“የምንናገረው፣ የምንተጋው ፣ አብዝተን የምንሻው ሰላም በሀገራችን እንዲሰፍን ነው” የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

 በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያ

የተከበሩ አፈጉባኤ፤ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት፤ ክብርት ፕሬዚዳንት በመክፈቻ ንግግራችው ያቀረቧቸውን የመንግሥት ዋና ዋና የትኩረት መስኮች አስመልክቶ እና ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እሞክራለሁ። በመጀመሪያ የፖለቲካና ፀጥታ ጉዳዮች ቀጥሎ ኢኮኖሚና ዲፕሎማሲ ጉዳዮችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

የተነሱ ጥያቄዎች አንድ በአንድ ምላሽ ከመስጠት በተጨማሪ፤ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፖለቲካል አኮኖሚ ሁኔታ ከመሰረቱ መገንዘብ፤ ከስሩ መተንተን፤ የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ። እያንዳንዱ ችግር ብለን የምናነሳው ሀሳብ፤ አሁን የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን፤ ተሳስሮ የመጣ ስለሆነ እነዚህን ጉዳዮች ከስር መሰረቱ መገንዘብና ማየት ካልቻልን መፍትሄ ለማምጣት እንቸገራለን።

አንደኛው ልንግባባበት የሚገባን ዋና ጉዳይ፤ ችግሮቻችን በጋራ እኩል የምንገነዘባቸው፤ የምንረዳቸው ከሆኑ ለመፍትሄ አማራጮች፤ የተለያየ መንገድ የምንከተል ቢሆንም ጉዞአችን ወደ መፍትሄ ሊሆን ይችላል። በችግሮች ላይ የማንግባባ ከሆነ ግን የመፍትሄ አማራጩ ምንም ይሁን ምን ውጤታማ ለመሆን ያስቸግራል።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለው አብዛኛው የችግር ትንታኔ ስሜት ይጫነዋል፡፡ ስሜት የሚጫነው የችግር ትንታኔ ደግሞ አያግባባም። ስሜት “ሎጂካል” እንዳንሆን፤ ከእውነት እንድንርቅ ስለሚያደርግ ነው። ሁለተኛው የሴራ ትንታኔ ይበዛዋል፤ ሁኔታውን እንዳለ ማየት ሳይሆን፤ የሚተነተኑ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሕዳሴን እንሰራለን ሲባል፤ ኤሌክትሪክ ሀይልን ለማመንጨት ነው ማለት ሳይሆን ሌላ ሀገር ለመጉዳት ነው የሚል ትንታኔ ሴራ ነው።

የባህር በር እንፈልጋለን ሲባል ተቸግረው ነው ያስፈልጋቸዋል ሳይሆን፤ ሌላ ሀገር ላይ ጉዳት ሊያመጡ ነው የሚባሉ መሰረት የሌላቸው ትንታኔዎች ችግሩን በትክክል እንዳንገነዘብ ያደርጉናል ፤ ከእውነት ያርቁናል። እነዚህ ጉዳዮች የተስተካከለ መፍትሄ ለማምጣት ያስቸግራሉ።

በብልፅግና የሚመራውን መንግሥት በሚመለከት ባለፉት አምስት አመታት በጣም የተለያዩ ወቀሳዎችና ክሶች ስንሰማ ነበር፡፡ እንዳንዶች ደርግ ናችሁ ይሉናል፤ ብልፅግና ደርግ ነው ይላሉ። ሌሎች የለም ብልፅግና ሸኔ ነው ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሸኔ አይደለም ዘውዳዊ ነው ይላሉ። መቼም ብልፅግና በአንድ ጊዜ ሶሰቱን መሆን አይችልም። ይሄ የሚያሳየው ስሜትና ሴራ የበዛበት ስለሆነ፤ የሚወጡ የዳቦ ስሞች በራሳቸው ገላጭ መሆን አይችሉም።

እነዚህ የዳቦ ስሞች እኛን አይገልፁንም። እኛ ለየትኛውም ሰፈር ፅንፍ የወጣ ዋልታ የረገጠ እሳቤ መጠቀሚያ አንሆንም። በደቡብ ጫፍ ያለው ፅንፈኛ፤ መጠቀሚያ ማድረግ ሲሳነው ዘውዳዊ ቢለን፤ በሰሜን ጫፍ ያለው ፅንፈኛ፤ ስሜትና ፍላጎቱን ማሳካት ሲሳነው ደርግ ቢለን እኛ አይደለንም።

እንደ እነዚህ አይነት ጉዳዮች በሀገራችን ባሉ ችግሮች በጋራ ግንዛቤ እንዳንይዝ ለመፍትሄ እንዳንተጋ እንዳንተባበር እንቅፋት ይሆናሉ። እኛ እንደፓርቲ ሀገራዊ እይታ ነው ያለን። ኢትዮጵያ ከሁሉም ጫፍ ያሉ ዜጎቿ፤ በእኩል በነፃነት የሚኖሩባት፤ ሁሉ እምነት የሚከበርበት፤ ሁሉ ቋንቋ ሁሉ ባህል የሚከበርበት፤ የጎላች ፤ያማረች ፤ የበለፀገች ሀገር የምትፈጥርበትን መንገድ እናያለን። ይሄ ደግሞ በስያሜያችን ሳይሆን በህገ ደንባችን ላይ ቁልጭ ብሎ ይታያል።

አንዱ በእኛ ፓርቲ ህገ ደንብ ላይ የሚታየው ህብረ ብሄራዊ አንድነት መፍጠር፤ አካታች ዲሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት፤ በንግግራችን ሳይሆን በህገ ደንባችን፤ በደንባችን ሳይሆን በአቀፍናቸው አባላት ሁሉ የሚንፀባረቅ ነው። ለምን አልን? ያልንበት ዋና ምክንያት የኢትዮጵያ መሰረቱ እያንዳንዱ ዜጋ ድምር ውጤት ነው። ያ ዜጋ በጊዜ ሄደት ውስጥ ያዳበረው ቋንቋ ፤ያዳበረው ባህል ፤ያዳበረው እምነት ቢኖረውም ሲጀመር ሰው ነበር።

አንድ ሰው ነበር፤ ኦሮሞ የሚባል፤ ሲዋለድ ሲዋለድ ኦሮሞን የሚያክል ብሔር ፈጠረ፤ አንድ ሰው ነበር፡፡ አማራ የሚባል ወይም ከአማራ አካባቢ የተነሳ ሲዋለድ፤ ሲዋለድ አማራን ፈጠረ እንጂ ሲጀመር ጀምሮ ኦሮሞ የሚባል ብሔር ወይም አማራ የሚባል ብሔር ኖሮ አይደለም፤ በጊዜ ብዛት የአንድ ቤተሰብ ብዜት ውጤት ናቸው።

ይሄ የሚያሳየው መሰረታችን ሰው መሆኑን ነው። ያዳበርናቸውን ቋንቋ ማንነትና በጊዜ ብዛት የገነባነውን ቤተሰብም ቢሆን የመጠበቅ ሃላፊነት ያለብን ቢሆንም፤ ያ ሃላፊነት ግን ከሌሎች ጋር የሚያጋጭና የሚያባላ መሆን የለበትም፡፡

