“በበጋ መስኖ 117 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ይጠበቃል”-የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

ባለፉት አምስት ዓመታት በዋና ዋና የግብርና ዘርፎች ላይ የተሰሩ ሥራዎች ሰፋ ያሉ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና በዚሁ በግብርናው ዘርፍ በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ ስኬታማ የተሆነውን ያህል በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ደግሞ ፈተና እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ፈተና በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ተቀርፏል? የሚለውን ጨምሮ ባለፉት አምስት ወራት የግብርና ዘርፉ አፈጻጸሙ ምን ይመስላል? በሚለው ዙሪያ የዛሬው የዘመን እንግዳችን የሆኑት የኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የሰጡትን ሰፊ ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በግብርናው ዘርፍ ባለፉት አምስት ዓመታት በዋና ዋና የግብርና ዘርፎች ላይ የተሰሩት ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

ግርማ (ዶ/ር)፡- በአስር ዓመቱ መሪ እቅዳችን ላይ እየተሰራ ያለው የግብርና አማካይ ዓመታዊ ምርት በስድስት በመቶ እንዲያድግ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያሉትን አማካይ ውጤቶችን ስንስወስድ ስድስት በመቶ ያክሉን ዓመታዊ የምርት እድገት ግብርና አስመዝግቧል፡፡ ይህም በአፍሪካ የግብርና እድገት ፕሮግራም ከተቀመጠው ግብ ጋር ሲታይ ተመሳሳይ ነው ማለት ያስችላል፡፡ ግብርናው እንዲያድግ የሚጠበቀው በስድስት በመቶ ነው፡፡

ለዚህኛው ስኬት ባለፉት ዓመታትም ሆነ ባለፉት አምስት ወራት በዋና ዋና የግብርና ዘርፎች የተሰሩ ስራዎች ሲታዩ ባለፈው አምስት ወራት እንደሚታወቀው ትልቁ ሥራ የመኸር ወቅት ስራችን ነው፡፡ መኸር ላይ በባለፈው በጀት ዓመት በተለይ በአራተኛው ሩብ ዓመት ማሳ የማዘጋጀትና የመዝራት ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም ምርቱ እንክብካቤ ተደርጎለት ወደመሰብሰቡ የሚመጣው በዚህኛው ዓመት ከመሆኑ አንጻር መኸር ላይ 17 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በተለይ በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳ ላይ የተዘራ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሔክታር በኩታ ገጠም እርሻ የተዘራ ነው፡፡

በመኸር የኩታ ገጠም እርሻን የምንሰራው ወደ 50 በመቶ የሚሆነው በአነስተኛ ማሳ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ግብርናችን በኩታ ገጠም እየተሰራ መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን፣ በጣም ትልቅ እድገት ነው፡፡ የኩታ ገጠም እርሻን ስንወስድ አርሶ አደሩ አንድ ላይ ተደራጅቶ ቴክኖሎጂውን ከመጠቀም አንጻርና እርስ በእርስ ከመማማር አንጻር ጥቅም ያለው ነው፡፡ እርሻውን ሜካናይዜሽን ከማድረግና አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር በጣም ትልቅ ለውጥ የመጣበት ነው ብለን መውሰድ እንችላለን።

ወደ አራት ሚሊዮን ሔክታር የሚደርስ መሬት በሜካናይዜሽን የታረሰ ነው፡፡ ይህን ከባለፈው ዓመት ጋር ስናነጻጽረው ወደ አንድ ሚሊዮን ሔክታር ብልጫ ያለው ነው።

የተዘራውን ዘር የመንከባከብ፣ ጸረ ተባይ ኬሚካሎች የመርጨት ሥራዎች በስፋት ሲሰራባቸው ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ባለፈው ዓመት የአንበጣና የተምች ክስተቶች ነበሩ፡፡ ምርቱ ሲደርስ ደግሞ የግሪሳ ወፍ ችግር ነበር፡፡ እነዚህን ችግሮች በጣም በተቀናጀ ሁኔታ ሰፊ ጉዳት ሳያደርሱ የመከላከል ሥራ ተሰርቷል፡፡

ከ17 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ የተዘራውን ምርት የመሰብሰብ ሒደት ላይ እንገኛለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ተሰብስቦ የተጠቃለለም ባይሆን እስካሁን ወደ 11 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሔክታር አካባቢ ምርት የመሰብሰብ ሒደት ተካሂዷል፡፡

