የጨው አምራችና አቀነባባሪ ፋብሪካዎች ፈተና- የዋጋ ተመን ዝቅተኛነት

መንግሥት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ችግሮች ለማቃለል የተለያዩ ተግባሮች እያከናወነ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ይጠቀሳል። በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው ከነበሩ ኢንዱስትሪዎች መካከል በርካታ የሚባሉት በንቅናቄው ወደ ሥራ ተመልሰዋል። ንቅናቄው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ተስፋ ሰጪ የሆኑ ውጤቶች እንደተመዘገቡበት በተለያዩ መድረኮች ተጠቁሟል።

በሀገሪቱ አምራቾችና ተጠቃሚዎች የሚያስተሳስሩ፣ ግብዓት አቅራቢዎችንና አምራቾችን የሚያቀራርቡ ባዛርና ኢግዚቢሽኖችም በተለያዩ አካላት እየተካሄዱ ይገኛሉ። ጎን ለጎን የሚካሄዱ ውይይቶችም የዘርፉን መልካም አጋጣሚዎች ለመጋራት ችግሮችን ለማዳመጥና መፍትሄ ለማመላከት እያገለገሉ ናቸው።

እንደ ሀገር ተጠናክሮ በቀጠለው በዚህ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢንዱስትሪዎችና ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ ስለመግባታቸው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መረጃ ያመላክታል። ከሰሞኑም የዚህ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አንድ አካል የሆነው ባዛርና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል።

‹‹ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት›› በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አዘጋጅነት የተካሄደው ይህ ባዛርና ኤግዚቢሽን የሀገር ውስጥ ምርቶችን በማስተዋወቅና የገበያ ትስስር በመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ተሳታፊዎች አረጋግጠዋል። በተለይም ተኪ ምርቶችን በማበረታታት ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት እያበረከተ ያለው ድርሻ ጉልህ መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መረጃ እንዳመላከተው፤ ለአምስት ቀናት በተካሄደው በእዚህ ኤግዜቢሽንና ባዛር 85 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎችና ኢንተርፕራይዞች ተሳትፈዋል። ከእነዚህም መካከል የአልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ የውጤቶች፣ የእጅ ሥራዎች፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶች እንዲሁም ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን ይዘው የቀረቡት ይጠቀሳሉ።

የምግብ ጨው አምራችና አቀነባባሪዎችም በኢግዚቢሽንና ባዛሩ ተገኝተዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሰዎች በአዮዲንና ተያያዥ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች ይጋለጣሉ። በአዮዲን እጥረት ከሚከሰቱ የጤና እክሎች መካከል የአዕምሮ ውስንነት፣ ጎይተር (እንቅርት)ና የመቀንጨር ይጠቀሳሉ። እነዚህን የጤና እክሎች ለመከላከልም የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ይስተዋላል። መንግሥት በአዮዲን የበለጸገ ጨው ለማህበረሰቡ በስፋት ለማቅረብና ተደራሽነቱን ለማሳደግ ጥረቶችን ያደርጋል።

ኢትዮጵያ በአዮዲንና ተያያዥ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም በየዓመቱ ከ55 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መረጃዎች ይጠቁማሉ። መንግሥት በሀገሪቱ የሚገኘውም የጨው ሀብት በአዮዲን በማበልፀግ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ለማቅረብ፣ የጨው ምርት ዓለም አቀፍ ደረጃውንና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲመረት ለማድረግ የሚካሄዱ ተግባሮችን ይደግፋል።

ይህ ሁሉ ተሠርቶም የገበያ ሁኔታውን ጨምሮ በጨው ማምረትና ግብይት ወቅት የተለያዩ ችግሮች እንደሚከሰቱ ይጠቆማል። ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት›› በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው በዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ የተሳተፉ ጨው አምራችና አቀነባባሪዎችም ይህንኑ አረጋግጠውልናል። በተለይ መንግሥት ለፋብሪካዎች ያስቀመጠው የጨው መሸጫ ዋጋ በሥራቸው ላይ እንቅፋት እየፈጠረባቸው መሆኑን ነው እነዚህ አካላት ያመለከቱት።

