ከሰዎች ጋር የመግባባት ክህሎታቸውን መጨመር እና በአሁኑ ሰዓት በዘርፉ ላይ እየተዋወቁ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መላመድና ቴክኖሊጂዎችን ለመጠቀም ራሳቸውን ማብቃት ይጠበቅባቸዋል በማለት ትገልጻለች። ከዚህም ባሻገር አንድ ዳኛ ራሱን በአካል ብቃት ማዘጋጀት እና ብቁ መሆን እንዳለበት በተደጋጋሚ የምታነሳው ጉዳይ ነው ።

ሊዲያ ሥራዋን በጀመረችበት ወቅት በእግርኳስ ዳኝነት ውስጥ ብቸኛ ሴት እስከመባል ድረስ ጎልታ የምትታይ ባለሙያ ነበረች። በሥራ ቆይታዋም ለሌሎች ሴት ዳኞች መምጣት ምሳሌ ሆና በተለያየ ጊዜ ልምዷን ታካፍላለች። ነገር ግን አሁን ሊዲያ ይህንን የዳኝነት ሥራዋን በቃኝ ያለችበት ሰዓት ላይ ትገኛለች ። ታዲያ በሥራ በቆየችባቸው ዓመታትም ብዙዎች ራስሽን ሳትተኪ ነው የወጣሽው ይሏታል ። እሷ ደግሞ ‹‹ በአሁኑ ሰዓት አራት ዓለምአቀፍ ሴት የመሀል ዳኞች አራት ረዳት ዳኞች ያሉ ሲሆን ሌሎች ሴት ዳኞችም እድሉን እያገኙ እየወጡ ይገኛሉ።›› በማለት ትገልጻለች።

ሊዲያ ያሳለፈችው እና በሙያው ላይ የነበራት የሥራ ቆይታም እንደ ጥሩ ተሞክሮ ሊሆናቸው እንደሚችል ታስባለች ። ‹‹በሙያው ላይ እያለውም ጀምሮ ከሴት ዳኞች ጋር ልምድ የመለዋወጥ ፣ እነሱን የማስተማር ፣ ጨዋታዎችን የመገምገም እድሉን ስላገኘሁ እነዚህ ስራዎች ይጠቅማቸዋል ብዬ አስባለሁ።›› በማለት ትገልጻለች።

በሀገራችን ካሉ የሙያ ዘርፎች የስፖርት ዘርፍ ሴቶች እንደ እንግዳ የሚታዩበት የሙያ ዘርፍ ይመስላል ምንም እንኳን አሁን ላይ ይህ አመለካከት እየቀነሰ መጥቶ ሴቶች በዳኝነትም ሆነ በተጫዋችነት ሀገራቸውን ወክለው እየተሳተፉ ቢገኝም ቀድሞ የነበረው አመለካከት ቢኖርም። ታዲያ በዳኝነት ሙያ ላይ ያሉ ሴቶች በብዛት የሴቶችን ጨዋታ ብቻ የሚዳኙ ተደርጎ ይወሰዳል ። የወንዶችን ጨዋታ መዳኘት ለሴቶች የሚያስፈራ ነገር ይመስላል ። ‹‹ዳኝነት የሙያ ጉዳይ በመሆኑ ያስፈራል የሚል እምነት የለኝም ዳኝነት በባህሪው ለሴት ለወንድም የሚከብድ ነው ። ነገር ግን ጠንካራ መሆን እና የአዕምሮ ዝግጁነት ፣ ምንም ነገር አያቅተኝም የሚለውን ሃሳብ በውስጥ መያዝን ይጠይቃል።››

ሊዲያ የተለያዩ ጨዋታዎችን ዳኝታለች በሁሉም ጨዋታዎቿ ላይ የምታሳየው ኮስተር ያለ ባህሪም ተጫዋቾችም ሆኑ ደጋፊዎች በሜዳ ውስጥ በምትዳኝበት ጊዜ እንዲያከብሯት አድርጓል ። ከተጫዋቾች ጋርም ባላት መልካም ግንኙነት ከዳኝነት ባለፈ ለምትሰጣቸው ምክርም ‹‹ዳኛ ነች ወይስ አሠልጣኝ ›› ይባልላታል። ከሴቶች እና ከወንዶች ጨዋታ ምርጫ ቢሰጣትም‹‹ የወንዶችን ጨዋታ በምዳኝበት ወቅት ጠንካራ ሆናለሁ ፣ ኮስታራ ሆናለሁ እና ለኔ የወንዶችን ጨዋታ መዳኘት ይቀለኛል።›› በማለት ትገልጸዋለች።