ምርት የደረሰባቸው ቦታዎች ብለን ግምት የወሰድነው 12 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሔክታር አካባቢ ላይ ነው። ስለዚህ አሁን ያለው 11 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በጣም በበቂ ሁኔታ የደረሱ ምርቶች የተሰበሰቡበትን ሁኔታ እንዳለ የሚያሳይ ነው። በተለይ ባለፉት ወራት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከመኖሩ አንጻር የአርሶ አደሩን ምርት የማሰባሰብ ሌሎቹም የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማነቃነቅ ምርት እንዲሰበሰብ ጥረት ሲደረግ ነበር።

ምርት ሲሰበሰብ በሁለት አኳኋን ነው፡፡ አንዱ በባህላዊ መንገድ ሲሆን፣ ሁለተኛው መካናይዝድ በሆነ መንገድ ነው። በተለይ በባህላዊ መንገድ የሚሰበሰበው አርሶ አደሩ ሰብስቦ፣ ወቅቶና አስግብቶ እስኪረጋጋ ድረስ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ነገር ግን በሜካናይዜሽን የሚሰበሰበው ጊዜ ቆጣቢ ሲሆን፣ እስካሁን የተወቃውም ወደ 140 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ነው፡፡ ይህ ማለት አብዛኛው ምርት የሚሰበሰበው በባህላዊ በመሆኑ የታጨደው ሁሉ ወደምርት ተቀይሯል ማለት አይደለም። በአጠቃላይ ከመኸር ምርት የምንጠብቀው ወደ 513 ሚሊዮን ኩንታል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ባለፈው በአምስት ወራት ውስጥ በስፋት ከተጀመረው ሥራ አንዱ የበጋ መስኖ ነውና በዚህስ ዙሪያ ምን እየተሰራ ነው?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ሁለተኛው የማነሳው ነጥብ የበጋ መስኖ ነው፡፡ ባለፈው በአምስት ወራት ውስጥ በስፋት ከጀመርናቸው ስራዎች አንዱ የበጋ መስኖ ሥራ ነው፡፡ ይህ በሁለት የሚከፈል ሥራ ነው፡፡ አንዱ የበጋ የመስኖ ስንዴ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የአትክልትና ፍራፍሬ ሥራ ነው፡፡

የበጋ መስኖን በተመለከተ ባለፈው ዓመት አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሔክታር በበጋ መስኖ ስንዴ ተሸፍኗል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ሶስት ሚሊዮን ሔክታር ስንዴ ለመሸፈን አቅደናል፡፡ ከዚህ የምንጠብቀው ወደ 117 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ነው፡፡

አሁን እስከዚህ ሳምንት ድረስ ያለን አጠቃላይ እድገት ሲታይ ወደ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ታርሶ ዝግጁ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ወደ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሔክታር በዘር ተሸፍኗል፡፡

ይህ አምና የበጋ መስኖን ከሰራንበት ፍጥነት አንጻር ሲታይ በጣም የፈጠነ ነው፡፡ እንደሚታወቀው መሬቱ ወደመስኖ የሚሸጋገረው የቀደመው ምርት ታጭዶ ሲሰበሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንጻር ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር አርሰን ከማዘጋጀት አንጻር የተኬደው ርቀት ሶስት ሚሊዮን ሔክታር ለመሸፈን ብዙ የሚቸግረን እንዳልሆነ ነው፡፡