በባዛርና ኤግዚቢሽኑ ከተሳተፉት የምግብ ጨው አምራችና አቀነባባሪዎች መካከል አሽ አሌ ጨው ማምረቻና ማቀነባበሪያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር /ፋብሪካ/ አንዱ ነው። ፋብሪካው በአፋር ክልል በርሃሌ ወረዳ ዞን ሁለት አካባቢ ነው የሚገኘው። ፋብሪካው የተለያዩ ችግሮችን በመቋቋም ጥሬ ጨው ከአምራቾች እየተረከበ ሙሉ ለሙሉ አዮዳይዝድ በማድረግ ለገበያ ያቀርባል።

የፋብሪካው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላዬ ይትባረክ እንዳሉት፤ ተፈላጊ ግብዓቶችን አሟልቶ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ የምግብ ጨው እያመረተ ለገበያ የሚያቀርበው አሽ አሌ የምግብ ጨው ፋብሪካ በ33 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ያረፈ ነው። ፋብሪካው በተወሰኑ ባለድርሻ አካላት በ400 ሚሊዮን ብር የተከፈለ መነሻ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ በሰዓት 40 ቶን የምግብ ጨው የማምረት አቅምም አለው።

‹‹በኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት›› በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው ባዛርና ኤግዚቢሽን በመሳተፍ ምርትና አገልግሎታቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ በዘርፉ እያጋጠመው ያለውን ችግርም ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ መቻሉን አቶ ጥላዬ ይገልጻሉ። ባዛርና ኤግዚቢሽኑ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ ከግብዓት አቅራቢዎች ጋር ለመገናኘትና ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ማበርከቱንም ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም የምግብ ጨው ያመርት የነበረው በባህላዊ መንገድ በመንፊያ በመጠቀም በሰው ጉልበት መሆኑን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ከፍተኛ ወጪ በማድረግ ዘመናዊ በሆኑ ማሽነሪዎች በመጠቀም እያመረተ ይገኛል ብለዋል። ፋብሪካው የሚያመርተው የምግብ ጨው ሙሉ ለሙሉ አዮዳይዝድ የሆነና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የምግብ ጨው ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ የጠቀሱት አቶ ጥላዬ፤ የገበያ ችግር እንደሌለም አስታውቀዋል። ፋብሪካው ችግር የሆነበት በሚያመርተው የምግብ ጨው ላይ በመንግሥት የተጣለው የመሸጫ ዋጋ ተመን ዝቅተኛነት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፋብሪካው ጥሬ ጨው ከአምራቾች ተረክቦ አቀነባብሮና አስፈላጊውን ሂደት አልፎ ለምግብነት እንዲውል ለማድረግ ከፍተኛ ወጪ እንደሚያደርግ አቶ ጥላዬ ተናግረዋል። ይህ ወጪ መንግሥት ከጣለው የመሸጫ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በሥራው ላይ እንቅፋት ፈጥሮበታል ብለዋል። መንግሥት አንድ ኩንታል ጨው ከፋብሪካ እንዲወጣ በተመነው ዋጋ መሠረት ጨው እያመረተ ለገበያ የሚያቀርበው አሽ አሌ፣ ጨው ማምረቻና ማቀነባባሪያ ፋብሪካ ምርቱን በኪሳራ እየሸጠ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

በአካባቢው በተካሄደው ጦርነት የተነሳ ፋብሪካው ለዘረፋና ውድመት መዳረጉንም አስታውሰው፣ ፋብሪካው ግን እነዚህን ችግሮች ሁሉ ተቋቁሞ በአሁኑ ወቅት በሁለት እግሩ በመቆም በሙሉ አቅሙ እያመረተ መሆኑን አስታውቀዋል። በጦርነት ወቅት ለደረሰበት መጠነኛ ጉዳትና ዘረፋም የክልሉን መንግሥት ጨምሮ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

አቶ ጥላዬ እንዳመለከቱት፤ ፋብሪካው ከመንግሥት ያገኛቸውን የተለያዩ ድጋፎች ምርኩዝ አድርጎ ያለምንም የባንክ ብድር ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን መንግሥት በጣለው የጨው መሸጫ ዋጋ ተጎጂ እየሆነ ነው። ፋብሪካው በምግብ ጨው ውስጥ አስፈላጊዎቹን ንጥረ ነገሮች ከማሟላት በተጨማሪ ለጨው ምርት ማሸጊያ የሚውሉ ማሸጊያዎችን ከፋብሪካዎች ገዝቶ ይጠቀማል፤ ይህም ሌላው ወጪው ነው። ለሰው ኃይል የሚደረገው ክፍያና የነዳጅ ዋጋም በየጊዜው እየጨመረ ነው።

