ኢትዮጵያ ተደጋግመው የሚነገሩ የድል ታሪኮች አሏት፡፡ ታሪክ ደግሞ የአንዲትን ሀገር ምንነት ያሳያል፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ የድል ታሪኮች በተለያየ ጊዜና አጋጣሚ ይነገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ምን አይነት ሀገር እንደሆነችም ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዓመት በዚህ ሰሞን የኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይ አጀንዳ ሆኗል፡፡ በእንዲህ አይነት አጋጣሚዎች መቼ ምን ተደረገ? የሚለውን ለማወቅ የቀደምት መሪዎቻችን ለሀገር ጉዳይ ያደረጓቸውን ትግሎች እንጠቃቅሳለን፡፡ እነዚህ ታሪኮች ለዛሬው ትውልድ የሚነግሩት እውነታ ይኖራልና እኛም የጀግኖች አባቶቻችንን ታሪክ እናስታውሳለን፡፡
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ148 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል የተካሄደውን እና በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የጉንደነት ጦርነት እናስታውሳለን፡፡ ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ የታሪክ ሁነቶችን እናስታውስ፡፡
ከ25 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 3 ቀን 1991 ዓ.ም ደራሲ፣ መምህር፣ ባለቅኔ፣ ፀሐፌ ተውኔት፣ ፖለቲከኛ፣ ገጣሚ የክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል አረፉ፡፡ በነገራችን ላይ ከበደ ሚካኤል የተለወዱት በጥቅምት ወር ውስጥ (23 ቀን 1909 ዓ.ም) ስለነበር በቅርቡ አስታውሰናቸው እንደነበርም ልብ ይሏል፡፡
ከ144 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 5 ቀን 1872 ዓ.ም ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ በሚያዚያ ወር 1860 ዓ.ም መቅደላ ላይ ከሞቱ በኋላ፣ ወደ እንግሊዝ ተወስዶ የነበረው የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ልጅ፣ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ አረፈ፡፡
156 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 6 ቀን 1860 ዓ.ም የጎጃም ገዢ የነበሩትና እና የደብረ ማርቆስ (መንቆረር) ከተማ መስራች የሆኑት ደጃዝማች ተድላ ጓሉ መርዕድ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ከ78 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 7 ቀን 1938 ዓ.ም (ኖቨምበር 16 ቀን 1945) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፤ የሳይንስና እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በእንግሊዝ ሎንደን ተመሠረተ።