በጋራ መኖር በጋራ መበልፀግ እንችላለን የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ለዚህ ነው በቅርቡ እንደገለፅኩት የብልፅግና ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና በገቡበት ወቅት 65 ብሔር ብሔረሰቦች ሁለት ሺህ በማይሞላ ከፍተኛ አመራር ውስጥ ነበሩበት፡፡ በዚህ ደረጃ በኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉን ያቀፈ የኢትዮጵያን ስም የያዘ አይደለም፤ ሁሉን ያቀፈ ፓርቲ ኖሮ አያውቅም። አካታችና አሳታፊ፤ ሁሉን ያቀፈ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡

ይሄ ፍላጐት ነው ፤ይሄንን ደግሞ ወደ ተግባር መቀየር ከፍተኛ ትጋትና ጥረት ይጠይቃል። ብልፅግና በተለመደው መንገድ ተጉዘን የምናሳካው ጉዳይ አይደለም።

የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት የበቆሎ ቂጣ በጎመን በልቶ ማደግ ለእናንተ ብርቅ ነው እንዴ? ያደግንበት እኮ ነው። በቀን አንዴ ለመብላት መቸገር ለእኛ ለኢትዮጵያውያን፤ አዲስ ነገር ነው እንዴ? ችግር የሆነው ያንን ቀይሮ አምርቶ መብላት ነው እንጂ፤ ድህነትማ ኖርንበት እኮ! ጦርነትና ግጭት ለእኛ አዲስ ነው እንዴ? ታሪካችን በሙሉ እኮ ጦርነት ነው።

ለእኛ የቸገረን ነገር ሰላም ነው። የትኛውን መንግሥት ነው ኢትዮጵያውያን በጄ ብለው፤ መንግሥት ነው ብለው ተቀብለው አብረው ኖሩ ብላችሁ ታሪክ ብታዩ ያስቸግራል:: ሁሌም እንደዚህ አለ:: ሳይዙ ይብዛም ይነስም፤ ከእነዚህ ከለመድናቸው ጉዳዮች እንውጣ:: ንግግርን እናስቀድም፤ ሰላምን እናስቀድም፤ መትጋትን እናስቀድምና የደህንነት ታሪካችንን እጥፈት እናበጅለት ነው የእኛ ፍላጐት። ይሄ ግን ዝም ብሎ እንዲሁ አይሆንም:: አንደኛ የሀሳብ ጥራት፤ የሀሳብ ብቃት ይፈልጋል::

ሀሳብ ሲኖር ሰዎች ከግለሰብ ጋር ሳይሆን ከሀሳብ ጋር ይጨቃጨቃሉ:: አሁን ብዙ ሰው የተሻለ አማራጭ ሲያመጣ አይታይም:: የመጣን አማራጭ በግራና በቀኝ በስሜትና በተሳሳተ ስሌት መተንተን ነው የሚታያው:: ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያን ወደ ፊት አይወስድም። ሁለተኛው ሀሳብ ብቻውን በቂ አይደለም፤ ትጋት ይጠይቃል:: ቀን ከሌት መልፋት አለብን:: ካልሰራን ካልለፋን በስተቀር ለውጥ አናመጣም::

ያ ልፋትም ቀጣይነት ያለው፤ የአንድ ሰሞን ሳይሆን ሁሌ የሚደረግ መሆን አለበት:: ይህንን ስናረጋግጥ፤ ብዙዎቻችሁ እንደምትመኙት በልማቱም፣ በሰላሙም፣ በመልካም አስተዳደሩም የሚፎካከሩ ፓርቲዎች በበቂ ማሳተፍም ባህል እየሰፋ እያደገ እንደሚሄድ ተስፋ ይደረጋል።ይሄ ግን አታካችና አድካሚ ሥራ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል:: እንዲሁ ተመኝተን የምናሳካው ጉዳይ የነበረና ያጣነው ሳይሆን፤ ለዘመናት ልንጎናፀፈው ያልቻልነው እውነታ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች ያሉ ቢሆንም፤ አንዱ ችግር አባባሽ ነገር ትርክት ነው። ነጠላ ትርክት፤ የታዘበ ትርክት፤ አፍራሽ ትርክት ሀገር አይገነባም:: ሁሉ የእራሱን ሰፈር ቢያወድስ፤ የራሱን እምነት ቢያሞግስ፤ የራሱን ማንነት አጉልቶ ቢናገር፤ ሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር የሌላን የተለየ እምነትና እሳቤ መቀበል፤ የሚል እምነት በውስጡ ካላሳዳረ በስተቀረ የእኔን አብዝቼ በማጉላቴና በማድነቄ ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር አልችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ልዩ እምነቶች አሉ:: ልዩ ልዩ ቋንቋዎች አሉ፤ እሳቤዎች አሉ፤ እነዚህን ማክበር ያስፈልጋል።

እኛ የተለየን አይደለንም:: በህንድ ሀገር እርስ በእርስ ሊደማመጡ የማይችሉ ከ120 በላይ ቋንቋዎች አሉ:: ለዘመናት ይሄ ልዩነት ሲያስቸግራቸው ኖረው፤ አሁን ሰልጥነው አድገው፤ በዓለም ላይ አምስተኛውን ኢኮኖሚ መገንባት ችለው ከድህነት ለመውጣት የሚፍጨረጨሩት፤ ‹‹ይሄንን ልዩነት ጠላት፤ ይሄንን ልዩነት ሌሎች መባያ አድርገውታል:: ልንባላ አይገባም፤ የሚያለያየንን ነገር ይዘን፤ ለጋራ ሀገር ብንተጋ ይሻላል::›› የሚል እምነት በመያዛቸው ነው። እኛም በአሉታዊ ትርክት ሀገር እንደማይገነባ፣ በአንድ ሰፈር ትርክት ሀገር እንደማይገነባ ማመንና አብሮነትን እና አቃፊነትን መቀበል ያስፈልጋል የሚል እምነት አለን።

ታላቅ ትርክት ሀገራዊ ትርክት ይሰበስባል:: ከዛ የሚቃረነው ነጠላ ትርክት ደግሞ ይለያያናል:: ስንለያይ አቅማችን ያንሳል፤ ስንለያይ እንበተናለን እንጎዳለን ከዛ የሚያወጣንን የሚያሰባስበንን ነገር እናምጣ ነው። ለምሳሌ ዓባይ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ አስራ ሁለት ገደማ መጋቢ ጅረቶች አሉት:: አንድ ወንዝ ተነስቶ አይደለም ዓባይ የሚሆነው፤ በጣም ብዙ መጋቢዎችን ይዞ ነው ተደምሮ ዓባይ የሚሆነው።