ይህ የማምረቻ ወጪና መንግሥት ያወጣው የአንድ ኩንታል ጨው መሸጫ ዋጋ አይጣጣምም ሲሉ አመልክተው፣ ይህም በፋብሪካው ሥራ ላይ ችግር መፍጠሩን አስታውቀዋል። መንግሥት ችግሩን ተረድቶ በዋጋው ላይ በድጋሚ ክለሳ እንዲያደርግ አቶ ጥላዬ ጠይቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ እሳቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በጨው ዋጋ ላይ የሚጣለው ዋጋ እና ለማምረት የሚወጣው ወጪ ከፍተኛነት አሳሳቢ ስለመሆኑ ለመንግሥት እያስረዱ ናቸው፤ ችግሩ የትኛውንም ያህል ፋብሪካውን እየፈተነ ቢሆንም፣ ፋብሪካው ከማምረት ሥራው ግን አልተቆጠበም። ሥራውን እየሠራ ጥያቄውን ማቅረቡን ቀጥሏል።

መንግሥት አዮዳይዝድ የሆነ ጨው ለማህበረሰቡ ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት በብርቱ ከሚደግፉ ጨው አምራቾችና አቀነባባሪዎች ጋር በቅርበት መሥራት እንዳለበት ያመለከቱት አቶ ጥላዬ፤ ጨው አምራቾችና አቀነባባሪዎች ጨው ለማምረት የሚያወጡትን ወጪ አጥንቶና አስልቶ የዋጋ ተመኑን ሊያስተካክል እንደሚገባ አመልክተዋል፤ አዮዳይዝድ የሆነና ለጤና ተስማሚ የሆነ የምግብ ጨው አሁንም ድረስ ገበያው ላይ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ እንዳልሆነ ገልጸው፤ ለዘርፉ ትኩረት ቢሰጥ መልካም ነው ብለዋል።

ከአፍዴራ ሀይቅ የሚወጣውን ጨው ለአቀነባባሪዎች የሚያስረክበው አፍዴራ ጨው አምራቾች ኃላፊነቱ የተወሰነ ህብረት ሥራ ማህበር ሌላኛው የዘርፉ ተዋናይ ነው። ማህበሩ ሁለት ሺ 650 የሚደርሱ አባላት አሉት። ጥሬ ጨው በአግባቡ ከአምራቾች በመሰብሰብ ለፋብሪካዎች ያስረክባል።

የአፍዴራ ጨው አምራቾች ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ሥራ ማህበር የግብይት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ጽጌ በለጠ ፋብሪካዎች ከአምራቹ የተሰበሰበውን ጨው አስፈላጊውን እሴት ጨምረው ለምግብነትና ለኢንዱስትሪ እንደሚያቀርቡ ይገልጻሉ። ጥሬ ጨውን አጥበው አድርቀውና እሴት ጨምረው እንዲሁም ለምግብነት የሚውለውን ደግሞ አዮዳይዝድ በማድረግ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ጠቅሰው፣ ለፋብሪካ የሚውለውንም እንዲሁ እንደ ደንበኞቹ ፍላጎት የሚታጠብ ከሆነ አጥበው፤ የማይታጠብ ከሆነም ሳይታጠብ ያቀርባሉ ይላሉ። ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውለው ጨው ናፍታሊም የተባለ ጋዝ ተረጭቶ ለገበያ እንደሚቀርብ ጠቅሰው፣ ይህም አዮዳይዝድ ያልሆነ ጨው ለምግብነት እንዳይውል የመከላከያ አንዱ መንገድ ነው ብለዋል።

ሰዎች አዮዳይዝድ የሆነና አስፈላጊውን ንጥረ ነገር ያሟላ ጨው መመገብ እንዳለባቸው የጠቀሱት ወይዘሮ ጽጌ፤ አዮዳይዝድ ያልሆነ ጨው መመገብ የጤና ችግሮችን የሚያስከትልና በተመሳሳይ ደግሞ ከጨው የሚገኘውን ጥቅም የሚያሳጣ መሆኑን ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ጨው በሁለት መንገድ ተዘጋጅቶ ለገበያ ይቀርባል። አርሶ አደሩ የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ የሚያወጣውን የጥሬ ጨው ምርት ማህበሩ ሰብስቦ ለፋብሪካዎች ያቀርባል። በሄክታር በሄክታር ተከፋፍሎ የሚገኘውን የጨው ክምር ህብረት ሥራ ማህበራቱ በምድብ ቦታቸው ተገኝተው አርሶ አደሩ ቆፍሮና በብዙ ድካም ያወጣውን የጨው ክምር በማዳበሪያ እያዘጋጁ ወደ ፋብሪካዎች ያደርሳሉ። አንድ ማዳበሪያ ጨው ከ50 እስከ 52 ኪሎ ግራም የሚይዝ ቢሆንም፤ ለሽያጭ ወደ ፋብሪካዎቹ ሲቀርብ በኩንታል ነው። አንድ መኪና አራት መቶ ሃያ ኩንታል ይይዛል። ማህበሩ በዚህ መሰረት ያዘጋጀውን ጥሬ ጨው ለፋብሪካዎች ያቀርባል።