ከ67 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 9 ቀን 1949 ዓ.ም የሰላሌና አካባቢው ገዢ፣ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት የዘውድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አማካሪ፣ ደራሲ እና የፍልስፍና ሊቅ የነበሩት ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ አረፉ፡፡ አሁን በዕለቱ በዝርዝር ወደምናየው የጉንደት ጦርነት እንሂድ፡፡
የታሪክ መነሻውን እናስፋው ከተባለ ከኢትዮጵያና ግብጽ ሰፊ የታሪክ ቁርኝት ጋር ይገናኛል፡፡ ግብጽ የአባይን ወንዝ መነሻ በመቆጣጠር የወንዙን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የብዙ ዘመን ፍላጎት እና ጥረቷ ነበር:: ግብጽን የመሩ ነገሥታቶችም ሰሜን ምስራቅ አፍሪካን የማቀፍና የመቆጣጠር ህልም ነበራቸው፡፡
የቀይ ባህርን የበላይነት ከኦቶማን ቱርክ የተረከበው የግብጽ ኃይል በቀጠናው የነበረውን ፍላጎት ለማሳካት ወደ ኢትዮጵያ ውስጣዊ ግዛት በሶስት አቅጣጫዎች ተመመ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው ከዘይላ ወደብ ተነስቶ ወደ ሐረር የተደረገው ዘመቻ በስኬት ሐረር ከተማን በመያዝ ቢጠናቀቅም ሁለቱ ግን የውርደት ካባ በመልበስ በሽንፈት ተደምድመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ከ148 ዓመታት በፊት የተደረገውና ዛሬ የምናስታውሰው የጉንደት ጦርነት ነው ማለት ነው፡፡
የግብጽ ጦር በጥቅምት 1868 ዓ.ም ከምጽዋ ወደብ በመነሳት ወደ መሃል ሀገር በመግባት ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ተንቀሳቀሰ:: ይህ ሊመጣ እንደሚችል በመገመት የዲፕሎማሲ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ አጼ ዮሐንስ 4ኛ የክተት አዋጅ በማሳወጅ በአካባቢው የነበሩ ባላባቶች ከእርሳቸው ጋር እንዲሰለፉ ጥሪ አደረጉ፤ በርካታ ወታደርም ማሰባሰብ ቻሉ፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ጦር ማሸነፍ ቻለ፡፡
የኦቶማን ቱርክ ግዛተ አጼ መዳከምን ያስተዋለው አልባኒያዊው ሙሀመድ ዓሊ ፓሻ የራሱን ግዛተ አጼ ከግብፅ ወደ ደቡብ እና ከሰሜን እስከ መካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ለመዘርጋት ዕቅድ ነበረው። ይሁን እንጂ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሊያደርግ ያሰበው ዘመቻ በወቅቱ አካባቢውን ይቃኙ በነበሩት በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ ኃይሎች ሳቢያ ሊሳካለት አልቻለም።
በደቡብ በኩል ከልካይ ያላገኘው ሙሀመድ ዓሊ በ1821 ሰሜን ሱዳንን ተቆጣጠረ። ይኸኔ ወደ ኢትዮጵያም ማማተር አማረው። ከ1812 እስከ 1857 በሥልጣን ላይ የቆየው ሙሐመድ ዓሊ በዋናነት ራሷን የቻለች እና ከኦቶማን ቱርኮች ነፃ የሆነች ግብፅን መሠረተ። ከዚህም ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የኦቶማን ግዛቶች የነበሩ የቀይ ባህር እና የህንድ ውቅያኖስ አዋሳኝ ጠረፎችንም በግብፅ ሥር ለማድረግ ጥሯል።