እያንዳንዱ ጅረት አንድ አይነት ሚነራል የለውም:: አንድ አይነት ሀይል የለውም:: አንድ አይነት ከለርም የለውም:: ካርቱም ላይ ሄዳችሁ ብታዩት፤ ከጣና የሚነሳው ዓባይና ከቪክቶሪያ ሀይቅ የሚነሳው ዓባይ አንድ አይነት ከለር የላቸውም ፤ ስማቸውም እንደ ከለራቸው ይለያያል:: ካርቱም ተደምረው ወደ ግብጽ ሲሄዱ ደግሞ አንድ ዓባይ ይሆናሉ:: አንድ ሀይል የላቸውም፤ ከአንድ ሰፈር አልተነሱም፤ መልካቸው ይለያያል፤ ሚንራላቸው ይለያያል ማለት ግን ውሃ አይደሉም ማለት አይደለም::ውሃ ናቸው ፤ ዓባይ ናቸው::

ከየትኛውም ሰፈር ብንነሳ ቋንቋችንም የተለያየ ቢሆን “አልቲሜትሊ” ሰው ነን:: ሰው መሆናችንን አያስቀረውም፤ የምንገነባው ትርክት ለሰው ልጅ ክብር ያለው፤ የምንገነባው ትርክት የሰው ልጅን የህይወት ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ቢሆን ይሻላል ፤ያዋጣናል :: ያቃተን ምንድነው አሁን? አንደኛው ዋልታ የረገጠ እሳቤ፤ ሊሳካ የማይችል ሊተገበር፤ የማይችል ሊያቀራርብ የማይችል፤ እሳቤዎች ማስፋት፤ እነዚህ ጎጂ ናቸው:: ዋልታ ከሚረግጥ እሳቤ ሚዛን ወደ ጠበቀ እሳቤ መምጣት ያስፈልጋል::

ሁለተኛው አላካኪነት ነው:: ኑሮ ውድነት አለ ማላከክ፤ ግጭት አለ ማላከክ ፣ ያልተሰራ ጉዳይ አለ ማላከክ፤ በማላከክ መፍትሄ አናመጣም:: ሃላፊነት ወስደን በመስራት ነው የምናመጣው :: ሰሞኑን ባያችሁት ስራ እንደገለፃችሁት፤ ቀን ከለሌት የሚተጉ ሰዎች አሉ:: እነሱ ቢያላክኩ የበጀት ችግር አለባቸው:: ፓርላማ አልተረዳቸውም ሰው ባልተገባ መንገድ የሚናገርለት ፕሮጀክት ነው:: አንሰራም ቢሉ እና ቢያሳብቡ አይሆንም፤ በማላከክ ውጤት አይመጣም፤ ሀላፊነት መውሰድ ያስፈልጋል ::

ሶስተኛው ችግር ጊዜ ታካኪነት ነው:: የተሰጠንን ጊዜ ተገንዝቦ ከመጠቀም ይልቅ ወይም ትላንትና ላይ መጮህ ወይም ነገ ላይ መጮህ፤ ዛሬን ሳንኖር እንድናልፍ የሚያደርጉ በጊዜ የተንተራሱ ግን ደግሞ ወደ ውጤት የማይወስዱ ናቸው:: አራተኛው አደገኛ ነገር አቅላይነት ነው:: ሁሉን ነገር ማቅለል፤ ህዳሴ ቀላል ነው፤ ሲሠራ:: ካልተሰራ ግን መከራ ነው:: የምንናገራቸው የቀለሉብን ነገሮች በብዙ መስዋዕትነትና ትጋት እንደሚመጡ አለማሰብ ነው::

እነዚህን ጉዳዮች ብናስተካክል፤ ትርክታችን የተስተካከለ ቢሆን ይጠቅማል:: የሚል እምነት ነው የኛ መንግሥት ያለው:: ለዛም ነው ትርክቱ አሰባሳቢ፤ የጋራ የሆነ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ ይሁን፤ ያ ባይሆንስ አይሳካም፤ አያዋጣም ወደ ሌላ አይወስድም:: የእኛ ሳያንስ ልጆቻችንን እንዲቸገሩ ያደርጋል::የደህንነት ችግር እኛ ላይ እንዲያበቃ ከፈለግን አሰባሳቢ ተረክን መፍጠር፤ መገንባትና ለዚያም ታምነን መስራት ያስፈልጋል:: ለኢትዮጵያም የሚጠቅመው እሱ ነው ::

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ብሔራዊነትና አርበኝነትን አስመልክቶ የተነሳው ጥያቄ ብሄራዊነት ምንድነው? ከዚህ ቀደም ከምናውቀው ይለያል ወይ ለተባለው ያው በዚሁ በምናውቀው ህገ-መንግስት አንቀፅ 69 ፕሬዚዳንቱ ወይም ፕሬዚዳንቷ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ናቸው ይላል:: ምን ማለት ነው ርዕሰ ብሄር ማለት? ወይም ደግሞ እናንተ ያወጣችሁት አዋጅ ብሔራዊ ባንክ ሌሎች ባንኮችን ይቆጣጠራል ይላል:: በቃ እሱ ማለት ነው::

በብልፅግና ህገ-ደንብ ላይ በግልፅ እንዳመላከትነው ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ መገንባት እንፈልጋለን:: ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ግን ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያዎች ማለት አይጠበቅብንም:: ኢትዮጵያ በሚል ስያሜ ውስጥ እነዚያ ብሔሮች ሊከበሩ ፤ባህላቸውን ቋንቋቸውን ሊያዳብሩ ይችላሉ:: እና ብሔራዊ ስንል ህብረ ብሔራዊነትን ረስተን አይደለም:: ሁሌም እንደምናምነው ልዩ ልዩ ቋንቋ ፣ ልዩ ልዩ እሳቤ ፣ ልዩ ልዩ የንግግር ዘዬ ባህል ያለባት ሀገር ናት:: ሁሉን ተቀብላ አምና አቻችላ፤ በሰላም መኖርና ማደግ ያለባት ሀገር ናት – ኢትዮጵያ:: ብሔራዊ ስንል ይሄንን ሰብስቦ የያዘ ለማለት እንጂ ህብረ ብሔራዊነትን ያልተቀበለ ማለት አይደለም::

ለነገሩ ብሔር ብሔራዊ የሚለውን ነገር ፖለቲካል “ጃርገንስ” ከቃላት ብያኔ ተመዘው የሚነገሩ ስለሆነ፤ ይሄንን ቃላት እንዴት ተተረጎመ ኢትዮጵያ ውስጥ ብለን መዝገበ-ቃላት ብናገላብጥ ብዙ ስጋት የሚጥል ነገር አናይም:: ለምሳሌ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ብሔር ብሔራዊነትን በሚመለከት በተረጎሙት መዝገበ -ቃላት ላይ ብሔር ማለት መንደር፣ ከተማ፣ ከባቢ፣ ምድር፣ ሀገር ብለው ተርጉመው እንደገና እሳቸው ብሔር ማለት ወገን፣ ነገድ፣ ህዝብ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ብለውታል:: ትርጓሜው ይኸው ነው:: ምድርም ነው ሰውም ነው::