ዳኛ መሆን ማለት በሜዳው መሀል ላይ ሆነው ለአሸናፊነት የሚፋለሙት የሁለት እግርኳ ቡድኖችን በእኩል አይን ሕጉን ተከትሎ መዳኘት ነው ። ሁለቱም ቡድኖች መጨረሻ ላይ አሸናፊ መሆን ህልማቸው ነው። ዳኛ ደግሞ ጨዋታውን ሕጉን በተከተለ መልኩ ማስኬድ ፤ ታዲያ በዚ መሀል ሕግ ቢኖር ፣ ሃላፊነት ቢኖር ሰው ናቸው እና ልባቸው ለማን ያደላ ይሆን ? የትኛው ጨዋታ ይማርካቸው ይሆን ? ፤ ይህ ቡድን ባሸነፈ የሚሉት የላቸውም ይሆን ? የሚለው ጥያቄ በተለይ በሜዳው ውስጥ ታድመው ባሉ ደጋፊዎች ላይ የሚመላለስ ጥያቄ ነው። ‹‹ዳኛ ብሆንም ጨዋታውን መመልከቴ ስለማይቀር የምደግፈው ቡድን ይኖራል ። ነገር ግን ይህን ቡድን ነው የምደግፈው ብሎ በይፋ መናገር በተለይ በእኛ ሀገር ነገሮች በተለየ አቅጣጫ የሚታዩ በመሆናቸው ከባድ ነው ። ›› የምትለው ሊዲያ ‹‹እንደ እግር ኳስ ተመልካች ግን የምደግፈው ቢኖርም በዳኝነት ሕይወቴ ግን የሚቆጨኝንና ህሊናዬን የሚጸጽተኝን ነገር አላደረኩም።›› ባይ ነች። በዚህም የሙያ ጓደኞቿም ሆኑ ተጫዋቾች የሚመሰክሩላት ነው ።

ሆኖም ሊዲያ ከኢትዮጵያ ውጪ የማንቺስተር ደጋፊ ስትሆን ልክ እንደሌሎች ደጋፊዎች ሲያሸንፍ በደስታ ሲሸነፍ ደግሞ በጣም በንዴት ስሜት የምትደግፈው ቡድን ነው ። በትርፍ ሰዓቷን ልምዷን ከማካፈል ባለፈ የተለያዩ ጨዋታዎችን በማየት ታሳልፋለች።

‹‹በዳኝነት ሙያ ቆይታዬ ይህ ቀረኝ የምለው የለም ብዙ ሥራዎች ብዙ ስኬቶችን አግኝቻለሁ›› የምትለው ሊዲያ በቆይታዋ በአፍሪካ የወንዶችን የቻን ውድድር የመራች ፣የዳኘች ፣ ያጫወተች የመጀመሪያዋ ሴት ዳኛ ናት። ከሷ በመቀጠልም ሌሎች ሴት ዳኞች በአፍሪካ ይህንን እድል አግኝተዋል ሊዲያም ለዚህ በር ከፋች በመሆኗ ደስተኛ እና ትልቅ እድል እንደሆነ ትናገራለች። በእግርኳሱ ዓለም በነበራት ቆይታም የተለያዩ እውቅናዎች እና ሽልማቶችን ያገኘች ሲሆን ራሷን ከዳኝነት ባገለለችበት ወቅትም ምስጋና እውቅና ተሰጥቷታል ።

ሊዲያ ታፈሰ ዳኝነት በሜዳ ውስጥ እንኳን ጉዳት ደርሶባቸው ተመልሰው ግን ጨዋታ ለመዳኘት የሚመጡበትና ለመተው ቀላል ያልሆነ ሙያ መሆኑን ትገልጻለች። ሊዲያ ከ15 ዓመት በላይ ቆይታ በኋላ ይህንን ሥራዋን ጨርሳ ወጥታለች። ዳኝነትን ከመተዋም በፊት እና አሁንም ከሴትም ወንዶች ዳኞች ጋር በመሆን ጨዋታዎችን ትገመግማለች ታስተምራለች። ዳኞችም የተሰጣቸውን ሥልጠና ተቀብለው የመተግበር ራሳቸውን የማብቃት እና የሚያገኙትን እድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባቸው ትገልጻለች።

ሊዲያ ከዚህ ሁሉ ዓመት የሥራ ቆይታ በኋላ ሥራዋን የመተው ሃሳብ በውስጧ የነበረ ሲሆን ነገር ግን ፊፋ በአዘጋጀው ሥልጠና ላይ እንድትጋበዝ ጥሪ ሲቀርብላት ሥልጠናውን የወሰድኩ እንደሆን በሥራው ላይ ልቀጥልበት ይገባል በማለት የተሰጣትን እድል አመስግና ሥራዋን በዚሁ ልታቆም ችላለች። ሊዲያ ከሥራዋ ባሻገር ትዳር የመሰረተች ሲሆን የአንድ ሴት ልጅ እናትም ነች ። በሀገራችን የተለያየ ዘርፍ ላይ በርካታ አስተዋጽኦ ያደረጉ ባለሙያዎች ታሪካቸውን የመጻፍ እና ለሌሎች እንዲቀመጥ የማድረግ ልምድ የላቸውም። ሊዲያ በተለያዩ መድረኮች ላይ ልምዷን ያካፈለች ሲሆን ይህንን ታሪኳን እና የሕይወት ልምዷን በአንድ የመሰነድ ሃሳብም አላት።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You