በአንድ ወር ውስጥ ለሀገሪቷ የሚያስፈልገው የጨው መጠን ምን ያህል እንደሆነ በመንግሥት እንደሚወሰን ወይዘሮ ጽጌ ጠቅሰው፤ ከምርት መጠኑ በተጨማሪም የመሸጫ ዋጋውም በመንግሥት እንደሚወሰን ተናግረዋል። በሀገሪቱ የሚገኙት ጨው አምራችና አቀነባባሪ ፋብሪካዎች ከህብረት ሥራ ማህበራቱ ጋር በሚገቡት ውል መሠረት ጥሬ ጨው ተረክበው እሴት በመጨመር ለገበያ ያቀርባሉ ብለዋል።

ጨው አቀነባባሪ ፋብሪካዎች ከመንግሥት በሚያገኙት ፈቃድ መሠረት ወደ ምርት ሲገቡ ከጨው አምራችና አቅራቢዎች ጋርም እንዲሁ ውል በማሰር ነው ያሉት ወይዘሮ ጽጌ፤ መንግሥት ያስቀመጠውን የወር ፍጆታ መጠን መሠረት በማድረግ ከጨው አምራችና አቅራቢዎች ጋር ውል እንደሚገባም አስታውቀዋል። በገቡት ውል መሠረትም በወር ውስጥ ምን ያህል የጨው ምርት ከአምራችና አቅራቢው እንደሚያገኙ እንደሚታወቅ ጠቅሰው፣ ማህበራቱ ከመንግሥት በሚያገኙት ፈቃድ መሠረት በጠቅላላው እስከ 650 ሺ ኩንታል ጨው ለፋብሪካዎች ይቀርባሉ ብለዋል።

ወይዘሮ ጽጌ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ በስፋት የሚሰራጨው የአፍዴራ ጨው ነው። ማህበራቱ መንግሥት ባስቀመጠላቸው ኮታ መሠረት ምርቱን በየወሩ ለፋብሪካዎች ያቀርባሉ። በወር ውስጥ ከሚያስፈልገው የጨው መጠን በላይ አይመረትም፤ አልፎ አልፎም በተለይ በክረምት ወቅት የጨው ምርት ተፈላጊነት የሚቀንስበት ወቅትም አለ።

እሳቸውም የጨው መሸጫ ዋጋው በመንግሥት እንደሚተመን ጠቅሰው፣ የዋጋ ተመኑ አምራቹን እየጎዳው መሆኑንም አስታውቀዋል። መንግሥት የዋጋ ተመኑን በተለያየ ጊዜ እንደሚያሻሽል ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩ በጨው ምርት ሂደት ውስጥ ከሚጠበቅበት ድካም አንጻር ዋጋው ግን ተመጣጣኝ አይደለም ብለዋል።

ለአብነትም በቅርቡ የጨው መሸጫ ዋጋ ከመሻሻሉ በፊት አንድ ኩንታል ጨው 283 ብር ከ57 ሳንቲም እንደነበር ጠቅሰው፣ ይህ ማለት አንድ ኪሎ ጨው በአማካኝ ሁለት ብር ከሰማንያ ሳንቲም አካባቢ ይሸጥ እንደነበር አስታውሰዋል፤ በቅርቡ መንግሥት ባደረገው ማሻሻያ መሠረት አንድ ኩንታል ጨው 557 ብር ከ88 ሳንቲም እንዲሸጥ መወሰኑን አስታውቀዋል። ይህም ቢሆን አርሶ አደሩ ጨው ለማምረት ከሚያወጣው ወጪና ድካም አንጻር አሁንም ተመጣጣኝ ዋጋ አለመሆኑን አስገንዝበዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You