በጥናት ላይ ለተመሠረተ ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓት

ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዋናነት ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል የንግድ አሠራርን ማዘመን፣ ግልጽ፣ ተደራሽና ፍትሃዊ ውድድር የሰፈነበት እንዲሆን ማድረግ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ቀጠናዊ ትስስርን ማጠናከር፣ የውጭ ንግድን ማስፋትና ማሳደግ፣ የዕቃዎችንና አገልግሎት የጥራት ደረጃ ማዘጋጀትና መቆጣጠር፣ የሸማቹንና የንግዱን ማህበረሰብ እንዲሁም የሀገርን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የንግድ ሥርዓት መገንባት የሚሉትም ተልዕኮዎቹ ናቸው፡፡

ሚኒስቴሩ በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ በንግዱ ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ስለመኖራቸው ይገለጻል፡፡ በዘርፉ የሚስተዋሉትን እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በሚኒስቴሩ በኩል በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል፡፡ ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት በቅርቡ ፈጽሟል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በጥናትና ምርምር የተደገፈ ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ባደረገበት ወቅት፤ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናትና ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ደስታው መኳንንት፣ የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት ተግዳሮቶች በአግባቡ ለመፍታት አስቻይ የሆነው መንገድ ጥናትና ምርምርን መሠረት ያደረገ አሠራር መዘርጋት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የንግድ ጉዳይ በተለያዩ አደረጃጀቶች ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ንግድና ኢንዱስትሪ ይባል ነበር፤ ንግድ ሚኒስቴር ተብሎም የተጠራበት ወቅትም ነበር፤ አሁን ደግሞ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሚል እየተጠራ ይገኛል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ፖሊሲዎች እንዲሁም የንግድና አጠቃላይ ሀገራዊ የጥራት ፖሊሲ አዘጋጅቶ በ2022 የንግድ ዘርፍ በአፍሪካ ደረጃ ዘመናዊና ተወዳዳሪ ሆኖ ማየት የሚል ራዕይ ሰንቆ እየሠራ ይገኛል፡፡

በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ የአሠራር ለውጦችን ያደረገው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በተጨማሪ 30 የሚደርሱ የተለያዩ መመሪያዎችን በማሻሻል የአሠራር ለውጦችን አድርጓል፡፡ ስታንዳርዶችንም አዘጋጅቷል፡፡ ያም ቢሆን ታዲያ አሁንም ድረስ በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ አልተቻለም፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓት ለመገንባት ጥናትና ምርምርን የተከተለ ትግበራ ማስፈለጉ እንደታመነበት አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሶስት ትላልቅ ዘርፎች የሚመራ ሲሆን፤ አንደኛው የንግድ ሥርዓትና ላይሰንሲንግ ዘርፍ የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃን ጨምሮ በውስጡ ሁለት ትላልቅ ዘርፎች አሉት፡፡ ሁለተኛው የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ነው፡፡ ይህም ሶስት ትላልቅ ዘርፎችን የያዘ ሲሆን የውጭ ንግድ ግብይት፣ የውጭ ንግድ ፕሮሞሽንና ግብይት ማሳለጥ እንዲሁም የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ትስስር ናቸው፡ ፡ ሶስተኛው የጥራት መሠረተ ልማት ማረጋገጫ ዘርፍ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥም ሶስት ዋና ዋና ዘርፎች ይገኛሉ፡፡ እነሱም የሕጋዊ ሥነ ልክና የቴክኒክ ደንብ ማስተባበር፣ የጥራት ማረጋገጫ ሲሆን፣ በገቢና ወጪ ቁጥጥር ላይ ትኩረት አድርገው ይሰራሉ፡፡

ከእነዚህ ሶስት ዋና ዋና ዘርፎች በተጨማሪም የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ከምርምር ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ይሠራል፡፡ ዘርፉ ከፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋማት ጋር በመገናኘት በፖሊሲ መነሻ ሃሳቦች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ ይህም በጥናት ላይ የተመሰረቱ የአሰራር ለውጦች እንዲኖሩ ማድረግ ያስችላል፡፡ በአጠቃላይ የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ብርቱ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

