የአርበኞች ማኅበር አመሠራረት

ይህ ማኅበር የጀግኖችን ሁሉ ታሪክ የሚዘክር ማኅበር ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ላይ በሕይወት ያሉ የማኅበሩ አባላት አባት አርበኞች በሕይወት በመኖር የሚያውቁትና በቃል የሚናገሩት ራሱ ብዙ ታሪክ ይናገራል፡፡ ማኅበሩ በተለያዩ የድል በዓላት ላይ በመገኘት የጀግኖችን ታሪክ ያስታውሳል፤ የኢትዮጵያ ጀግኖች ሀገራቸውን በምን አይነት መንገድ ከወራሪ ተከላክለው የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ተምሳሌት እንድትሆን እንዳደረጓት ለአሁኑ ትውልድ መልዕክት ያስተላልፋል።

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 85 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አመሠራረትና ያሳለፋቸውን ውጣ ውረዶች እናስታውሳለን፡፡ ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት የታሪክ ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውስ፡፡

ከ104 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 2 ቀን 1912 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 1920) ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በመላው ዓለም ሰላምን የማስፈን ዓላማ ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ‹‹የዓለም መንግሥታት ማኅበር›› (በእንግሊዘኛ አጠራሩ League of Nations) ተመሠረተ፡፡

ተቋሙ የተመሠረተው በፓሪስ የሠላም ጉባዔ ሲሆን በሚያዝያ 1938 ዓ.ም ፈርሶ ሥልጣንና ተግባራቱ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (United Nations) እንዲተላለፉ ተደርጓል፡፡

በሌላ በኩል ጥር 2 ቀን 1912 ዓ.ም የተመሠረተውን የዓለም መንግሥታት ማኅበርን (League of Na­tions) የተካው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ (United Nations General As­sembly)፤ የመጀመሪያ ስብሰባውን ያካሄደው ከ78 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 2 ቀን 1938 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ 1946) ነበር፡፡ የጠቅላላ ጉባዔው የመጀመሪያ ስብሰባ የተካሄደው በለንደን ከተማ ሲሆን የ51 ሀገራት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

ከ123 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 3 ቀን 1893 ዓ.ም የጎጃም ንጉሥ የነበሩት፣ ንጉሥ ተክለኃይማኖት ተሰማ አረፉ፡፡

ከ79 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 5 ቀን 1937 ዓ.ም ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ (አባ ኮስትር) እና ወንድማቸው እጅጉ ዘለቀ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ተሰቀሉ፡፡

በዕለቱ በዝርዝር ወደምናየው ታሪክ ስንሄድ ከ85 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም የተመሠረተውን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አመሠራረት እንቃኛለን፡፡

ያሳለፍነው ሳምንት ከላይ የገለጽናቸውን የታሪክ ክስተቶች በተለያዩ ዘመናት አስተናግዶ ነበር። የአንዳንዶቹ ብዙ የተባለለት ሲሆን የአንዳንዶቹ ደግሞ ምናልባትም ልብ የማይባል ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህን ሁሉ የሚዘክረውና የሚያስታውሰው ግን ይህ ማኅበር ነው፡፡ ስለዚህ የጀግኖችን ታሪክ የሚዘክረውን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ምሥረታ እና ታሪካዊ ክ ስተቶቹን እና ስታውስ፡፡

ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ‹‹የታሪክ ማስታወሻ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፣ ይህ ማኅበር በአርበኝነት ዘመን በሸዋ ክፍለ ሀገር በ1931 ዓ.ም «የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማኅበር» በሚል ስም ተሠይሞ የተቋቋመ ማኅበር እንደነበርና ዓላማውም የአርበኞችን ክብር በማበረታታትና በየሀገሩ ካሉ አርበኞች ጋር በመላላክ የሚገኘውን ሥራ ፍሬ እርስ በእርስም ሆነ በስደት ላይ ከነበሩት ንጉሠ ነገሥት ጋርም መካፈል እንደነበር ገልፀዋል።

ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም ባላምባራስ አበበ አረጋይ (በኋላ ራስ)፣ ሻለቃ መስፍን ስለሺ (በኋላ ራስ)፣ ልጅ ግዛቸው ኃይሌ፣ ወንድማማቾቹ ደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቁሥላሴ እና ደጃዝማች ተስፋዬ ዕንቁሥላሴ፣ አቶ እምአእላፍ ኅሩይ፣ ደጃዝማች ሀብተሥላሴ በላይነህ፣ ደጃዝማች ታከለ ወልደሐዋርያት … በአጠቃላይ 29 ስመ ጥር አርበኞች በተገኙበት በሞጃና ወደራ (ተጉለት)፣ በልዩ ስሙ አንቀላፊኝ ሜዳ፣ ‹‹አንዲት ግራር›› በሚባለው ቦታ ለሀገር ፍቅር ሲባል ማኅበሩ ተመሠረተ፡፡

