በየታክሲው፣ በየሱቁ፣ በየምግብ ቤቱ፣ በአጠቃላይ ግብይት በሚፈጸምባቸው ቦታዎች ሁሉ የምንሰማው ‹‹ይህን አልቀበልም›› የሚል የተቀደደ የወረቀት ብር ጭቅጭቅ ነው፡፡ ሻጩ ‹‹ይህን አልቀበልም›› ይላል፤ ሸማቹም መልስ ሲመለስለት ‹‹ይህን አልቀበልም›› ይላል፡፡ አስተናጋጆች ወይም የታክሲ ረዳቶች ‹‹ይህን አይቀበሉኝም›› ይላሉ። ተሳፋሪው ‹‹ከእናንተው ነው የተቀበልኩት›› ይላል። ረዳቱም ‹‹እና ከእኔ አልተቀበልከው›› እያለ ጭቅጭቃቸው ይቀጥላል፡፡
በተቀደደ ብር ጭቅጭቅ ውስጥ ሁሉም ራሱን ለማዳን ብቻ ነው የሚከራከረው፡፡ ሲሰጥ፤ እንዲቀበሉት ለማግባባት ‹‹ቁጥሩ ካለ ደግሞ ምን ችግር አለው? ምን ታካብዳለህ!›› ይላል። ለእሱ ሲሰጠው ግን እየመረጠ እያወጣ ‹‹ይህን ቀይርልኝ፣ ይህን አይቀበሉኝም›› ይላል፡፡ እምቢ ብለውት ወይም ልብ ሳይለው ተሳስቶ የመጣበት ብር ካለ ግን ሲነጫነጭ እንዳልነበር ሁሉ ምንም ችግር እንደሌለው አድርጎ አግባብቶ ለመስጠት ይሞክራል።
ለዚህ ሁሉ የዳረገን ግን እጅግ ኋላቀር የሆነ የወረቀት ብር አያያዝ ልማዳችን ነው፡፡ ዓለም የዲጂታል ግብይት ላይ ደርሷል፤ እሱን መጠቀም ቢያቅተን የወረቀት ብር እንኳን በአግባቡ መያዝ የማንችል ሆነናል፡፡ ከብዙ ሰዎች የታዘብኩት ነገር የወረቀት ብር በጥንቃቄ በሚይዝ ሰው ይስቃሉ፤ ይባስ ብሎ ‹‹እኔ እንደዚህ እጥፍጥፍ እና ስብርብር ካላለ ደስ አይለኝም›› የሚሉ አሉ፡፡ እንደ ሳር በአምስቱም ጣታቸው እያግበሰበሱ ይይዙታል።
ወንዶች ከኪሳቸው ካወጡ በኋላ የሚፈለገውን ነጥለው የተረፈውን ወደኪሳቸው ሲከቱ እንደተጣጠፈ በኃይል በመጠቅጠቅ ነው፣ ወደታች በመግፋት ነው፡፡ ብሮችን አነባብሮ አንድ ጊዜ ብቻ አጥፎ ማስቀመጥ ምን ያህል ጊዜ የሚወስድ ሆኖ ነው?
ሴቶች ደግሞ ከቦርሳቸው ውስጥ ሲያወጡ ከጆሮ ማዳመጫ (ኤርፎን) ገመድ ጋር በመጠላለፍ የብሩን ጫፍ በመያዝ በኃይል በመጎተት ነው፡፡ ከብዙ ኮተት ውስጥ በመጎተት ብሩ እየተጎዳ ይሄዳል ማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ ብር መቅደድ ሕገ ወጥ ድርጊት ነው፡፡ እርግጥ ነው ለራሱ ጥቅም ሲል ማንም ሰው ሆን ብሎ አይቀድም፤ ዳሩ ግን በግደለሽነት ብሩ ይቀደዳል፡፡ የወረቀት ብር በጥንቃቄ መያዝ እንደ ሥራ ፈትነት፣ ወይም እንደ ወግ አጥባቂነት (እንደ ፋራነት)፣ የሚያዩት ብዙዎች ናቸው፡፡ ዳሩ ግን በሀገርና በሕዝብ ላይ ኪሳራ እያደረሱ ነው፡፡ የንግድ ተቋማት የተቀደዱና አገልግሎት ላይ መዋል የማይችሉ ብሮችን ይዘው ወደ ባንክ ይሄዳሉ፡፡ በእነዚያ ከጥቅም ውጪ በሆኑ ብሮች ምትክ ሌላ ብር ይታተማል፤ ስለዚህ ሀገሪቱ ያልተፈለገ ወጪ አወጣች ማለት ነው፡፡ የታተመ ብር ከጥቅም ውጪ በሆነ ቁጥር ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡
አሁን አሁን የኤ ቲ ኤም ማሽኖች ራሱ የተቀደደ ብር መስጠት ጀምረዋል፤ ምክንያቱም ወደ ማሽኑ የሚገባው ብር ከባንኩ ካዝና የሚወጣ ነው፡፡ ወደ ካዝናው የሚገባው ብር ደግሞ አዲስ የታተመ ብቻ ሳይሆን ከሰዎች የገንዘብ ዝውውር የሚገኝ ነው። ስለዚህ በሰዎች እጅ ላይ ጉዳት የደረሰበት ብር ተመልሶ ወደ ሰዎች ይሄዳል ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው የተቀደደ ብር ባንክ ቢያስገባ ተዘዋውሮ ድጋሚ በራሱ እጅ ሊገባ ይችላል፡፡ ስለዚህ እኛ የፈጠርነው ግደለሽነት እኛኑ ይጎዳል ማለት ነው፡፡
የወረቀት ብር በጥንቃቄ የማይዙ ሰዎች ናቸው የተቀደደ ብር አልቀበልም በማለት የሚጨቃጨቁት፡፡ እነዚህ ሰዎች ራስ ወዳድ እና ግደለሽ ስለሆኑ የራሳቸውን ስሜት ብቻ የሚከተሉ ናቸው፡፡ የራሳቸው ስሜት ብር አጣጥፎ እና ሰባብሮ መያዝ ስለሆነ እንደዚያ ማድረግ ያስደስታቸዋል፤ ስለዚህ ብሩ ይቀደዳል፡፡ ብር በማበላሸት ተዝናኑ ማለት ነው፡፡ ‹‹ብር በጥንቃቄ መያዝ አይመቸኝም፤ ይጨንቀኛል›› ይላሉ፡፡
አንዳንድ ነገሮች ላይ የግል ስሜት አንከተልም። መርህ እና ሕግ ሊገድበን ይገባል፡፡ ብር የጋራ መገበያያ ነው፡፡ እኔ ጋ ያለ ብር ነገ ሌላ ሰው ጋ ይሄዳል፤ ስለዚህ አይቀበለኝም ማለት ነው፡፡ ራሳችንንም ጭምር እየጎዳን እና እያከሰርን ነው፡፡ የግል ስሜታችንን መከተል ያለብን የግል በሆነ ነገር ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ የልብስ ቀለም ምርጫ፣ የምግብ ምርጫ… የመሳሰሉት በግል ስሜት የሚደረጉ ናቸው፡፡ የሕዝብ ንብረት በግል ስሜቴ ነው የምጠቀምበት ማለት ግን ስንፍና እና አላዋቂነት ነው፡፡ አንዱ የኋላቀርነት ምልክት የሰው ልጅ መተዳደሪያ የሆነውን ሕግ እና መርህ አለማክበር ነው፡፡ ምንም እንኳን ስለብር አያያዝ የወጣ አዋጅ ባይኖርም ብር መቅደድ ግን ሕገ ወጥ ነው፡፡
የራሴን ተሞክሮ ልናገር፡፡ በዚህ ባህሪዬ የሚስቁብኝ ጓደኞቼ ሁሉ አሉ፡፡ በዚሁ ምክንያት ተደብቄ ሁሉ አደርገዋለሁ፡፡ ይሄውም የብር አቀማመጥን ማስተካከል ነው፡፡ የሆነ ነገር ገዝቼ መልስ ስቀበል ወደ ኪሴ የምከተው መሐሉ ላይ አንድ ጊዜ ብቻ አጥፌ ነው፡፡ በግብይቱ ቅጽበት እንደዚያ ማድረግ ምቾት አይሰጥም፤ ጊዜም ይወስዳል፡፡ ተቀብዬ ኪሴ ካስገባሁ በኋላ ቁጭ (ቆም) ብዬ አደራጀዋለሁ፡፡ የታጠፉ ብሮችን እየዘረጋሁ አስተካክላለሁ፡፡ ይህን የማደርገው ጫፉ የታጠፈው ብር የተሰነጠቀ ስለሚሆን እና በዚያው ልክ እየሰፋ ስለሚሄድ ነው፡፡ አስተካክዬ ባልተቀደዱ ብሮች መካከል በማድረግ ሳወጣ ሳስገባ ተጨማሪ እንዳይቀደድ አደርገዋለሁ፡፡ ከኤ ቲ ኤም ማሽን ብር ሳወጣ፤ ልክ እንዳወጣሁ የብሮችን ጫፍ እኩል አድርጌ መሐሉ ላይ ማጠፍ ነው፡፡ ከዚያ በሚያስፈልገኝ ልክ እያወጣሁ መጠቀም ነው፡፡
ይህ ለብዙዎች ሥራ ፈትነት ሊመስል ይችላል። ወይም አጉል ወግ አጥባቂነትና ልዩ የሆነ ባህሪ ሊመስል ይችላል፡፡ እኔ ግን ኃላፊነቴን እየተወጣሁ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ያ ብር ከኪሴ ውሎ አያድርም፤ ቢያንስ ግን የተቀደደ ብር ተቀበሉኝ እያልኩ መጨቃጨቅ ያስቀርልኛል፤ የተበላሸ ነገር መስጠት ይከብደኛል፡፡ ብዙ ሰው ደግሞ አዲስ ብር ይወዳል፤ ችግሩ ግን በመውደዱ ልክ በአግባቡ አለመያዙ ነው።
የወረቀት ብር አያያዝ ይህን ያህል ጉዳይ ሆኖ ነው ወይ? ያሰኝ ይሆናል! አዎ! ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም ግለሰባዊም ሆነ ሀገራዊ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ወጪ ወጥቶበት የታተመ ብር ከጥቅም ውጪ ማድረግ ኪሳራ ነው፡፡ አንድ የብር ኖት (5፣10፣ 50፣ 100፣ 200) በጣም ከተቀዳደደ ከጥቅም ውጪ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ዋጋውን አጣ ማለት ነው፤ ታዲያ ይህ እንዴት ጉዳይ አይሆንም?
‹‹የተቀደደ ብር አልቀበልም›› እያሉ የሚጨቃጨቁት ሰዎች የወረቀት ብር በአግባቡ የማይዙ ሰዎች ናቸው! ስለዚህ ራሳችን የማንፈልገውን ነገር አናድርግ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2016 ዓ.ም