በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን በነበረ የጂኦግራፊ ፅንሰ ሀሳብ የአካባቢ ውሳኔ (Environmental determinism) የሚባል ነበር፡፡ አካባቢ (ተፈጥሮ) የሰውን ልጅ ሕይወት ሲቆጣጠር ማለት ነው፡፡ የዚህ ተቃራኒ ደግሞ አካባቢን መቆጣጠር (Environmental Possibilism) ይባል ነበር፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ሲቆጣጠር ማለት ነው፡፡
ዓለም እየዘመነ፣ ነገሮች እየተለወጡ፣ የሰው ልጅ ሥልጣኔ እያደገ ሲሄዱ ተፈጥሮ የሰውን ልጅ ከሚቆጣጠረው ይልቅ የሰው ልጅ ተፈጥሮን የሚቆጣጠረው በለጠ፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮን መቆጣጠር (Environmental Possibilism) ያደጉ እና የበለጸጉ አገራት የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ገና በማደግ ላይ ያሉ እና ያላደጉ አገራት ግን ዛሬም ተፈጥሮ ናት የምትቆጣጠራቸው፡፡ ተፈጥሮ በሰጠቻቸው ነገር ብቻ ነው የሚኖሩት፡፡
ወደ አገራችን ኢትዮጵያ እንምጣ፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታለደች አገር ናት፡፡ ተስማሚ አየር እና ለምለም ምድር ያላት ናት፡፡ ችግሩ ግን እኛ ሰዎቿ ለሥልጣኔ ቅርብ አይደለንም፡፡ ይህ ምቹ አየርና ተፈጥሮ ሲራቆት ምን እንደሚውጠን ያስፈራል፡፡ እየኖርን ያለነው ተፈጥሮ በሰጠችን ፀጋ ብቻ ነው፡፡ ተፈጥሮ የምታስከትላቸውን ጉዳቶች መቋቋምና መከላከል የሚያስችሉ ዘመኑ የፈጠራቸውን ነገሮች መጠቀም አልቻልንም፡፡ ይህ ማለት ተፈጥሮ እየተራቆተች በሄደች ቁጥር ድህነታችን እየባሰበት ይሄዳል ማለት ነው፡፡
ብዙ የዓለም አገራት የአየር ንብረታቸው እንደ ኢትዮጵያ ምቹ አይደለም፡፡ ዳሩ ግን ተፈጥሮን በቁጥጥራቸው ሥር ስላደረጉ በሰው ሰራሽ ኃይል ምቹ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ያለባቸው አገራት የአየር ማሞቂያ አላቸው፡፡ ከፍተኛ ሙቀት ያለባቸው አገራት የአየር ማቀዝቀዣ
አላቸው፡፡ ማሞቂያውም ሆነ ማዝቀዣው በክፍል ውስጥ ብቻ አይደለም፤ እንደ ስቴዲየም ያሉ ሰፋፊ ቦታዎችን
ጨምሮ በሁሉም የአገልግሎት ቦታዎች ነው፡፡
በኢኮኖሚ ደረጃ እንደ አገር ከፍተኛ ዕድገት የሚያስመዘግቡ አገራት ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ካላቸው የአፍሪካ አገራት በዕድገት በልጠዋል፡፡ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው የአፍሪካ አገራት በተፈጥሮ ውሳኔ ላይ ብቻ የሚኖሩ ስለሆነ ድሃ ናቸው፡፡ ተፈጥሮን መቆጣጠር የቻሉት ግን ምድረ በዳ ሆነው ሳለ ምቹ ኑሮ ያለው ግን ከእነርሱ ጋር ነው፡፡
በነገራችን ላይ የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ተፈጥሮን መቆጣጠር አሉታዊ ጎኖችም አሉት፡፡ ከተፈጥሮ መገኘት ያላበትን ይዘት ያሳጣል፡፡ ራሱ ተፈጥሮን እያመነመነ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ፤ የፋብሪካ ምግብ እና በልማዳዊ መንገድ ከሚዘጋጀው የእህል ወይም አትክልትና ፍራፍሬ ምግብ የሚገኘው ይዘት እኩል አይሆንም፡፡ ሳር እና ለምለም ዛፎች ያሉበት ቦታ ላይ የሚገኘውን ቅዝቃዜ በማሽን ማቀዝቀዛ ማግኘት አይቻልም፡፡ በቬንትሌተር ከመቀዝቀዝ በዋርካ ጥላ ሥር መቀዝቀዝ ይሻላል፡፡ በዘመናዊ ማሽን ቤትን ማሞቅ ፀሐይ እንደመሞቅ ሊሆን አይችልም፡፡
ይህንንም ለማግኘት ግን ተፈጥሮን መንከባከብ ያስፈልጋል፡፡ ተፈጥሮን መንከባከብ ደግሞ ተፈጥሮን መጠቀም ማለት ነው፡፡ ተፈጥሮ በራሱ ጊዜ ይወድቃል፤ ያንን መንከባከብ የሰው ልጅ ድርሻ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ፤ ተክሎችን ውሃ ማጠጣትና መንከባከብ ጥቅሙ ለተክሎች ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ጭምር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ተክሎች ሕይወት ቢኖራቸውም ነፍስ ስለሌላቸው መጎዳታቸውና መጎሳቆላቸው አይሰማቸውም፤ ስለዚህ ጠቀሜታው የበለጠ ለሰው ልጅ ይሆናል ማለት ነው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ግን ምቹ አየር፣ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ይዘው ተፈጥሮ በምትወስንላቸው ብቻ ይኖራሉ፡፡ ያ ደግሞ የሕዝብ ብዛት እየጨመረ በሄደ ቁጥር እየተመናመነ ይሄዳል፡፡ የሰው ልጅ ጥበበኛ ነው፤ አሳቢ ነው፡፡ ስለዚህ ወደፊት ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ አለበት፣ አስቦም መሥራት አለበት፡፡ ስለዚህ እንዴት ይህን ማሰብ አልቻልንም?