ብዙ ጊዜ የስንዴ ጉዳይ ሲነሳ አብሮ የሚነሳው ነገር ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ስራዎች በመዘንጋት የሚሰራ ይሆን የሚል ስጋት ነው፡፡ ባለፈው አምስት ወራት 652 ሺ ሔክታር ለመሸፈን አቅደን ወደ 460 መሸፈን ችለናል። ይህም ማለት የእቅዱን 80 በመቶ አካባቢ እንደማለት ነው፡፡ ይህ ማለት አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ስራስር ሌላውን ጨምሮ የሚሰራ ነው፡፡ ስለዚህ የስንዴው ሥራ በመስኖ እንደሚሰራ ሁሉ በበጋ ወቅት የአትክልትና ፍራፍሬ ስራዎችንም በዚሁ ልክ እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዚሁ በግብርናው ውስጥ ከሚካተተው ዘርፍ አንደኛ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ነውና ከዚህ አንጻር እየተከናወነ ያለ ተግባር ምንድን ነው?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ከሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርታችን ባለፈ ሁለተኛው ትልቁ የግብርናው ዘርፍ የእንስሳትና የዓሳ ሀብት ዘርፋችን ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባለፈው ዓመት ያስጀመሩት የሌማት ትሩፋት ሥራ ይገኛል፡፡ የሌማት ትሩፋቱ ሥራ በተለይ ወተት፣ ማር፣ ዶሮና የእንቁላል ምርቶችን በስፋትና በብዛት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የተሰራ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ ምርት አንጻር ቁጥሮቹ እንደሚያመለክቱት በወተትም በማርም እንዲሁም በዶሮና እንቁላል ምርቶች ባለፉት አምስት ወራት ያቀድናቸው እቅዶች ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ ስኬታማ ሆነዋል፡፡

ይህን ለማሳካት እንደ አማላካችነት አንዱ ከምንወስዳቸው ማሳያዎች በሚቀርቡ ግብዓቶች ላይ የሚያደርገው ክትትል በጣም ሰፊ መሆኑ ነው፡፡ ግብዓት ካልቀረበ ውጤት አይኖርም። ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋንኛው ግብዓት በተለይ በዶሮ ልማት ላይ የአንድ ቀን ጫጩት ዶሮን ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ባለፈው ዓመት፣ ዓመቱን ሙሉ 42 ሚሊዮን ያህል ሰርተናል፡፡ ዘንድሮ የዓመት እቅዳችን 62 ሚሊዮን ነው፤ ይህ ከአምናው ጋር ሲተያይ በ20 ሚሊዮን ያደገ ነው፡፡

ባለፈው አምስት ወራት ለመስራት ያቀድነው 25 ሚሊዮን ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ አሁን 29 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰርተናል፡፡ ይህ በጣም ትልቅ እድገት ነው። ከአምናው እቅድ ጋር ስናስተያይ ግማሽ ዓመት ላይ የባለፈው እቅዳችንን ልናሳካ የምንችልበት ሁኔታ እንዳለ ነው፡፡ ሁለተኛው አመላካች በተለይ ወተቱ ልማት ላይ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶና ለአርብቶ አደሩ ከማቅረብ አንጻር በጣም ትልቅ ተግዳሮት ነበር፡፡ በተለይ በአካባቢው ያሉ መሰረት ልማቶች አነስተኛ ከመሆን አንጻር ባለፈው ዓመቱን ሙሉ ማቅረብ የተቻለው አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ነው፡፡ ዘንድሮ ወደ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ለማቅረብ አቅደናል፡፡ ባለፈው አምስት ወራት ውስጥ 920 ሺ ወይም ደግሞ ለአንድ ሚሊዮን የቀረበ ለማቅረብ ችለናል፡፡ ይህ ከእቅዳችን ጋር ተቀራራቢ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ዘመናዊ ቀፎ ከማቅረብ አንጻር ከማሩ ጋር ተያይዞ ወደ 250 ሺ አካባቢ ለማቅረብ ታስቦ ወደ 315 ሺ ማቅረብ ችለናል። ለዚህ የግብዓት አቅርቦት ለውጥ በአምስት ወራት የተወሰደ እርምጃ ለመግለጽ ያህል ለመጀመሪያ ጊዜ 30 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንዲፈቀድ አድርገን በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ ባለሀብቶች ማን ምን ያደርጋል? የሚለው እቅድ ለይተንና አውጥተን በዚህ መሰረት እንዲያስገቡ ማድረጋችን ተጠቃሽ ነው፡፡

በዚህ አምስት ወር በእንስሳት ዘርፉ ወደ 84 ሚሊዮን እንስሳትን ለመከተብ ታቅዶ ወደ 71 ሚሊዮን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የተገባው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ምን ያህል ውጤት እያስገኘ ነው?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ሶስተኛው በግብርናችን ላይ ያለው ዘርፍ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፉ ሲሆን፣ በዚህ በተፈጥሮ ሀብት ልማት ዙሪያ አንደኛው ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ተያይዞ የተሰራ ሥራ ነው፤ ሁለተኛ ደግሞ መሬትን ከመመዝገብና ሰርተፍኬት ከመስጠት አኳያ የተሰራ ሥራ አለ፡፡