የፋሺስት ጦር ተሸንፎ የኢትዮጵያ ነፃነት ከተመለሰ ከ21 ዓመታት በኋላ፣ በሚያዝያ ወር 1954 ዓ.ም ሌተናል ጀኔራል ነጋ ኃይለሥላሴ ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከሌሎች ሰዎች አገር አፍቃሪዎች ጋር በመሆን ‹‹ጥንታዊት ኢትዮጵያ ሀገራዊ የጀግኖች ማኅበር››ን በታደሰ ሀገራዊ ዓላማና በተሻሻለ ደንብ አቋቋሙት። ይሁን እንጂ ማኅበሩ ከመንግሥት እውቅና ያገኘው ሰኔ 19 ቀን 1956 ዓ.ም ነበር፡፡

ሌተናል ጀኔራል ነጋና ባልደረቦቻቸውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ አባላትን መመዝገብ ችለዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብዙ መሰናክሎችን እያለፈ ዛሬ ላይ የደረሰው ይህ ማኅበር፣ በአሁኑ ወቅት የራስ መስፍን ስለሺ ልጅ በሆኑት በልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ስለሺ እየተመራ ይገኛል፡፡

በ2006 ዓ.ም የታተመውና ‹‹እኔ ለአገሬ›› የተሰኘው የማኅበሩ መጽሔት ስለአመሠራረቱ በሰፊው ያስረዳል። ከመጽሔቱ በተገኘው መረጃ፤ የማኅበሩ የመጠሪያ ሥያሜ “የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር” ይባላል፡፡ ማኅበሩ በዚያን ጊዜ በነበሩት ጎበዛዝትና የጎበዝ አለቆች የማስተባበሪያና የመምሪያ አካል ነው፡፡

የጀግኖች አርበኞች መሰባሰቢያና መመሪያ ጥላ የሆነው ይህ ማኅበር በሰሜን ሸዋ ተጉለት አውራጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመሥረት እንጂ ቀስ በቀስ በመስፋፋትና በመጠናከር፤ በእንግሊዝ መንግሥት በመታገዝ በ1933 ዓ.ም የወራሪውን የፋሽስት እብሪተኛ ኃይል በድል አድራጊነት ሚያዚያ 27 ቀን በታላቅ ገድል ድል ተጎናጽፏል፤ መላ አገሪቷ ነፃ ወጥታለች፤ ከዚህ ጣፋጭና አስደናቂ ድል በኋላም ማኅበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያውቅና እንዲስማማ አድርጎ መተዳደሪያ ደንቡ ተሻሽሎ ተጠናክሮ ተቋቋመ። ይህ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር መጀመሪያ አንቀላፊኝ ላይ ሲመሠረት ዓላማው የአርበኝነቱን ትግል ለማስተባበር ነበር፡፡

ማኅበሩ ከድል በኋላ እንደገና ሲጠናከርና ሲቋቋም ደግሞ ዓላማ ያደረገው የአርበኝነት ትግሉንና የታጋዮቹን ታሪክ ለመዘከርና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ፣ እንዲሁም በሕይወት ያሉት ጀግኖች አርበኞች የሚደገፉበትን መንገድ ለመፍጠርና ሀገር ተረካቢው ትውልድ መብቱንና ግዴታውን የሚያውቅበትና የሚረዳበትን ማዕከል የሚያገለግልበትን መንገድ በማሰበም ጭምር ነው፡፡

የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ከተቋቋመ በኋላ አሁን ባለበት አራት ኪሎ የራሱን ሕንፃ በማሠራት በየጊዜው ከአርበኞቹ መካከል መሪዎቹን እየመረጠ በዚያው መንገድ ቀጥሏል። ማኅበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ ይዞ እንዲቀጥልም ይሁን የመታሰቢያ ሕልውናውን በሕያውነት ለማቆየት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የቅርብ ድጋፍና ክትትል እንዳልተለየው የመጽሔቱ መረጃ ያሳያል፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አንቀላፊኝ ላይ ሲመሠረት በሰብሳቢነትና በአባልነት የነበሩት አባት አርበኞች ቃል ኪዳን ተገባብተው ነበር። ከቃል ኪዳናቸው ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ፡፡

