ሌባ ተይዞ ዱላ አይጠየቅም?

ሌሊት ነው። ድቅድቅ ያለ። ዓይንን ቢወጉት እንኳን የማይታይበት ዓይነት ሌሊት። በዛ ሰዓት ያለ ቦታው የተገኘ ወጣት ነበር። በሰዓቱ ሊሰርቅ ይሁን ሌላ አላማን ይዞ በቦታው ተገኝቷል። ያለ ቦታው ተገኘ የተባለውን ወጣት ግዛታችን ነው፤ እንዴት ይዳፈረዋል ያሉቱ በእጃቸው ፍትህን ስለመስጠታቸው የሚነግር ታሪክ ከፖሊስ የመረጃ ቋት አግኝተናል። ሙሉ ታሪኩን እነሆ ብለናል።

ነገሩ እንዲህ ነው። ወጣት ለታ ዳዲ ይባላል። የደስ ደስ ያለው ሸንቀጥ ያለ ወጣት ነው። ወጣቱ መታተር እንጂ ስኬትን ቶሎ የማግኘት ነገር አይሳካለትም ነበር። የሚይዘውንም ሥራ እስከ ጥግ ለማድረስ መጀመሪያ ላይ እንቅፋት ስለሚገጥመው ተስፋ ቆርጦ ይተወዋል። ሁሉንም ነገር ትቶ እጁን አጣጥፎ እንዳይቀመጥ፤ መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ለመሙላት እንኳን የሚሆን አቅም የሌለው ወጣት ነው።

ወጣትነት ውበትም ጉልበትም መሆኑን ቢረዳም ለእሱ ግን ሰኬት ፊቷን ካዞረችበት ሰነባብታለችና የሞከረው የማይሆንለት፤ ሲናገር የማያምርበት፤ ለበጎ የተናገረው እንደ ክፋት የሚቆጠርበት ልጅ ሆኖ መጣፊያ አጥሮት እንዲሁ ይንጠራወዛል።

ስኬት የራቀውና ተስፋ መቁረጥ የጎበኘው ወጣት በሥራ ባይሳካልኝ ነጥቄ መብላት አያቀተኝም የሚል ሃሳብ ልቡ ውስጥ መመላለስ ከጀመረ ሰነባብቷል። ይህን ሃሳቡን ግን ለማንም የማካፈል ሃሳብ አልነበረውም። መካሪ መክሮ ካሰበበት ይመልሰኛል በሚል ማንንም መናገር አልፈለገም።

በልቡ የያዘውን ይዞ እጁን በረብጣ ብሮች ሊሞላ የሚችል ሃሳብ ማሰብ ከጀመረ ግን ሰነባብቷል። ምንም ዓይነት የስርቆት ልምድ ያልነበረው ወጣት የሚያገኘውን ገንዘብ እንጂ የሚደርስበትን ነገር ለማሰብ አንድም ደቂቃ አላጠፋም ነበር።

ስለዚህ በአካባቢው የሚገኝን አንድ ተቋም በመድፈር ዋጋው ወደድ ያለ ነገር በመውሰድ እሱ ስኬቴ የሚለውን ገንዘብ በማግኘት ሊጠቀምበት ወደደ። ከዚያም ለዚህ ተግባሩ መሳካት ይጠቅማል ያለውን በሙሉ አሟልቶ አካባቢውን ማጥናት ጀመረ።

በክትትሉ የድርጅቱ ጥበቃዎች ብሎም ጓደኞቻቸው አካባቢያቸውን ሲቃኙ ቆይተው ሰብሰብ ብለው ከተጨዋወቱ በኋላ በግምት ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ ተነስተው ወደ ማረፊያቸው ሲሄዱ ተመልክቷል። ስለዚህ እሱ ላሰበው ሃሳብ ከስምንት ሰዓት በኋላ ያለው ጊዜ ተመራጭ ሊሆን እንደሚችል ወስኗል።

ይህንን ካረጋገጠ በኋላ ለበሮቹ መክፈቻ የሚሆን ማስተር ኪ የሚሰሩ ሰዎች ጋር በመሄድ የጠየቁትን ተበድሮ ከፍሎ በርካታ ዓይነት ቁልፎችን ይዟል። በሱ እቅድ የጥበቃ ሠራተኞቹ እንደተኙ የተቋሙን ቢሮዎች ከፍቶ በአቅም ልክ ጠቀም ያለ ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችል ነገር አንስቶ ለመውጣት ነበር። ብዙም የስርቆት ልምድ ያልነበረው ወጣት ገሚሶቹ የጥበቃ ሠራተኞች ሲተኙ ገሚሶቹ የጥበቃ ማማቸው ላይ ተቀምጠው በንቃት እንደሚጠብቁ አላሰበም ነበር።

ልምድ አልባው ሌባ

ቀኑን ሙሉ ተኝቶ የዋለው ለታ ዳዲ ከእንቅልፉ የነቃው ከቀኑ አስር ሰዓት አካባቢ ነበር። በእለቱ ለስኬቴ ቁልፍ ርምጃ ነው ያለውን ተግባር ሊያከናውን ስለሆነ ሰውነቱን ታጥቦ በጊዜ እራቱን በልቶ ከጨለማው ጋር ሊስማማ የሚችል ዓይነት አለባበስ ለብሶ ነበር ከቤቱ የወጣው። ለሥራው ያገለገለኛል ያለውን በሙሉ በቦርሳው የሸከፈው ወጣት ለዓይን ያዝ ሲያደርግ መንገድ ጀመረ።

ቀጥሎም ተደብቆ ይከታተል የነበረበት ቦታ ላይ በማድፈጥ ለሥራው ምቹን ሰዓት መጠበቅ ጀመረ። በግምት 8፡40 አካባቢ ሲሆንና ጊቢው ረጭ ማለቱን ሲመለከት ከተደበቀበት ወጥቶ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 አይ ሲ ቲ ፓርክ ግቢ ውስጥ ወደሚገኘው ጠቀም ያለ ንብረት ይዟል ብሎ ወዳሰበው ሕንፃ ማቅናት ጀመረ። ወደቢሮዎቹ ለመግባት ትንሽ ሲቀረው የሆነ ፉጨት አይሉት ጩኸት ዓይነት ድምፅ ሰማ።

ከተደበቀበት ከለላ ስር የወጣው ወጣት ከየአቅጣጫው ያረፈበትን የፓውዛ መብራት ለማምለጥ ቢሞከርም ከሁሉም አቅጣጫ እየተንደረደሩ የሚመጡ እግሮች እየቀረቡት ሲመጡ ተስፋ በማጣት ሰሜት ኩርምት አለ።

ወትሮም የእድሌን ልሞከር ብሎ መጣጣር የማይሆንለት ወጣት ባለ ፓውዛ መብራቶቹ ሰዎች አጠገቡ እስኪደርሱ ድረስ ጭንቅላቱን ይዞ እጥፍጥፍ አለ። በቀላሉ አልፈዋለሁ ብሎ ያሰበው ነገር እንኳን በቀላሉ ሊሆን እስከ ወዲያኛው እንዲያሸልብ አደረገው።

ሌባ ተይዞ ዱላ አይጠየቅም

በግምት 8፡40 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 አይ ሲ ቲ ፓርክ ግቢ ውስጥ ነበር። ብርዱን ለመሽሽ ወደጥበቃ ማማቸው የገቡት የጥበቃ ሠራተኞች የሥራ ቦታቸው ግቢ ውስጥ ሰው መግባቱን ያወቁት። በልዩ የፉጨት መልዕክታቸው ሲጠራሩ ከቆዩ በኋላ ረጃጅም የፓውዛ መብራት እያበሩ ወደተመለከቱት ሰው ጋር ደረሱ።

ስድስቱ የጥበቃ ሠራተኞች ራሱን ይዞ እጥፍጥፍ ያለውን ወጣት ሲመለከቱ እንዴት ተደፈርን በሚል ንዴታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ለጥበቃ በያዙት የእንጨት ዱላ ወገቡን፣ ትክሻውን፣ እና እግሩን ደጋግመው በኃይል መምታት ጀመሩ። ሌባ ተይዞ ዱላ አይጠየቅም ያሉት የጥበቃ ሠራተኞች ወጣቱን ለሕግ ከማቅረብ ይልቅ ከፍርድ ውጭ ፍትሕን በእጅ የማድረግ ነጻነትን በመጠቀም ልጁ ሕይወቱን እስኪያጣ ድረስ ቀጠቀጡት።

ከፍርድ ውጭ ፍትሕን በእጅ ማድረግ ነፃነትን ለሚያሳጣ ቅጣት የሚዳርግ ሲሆን በወንጀለኛነት መሰየምንም ያስከትላል። ፍትሕ በግለሰቦች እጅ መውደቅ የለበትም። ወንጀለኞችን በሕግ እና ሥርዓት መሠረት እንዲቀጡ ወደሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት መቅረብ ይኖርባቸዋል የሚለውን የፍትህ አካላት መልዕክትን ወደጎን በመተው ራሳቸው የፈረዱትን አደረጉ።

ወጣቱ ሕይወቱ እንዳለፈ ሲረዱ ገሚሱ ለማምለጥ ሲሞከረ ገሚሱ ደግሞ ለሕገ ማመልከትን መርጫው በማድረግ ሁሉም እንደየውሳኔያቸው የወደዱትን አደረጉ። ፖሊስም ጠቆማው እንደደረሰው ነበር በአካባቢው ያገኛቸውን ተጠርጣሪዎች ወደ ሕግ፤ የሟችን አስክሬን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ድርጅቱን ማስጠበቅ የጀመረው።

የፖሊስ ምርመራ

ምሽቱን ከታሰበው የስኬት ደስታ ወደ ሀዘን የቀየረው አጋጣሚ እንደተፈጠረ በቦታው የደረሱት የፀጥታ ኃይሎች እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ፊቱ በሙሉ በደም የተሸፈነውን ወጣትና፤ በንዴትና በስጋት ያጠፉበትን መሳሪያ በእጃቸው የያዙ የጥበቃ ሠራተኞችን የተመለከቱት። ያኔ አንዱን ወደ ሆስፒታል አንዱን ደግሞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ ምርመራቸውን ይጀምራሉ።

አስክሬኑ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንስክ ሜደስንና ቶክሲድ ትምህርት ክፍል በመሄድ ምርመራ የተደረገለት ሲሆን በቁጥር የተሰጠው የአስክሬን ምርመራ እራስ ቅሉ ላይ፤ በወገቡና በእግሩ ላይ በደረሰው ጉዳት መሞቱን የሚያስረዳ መረጃ ለፖሊስ ቀርቧል።

ፖሊስም የሰው ምስክሮችን፤ የተከሳሽ የእምነት ክህደት ቃልንና የሰነድ ማስረጃ ማለትም የፎረንሲክ ምርመራውን በማጠናቀር ለፌዴራል አቃቤ ሕግ ልኳል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ ዓለሙ መለሰ፣ 2ኛ ታከለ አበራ፣ 3ኛ ብርሌው ጫኔ፣ 4ኛ ዋቁማ ልሳኑ፣ 5ኛ አስቻለው ታደለ፣ 6ኛ ደሳለኝ መንግስቴ፣ የተባሉ ተከሳሾች ካልተያዙ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን ታኅሣሥ 01 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት 8፡40 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 አይ ሲ ቲ ፓርክ ግቢ ውስጥ ሟች ለታ ዳዲን ሊሰርቅ ግቢ ውስጥ ግብቷል በሚል ምክንያት 1ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ ተከሳሾች እና አንድ ያልተያዘው ግብረ-አበራቸው ለጥበቃ በያዙት የእንጨት ዱላ ወገቡን፣ ትክሻውን፣ እና እግሩን ደጋግመው በኃይል ሲመቱት፣ 2ኛ ተከሳሽ በደንብ ደብድባችሁ ግደሉት ሲል፣ ሌላ ያልተያዘው ግብረ-አበራቸው ደግሞ የሟችን እግሮች በእንጨት ዱላ ደጋግሞ እየመታ በሽቦ ሁለት እግሮቹን ያሰረው በመሆኑ በደረሰበት ጉዳት ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በፈጸሙት የግድያ ወንጀል በዐቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች የተከሰሱበት ክስ በችሎት ተነቦላቸው የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም ያሉ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን አቅርቦ ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በሚገባ በማስረዳቱ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል። ተከሳሾችም በቀረበባቸው ክስ መሠረት የመከላከያ ምስክር አቅርበው ቢያሰሙም የዐቃቤ ሕግን ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ማስተባበል ባለመቻላቸው ይከላከሉ በተባለበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ ተሰጥቶበታል።

 ውሳኔ

 የቅጣት ውሳኔ ያሳረፈባቸው ሲሆን በዚህም በ1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 5ኛ ተከሳሾች ላይ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 4ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ላይ ደግሞ በ11 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ እንዲሁም ሁሉም ተከሳሾች ከሕዝባዊ መብቶቻቸው ለ2 ዓመት እንዲሻሩ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ሟችን ሊሰርቅ ግቢ ውስጥ ግብቷል በሚል ምክንያት ደብድባችሁ ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጋችኋል ባላቸው ተከሳሾች ላይ ክስ መስርቶባቸው ከ10 እስከ 11 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ አደረገ፡፡ እንዲሁም ፍርድ ቤቱ ሁሉም ተከሳሾች ከሕዝባዊ መብቶቻቸው ለ2 ዓመት እንዲሻሩ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን   ኅዳር 29  ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You