በአረንጓዴ አሻራ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንም በተደጋጋሚ እንዳስቀመጡት በሁለት ምዕራፎች የሚሰራ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ 25 ቢሊዮን ችግኝ፤ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 25 ቢሊዮን ችግኝ ነው፡፡ በጥቅሉ በ2018 ዓ.ም 50 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል በዓለም ላይ ትልቁ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም ኢትዮጵያ ነድፋ እየሰራች ነው፡፡

ከ50 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት ያለፈውን ዓመት ጨምሮ 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ተክለናል፡፡ ይህ ባለፈው በዱባይ በተካሔደው ኤክስፖ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራሟ ምን አይነት እንደሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልምድ እንዲወሰድ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በተለይ በ2015/16 ክረምት የተተከሉ ችግኞች ባለፈው ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅደን የ2015ቱ ወደ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች መትከል ችለናል፡፡

ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባስቀመጡት መሰረት ወደ 60 በመቶ የጥምር ግብርናን እና የፍራፍሬ ችግኞች እንዲሆኑ በሚል በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወደ 57 በመቶ የጥምር ግብርና እና የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ ቀሪው ደግሞ ትልቁ ወደ 42 በመቶ የደን ችግኞች መተከል ችለዋል፡፡ ወደ አንድ በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የውበት ችግኞች ናቸው፡፡

የጽድቀት መጠኑን በተመለከተ የሚሰራው ሁለት ጊዜ ነው፡፡ አንደኛው ወዲያው ክረምቱ እንዳለፈ የሚታይ አሰሳ አለ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በጋው አለ፡፡ በመጀመሪያ ዙር ላይ በተደረገው አሰሳ ባለፈው ክረምት ከተከልናቸው ችግኞች 85 በመቶ ጸድቀዋል፡፡ በቀጣይም እንክብካቤውን አጠናክረን እንቅጥላለን፡፡

የ2016/17 ላይ 50 ቢሊዮን ችግኙ ጋር ለመድረስ የሚቀሩን ሶስት ዓመታት ናቸው፡፡ ስለሆነም የሚቀረን ወደ 18 ቢሊዮን ነው፡፡ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት በእኛ በኩል እንደግብርና ሚኒስቴር ቢያንስ በየዓመቱ ከስድስት ቢሊዮን እስከ ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብንሰራ የቀረ የሶስት ዓመት እቅዳችንን ለማሳሳካት ከክልሎች ጋር ስለምንሰራ ሁለት ዙር ውይይት አድርገናል፡፡

ከክልሎቻችን የመጣው እቅድ በባለፈው ዓመት የተገኙ የችግኝ ጣቢያዎች ልምዶች አሉ፡፡ ብዙ የተቋቋሙ ችግኝ ጣቢያዎች አሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ችግኞች ማዘጋጀት ይቻላል የሚል እቅድ ከክልሎቻችን መጥቷል፡፡ ይህ ማለት ከእቅዱ በላይ ነው። ከክልሎች ጋር ባረግነው ውይይት በጥራት ላይ ትኩረት እንድናደርግና ቦታዎች ቀድሞ የመለየት ሥራ ከመስራት አንጻር በስፋት እንዲሰራ አቅጣጫ አስቀምጠን እየሰራን ነው፡፡ እቅድ ተዘጋጅቶ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ወደስራም ተገብቷል፡፡

ሁለተኛው ከተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ አንጻር ከወሰድን የገጠር መሬት የመመዝገብና ይዞታ ማረጋገጫ የመስጠት በጣም ትልቁ የግብርና ዘርፍ ሥራ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ወራት ለመመዝገብ ያቀድነው 600 ሺ ማሳዎችን ነበር። የመጀመሪያ ደረጃ ማረጋገጫ የሰጠነው ወደ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ይዞታዎችን ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ሰርተፍኬት የሚባል አለ፤ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በተሻለ ጂፒኤስና በቴክኖሎጂ ተወስዶ የሚሰጠው ሁለተኛ ደረጃ ማረጋገጫ በተመለከተ ወደ 170 ሺ ለመስጠት አቅደን ወደ 317 ሺ ማሳዎች ላይ ሁለተኛ ደረጃ ሰርተፍኬት ለመስጠት ችለናል፡፡