በተለይም በግብይት ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ዛሬም ድረስ መቅረፍ እንዳልተቻለ ጠቅሰው፣ ችግሩ ሳይንሳዊ የሆነ ጥናትና ምርምርን እንደሚጠይቅ ዶክተር ደስታው አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ በተለይም በግብይት ሥርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን የመፍታቱ ሥራ ሳይንሳዊ ጥናቶችን የሚጠይቅ፤ የምርምርና የጥናት ተቋማትን እገዛ የሚያፈልግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የንግድና የጥራት ፖሊሲዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፣ በቅርቡ እንደሚጸድቁም ዶክተር ደስታው አስታውቀዋል፡፡ ይህም ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በንግዱ ዘርፍ ትልቅ ችግር ያለባቸውና ጥናትና ምርምር ያስፈልጋቸዋል ብሎ ከለያቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

ዶክተር ደስታው እንደተናገሩት፤ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ በፍትሃዊ የንግድ ውድድር ላይ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ችግሮቹን በጥናትና ምርምር መለየት ያስፈልጋል፡፡ በንግድ ሥርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮች፣ የፍትሃዊነት ችግሮችና የሕግ ጥሰቶችን ያጠቃልላሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ትልቅ ጥናትና ምርምር በማካሄድ የአሠራር ማሻሻያዎችን የሚጠይቁ ሰፋፊ ሥራዎች ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሀገር ውስጥ ንግድን ማስጀመር ትልቅ አበርክቶ እንዳለው የጠቀሱት ዶክተር ደስታው፤ በዚህ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችንም እንዲሁ በጥናትና ምርምር መለየትና ማጥናት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በዓለም አቀፍ መለኪያ መሠረት ሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድ በማስጀመር ሥራ በኩል በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ላይ መሥራት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ መሳሪያ መሆን ይችላል፡፡ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ፈቃድና ምዝገባ አሰጣጥን ለማሳለጥ በርካታ ሥራዎችን የሠራ ቢሆንም፣ በንግድ ማስጀመር ላይ ግን አሁንም በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም የብዙ ተቋማትን እገዛና ሚና የሚጠይቅ በመሆኑ ተቋማትን ለማስተሳሰር በፖሊሲና ጥናት ምርምር ኢንስቲትዩት እገዛ ጥናት ይደረጋል፡፡

በንግድ ውድድርና የሸማቾች መብት ጥበቃ በኩል አሁንም በሸማቾች በኩል ያለው ግንዛቤ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ደስታው፤ ይህም የጥናትና ምርምር ሥራን እንደሚጠይቅ አመልክተዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦትና ፍላጎት ዝንባሌንና ልምዱንም በሚገባ ማጥናት ያስፈልጋል። አሁንም ድረስ መንግሥት በመሠረታዊ ሸቀጥ አቅርቦት ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ እስከመቼ ይዘልቃል? ምን ዓይነት የአቅርቦት ሥርዓት ሊኖር ይገባል? የሚል ጥናት ማድረግንም ይጠይቃል፡፡ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የመሠረታዊ ሸቀጥ ፍላጎትንም ከምርቱ ጋር የማስተሳሰር ሥራን መሥራትም ያስፈልጋል፡፡

የአክሲዮን ማህበራት ሕጋዊነት አሠራርን በተመለከተም ጥናት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ዶክተር ደስታው፤ በኤክስፖርት ንግድ ዘርፍ አፈጻጸምም እንዲሁ ሰፊ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሀገሪቱ በርካታ የኤክስፖርት ምርት ይመረታል፡፡ በሚመረተው ምርት መጠን ልክ ግን የውጭ ምንዛሪ እየተገኘ አይደለም፡፡›› ሲሉ የሚገልጹት ዶክተር ደስታው፣ በዚህ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች በተለይም ከምርት እስከ ውጭ ገበያ ድረስ ያለውን ሂደት በጥናት መለየትና መፍትሔ ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የግብርና ወጪ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነት ላይ ክፍተት ስለመኖሩ አንስተው፤ ብዙ ምርቶች በሚጠበቀው የጥራት ደረጃ ላይ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም ማለት አብዛኞቹ የግብርና ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ አይደሉም ማለት እንዳልሆነም ገልጸው፣ ጉዳዩ በጥናትና ምርምር ከሚፈልጉ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የገቢና የወጪ ንግድ ምርት ጥራት ቁጥጥር ሥርዓት ችግሮች እንዳሉበትም አመልክተዋል።