ስንፈልግ አንድ አካባቢ እንወስነዋለን ስንፈልግ እናሰፋዋለን:: አንዳንዴ በአንድ ቋንቋ እናጥረዋለን:: አንዳንዴ ከቋንቋዎችም ሊያልፍ ይችላል:: ከዚህ ያለፈ ትርጓሜ አልተቀመጠለትም:: እኛ ብሔራዊነት ያልነው፤ የጋራ የሆነ፤ የወል የሆነ፤ ሁሉን የሚያቅፍ የማይገፋ ትርክት እንገንባ ነው:: የአንድ ብሔር ማለታችን አይደለም:: ወይም እንደሚጠረጠረው ዘውዳዊ ከመሆን የመጣ አይደለም:: እንደዛ አይደለም:: እና በዛው መንገድ መረዳት ጠቃሚ የሚሆን ይመስለኛል:: ታሪክን በሚመለከት በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት ታሪክ ሞያዊ ዘርፍ ነው::

ሁሉም ሰው ታሪክን እኩል አይረዳውም፤ እኩል አይናገረውም፤ እኩል አይፅፈውም:: በዚያ ዘርፍ የተማሩ እንዴት ታሪክ እንደሚነገር፤ እንዴት እንደሚመረመር የሚያውቁ ሰዎች አሉ:: ያንን ጉዳይ ለሞያተኞች መተው ጠቃሚ ይሆናል:: ግን ለሁላችን በሚገባን መንገድ ባለፈው መስከረም 28 ክብርት ፕሬዚዳንት ንግግር ሲያደርጉ፤ ‹‹ሶስት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ጠቆር ያለ ልብስ ለብሰው፤ ንግግራቸውን ጀምረው፤ 30 ደቂቃ ተናገሩ::›› ብሎ አንድ ሰው ከእናንተ መካከል ቢፅፍ፤ አንደኛው ደግሞ ‹‹የለም 3 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ነው የጀመሩት አስታውሳለሁኝ፤ የለበሱት ደግሞ ጥቁር ሳይሆን ነጭ ነው፤ ንግግራቸውም›› ብሎ ሊፅፍ ይችላል::

የሚመራመረው ሰውዬ ስለ አንድ ጉዳይ ስንት ሰው ፃፈ? ስንት ሰው ተናገረ? ብሎ ካገላበጠ (ቲሪያንጉሌት) ካደረገ በኋላ፤ ለእውነት የቀረበውን ነገር ነው መዞ የሚያወጣው እንጂ፤ እውነት አንዳለ እንድ እና ያው የሆነን ነገር ማስቀመጥ አይቻልም:: ምክንያቱም ታሪክ ማለት የዛሬ መቶ፣ ሁለት መቶ እና ሶስት መቶ ዓመት የሆነ ነገር ነው:: ያላየነው ያልሰማነው ነገር ነው:: እንደዛሬው ቪዲዮ የለውም ቪዲዮ እንዳናመሳክር፤ ይህንን ጉዳይ ሞያተኞች ባላቸው ዕውቀት ቢሠሩት መልካም ይሆናል::

ለእኛ ግን በቀለለው መንገድ ለመገንዘብ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ብቻ አይደለም ያላት:: አሁን አየሩን የያዘው ፖለቲካዊ ታሪካችን ነው:: ማህበራዊ ታሪክም አለ:: በጋራ የኖርንበት፤ በጋራ የተዋጋንበት፤ ነፃ ሃገር የፈጠርንበት ለሌሎች ምሳሌ የሆንበት በጣም በርካታ ታሪክ አለን:: በእምነት በባህል ሊነገሩ የሚችሉ በርካታ ነገሮች ስላሉ:: ፖለቲካዊ ነገር ብቻ ላይ አጉልተን፤ ሌላውን ታሪክ እንዳንደፈጥጥ ሚዛን መጠበቅ ያስፈልጋል::

ሚዛን ያልጠበቀ ነገን የማይዋጅ፤ ምክንያታዊ (ሎጂካል) ያልሆነ፤ እንዲሁ ዝም ብሎ የሚነገር ከሆነ ጥፋት ነው የሚያመጣው:: ሚዛን ምን ማለት ነው:: አንድ ሰው ተነስቶ ከዛሬ ጀምሮ ምግብ ብቻ ነው የምበላው፤ ውሃ አልጠጣም የሚያስፈልገኝ ምግብ ብቻ ነው ቢል ምግብ መብላት ብቻውን ሰውየውን ጤነኛ አያደርገውም:: የለም ምግብ አልበላም፤ የምጠጣው ውሃ ብቻ ነው ምግብ አያስፈልገኝም፤ ቢልም እንዲሁ ሙሉ አያደርገውም::

ዝም ብዬ እተኛለሁ እንቅልፍ ብቻ ያስፈልገኛል ቢል እንቅልፍ ራሱ አድካሚ ነው:: የበዛ እንደሆነ፤ እንቅልፍን በሚዛን፤ ሥራን በሚዛን፤ ምግብን በሚዛን ፤ መጠጥን በሚዛን ለአንድ ሰው ጤነኛ አካል አስፈላጊ እንደሆነው ሁሉ፤ ታሪክን የምናይበት መነፅርም እንደዚሁ ሚዛን ያለው እና ነገን የሚዋጅ ለልጆቻችን መልካም አገር የሚጥል መሆን ይኖርበታል:: ያ ከሆነ ሁላችንንም ተጠቃሚ ያደርገናል::

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአማራና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ለተባለው፤ እንግዲህ በአማራና በኦሮሚያ የሚለው ገላጭ መሆኑን እርግጠኛ አይደለሁም:: በየሰፈሩ በአማራ ውስጥም በኦሮሚያ ውስጥም ፤ በአማራና በኦሮሚያ አካባቢ፤ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ይታያሉ:: እነዚህ ግጭቶች ሰው የሚገድሉ፤ ንብረት የሚያወድሙ፤ ከጉዟችን የሚያዘገዩ አላስፈላጊ ነገሮች ናቸው::

የእኛ መሻት ሁልጊዜ ሰላም ነው:: የምንናገረው፣ የምንተጋው አብዝተን የምንሻው ሰላም በአገራችን እንዲሰፍን ነው:: እስከ ዛሬ ድረስ ባለፉት አምስት ዓመታት በእኛ መሻት፣ በእኛ ዕቅድ አንድም ጦርነት አልተካሔደም:: ይሔ እውነት ነው:: አንድም ግጭት እኛ አስበን እና አቅደን አናውቅም:: ያም ይነሳል በሶስት ወር እገለብጣቸዋለሁ ይላል:: ያም ይነሳል ሁለት ወር ይበቃኛል ይላል:: ያም ይነሳል ይሄ መንግሥት በቀላሉ በሃይል ልገለብጠው እችላለሁ ይላል::

ያኔ መቼም አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆነን እንከላከልላታለን እንጂ፤ እስካሁን ኢንሼቲቭ ወስደን ለማጥቃት ሙከራ አድርገን አናውቅም:: ለምን? እኛ ኢትዮጵያ አትቀልብንም:: ኢትዮጵያን ከውስጥ ስናያት በምትቀልብን ደረጃ አይደለችም:: ብዙዎች አክብደው ያዩዋታል::