በየቦታው የምናየው ነገር አደገኛ አየር ሊፈጥር የሚችል ቆሻሻ መጣል ነው፡፡ የተፈጥሮ ተረፈ ምርቶችን በየመንገዱ በመጣል ለበሽታ የሚያጋልጡ ነገሮችን ማስፋፋት ነው፡፡ በተፈጥሮ የበቀሉትን መንከባከብ ሲገባን ጭራሽ የሚጎዳ ነገር እናደርግባቸዋለን፡፡ ታዲያ የሰው ልጅ ጥበበኛ እና አሳቢነታችን የቱ ነው?
የሰው ልጅ ከእንስሳት የሚለየው አሳቢ በመሆኑ ነው፤ ስለዚህ ነገውን ማሰብ አለበት፡፡ ነገን ለማሰብ ደግሞ ተፈጥሮን በምትመቸው ልክ መቆጣጠር
አለበት፡፡ ለምሳሌ፤ ያደጉት አገራት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የላቸውም፡፡ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ያላደጉት አገራት ናቸው፡፡ ለነገ እያሰቡ አይደለም ማለት
ነው፡፡ ከዘመን ወደ ዘመን የሚያሸጋግሩት ድሃ ሕዝብ ነው፡፡ የአውሮፓ አገራት ግን ወጥነት ያለውና ያልተቆሳቆለ ሕዝብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላልፋሉ፡፡ የሥልጣኔ ደረጃቸው ሲጨምር የሕዝብ ቁጥራቸውን ግን ይመጥናሉ፡፡ ይህ የሚሆነው በትዕዛዝ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ በሚሰማው ግላዊም ሆነ አገራዊ ኃላፊነት ነው፡፡ ያላደጉት አገራት ግን የሕዝብ ቁጥራቸው በከፍተኛ ፍጥነት ይጨምራል፣ ተፈጥሮን አይንከባከቡም፣ ይባስ ብሎ በተፈጥሮ ቁጥጥር ሥር ከመሆናቸውም ባሻገር ተጨማሪ ጥፋቶችን ያጠፋሉ፡፡
ብዙዎቻችን ዝግመተ ለውጥ ሲባል አካላዊ ብቻ ይመስለናል፡፡ የሰው ልጅ በዋሻ ውስጥ ይኖር በነበረበት ዘመን ያለው አካላዊ ቅርጽ እና ዛሬ ላይ ያለው አካላዊ ቅርጽ ሌላ ፍጥረት እስከሚመስል ድረስ በብዙ ይራራቃል፡፡ ይህ ዝግመተ ለውጥ ነው፡፡ ዝግመተ ለውጥ ግን በአካላዊ ቅርጽ ብቻ ሳይሆን በስነ ልቦና (አስተሳሰብ) ጭምር
ነው፡፡ የሰው ልጅ በዋሻ ውስጥ ይኖር በነበረበት ዘመን ያለው አስተሳሰብና የዛሬው በእጅጉ
ይለያያል፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ስላመጣ ነው ዛሬ ላይ ያለውን የረቀቀ ቴክኖሎጂ መፍጠር የቻለው፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ስላመጣ ነው ተፈጥሮን በከፍተኛ ደረጃ መጠቀም የቻለው፡፡
በዚህ ተፈጥሯዊ ሂደት መሰረት ከዛሬ 100 እና 1000 ዓመታት በኋላ የሰው ልጅ በቁጥርም በአኗኗር ሁኔታም ሌላ መልክ ይይዛል፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮን ማስቀጠል እና ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያመች ማድረግ አለብን፡፡ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠበቅ፣ የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ∙ ∙ ∙ የዚህ ትውልድ ኃላፊነቶች ናቸውና ተፈጥሮን እንታደግ!!!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም