የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሞተር

በዓለም ላይ ከሚዘጋጁ የጎዳና ላይ ውድድሮች በአስደሳችነቱ ከቀዳሚዎቹ መካከል አንዱ፣ በአፍሪካ ደግሞ በግዝፈቱ ቀዳሚው ሩጫ፤ ኢትዮጵያዊው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ነው። ከተለያዩ የዓለም ሃገራት ተሳታፊዎችን የሚስበው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እስከ 50ሺ የሚደርሱ ተሳታፊዎችን በማስሮጥ በአውሮፓና አሜሪካ ከሚደረጉት ታላላቅ የሩጫ ውድድሮች ተርታ ይሰለፋል። የኢትዮጵያዊያን ኩራት የሆነው ይህ ተቋም በርካቶችን በሩጫ ከማሳተፍ ባለፈ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ (የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር አባል) በመሆኑ ታዋቂና ጀማሪ አትሌቶችንም በማፎካከር የገቡበትን ሰዓት ያስመዘግባል።

‹‹የሯጮቹ ምድር›› የሚል ቅጽል ያተረፈችው ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት መልካም ገጽታዋን የገነባች እንደመሆኑ በዚህ ሩጫ ላይ መሳተፍ ከዓለም የአትሌቲክስ ከዋክብት ጋር መሮጥ በመሆኑም የተለየ ትርጉም ያሰጠዋል። እጅግ ደማቅ፣ በአስደሳች ድምጽ የታጀበ እና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን በቅርበት ለማወቅ ምቹ እንደሆነ ስለሚነገርለትም የውጪ ዜጎችን ይስባል። ይህም በስፖርት ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦን ያበረክታል። ከሚያገኘው ገቢ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች በየዓመቱ በማበርከት ማህበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣው ተቋሙ፣ ሴቶችን፣ ህጻናትን፣ ተፈጥሮን፣ ጤናን፣… የሚመለከቱ መልዕክቶችን በማስተላለፍም ይታወቃል። በዛሬው ዕለት የሚከበረውን የሴቶች ቀንን (ማርች8) ተከትሎም የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ በማከናወን ሴቶችን የማነሳሳትና የማነቃቃት ስራ ያከናውናል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስተዋወቀው ተቋም የሩጫውን የደስታ መንፈስ እንደጠበቀ ቆይቷል። ኢትዮጵያን ተሻግሮም በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ጭምር የሩጫ ውድድርን ለማዘጋጀትም ችሏል። በስራ ባህሉ ለበርካቶች ተምሳሌት ሲሆን፤ በሃገር አቀፍ ደረጃ ግዙፍ ውድድሮችን በማስተናገድ የሚስተካከለው የለም። ከዚህም በላይ ሊባልለት የሚገባውን ይህንን ተቋም የምታንቀሳቅሰው ሞተር ደግሞ ሴት ናት። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ዳግማዊት አማረ ልምዷ ለብዙዎች አርዓያ ሊሆንና ተነሳሽነትን ሊፈጥር ይችላል በሚል የዛሬው ልዩ እትም እንግዳ ሆናለች።

አዲስ ዘመን፡- ታላቁ ሩጫ በዓመት ውስጥ ምን ያህል ውድድሮችን ያዘጋጃል?

ወይዘሪት ዳግማዊት፡- በየዓመቱ በአማካይ ከ6 እስከ 8 የሚደርሱ ሩጫዎችን ያካሂዳል። በዋናነት 10 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ታላቁ ሩጫ፣ የሴቶች 5 ኪሎ ሜትር፣ የሃዋሳ ሃይቅ ግማሽ ማራቶን፣ የዱላ ቅብብል፣ የህጻናት እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ሩጫዎችም ይደረጋሉ።

አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሁሉ ውድድር ማዘጋጀት እና መምራትስ ምን ያህል አቅም ይጠይቃል?

ወይዘሪት ዳግማዊት፡ ውድድር ማዘጋጀት የሩጫ ቲሸርት መሸጥ ብቻ የሚመስላቸው በርካቶች ናቸው። ነገር ግን በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚዘጋጁ አብዛኛዎቹ ሩጫዎች እንደሃገር የሚደረጉ በመሆናቸው፤ ከአትሌቶችና ተሳታፊ (የውጪ ዜጎችን ጨምሮ) ባለፈ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት፣ ከአጋር ድርጅቶች፣ በጎ ፈቃፈኞች፣ የመገናኛ ብዙሃን፣… ጋር መስራት የግድ ይላል። ሁሉም ሩጫዎች የየራሳቸው ባህሪ ያላቸው ከመሆኑም ባለፈ ሁሌም አዲስ ነገርን ለመፍጠር እንጥራለን። ይኸውም ከፍተኛ ስራ የሚጠይቅ ሲሆን፤ አንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አቅምንና ማንነትን የሚፈታተኑ ይሆናሉ። በእርግጥ ራስን መለካት የሚቻለው በተጓዙበት ርቀት ልክ ነው። በተለይ ውድድሮች ሲቃረቡ ከፍተኛ ጭንቀት ስለሚኖር ጠንካራ ስራ እና ተነሳሽነትን ይጠይቃል።