እኛ ኢትዮጵያ ቀላብን በግራ በቀኝ ቦጨቅ ቦጨቅ ስናደርጋት እና ስንከፋፍታት እኛ በቀደድነው፤ እጃቸውን የሚሰዱ ያቺን ብጫቂ ቀዳዳ የሚያሰፉ፤ ለማስፋት ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች ይጠቀሙበታል::” ውሻ በቀደደው ጅብ ” እንደሚባለው ማለት ነው። ሳታንስብን ሳንቦጫጭቃት ብንጠግናት፤ ብንሰራላት ብናበለፅጋት ግን ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ስመጥር ሀገራት መሆን የሚያስችል ብቃት አላት። ለዚህም ሀገራችንን ከሚያዳክም፤ ህዝባችንን ከሚያውክ እርስ በእርስ ከሚያገዳድል ነገር መጠበቅ ያስፈልጋል።

አማራና ኦሮሞ በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት ቢፈልጉም ባይፈልጉም በሰላም ለመኖር ያላቸው ምርጫ አንድ ብቻ ነው። የአንድ አባት ልጆች የአንድ ሀገር ዜጎች ወንድማማች መሆናቸውን አውቀው፤ በተከባበረ አብሮ ለመኖር በሚያስችል ማንነት መጓዝ ብቻ ነው። ከዛ ውጪ ያለው አማራጭ ምንም ፋይዳም የለው፤ ወደ ውጤትም አይወስድም።

ሌሎቹም ብሔሮችም ቢሆኑ፤ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በሰላም በፍቅር በትብብር ከመኖር ውጪ ያለው አማራጭ አዋጭ አይደለም። በነገራችን ላይ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በአንድም ሀገር የሆኑ ሀይሎች ተደራጅተው ታጥቀው ተዋግተው መንግሥትን አሸንፈው አያውቁም። እነዚህ የሚታገሉ ሰዎች ይህንን ታሪክ በደንብ የሚያውቁ አይመሰለኝም።

አሁን በሚደረጉ ትግሎች ግራና ቀኝ መንግሥት ማሸነፍ ይከብዳል። ምን መሰላችሁ? የደርግ መንግሥት ሊወድቅ አካባቢ በመጨረሻው አመታት ገደማ የኢትዮጵያ ጂዲፒ አስር ሚሊየን ገደማ ነው። ደርግ ሲመጣ በጣም በጣም ዝቅተኛ ነው፤ ሊወድቅ ገደማ ደግሞ አስር ሚሊየን ገደማ ነው። ስለዚህ ያኔ አንድ ሚሊየን ዶላር ለታጠቁ ሃይሎች የሚረዳ አካል ከተገኘ በጣም ብዙ ብር ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ካፒታል ፕሮጀክቷ ከአስር ቢሊየን ዶላር በላይ ነው። ከቸገራት በህልውናዋ ከመጣ እነዛን ፕሮጀክቶች አዘግይታ እራሷን ትከላከላለች ማለት ነው። አስር ቢሊየን ዶላር ታጥቀው ለሚታገሉ መርዳት ቀርቶ ማበደር የሚችል አንድ መንግሥት ዓለም ላይ የለም። አንድ ፤ መቶ ሀምሳ ክላሽ ይኖራል :: አስር ቢለየን ዶላር ገና ለገና ነገ መንግሥት ትሆናለህና አሁን ላበድርህ የሚል አንድ መንግሥት የለም። እንኳን ለታጠቀው ለመንግሥት የሚሰጠው የለም። የአቅም ልዩነት አለ ማለት ነው።

ነገር ግን በብዙ ሀገራት እንደሚታየው ባደጉትም ጭምር፤ የታጠቁ ሀይሎች አንዳንዴ ሞል ውስጥ ሰው ይገድላሉ:: ሌላ ጊዜ ትምህርት ቤት ሰው ይገድላሉ:: አንዳንድ ከተማ ያሸብረሉ:: ይሄ በብዙ ሀገራት አለ:: እኛም ሀገር ሊኖር ይችላል። ያ ማለት ግን ወደ ድል አይወስድም:: ለኢትዮጵያውያን ያለኝ ምክር በዶላር ከመገዳደል በሃሳብ መገዳደር ይሻላል። ከመገዳደል መገዳደር፤ ለምን ጥይት ዶላር ነው።

የውጭ ምንዛሬ የለም እንላለን፤ ስንታኩስ እንውላለን:: ውጭ ምንዛሬ የለም፤ እንላለን ክላሽ በኮንትሮባንድ ስንሸምት እንውላለን:: ይሄ የሀገር ኢኮኖሚ የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን፤ ሰው የሚገድል ብቻ ሳይሆን ወደ ፊትም ቀና እንዳንል የሚያደርገን፤ ከሁሉ በላይ ግን በዚህ ዓላማ ውስጥ የተሰበሰቡ ሰዎች ምንም ነገር ማሳካት እንዲችሉ አያደርጋቸውም። ስለዚህ ከዚህ ተቆጥቦ ወደ ሰላም፣ ወደ ንግግር፣ ወደ ውይይት መሄዱን እንደ ትልቅ አማራጭ ነው እኛ የሚንወስደው:: የእኛ ሀሳብ ግልፅ ነው። በተደጋጋሚ እኮ ብለነዋል፤ የእኛ ሀሳብ ግንቡን እናፍርስ ድልድይ እንገንባ ነው።

ግንብ አለ፤ እናውቃለን በብሔሮች መካከል ግንቦች እንደነበሩ እናውቃለን:: እነርሱን እናፍርስና ድልድይ እንገንባ ነው። የእኛ ሀሳብ በፍቅር እንደመር ፤በይቅርታ እንሻገር ነው። ይቅር የሚያባብለን ጉዳይ የለም ሳይሆን፡ ይቅር ተባብለን እንሻገር:: ፍቅር ስለሚሻል ከጥላቻ፤ እንደመር:: ገዳዩን ሰይፍ እንቀይረው፤ ገዳዩን ሰይፍ ወደ ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር እንቀይረው:: የፃፍናው የተናገርነው ልንተገብር የሞከርነው ይሄንን ብቻ ነው። ከፃፍነው ፤ከተናገርነው ፤ከተወያያንበት ከሰራንበት ጉዳይ ውጭ የሚነገሩ ጉዳዮች፤ እነርሱ የደቦ ስሞች ናቸው፤ ስሞች አይደሉም።

የእኛ መሻት ይሄ ነው። ሰላም ነው፤ ይቅርታ ነው፤ ፍቅር እና አብሮነት ነው። በጋራ ልማትና ብልፅግናን ማምጣት ነው። በተለያየ ቦታ ክላሽ አንግበው፤ በየጫካው ላሉ ወንድሞቻችን እባካችሁን ሰላምን ናቅ አናድርጋት። ስላምን እንጠብቃት፤ የምትሻለው እሷ ናት ነው መልሱ። ለምሳሌ ኦሮሚያ አካባቢ ጥያቄ አለ:: ኦሮሚያ አካባቢ ችግር አለ:: ኦሮሚያ አካባቢ ያለውን ችግር ኦፌኮ የሚባል ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ ከተማ ውስጥ ተቀምጦ በንግግር እታገላለሁ ካለ ሸኔን ከኦፌኮ ምን ይለየዋል?