የግብፅ ሱዳንን መያዝ ተከትሎም ከኢትዮጵያ ጋር በዋድ ካልታቡ፣ በወልቃይት እና በጠገዴ አካባቢ የተደረጉ ጦርነቶች ነበሩ። ጠንከር ያሉ ጦርነቶች የተካሄዱት ግን የሙሐመድ ዓሊ የልጅ ልጅ ኬዲቭ እስማኤል ፓሻ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ነው።
የአያቱን የመስፋፋት ሀሳብ ለማሳካት፤ በአሜሪካውያን እና በአውሮፓውያን አማካሪዎች እና በቅጥረኛ ወታደሮች ታጅቦ ግዛቱን ለማስፋፋት ፈለገ። የኬዲቭ ኢስማኤል ፓሻ ግቡ በግዛት ማስፋፋት ብቻ የተገታ አልነበረም። የታሪክ ሰነዶች እንደሚያስረዱት፤ ኢትዮጵያን ለመውረር ቆርጦ የነበረው በዋናነት በጣና ሐይቅ እና በጥቁር አባይ ላይ ያነጣጠረ የግብፅን ኢምፔሪያሊስታዊ ፍላጎት ለማሳካት ነበር።
የኬዲቭ እስማኤል ታሪክ ጸሐፊ እንደገለጸው እና በስቨን ሩቢንሰን (1976) እንደተጠቀሰው «የኬዲቩን ቅኝ ግዛት ሥራ በአንድ አገላለጽ ማጠቃለል ይቻላል፤ ሁሉንም የናይል ተፋሰስ መሬት በሀገሩ ቁጥጥር ሥር በማድረግ የናይልን ወንዝ ግብፃዊ ወንዝ ማድረግ ይፈልግ ነበር» ይባላል፡፡
ይህንን ለማሳካትም ተደጋጋሚ እና ያላቋረጡ የወረራ ሙከራዎችን አድርጓል። ነገር ግን ሁሉም ሙከራዎች እየከሸፉ በግብጾች ላይ መከራና ውርደት አስከተሉ። በዋናነት ከሚጠቀሱት ሁለት ዓበይት ጦርነቶች አንዱ ይሄው የጉንደት ጦርነት ነው፡፡
ይህ በሆነ በዓመቱ ደግሞ የተካሄደው የጉራዕ ጦርነት ነው፤ አሁንም የወቅቱ ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ 4ኛ ናቸው፡፡ አጼ ዮሐንስ ግብፅ የኢትዮጵያን ግዛት መድፈሯን ለወቅቱ የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ከጦርነቱ ቀድመው በተደጋጋሚ አስታውቀው ነበር። ከዲቭ እስማኤል ግን ሲመቸው በትዕቢት ሳይመቸው ደግሞ በትሁት ዘዴ (በመቅለስለስ) የአፄ ዮሐንስ አራተኛን መልዕክትና ጥያቄ ሳይቀበል ቀረ። አውሮፓውያኑ መንግሥታትም ለንጉሰ ነገስቱ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም ነበር።
አጼ ዮሐንስ 4ኛ በ1872 ዓ.ም ወደ ንጉሠ ነገሥትነት በመጡበት ወቅት ኢትዮጵያ በሦስት አቅጣጫ በወራሪዎች የተወጠረችበት ወቅት ነበር። ይኸውም በሰሜን አቅጣጫ ግብፅና ጣሊያን፣ በስተምዕራብ ደግሞ መሀዲስት ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈጸሙበት ወቅት እንደነበር ታዬ ቦጋለ የጻፉት መራራ እውነት የተባለው የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ያስረዳል።
ንጉሡ በተለያዩ ጦር ሜዳዎች ከግብፃውያን ጋር ተፋልመዋል። በ1870ዎቹ የግብፁ ከዲቭ እስማኤል በሚያስተዳድረው የሱዳን ግዛትና በኢትዮጵያ ድንበር መካከል ግጭቶች ነበሩ። በተለይ የትግራይና ኤርትራ ግዛትን የሚዋሰኑት አካባቢዎች ስጋት የተጋረጠባቸው ነበሩ። ምፅዋም በወቅቱ በግብፅ ሥር መሆኗ አንዱ ስጋት ሆኖ ነበር፤ ምፅዋን የተቆጣጠረው የግብፅ ጦር በዘመናዊ መንገድ የታነፀ ጥብቅ ወታደራዊ ኃይል እንደነበረው ሃሮልድ ጂ.ማርኩስ የጻፉት እና ሙሉቀን ታሪኩ የተረጎሙት የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ያስረዳል።
በወቅቱ ‹‹ወርነር ሙዚንገር›› ምጽዋን ያስተዳድር ስለነበር ወደ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ነገር እንዳይገባ በመጠበቅ ከንጉሥ ዮሐንስ ሊቃጣበት የሚችለውን ጥቃት ለመከላከል ይጥር ነበር። አጼ ዮሐንስ ከነገሡ በኋላ በ1873 ወደ ጎንደር ሄደው የበጌምድርን ዕውቅና አገኙ፤ የጎጃሙን ራስ አዳል (በኋላ ንጉሥ) ተክለሃይማኖት እና የየጁውን ራስ ወሌ በማስገበር በሥራቸው አዋሉ፤ የሸዋው ምኒልክም ለመገበር ተስማሙ።
በ1875 ወደ ትግራይ ሲመለሱ ሀገሪቱን በአንድ ላይ አስተባብረው ጨርሰው እንደነበር ከላይ የጠቀስናቸው መጽሐፍት ያስረዳሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግብጻውያን ክፍተቱን ተጠቅመው ገላባትን እና የምፅዋን ደቡባዊ ግዛቶች ተቆጣጥሩ። በወቅቱ የግብፁ ካዲቭ እስማኤል ፓሻ ጀርመናዊውን ወርነር ሙዚንገርን የምስራቅ ሱዳንና የቀይ ባህር ዳርቻ አስተዳዳሪ አድርገው ሾሙ። በሙዚንገር ተተክቶም አራኪል ቤይ ኑባር ምፅዋን ማስተዳደርም ጀምሮ ነበር።
ወደ ኢትዮጵያ ለመዝለቅ ሙዚንገር የአቅጣጫ ማሳያ ካርታ፣ ጥቂት የጦር መሪዎችና ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮች በቂ መሆናቸውን ለካዲቭ እስማኤል አስረዳ። በ1875 ላይ ሁሉም ነገር ከተሟላ በኋላ ካዲቭ እስማኤል መላው የአፍሪካ ቀንድን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አራት ዘመቻዎች አዘዘ። በዘመቻዎቹ ግብፅ ሐረርንና የሱማሌን ጠረፎች ያዘች። በሙዚንገር የተመራው ዘመቻ በታጁራ በኩል አድርጎ ሸዋን እንዲቀላቀል የታለመ ነበር። ነገር ግን ጥቅምት 14 ቀን 1875 ዓ.ም ላይ በአውሳ አፋሮች በደረሰበት ጥቃት ዘመቻው ከሸፈ። አፋሮች በወቅቱ በግብጽ ጦር ላይ በሰነዘሩት ጥቃት የጦሩን አዛዥ ሙዚንገርን ጨምሮ ሁለት ሦስተኛውን የግብጽን ጦር ደመሰሱት።
ከሽንፈቱ በኋላ ግብፅ በአራኪል ቤይ ኑባር እና ኮሬን አሬንድሮፕ ፓሻ የሚመራ ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ በማዝለቅ የሠራዬንና የሀማሴን ግዛቶች ተቆጣጠረች። አፄ ዮሐንስ ጥቅምት 15 እና 16 ምሽት ላይ ወደ 70 ሺህ የሚጠጋ ጦራቸውን በማንቀሳቀስ ከመረብ ዳርቻ በምትገኘው (በዛሬዋ ኤርትራ ውስጥ) ጉንደት የተባለች ቦታ ላይ የግብፅን ጦር ደመሰሱት። በወቅቱ የግብጽ ወራሪ ሙሉ በሙሉ ሲደመሰስ የጦር መሪዎቹ አራኪልና ኢሬንድሮፕ ሳይቀር ተገደሉ።
በወቅቱ የግብጽ ጦር የታጠቀው ዘመናዊ መሣሪያ ሁሉ በኢትዮጵያው ንጉሥ እጅ ገባ። የጉንደት እና ጉራዕ ጦርነት በዓመት ልዩነት በኢትዮጵያ እና ግብፅ መካከል የተካሄደ ጦርነት ነው። አጼ ዮሐንስ 4ኛ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1876 እስከ 1885 ባሉት አስር ዓመታት ግብፅ ከያዘቻቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ጠራርጎ ለማስወጣት አልቻሉም ነበር። የምፅዋ ወደብና የዳህላክ ደሴቶች እና የሰሜኑ ግዛት በዚህ ጊዜ በግብፆች እጅ ነበሩ።
ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ በ1901 ዓ.ም የጻፉት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ መፅሐፍ « የምስር (ግብፅ) ንጉሥ ወዳጤ ዮሐንስ ብዙ ጦር ለመዋጋት ላከ … ዐጤ ዮሐንስ በቱርክ መምጣት ደንግጠው የድፍን ኢትዮጵያን ጦር ክተት አሉ። … የምስር ጦርም ጉንዳጉንዲ ደረሰና ምሽጉን አበጀ። ጦርነቱ እስማኤል ፓሻ ከፍተኛ በራስ የመተማመን ስሜትና ድል አድራጊነት ተስፋ ሰጥቶት ነበረ። ይህም የሆነው ብዙ ሰራዊቱ ይመራ የነበረው ሠፊ ወታደራዊ ስልጠና በወሰዱ አውሮፓውያን እና የአሜሪካን የጦር መኮንኖች ነበር…›› ይላሉ፡፡
ቀጥለውም ‹‹ህዳር 8 ቀን 1868 ዓ.ም አጤ ዮሐንስ የእስማኤል ባሻን ሠራዊት ገጠሙ። አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ተዋጊዎች በኮረብቶችና ምሽጎች ተሸሽገው ሲዋጉ የነበሩ ግብፃውያንን በመግደልና በመማረክ ድልን ተጎናፀፉ። ወሬ ነጋሪም ሳይቀር ቱርክን እንደ ካንቻ (በጎራዴ እንደ መጨፍጨፍ) መቱት። ባውሳ የወጣውም የምስር ጦር ያውሳው ንጉሥ መሐመድ ሃንፈሬ ወዳጅ መስሎ ፍሪዳውን ወተቱን ሰጥቶ እንግድነት ተቀብሎ አሳድሮ ሌሊት ምንም የለብን ብሎ ከተኛበት ለዘር ሳይቀር አርዶ አርዶ ጣለው ። » ሲል መጽሐፉ ያትታል።
በዘመናዊው ዘመን በሁለቱ ሀገሮች የተካሄደ ጦርነት ነው። በጦርነቱ የተገኘው ድል አፍሪካን ለመቀራመት ለሚያስቡት ነፃነቷን ጠብቃ የኖረችን ኢትዮጵያን ለመቀራመት የማይቻል መሆኑን አመላከታቸው። በአንፃሩ ራሷን የአፍሪካ ኢምፓየር አድርጋ ታስብ የነበረችው ግብፅ በጦርነቱ በደረሰባት ምጣኔ ሀብታዊና ስነ ልቦናዊ ኪሳራ ልታንሠራራ አልቻለችም፤ ከአስር ዓመታት በኋላም የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ለመሆን በቃች።
የጉንደት ጦርነት በኢትዮጵያና በግብጽ ከተደረጉ ዘመናዊ ጦርነቶች አንዱ ሲሆን ግጭቱ ለኢትዮጵያ አሻሚ ያልሆነ ድልን ያጎናጸፈ ብቻ ሳይሆን፣ ነፃነቷን አስከብራ ለዘለቀችው ኢትዮጵያ ቀጥሎ የመጣውን አፍሪካን የመቀራመት የአውሮፓውያን ዕቅድ እንዳትታሰብ ያደረጋትም ነው። በተቃራኒው፤ ከላይ እንደገለጽነው ጦርነቱ ግብፅ በኢትዮጵያ ጦር ሽንፈትንና ውርደትን መጎናጸፏን ዕዳና ፍዳ አምጥቶባታል። ከ10 ዓመት በኋላ አቅመቢስ ሆና በባርነት ቅኝ እንድትገዛ አድርጓታል ሲሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ኢምፓየር ለመሆን ያሰበችው ግብፅ በጦርነቱ በደረሰባት ምጣኔ ሀብታዊና ስነልቡናዊ ጉዳት ለእንግሊዝ ቅኝ ግዛትነት ተዳርጋለች። የግብፅ ሀሳብ የነበረው የአባይ ሸለቆን አካባቢና የጥቁር አባይን ምንጭን መያዝ ቀጥሎም የነጭ አባይን ተፋሰስ ሀገሮች መቆጣጠርና ምንጩን መያዝ ነበር። ቻድንና ጅቡቲን ጨምሮ እስከ ዑጋንዳ ያሉ ሀገሮች በማጠቃለል ለመዝለቅ እና ከአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ጋር ለመፎካከር ነበር። ሁሉም ግን በኢትዮጵያ ትግል ቅዠት ሆኖ ቀረ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ህዳር 9/2016