እንደ ሴት ደግሞ ሁሉም ነገር የተስተካከለ እንዲሆን መጠንቀቅን ጨምሮ ስሜታዊ (የሚያስደስት፣ የሚያስለቅስ፣…) ሊያደርግ ይችላል። የምንሰራው ሰው ላይ በመሆኑ ከእኔ ውጪ ያሉ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሰራተኞች የሩጫውን ተሳታፊ በሙሉ ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ኃላፊነትን በእኩል በመጋራት ጫናውን ለማቅለልም እንሞክራለን። ከሩጫው አስቀድሞ ያለውን ውጥረት በሩጫው ዕለት የህዝቡን ደስታ ስንመለከት ወደ ሃሴት ተቀይሮ ስለሚቀጥለው ሩጫ ማሰብም እንጀምራለን። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እንደሃገር ትልቁ ሩጫ በመሆኑ በዚህ ተቋም ውስጥ ህዝብን ማገልገል ኩራት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በእርግጥም ስራው ትከሻ የሚጠይቅ ነው፤ ታዲያ አንቺ ይህንን ስፖርታዊ ተቋም የመምራት ችሎታ እንዴት ልታዳብሪ ቻልሽ?

ወይዘሪት ዳግማዊት፡- አሁን ያለሁበት የደረስኩት በሂደት ነው፤ ከእንግዳ ተቀባይነት አንስቶ ሌሎች ስራዎችን በመስራት ለዓመታት በዚህ ተቋም ልምዴን ማዳበር ችያለሁ። እያንዳንዱ እርምጃ አዲስ ነገር ይጨምራል፤ የማይታለፉ የሚመስሉ ሁኔታዎች ጭምር አስተምረውን የሚያልፉት ነገር አለ። ሁሌም ራስን ለትምህርት ማዘጋጀትም አስፈላጊ ነው፤ ስራው የብዙዎች እንደመሆኑ የሌሎች ሰዎችን አስተያየትና ምክርን መውሰድም ይለውጣል። ከእኔ በፊት ከነበሩት የታላቁ ሩጫ መሪዎች እንዲሁም በአውሮፓ ሃገራት ካሉ የውድድር አዘጋጅ ድርጅቶችም በርካታ ዕውቀት አግኝቻለሁ። በእርግጥ ማንነትም የራሱ ሚና አለው፤ ባህሪዬ ተፎካካሪ የሚባል ነው፤ ከልጅነቴ አንስቶ አሸናፊ ለመሆን፣ አዲስ ነገር ለመፍጠር እና ችግሮችን በቶሎ ለማለፍ የነበረኝ ነገር አድጎ አሁንም በስራ ላይ እየተገበርኩት ነው። በስራዬ ቀጥተኛና እውነተኛ ያደረገኝን ባህሪ ያዳበርኩት ደግሞ ከአባቴ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በሌላው ዓለምም የሩጫ ውድድሮችን የሚያዘጋጁ በርካታ ተቋማት አሉ፤ ካለሽ ልምድ በሴቶች የሚመራ ውድድር ይኖር ይሆን?

ወይዘሪት ዳግማዊት፡– ከዚህ ቀደም የነበረችው የኒውዮርክ ማራቶን ዳይሬክተር ሴት እንደነበረች አውቃለሁ። የዓለም ጎዳና ላይ ውድድሮች ማህበር (AIMS) ጨምሮ በርካታ የጎዳና የውድድር የሚያዘጋጁ ድርጅቶች ውስጥ ያሉት ሴቶችን የሚመለከት ካልሆነ በቀር በመሪነት ደረጃ የሉም።

አዲስ ዘመን፡- ይህ ትልቅ ስኬት ነው፤ ለበርካቶችም መነሳሳትን ይፈጥራል።

ወይዘሪት ዳግማዊት፡– ልክ ነው፤ ነገር ግን ዋናው ነገር ቦታውን መያዝ ብቻ ሳይሆን እንደሃገር የሚያኮራና ሁሉንም የሚያስደስት ስራ ማከናወን ነው። በዚህ ውስጥ የሚመለከቱን ይኖራሉ ስለዚህም እኔ ብቻ ሳልሆን እንደተቋም ካለንበት ሸርተት ማለት የለብንም ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በዚህ ስራ ላይ ባሳለፍሻቸው ዓመታት ሴቶችን በሚመለከት ምን ታዝበሻል?