ኦፌኮን በሰላም የሚያታግል አገር፤ ሸኔን በሰላም የማያታግል ሊሆን አይችልም:: ወይም በአማራ አካባቢ ችግር አለ፤ አብን የሚባል ድርጅት በሰላማዊ መንገድ መታገል የሚችል ከሆነ፤ ከዚያ ውጭ አማራጭ አለ ብለው የሚያስቡ ሰዎች ልክ እንደእነሱ የሰላሙን ምርጫ ለመከተል የሚከለክላቸው ነገር የለም:: አንደኛው ከፍ ያለ አማራ፤ ሌላኛውን ያነሰ አማራ፤ ወይም ከፍ ያለ ኦሮሞ ዝቅ ያለ ኦሮሞ የሚያደርገው ጉዳይ የለም:: ጥያቄ አለ፡ ሊኖር ይችላል:: ያን ጥያቄ ግን በሰላማዊ መንገድ መታገል እንችላለን::

ጠብ መንጃ ማውረድና ሃሳብ መንጃ የሆነውን መያዝ ያስፈልጋል:: ጠብ መንጃ ከጅምሩ ከነስያሜው ስንሸከመው ኃይል ሊሰማን የሚያደርግ፤ ጠብን እንድናበረታታ የሚያደርግ፤ በተለይ ሳንሰለጥንበት ሳናቅበት ከሆነ ደግሞ ወደ ጥፋት ይወስዳል:: ሃሳብ እንድንነዳ ፤ሃሳብ እንድናሸራሽር የሚያደርገንን መያዙ የተሻለ ጥቅም ያለው ይመስለኛል:: ለሁሉም ያለው መልዕክት እሱ ነው:: ያው ሆኖ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ አለን፣ ንግግር እንፈልጋለን፤ ላሉት ወንድሜ በማንኛውም ሰዓት በሰላማዊ መንገድ ንግግር ካላችሁ መድረኩ ክፍት ነው::

የጋራ ምክር ቤትም አለን:: ከዚያም በሻገር ፍላጎት ካለ ለመወያየት ምንም የሚያግደን ነገር የለም:: ነገር ግን ከፖሊሲ ጋር ተያይዞ ለተነሳው፤ ያው የእኛ መንግሥት እንደምታውቁት ቢያንስ የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የካቢኒ አባላት ሆነው በሁሉም ሕጎቻችን ፣አዋጆቻችን ፣ ፖሊሲዎቻችን ከእኛ ጋር ይወያያሉ:: በኢትዮጵያ ታሪክ ተቃዋሚን አስቀምጦ ፖሊሲውን አዋጁን የሚነጋገር መንግሥት የመጀመሪያው እኛ ነን:: የመጨረሻ እንደማንሆን ተስፋ እናደርጋለን:: የመጀመሪያ ግን እኛ ነን ::

ሥልጠናዎቻችን በገሀድ የምናሳይ፤ ንግግሮቻችንን በገሀድ የምናሳይ ውይይቶቻችንን በገሀድ የምናሳይ፤ የሚደበቅ ነገር የለንም::

 በሴራ አናምንም ብለን ስለምንሠራ የሚጎድል ነገር ካለ፤ እያከልን እየጨመርን እንሔድ እንደሆነ እንጂ ከፖሊሲ አንፃር ብዙ የሚሸፈን ነገር ያለ አይመስለኝም:: ነገር ግን ተጨማሪ ውይይት ያስፈልጋል ከተባለ በማንኛውም ጊዜ ማድረግ ይቻላል::

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁላችሁም እንደምታስታውሱት ዋነኛ ዓላማው ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ነው:: በጉልበት የክልል መንግሥት እናፈርሳለን ብለው የተነሱ ኃይሎች ነበሩ፤ የክልሉ መንግሥት የራሱን ሙከራ አድርጎ ሳይሳካለት ሲቀር በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት ይህ ጉዳይ የፌዴራል መንግሥቱ ገብቶ ሊያግዝ ይገባል የሚል ጥያቄ ቀርቦ በዚያው አግባብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በእናንተ ጸደቋል:: ይሄም አንፃራዊ ሰላም አምጥቷል:: ይሄም የክልሉን መንግሥት ከመፍረስ አደጋ ታድጓል:: ነገር ግን የተሟላ ሰላም አልመጣም ::

ተጨማሪ ውይይት ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል:: ያኔ የነበረው ስጋት ተቀልብሷል:: የተሟላ ሰላም እንዲመጣ ግን ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሕዝብ ጥያቄ፤ ሕዝቡ እናንተን ወዶ እናንተን ጠብቆ፤ ሕዝቡ የሚባል ጉዳይ በጣም በተደጋጋሚ ይነሳል:: በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብልፅግናን አምኖ መምረጡ በጣም ትክክለኛ ምርጫ ነው:: የጠራ ሃሳብና ተግባር ያለው ፓርቲ ስለሆነ፤ በዚያም ፓርቲው እንደማያሳፍረው እርግጠኛ ነኝ:: ለሕዝባችን የገባነውን ቃል በከፍተኛ ትጋት እንሠራለን የሚል እምነት ነው ያለን::

ነገር ግን የሕዝብ ጥያቄ የማይል የኢትዮጵያ ውስጥ ማን አለ:: ትልቁም ትንሹም፣ የተደፋች ውሃ አቃንቶ የሚያውቀውም የማያቀውም፤ ቀበሌ አስተዳደሩ የሚያውቀውም የማያውቀውም፤ አንድ ፕሮጀክት ሠርቶ የሚያውቀውም የማያውቀውም ሁሉም ነው ሕዝብ የሚለው:: መቼም ይሄ ሕዝብ ‹‹መቼ ነው የጠየቅኩት ይሄን ጥያቄ?›› ብሎ ራሱ ወጥቶ መከላከል የሚችልበት ጊዜ እስኪመጣ ሁላችንም ያው ሕዝቡ ሕዝቡ እንላለን:: የሕዝቡ ጥያቄ ግልፅ ነው:: ሰላም ይፈልጋል:: ሁሉ ጉዳይ በውይይት እንዲፈታ ይፈልጋል:: እኛም ይሄን እንፈልጋለን::

ሕዝቡ ልማት ይፈልጋል፤ ድህነት እንዲቀንስ ይፈልጋል:: ኢትዮጵያ ከችግር እንድትገላገል ይፈልጋል:: ዴሞክራሲ እንዲገነባ ይፈልጋል:: ተቋማት እንዲገነቡ ይፈልጋል :: ለምን? ሕዝብ ማለት የቀጣይነት ምልክት ነው:: ልጆች አሉት ለልጆቹ የተሻለ ሀገር ይፈልጋል:: ይሄን የሚያደርግ ሁሉ የሕዝብን ያደመጠ ከዚህ በተቃራኒው የሚሄድ ደግሞ የሕዝብን ፍላጎት ናቅ ያደረገ ነው ማለት ነው:: ይሄ ጥቅል ዕውቀት ነው:: እያንዳንዱን ሰው ጠይቀን ምን ትፈልጋለህ? ባላልንበት ሁኔታ ሕዝቡ ያን ይላል ይሄን ይላል የሚለው ነገር ያስቸግራል:: ምክንያቱም እኛ ሕዝቡን እናገኘዋለን ፤እናወያየዋለን፣ እንጎበኘዋለን፤ ምን ስሜት እንዳለው እናውቃለን::

ከብዙ ሰው በተሻለ እናቃለን፤ ከብዙ ሰው በተሻለ ለሕዝባችን ቅርብ ነን:: እኛም ግምት አለን:: ሌሎቻችሁም ግምት አላችሁ:: ግን ለሁለታችን የጋራ የሆነው ሕዝቡ፣ ሰላም ዴሞክራሲና ልማት ይፈልጋል:: እዚህ ጋር ብንሠራ ጠቃሚ የሚሆን ይመስለኛል:: ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ ግንዛቤ መያዝ የሚያስፈልገው፤ አንድ ከባቢ ላይ የሚነሳ ጥያቄ ለእዚያ ከባቢ ምላሽ ቢሰጥ ሌላ ከባቢ ደግሞ ጥያቄ ይሆናል ብለን ማሰብ አለብን::

ለምሳሌ ኦሮሚያ መገንጠል አለባት፤ የኦሮሚያ ሪፐብሊክ መፈጠር አለበት:: በእነዚህና በዚያ ምክንያት ብሎ የሚያምን አንድ ስብስብ ቢኖር፤ ለእዚያ ስብስብ ምላሽ መስጠት ማለት ለተቀረው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥያቄ አይፈጥርም ማለት አይደለም:: የተቀረው ኢትዮጵያዊ ደግሞ እንዴት እንዲህ ይደረጋል? ሀገራችንን ለምን ትበትናላችሁ? የሚል ጥያቄ አለው ማለት ነው::

ለአንዱ መልስ ሲሆን ለሌላው ጥያቄ ነው የሚሆነው ማለት ነው:: ለአንዱ ስኬት ሲሆን ሌላውን በሰፈር ከሆነ ሊያስከፋው ይችላል :: ያ እንዳይሆን ሀገራዊ እይታ መፍጠር ያስፈልጋል:: የሚነሱ ማንኛውም ጥያቄዎች የሆነ አካባቢን የሚያስደስቱ ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያ ሁሉ የሚጠቅሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ::

ከእኛ አንፃር በኢትዮጵያ በጣም በርካታ ጥያቄዎች የነበሩ ቢሆንም፤ ብልፅግና ይወቀስ ከሆነ በድፍረት ነው:: ሊመልስ ያልሞከረው ጥያቄ የለም:: ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ላይ በጣም ከፍተኛ ጥያቄዎች የልማት ፍላጎቶች አሉ:: እነሱን ለመመለስ የደፈረበት እና የሄደበት መንገድ፤ ሌላው ቀርቶ ሕዳሴን የነካካበት መንገድ ራሱ ድፍረት ነው:: ሕዳሴን መነካካት ብዙ ጣጣ አምጥቶብናል በኋላ፤ ባንነካካው አንጨርሰውም እናውቃለን:: መነካካት ግን ቀላል አልነበረም::

በፋይናንሻል ሴክተር ፖሊሲ ሊሆን ይችላል:: በግብርና ሊሆን ይችላል በማንኛውም ኢኮኖሚ ጥያቄ ላይ ለመመለስ የነበረው ድፍረት፤ ፖለቲካሊ ተቃዋሚዎች ኑ፤ የካቢኔ አባላት ሁኑ አብረን እንስራ ማንም ብሎ አያውቅም:: እንደዚያ ማለታችን ደፋር ነን:: ሲበዛ ለምን ያ መሰባሰብ ያስተምራል ብለን ስለምናስብ ፤ ከማህበራዊም አንፃር በሀይማኖት ጉዳይ በትምህርት ጉዳይ የደፈርናቸው ፖሊሲዎች በጣም ሰፋፊ ናቸው:: በርካታ ጥያቄ ተመልሷል:: ለምሳሌ ደቡብ ላይ የነበሩ ሰፋፊ ጥያቄዎች ተመልሰዋል :: ያ ተመለሰ ማለት ደቡብ ጥያቄ የለውም ማለት አይደለም::

የክልልነት ጥያቄ ተመለሰ እንጂ የመንገድ ጥያቄ ይቀጥላል:: የመንገድ ደግሞ ሲመለስ የጤና ይቀጥላል:: ስለዚህ ሰው በጥያቄ የተሞላ ነው:: አንዱ ሲመለስ አዲስ እየጠየቀ ይቀጥላል:: አሁን ምናልባት አንዳንዶችን ግር የሚያሰኘው፤ በአማራ እና በትግራይ ጥያቄ የተነሳባቸው ኤሪያዎች ምላሽ አልተሰጣቸውም የሚል ጉዳይ በስፋት ይነሳል:: እኛ ምላሽ እየሠጠን ነው ብለን እናምናለን::

ችግሩን አውቀን የመፍቻ ቁልፍ መንገድ አስቀምጠናል:: ያ አቅጣጫ ያግባባል አያግባባም ንግግር ነው የሚያስፈልገው:: ነገር ግን ለተከበረው ምክር ቤት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ የምፈልገው የፌዴራል መንግሥት በትግራይ እና በአማራ ሕዝብ መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ አንዱ ተደስቶ ሌላኛው አኩርፎ ቀጣይ ግጭት እንዳይፈጠር ሕዝበ ውሳኔን ማዕከል ያደረገ አካሔድ ብንከተል ጥሩ ነው ብሎ ያምናል::

ይሔንን ለሁለቱ ክልል አመራሮች በጋራ አወያይቷል:: አቅጣጫ አስቀምጧል:: እየሠራበት ይገኛል:: ሕዝቡንም አወያይተናል:: የሕዝቡን ምላሽ እናውቃለን:: ነገር ግን ይሔ ምርጫ ይሔ መፍትሔ ብቸኛ ስላልሆነ የአማራ እና የትግራይ ምሁራን፤ የሃይማኖት አባቶች የአገር ሽማግሌዎች ተወያይተው ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ መፍትሔ አለን ካሉ በደስታ እንቀበላለን::

ችግር የለብንም እኛ:: እኛ የምንፈልገው በሁለቱ ክልል መካከል ሰላም እንዲኖርና ነገሮች በንግግር ፣ በውይይት እንዲፈቱ ማድረግ ነው:: ለዚያም ህግን የሚከተል፤ በሕገመንግስቱ አግባብ መሠረት ልክ ደቡብ ላይ እንዳደረግነው በሪፈረንደም የተወሰነ ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ እና የሕዝብን ውሳኔ ያከበረ አቅጣጫን እንከተል ብለን እናምናለን፤ ይሔንንም ገልፀናል::

ከዚህ ውጪ አማራጭ ካለ ግን በደስታ እንቀበላለን። ተወያይታችሁ ሀሳብ ማምጣት ይቻላል። መፍትሄ ሳናመጣ ግን የመጣውን መፍትሄ የማንቀበል ከሆነ ያ ወደ ሰላም አይወስድም። የአንዱ ቢመለስም የሌላው ጥያቄ ይሆናልና በሰከነ መንገድ ይህንን ጉዳይ አይተን ዘላቂ ሰላም በሚያመጣ አግባብ ብንፈታው ይሻላል፤ ይመረጣል።