‹‹እኛ ከዚህ በታች የመተማመኛ ቃል ፊርማችንን ያደረግን በጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች አርበኞች ማኅበር ስንገባ በጥቅምት 23 ቀን 1931 ዓ.ም የወጣውን ደንብ ወደናል፡፡ ግዴታውን ሁሉ እንፈጽማለን። ምንም ቢቸግረን በዚሁ ደንብ በአራተኛው ቁጥር እንደተፃፈው የመንፈስ ቅዱስ ወንድሞቻችንንና ጓደኞቻችንን አንከዳም፡፡ ሁለተኛ በሦስተኛው እንደተባለው የሀገራችንን ነፃነት በማናቸውም ምክንያት ቢሆን ክብሯ የሚጎድልበትን፣ ጓደኞቻችን የሚጎዱበትን አንሠራም፡፡ እራሳችንም ምንም ቢቸግረን ለጠላት አንገባም፡፡

…. በሃያ አንደኛው ተራ ቁጥር እንደተፃፈው የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት መቃወም የለብንም። ይህንን ሁሉ ባንፈጽም የእግዚአብሔር መቅሠፍት ያጥፋን፡፡ ለዚሁም ፈፃሚ መሆናችንን ለማሳወቅ ዋስ ጠርተናል። ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም አንቀላፊኝ መንዝ››

ፊርማ መሥራች አባላት (ሹማምንት) የነበሩትም የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. ክቡር ራስ አበበ አረጋይ፤ የክብር ሊቀመንበር

2. ባሻ ወልደኪሮስ ገብረመስቀል፤ የሥራ ሊቀመንበር

3. አቶ ፈለቀ ዳኜ፤ ዋና ፀሐፊ

4. አቶ ደምሴ ወልደአማኑዔል፤ አባል

5. አቶ ደሣለኝ ተክለወልድ፤ አባል

6. አቶ ልሳኑ ሀብተወልድ፤ አባል

7. ልጅ ፀሐይ እንቆሥላሴ፤ አባል

8. ልጅ ተስፋዬ እንቆሥላሴ፤ አባል

9. ልጅ ወልደዮሐንስ እምሩ፤ አባል

10. ልጅ ጽጌ ወልደማርያም፤ አባል

ማኅበሩ ተመሥርቶ፣ ኢትዮጵያም ድል አድርጋ ወራሪው የጣሊያን ፋሽስት ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ ወጣ፡፡ ከድል በኋላ ማኅበሩ መንግሥታዊ ድጋፍ እየተደረገለት፣ የጀግኖችን ታሪክ እየዘከረ እነሆ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፡፡

ከድል በኋላ ሀገሩን ላገለገለው አርበኛ ስደተኛና የውስጥ እርበኛ የመታሰቢያ ሜዳለያ ተሰጠ። ከዚህ ውጭ መንግሥት ለአርበኛው የሚሰጠው የጡረታ ክፍያ ስለሌለ ለጠየቀው አርበኛ መንግሥት ከሚያዝበት መሬት ለአርበኛው ርስት መሬት እንዲሰጠው ተደረገ፡፡

ለአርበኛው መጦሪያው ይሄው መሬቱ ሆነ። አርበኛው መንግሥት የሰጠውን መሬት አልምቶ፣ ቤት ሠርቶ ለመንግሥት የሚገባውን ግብር እየከፈለ በሰላም መኖር ጀመረ፡፡

በንጉሣዊ ሥርዓቱ በዚህ ሁኔታ የቆየው አርበኛ እና ማኅበሩ በ1967 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ሲከሰት ግን ችግር ገጠመው፡፡ ንጉሣዊ ሥርዓቱን የገረሰሰው አብዮታዊው ደርግ መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው የሚል አዋጅ አወጣ፡፡ በዚህ የደርግ አዋጅ ምክንያት በቢሮ የተያዘውን ቤት ብቻ በማስቀረት አርበኛው ሁሉ መሬቱንና ንብረቱን ተነጠቀ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ መነጠቅ ብቻ ሳይሆን ለሕይወታቸው የሚያሰጋቸው ሁኔታ ሁሉ ተፈጠረ፡፡ እንዲያም እንዲህም እያሉ ለቢሮ ብቻ በቀረችላቸው ቤት ማኅበሩን አቆዩት፡፡

ዳግም የመንግሥት ለውጥ ተፈጠረ፡፡ ወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ተገርስሶ ኢሕአዴግ ሀገሪቱን ማስተዳደር ጀመረ፡፡ የማኅበሩ ሰዎች ከደርግ አንፃር ኢሕአዴግን ያመሰግኑታል፡፡ ምክንያቱም በ2001 ዓ.ም አዲስ ሕንጻ ለማሠራት የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ወስኖ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ ሆኖም ግን ሕንጻው በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት እንደቆየ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በመጨረሻም ተሳክቶ አሁን ያለውን የአርበኞች ሕንጻ በተስፋፋ መልኩ ለመገንባት ተችሏል፡፡ ማኅበሩም እነሆ የጀግኖች አርበኞችን ታሪክ የሚዘክር ሆኗል፡፡

ዋለልኝ አየለ

 አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You