ወይዘሪት ዳግማዊት፡- ከሴቶች ጋር በተያያዘ የተለመደው ነገር እኩልነት የሚለው ነው፤ የመማር፣ የመስራት፣…። ነገር ግን አሁንም ጎታች የሆኑና ሊቀየሩ የሚገባቸው አስተሳሰቦች አሉ። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የሴቶች ቀንን (ማርች 8) አስመልክቶ የሚደረገው ሩጫ ሲሆን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ያሳትፋል። ስፖርት ውስጥ ነጻነት አለ፤ ሩጫው ላይ በብዙዎች ዘንድ የሚታየውም ይኸው ነው፣ በብዙ ምክንያቶች ያጧቸውን ደስታ ያጣጥማሉ። ከብዙዎች ጋር የመገናኘት እድልና በህይወታቸው ውስጥ ካለው ችግር አረፍ የሚሉበት የምንጊዜም ትውስታ ሊሆንም ይችላል።

ምናልባት የሴቶች ችግር በዚህ ላይቀረፍ ይችል ይሆናል። ነገር ግን በሩጫው ላይ የሚተላለፈው መልዕክት፣ ተምሳሌት ሴቶችን መመልከት፣… የማነቃቃት ኃይል አለው። የሴቶች ሩጫ ከተጀመረ ዘንድሮ 21ኛ ዓመቱ ነው፤ ይህ እድሜ በአብዛኞቻችን ህይወት ትምህርት ጨርሰን ወደ ስራ የምንገባበት ነው። ከትምህርት ቤት ባለፈ በርካታ ትምህርት የምናገኝበትና በህይወታችንም ለውጥ የምናመጣበት ወቅት ነው። በመሆኑም እርስ በእርስ በመተጋገዝ ወደ አዲስ ነገርና የተሻለ ነገር ማደግ እንዳለብን አስባለሁ።

በስፖርት ታሪክ የሴቶች ተሳትፎ 50 ዓመት ቢሆነው ነው፤ ይህም ብዙ ተከልክለን እንደቆየን የሚያሳይ በመሆኑ አነሳሽ ምክንያት ይሆናል። ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ግን ጠንክረን መስራት እንደሚገባን ያሳየናል። በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት በሚካሄዱ ውድድሮች ሴቶች ውጤታማ ቢሆኑም አሁንም ግን በቁጥር ረገድ ከፍተኛ ልዩነት አለ።

በሌላ በኩል በስፖርቱ አመራርነትም ተጨማሪ እድል ለሴቶች ሊሰጥ ይገባል። ዕድል ሲያገኙ ደግሞ መቻላቸውን ከመጠራጠር ይልቅ ድጋፍ ቢሆኑ፣ ባይሳካላቸውም ደግሞ እንደማንኛውም ሰው የመመልከት እንጂ ሴት ስለሆነች በሚል አለመመዘን ተገቢ ነው። ይህ ማለት ግን ዕድሉን የሚያገኙ ሴቶችም ራሳቸውን ማብቃትና በጥንካሬ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። ለምሳሌ እኔ የምሰራው ታላቁ ሩጫን ለማኩራት ነው፤ ይህ ሲሆን ኢትዮጵያን ማኩራት እንደሆነ አውቃለሁ። እኔ ካልቻልኩ ታላቁ ሩጫ እንዲሁም ኢትዮጵያ አትችልም እደሚያሰኝ እረዳለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቆይታሽ የማትረሻቸው አጋጣሚዎች ይኖሩ ይሆን?

ወይዘሪት ዳግማዊት፡– ከአስደሳቹ ስነሳ እ.አ.አ በ2015 ጀግናው አትሌትና የዚህ ውድድር መስራች የሆነው ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የመጨረሻውን ተሳትፎ ባደረገበት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቀዳሚው ነው። በወቅቱ ስሜታዊ ያደርግ የነበረው የአትሌቱ ስንብት መቼም የሚረሳ አይደለም። የፈተነኝ ደግሞ በ2014 ዓ.ም የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ውድድሩን ለማዘጋጀት አስጨናቂ ሁኔታዎችን ማለፍ ነበረብን። በወቅቱ አዕምሯዊም አካላዊም ፈተናዎችን እስተናግጃለሁ። በእርግጥ ከ40ሺ በላይ ሰዎችን አሳትፈን ሩጫውን አካሂደናል፤ ነገር ግን የሩጫው መዳረሻ ሊረሳ የማይችል ከባድ ሁኔታን አልፈናል። ‹የማይገልህ ነገር ያጠነክርሃል› እንደሚባለው ሆኖ ከባልደረቦቼ ጋር ሆነን የነበረውን ሁኔታ ልናልፈው ችለናል።

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም የምታስተላልፊው መልዕክት ካለ?

ወይዘሪት ዳግማዊት፡– በአንድ ጫካ እሳት ይነሳና አንዲት ትንሽ ወፍ በትንሹ መንቁሯ ውሃ በማመላለስ ለማጥፋት ጥረት ስታደርግ የተመለከቷት ምን አቅም አላት ብለው አሾፉባት። በዚህ ጊዜ ዋናው ነገር የአቅምን ማድረግ እንጂ መጠኑ አይደለም ስትል መለሰችላቸው። እኛም ባለንበት የትኛውም ቦታ የአቅማችንን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን እላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

ወይዘሪት ዳግማዊት፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You