‹‹በአሁኑ ወቅትም በአቅርቦትና ፍላጎት መሀል ያለው ልዩነት ስለሰፋ በአቅርቦት ላይ ትልቅ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ቢሆንም በንግድ ሥርዓቱ ላይ ትልቅ ችግር እየፈጠረ ያለው የምርት ጥራትን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው›› ያሉት ዶክተር ደስታው፤ ጥራትን በዘላቂነት ለማስቀጠል የጥናትና ምርምር ሥራ የግድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የምርት ጥራትን ለማሳደግ መሠረተ ልማት ከማሟላት በተጨማሪ ተጠቃሚው ለጥራት የሚሰጠው ዋጋ መጨመር እንዳለበት አስታውቀው፣ ማህበረሰቡ ለጥራት ያለው ዕይታ የተስተካከለ እንዲሆን መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን በሀገሪቱ ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓት ለመገንባት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በርካታ ጥረቶችን እያደረገ ነው፡፡ ጥረቶቹን ውጤታማ ለማድረግም ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሱ አንድ ርምጃ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ስለተሳለጠ የንግድ ሥርዓት፣ ስለሸማቾች መብት ጥበቃ፣ ስለወጪ ምርቶች እድገት፣ ስለመዳረሻ ገበያ ውጤት እንዲሁም ከጥራት አንጻር የኢትዮጵያ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሚገኝበት የተወዳዳሪነት ሁኔታ፣ ሰው ባወቀው ልክ ከሚሰጠው ምክረ ሃሳብ ይልቅ ደረጃውን በጠበቀ ጥናትና ምርምር ሊገለጽ ይገባል። በንግድ ሥርዓቱ ዙሪያ በዘፈቀደ የሚሰጡ ሃሳቦችና ችግሮችን የሚገልጹ አስተያየቶች ስለመኖራቸው ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚለየው፣ መፍትሔ የሚሰጠውና የሚያረጋግጠው የጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት እንደሆነ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ጥናት ችግሩን መለየትና ተቀባይነት ያለውን መፍትሔ ማቅረብ ይቻላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ እንደ ሀገር በንግድ ሥርዓቱ ላይ ሰፋፊ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙ አመልክተዋል:: ስምምነቱ እነዚህን ውስብስብ ችግሮች ግልጽ በሆነ የጥናትና ምርምር ምክረ ሃሳብ ለመፍታት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተቋሙን ሥራዎች የበለጠ ተቋማዊ ለማድረግ የጥናትና ምርምር ሥራ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የመንግሥትን ሥራ ለሚያከናውኑ ተቋማት በፖሊሲ ጉዳዮች በምርምር የተደገፈ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብዙ ጎልቶ የወጣ እንዳልነበረ ጠቅሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ወደ ተግባር ሊለወጡ የሚችሉ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በንግድ ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከኢንስቲትዩቱ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና የምርምር ውጤቶችን ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ከኢንስቲትዩቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው የሥራ መስኮች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ፤ ውጤቱንም ለባለድርሻ አካላት በመስጠትና በማስተቸት ምክረ ሃሳብ እንዲቀርብ ይደረጋል። በንግድ መስኩ እውቀት ላይ የተመሠረተ መረጃ ለመስጠት ኢንስቲትዩቱ በትኩረት ይሰራል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ እና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ስምምነቱን የፈረሙ ሲሆን፤ የጥናትና ምርምር ሥራው የንግድ ሥርዓትን የማዘመን፣ ግልጽ፣ ተደራሽና ፍትሐዊ ውድድር የማስፈን ተልዕኮን ለማሳካት አጋዥ እንደሆነ ተገልጿል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You