እስካሁን ይህ የመሬት ምዝገባ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ 25 ሚሊዮን ይዞታዎች የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህም ወደ ሰባት ሚሊዮን ባለይዞታዎች ይህ ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሰባት ሚሊዮን አርሶና በእርሻ ላይ የሚተዳደሩ አርብቶ አደሮች ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት በጣም ትልቅ ቁጥር ነው፡፡ ከዚህ ቁጥር ግንዛቤ ሊወሰድ የሚገባው ነገር ከሰባት ሚሊዮን ውስጥ ወደ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን አባወራዎች በተለይ በወንድ የሚመሩ አባወራዎችና ሁለት ነጠብ አምስት ሚሊዮን እማወራዎችን የሚያካትት መሆኑ ነው፡፡ በምዝገባው ሒደት ያየነው ነገር ቢኖር የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ትልቅ የመሬት ባለቤትነትን ያረጋገጠ የለውጥ ሒደት ነው፡፡

በገጠሩ አካባቢ ትልቁ ሀብት የሚባለው መሬት ነው። በዚህ በመሬት ባለቤትነት ደግሞ ሴቶችን ወደፊት ካመጣን ቀጥሎ ያንን በማስያዝ ብድር ከመበደር አንጻር እያዘጋጀን ያለነው የመሬት አዋጅ እሱ ነውና ብድር ሲሰጥ ዋስትና ከመስጠት አንጻር የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሥራ ነው ማለት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ባለፈው ዓመት ትልቅ ችግር ሆኖ ከሰነበተው ከአፈር ማዳበሪያ ጋር ተያይዞ ምን የተሰራው ሥራ አለ?

ግርማ (ዶ/ር)፡- አራተኛው የግብርና ዘርፋችን የኢንቨስትመንትና ግብዓት ጋር ተያይዞ ያለ ነው፡፡ በተለይ በ2016/17 የምርት ዘመን ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር ተያይዞ እየሰራን የነበረው ወደ 23 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ባለፈው ዓመት ማዳበሪያን በብዛትም ሆነ በወቅቱ ከማቅረብ አንጻር በተለይ ኤል.ሲን ከመክፈት አንጻር ትልልቅ ግዢዎች ነበሩ፡፡ የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት፣ ለዚያ ያጋለጡንና የተንዛዙ የአሰራር አካሄዶችን በማየት የማዳበሪያ ግዥ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቀየር አድርገናል፡፡ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ በምታገኝበት ሒደትና መንገድ የማዳበሪያ ግዥን የመፈጸም ሥራ ተሰርቷል። ግዥው በቀጥታ ከፋብሪካው መግዛት የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን የማዳበሪያ ዋጋ የሚወርድበትና የሚወጣበት ጊዜ አለ፡፡ ከዚህ በፊት በሚቀንስበት ጊዜ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት የማቅረብ ጉዳይ ስለነበረ በሚቀንስበት ጊዜ ሳንገዛ በሚጨምርበት ጊዜ ጨረታው ሲያልቅ የሚገዛበት ሁኔታና ማዳበሪያው በውድ ዋጋ የሚገዛበት ሁኔታ ነበር፡፡

ስለዚህ ለማዳበሪያ የሚመደበው ብድር በወቅቱ እንዲመደብና ይህንን የሚገዛው አካል የተሻለ ዋጋ በሚኖርበት ጊዜ እና ወቅት ላይ እንዲገዛ ትልቅ ኃይል ነው የተሰጠው፡፡ በተለይ ደግሞ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ቦርድ እንደ አዲስ ተቋቋሙ። ቦርዱ ውስጥ ውሳኔ መስጠት የሚችሉ ብሔራዊ ባንክ፣ ንግድ ባንክ፣ ሎጂስቲኪና ትራንስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎችም አካላት ተካተው ወደሥራ ተገብቷል፡፡

ከዚህ አንጻር አምና ለማዳበሪያ የተመደበው ግዥ አንድ ቢሊዮን 59 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህ ትግራይን ጨምሮ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የገዛነው ማዳበሪያ ትግራይን ጨምሮ በ13 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህ ማዳበሪያ በቂ እንዳልነበር ይታወቃል፡፡ ተቆራርጦ ያለወቅቱ መግባት ብቻ ሳይሆን በመጠንም በቂ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡

ዘንድሮ የተመደበልን ዶላር ወደ 930 ሚሊዮን ነው። ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በመቶ ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ነው። ነገር ግን ባደረግነው የአሰራር ለውጥ መሰረት በ930 ሚሊዮን ዶላር ወደ 19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መግዛት እንደምንችል ባደረግናቸው ጥረቶች ለማወቅ ችለናል፡፡

ይህ የሚያንስ ከሆነ ተጨማሪ ጥያቄዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አሁን በተፈቀደልን 930 ሚሊዮን ዶላር ሊገዛ የሚችለው ወደ 19 ነጥብ አራት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከዚህ ውስጥ 15 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ተገዝቷል፡፡

ይህን 19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል እንኳን ብንገዛ ከባለፈው 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ጋር ሲተያይ ወደ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው። ኢትዮጵያ በታሪኳ 19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ገዝታ አታውቅም። በመጠንም ትልቁ ሲሆን፣ የተገዛበትም ዋጋ የተሻለ ከመሆኑ አንጻር የተሻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ዋናው መግዛቱ ብቻ አይደለም፡፡ በወቅቱ ማምጣት መቻል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ዘንድሮ ያደረግነው በአጠቃላይ በዓመት ከምንገዛው ማዳበሪያ ለመስኖ፣ ለበልግ እንዲሁም ለመኸር ምን ያህሉ ነው የሚያስፈልገው የሚለውን ከክልሎች ጋር ሆነን ለይተናል፡፡ በአጠቃላይ ከሚገዛው ማዳበሪያ 25 በመቶ የመስኖ ስንዴን ጨምሮ ለመስኖ ጊዜ የሚፈለግ ነው። ወደ 20 በመቶ ደግሞ በልግ አካባቢ የሚፈለግ ሲሆን፣ 55 በመቶው በመኸር ጊዜ የሚፈለግ ነው፡፡ ሲገዛም ይህ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡

ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ለመስኖና ለበልግ የሚያስፈልገው ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ተገዝቷል። ሙሉ በሙሉ ኤል.ሲ ተከፍቷል፡፡ ሙሉ በሙሉ የመጫን ሂደቱም እየተካሄደ ነው። ባለኝ መረጃ ከተገዛው 15 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ ወደ ሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጂቡቲ ደርሷል፡፡ ጂቡቲ ከደረሰው ሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ማዳበሪያ ውስጥ ወደ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደክልሎች ተጓጉዟል፡፡

ማዳበሪያ የጫነችው የመጀመሪያዋ መርከብ ዘንድሮ ጂቡቲ የደረሰችው ጥቅምት ወር ነው፡፡ ይህም በየትኛውም ጊዜ የማዳበሪያ ግዥ ካደረግናቸው ሁሉ የፈጠነ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጂቡቲ ከደረሰው መካከል 74 በመቶ ማዳበሪያ ወደሀገር ውስጥ እንዲገባ እኔና የሎጂስቲክና ትራንስፖርት ሚኒስትሩ የምንመራው የሎጂስቲክ ኮሚቴ ተቋቁሞ በባቡርም በመኪና በፍጥነት እስከ ክልሎች የሚደርስበት ሁኔታ በጥልቅ ዲሲፒሊን እየተመራ ነው፡፡

ከማዳበሪያ አንጻር መንግሥት ትልቅ ውሳኔ ወስኗል። ምንም እንኳ በግዥ ሒደቱ ላይ ከአምና ጋር ሲተያይ በተሻለ ዋጋ ማዳበሪያ መግዛት ብንችልም ከአምናው ጋር ሲተያይ ወደ 20 ቢሊዮን ብር የሚሆን ቁጠባ ማድረግ ተችሏል፡፡ ነገር ግን እንዲያም ሆኖ አሁን በዓለም ላይ ያለው የማዳበሪያ ዋጋ ከአርሶ አደሮች የመግዛት አቅም ጋር ሲታይ ከፍ ያለ ከመሆኑ አንጻር ወደ 16 ቢሊዮን ብር መንግሥት ድጎማ በማድረጉ አምና ከነበረው የማዳበሪያ ዋጋ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ዋጋ ጭማሪ ሳይደረግበት ለአርሶ አደሩ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ እንዲህ ሲባል የተደጎመው አርሶ አደሩ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ አርሶ አደሩ ሲደጎም ኅብረተሰቡ በሙሉ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡

ማዳበሪያ በወቅቱ መግዛቱና ወደሀገር ውስጥ ማስገባቱ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በስርጭት ሒደት ባለፈው ዓመት ያጋጠመው ተግዳሮቶችን ከመቀነስ አንጻር የተሰሩ ስራዎች አሉ፤ ቀሪ ስራዎችም አሉ፡፡ የተሰሩ ስራዎች ስንል አንደኛው አቅርቦቱን ስለጨመርን የዘንድሮ የማዳበሪያ አቅርቦት ከአምናው አቅርቦት ጋር ሲተያይ በስድስት ሚሊዮን ብልጫ አለው፡፡ ይህ አምና የተፈጠረውን እጥረት ስለሚፈታ በገበያው ላይ ያለው ሽሚያ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡

ስርጭቱን በሚመለከት ከክልል አመራሮች፣ ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች እስከ ታች ድረስ ኮሚቴዎች ተቋቁሞ በክትትልና በድጋፍ በሥርዓቱ እንዲደርስ እየተኬደበት ይገኛል፡፡ በተጨማሪ ይህን የሚያክል ማዳበሪያ በሚንቀሳቀስበት የአሰራር ሥርዓት ውስጥ በማኑዋል ብቻ መከታተሉ ችግሮቹን ሙሉ በሙሉ ስለማይቀርፍ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮ ቴሌኮምና ሌሎቹም የሳይንስና ኢኖቬሽን ጋር አብረን እየሰራን እንገኛለን፡፡ ዲጂታል ትራኪኒግ ሲስተም እየዘረጋን ሲሆን፣ ዘንድሮ ለሙከራ የምንሄድበት ይሆናል፡፡

ይህ ማለት ማዳበሪያው ከጂቡቱ ሲጫንና ሲታሸግ እዛ ላይ ምልክቶች ማለትም ባር ኮዶች የሚደረጉ ይሆናል። ለምሳሌ ለአማራ ክልል ከተጫነው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የደረሰው ስንቱ ነው? በሕገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወር ማዳበሪያ ካለ የትኛው ክልል ነው? የሚለውን በቀላሉ መለየት ያስችላል። እንዲሁም ለሕገ ወጥ ንግዱ የተጋለጠው የት አካባቢ ነው? የሚለውን መለየት ስለሚያስችል የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ግብርናው በውጤት የታጀበ ይሆን ዘንድ የምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ ምን እየተሰራ ነው?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ከግብዓት አቅርቦት አንጻር ከማዳበሪያው ቀጥሎ በጣም በትልቁ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚፈለገው የምርጥ ዘር አቅርቦት ነው፡፡ ምርጥ ዘር ባለፉት ዓመታት በአማካይ ወደ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የሚቀርብበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዘንድሮ ጀምሮ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የዘር አቅርቦትን በእጥፍ ለመጨመር እየሰራን ነው። ዘንድሮ ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ዘር እናቀርባለን ብለን አቅደናል፡፡ በተለይ በዚህ በመስኖ ወቅት ወደ 128 ሺ ኩንታል ዘር ባለፉት አምስት ወራት ቀርቧል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ግብርና የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት አኳያ ሰፊ እድል ያለው በመሆኑ ከዚህ አንጻር የተገኘው ውጤት ምን ይመስላል?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ከግብርና ኢንቨስትመን ጋር ተያይዞ አንዱ በግብርናው ዘርፍ የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ ነው። ኤክስፖርቱን እንደ ማሳያ ለመጥቀስ ያህል የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተ ከ70 እስከ 80 በመቶ አስተዋጽኦ የሚያደርገው የግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ ሁለት ቦታ ላይ ለግብርና ምርቶች ክትትል የሚደረግባቸው ቦታዎች አሉ። ይህም በግብርና እና በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስር ነው፡፡ በተለይ በእኛ በኩል ቡና፣ ቅመማቅመም፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦ ሲሆኑ፣ የቅባት እህሎችንና የጥራጥሬ ሰብሎችን ጨምሮ ደግሞ ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር የሚከታተላቸው ናቸው፡፡

እኛ ከምንከታተላቸው ዘርፎች ባለፉት አምስት ወራት ወደ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ አቅደን ያስገኘነው ወደ 764 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነው፡፡ ይህ ከእቅዱ አንጻር ሲታይ ወደ 65 በመቶ ያህል ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ግኝታችንን በተመለከተ ከእቅድ አንጻር ብዙ ስራዎችን በቀጣዮቹ ወራት መስራት እንዳለብን ያመላክተናል።

ይህ እንዳለ ሆኖ በዓለም ላይ የቡና ዋጋ ከመቀነስና ከመቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ በአበባም ዋጋና ፍላጎት ላይ መጠነኛ መቀዛቀዝ ከመኖሩ አንጻር የተወሰነ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡። ስለዚህም በቀጣዮቹ ወራት ተጨማሪ ስራዎችን እንሰራለን፡፡

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ሰፊ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም አንዳንድ አካባቢዎች በተለይ ዝናብ አጠር የሆኑና በሴፍቲኔት የሚተዳደሩ አካባቢዎች አሁንም አሉ፡፡ እነዚህን ባሉን ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራሞች ለማስኬድ እንሞክራለን፡፡ በመደበኛ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራምና የእለት ደራሽ አሰራርም አለን፡፡ በመሆኑም ከልማት አጋሮቻችን ጋር በመሆን ባለፉት አምስት ወራት ወደ ሶስት ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር በልማታዊ ሴፍትኔትና በዕለት ደራሽ ለክልሎች ተላልፏል፡፡ ክልሎች የተላለፈላቸውን ፋይናንስ ወስደው እንደየአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ በተለይ ድርቅና የዝናብ እጥረት የተከሰተባቸው አካባቢዎችን እንዲደግፉ ታስቦ የሚደረግ ነው፡፡ በታህሳስ ወር ወደ 523 ሚሊዮን ተጨማሪ ድጋፍ ለክልሎች ለማስተላለፍ ጥያቄ ቀርቦ እየተሰራበት ነው፡፡

ሌላው ለክልሎች ድጋፍ ከመስጠት አንጻር ባለፉት አምስት ወራት ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሰርተናል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተለይ ለመስኖ ስንዴ ሊያግዝ የሚችል ወደ 12 ሺ 617 ፓምፖችን ለክልሎች ግዥ ተፈጽሞ እየተጓጓዘ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ አንድ ሺ 600 ፓምፖች ሀገር ውስጥ ገብተው ባለፈው ሳምንት ክፍፍል ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ የቀረበው ከመሬቱ ስፋት አንጻር ሲሆን፣ ወደ አንድ መቶ ሺ ሔክታር አካባቢ ላይ ድጋፍ ማድረግ የሚችልና 503 ሚሊዮን ብር የወጣበት ድጋፍ ነው፡፡

ሁለተኛው የሎጂስቲክስ ድጋፍ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ባለፉት አምስት ወራት ወደ 221 ተሽከርካሪዎች እና አንድ ሺ 800 አካባቢ ሞተር ሳይክሎች በመግዛት ለክልሎች ተሰራጭተዋል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ወራት የግብርናው ዘርፍ በዋና ዋና ዘርፎች ላይ የመኸር ሰብሉ ከመሰብሰብ፣ የበጋ መስኖ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በፍጥነት ከማስኬድና በተለይ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉትን ችግኞች ከመከታተል ብሎም የጽድቀት መጠናቸውን ከማሳደግ አንጻር መስራት አለበት፡፡ በቀጣዮቹም ወራት ለሚቀጥለው ክረምት ዝግጅት ከማድረግ አንጻር እንዲሁም አምና ካጋጠመን ችግር ትምህርት ወስደን በተለይ በማዳበሪያ ላይ ያደረግነው ለውጥ በዚህ አምስት ወር ከሰራነው ሥራ ትልቁና ውጤታማ ሥራ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በዚህ መልኩ ባለፉት አምስት ወራት ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል ማለት ይቻላል፡፡ ይህም በሀገራችን ማክሮ ኢኮኖሚ ውስጥ የግብርናው ዘርፍ የተሰጠውን ተልዕኮና ሥራ እየተወጣ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ውጤት ግን በግብርና ተቋም ብቻ የተገኘ ሳይሆን ከሚኒስቴሩ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው ርብርብ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ስራውን የሰሩት አርሶ እና አርብቶ አደሮቻችን እንዲሁም የልማት ሠራተኞቹ ናቸው፡፡ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ የሌሎችም ሴክተሮችና የልማት አጋሮች ድጋፍ ከጎናቸው ስለነበር ላመሰግን እወዳለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ግርማ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኀሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You