ሁሉንም ማርካት አይቻልም፤ ሁሉንም ለማርካት አይሰራም። እንኳን እኛ 120 ሚሊዮን ህዝብ ያለን ቀርቶ እኛን የፈጠረን ፈጣሪም አዳምና ሄዋን በገነት ፈጥሮ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አማልቶ ጥቂት ነገር ቢከለክላቸው፣ እንደምታውቁት ያንን የተከለከለ ነገር ፈልገው ለዚህ ሁሉ ጣጣ አምጥተውብናል። እናም በእኛ አቅም ሁሉም ይመለሳል፤ ሁሉም ይሟላል ብለን አናስብም።

የኛ መፍትሄ ብቸኛ መፍትሄ ይሆናል ብለን አናስብም። መፍትሄ ያለው ሰው ካለ ያምጣ። መፍትሄው ግን ሰላም የሚያመጣ ህዝብ የሚያቀራርብ፤ ጦርነት የማይፈጥር ብቻ ይሁን ፤ መፍትሄ ሳናመጣ ዝም ብለን የምንከራከር እንዳንሆን ብናስብበት ጥሩ ነው።በድምሩ ለአንዳንድ ችግሮች፣ ለአንዳንድ ግጭቶች ሰበብ እንጂ ምክንያት አያስፈልጋቸውም። ሰበብ ነው በቃ። የሆነ ጉዳይ ትፈጥርና የኑሮ ውድነት ስለተፈጠረብኝ ነው። የሆነ ችግር ትፈጥርና ሰው እየገደልክ ሰው ስለሞተብኝ ነው። እያፈናቀልክ አዳዲስ ሰበብ እየፈለክ መሄድ ተገቢ አይደለም።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት አብዛኛዎቹ ችግሮች በሰበብ የሚነዱ እንጂ በምክንያት የሚነዱ አይደሉም፤ ካጠፋ በኋላ እንዲሁ አጠፋህ እንዳይባል የሚሰጣቸው ምክንያቶች ወይም ስያሜዎች የበዙ ሆነው ይታያሉ። ይሄን በደንብ ማሰብ ያስፈልጋል፤ በምክንያት መነዳት ያስፈልጋል፤ ሰበብ ብቻ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ጥሩ ነው።

ሰራዊቱን በሚመለከት ፤ ያው ሁላችሁም እንደምታውቁት ህብረ ብሄራዊ ሰራዊት ተገንብቷል። የተገነባው በአካል Iፊዚካል ብቃት ወይም በትጥቅ ዘመናዊነት ብቻ ሳይሆን በአገር ፍቅርም ነው። አገሩን የሚወድ ሰራዊት ተገንብቷል። ይሄ የተገነባው ሰራዊት በሁሉም አካባቢ ላይ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን አስቀድሞ ይሰራል። ለዚህ ደግሞ የአገር መከላከያ ሰራዊት በተገነባበት መንገድ ከዚህ ቀደም ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን፤ አሁን ግን በተግባር ያለው ሁኔታ ጥያቄ ለማንሳት ያስቸግራል።

በሱማሌ ክልል ውስጥ የኢትዮጵያን ህልውና የሚያፈርስ ነገር አለ ብሎ ሲያስብ ሄዶ ሞቷል። በትግራይ ክልል ውስጥ የኢትዮጵያን ህልውና ሊሸረሽር ይችላል የተባለ ነገር አለ ብሎ ሲያስብ ሄዶ ሞቷል። በአማራ ክልል ሞቷል፣ በኦሮሚያ ክልል ሞቷል፣ በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ክልሎች ሞቷል። ይሄ ሰራዊት በየትኛውም ክልል የኢትዮጵያን ህልውና የሚገዳደር ነገር ሲነሳ ኢትዮጵያዊነትን አስቀድሞ የሚሰራ መሆኑን በስትራቴጂው ብቻ ሳይሆን በተግባር አረጋግጧል።

ከኦሮሚያም፣ ከአማራም፣ ከትግራይም፣ ከሶማሌም ከየትም ቢነሳ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነገር ካለ የማይታገስ፣ ከዚያ ውጪ ግን ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድም እና በኢትዮጵያ ፍቅር የታነፀ መሆኑ በተግባር የታየ ይመስለኛል።

በፌዴራል ስርዓት ውስጥ አንድ መታሰብ ያለበት ነገር ሎካል አድምንስትሬሽን / የአካባቢ አስተደደርን/ ቀበሌ፣ ወረዳ ማጠናከር፤ በቀበሌና በወረዳ ደረጃ የሚመለሱ ጉዳዮች እነርሱን በማጠናከር ብቻ ነው የምንመልሰው እንጂ፣ ሁሉንም ነገር በፌዴራል ደረጃ ማየት ያስቸግራል። ስርዓቱም እንደዚህ አይነት ነገር እንድናደርግ አይፈቅድምና ያንን እያጠናከርን ወደ ሰላም እየሄድን፣ ወደ ህብረት እየሄድን ኢኮኖሚያችን ሲሻሻል አብዛኛው ነገር መልክ እየያዘ እንደሚሄድ ተስፋ ይደረጋል።

ኢ-መደበኛን በሚመለከት፤ ያው ምቹ አጋጣሚን የሚጠብቁ ስብስቦች ናቸው። በውጪ ሀይሎች ጃስ የሚባሉ ሀይሎች ናቸው። በአንዳንድ የስራ ሁኔታ በቅርብ ርቀት ካሉ የአረብ አገራት ሰዎች ጋር ስንነጋገር ስለ ኢትዮጵያ የነበረን ግንዛቤ እስላምም ክርስቲያንም በነፃነት የሚኖርባት፤ የእስልምናም የክርስትናም የሺህ አመታት ታሪክ ያላት፣ ለሁሉም በእኩል የምታስተናግድ ቤተክርስቲያንና መስኪድ ጎን ለጎን የሚታይበት፣ አንዱ አንዱን እየረዳ የሚገነባባበት አገር ሳይሆን ለሙስሊም አገራት ስለ ኢትዮጵያ ሲነገር የነበረው ክርስቲያናዊ አገር እንደሆነች፣ ፀረ ሙስሊም እንደሆነች፣ ሙስሊም ጠል እንደሆነች፣ በፓርቲ ደረጃም ደግሞ የተለያየ ክርስቲያናዊ ስያሜ እየተሰጠ ሲነገራቸው ነበር። አሁን ገባ ብለው ሲያዩት እንደዚህ አለመሆናችንን ተገንዝበዋል።

የምእራቡ አገራት አካባቢ ደግሞ ፅንፈኝነት አክራሪነት የሚስፋፋበት፣ ሱማሌና ሱዳን መካከል ያለችው ኢትዮጵያ ፅንፈኝነት ከጀመረች ሁሉም ቀጣናው የአሸባሪዎች አገር እንደሚሆን፣ እስልምና ወደ ሽብር የተጠጋ የእምነት ልምምድ የሚያካሄድበት አገር እንደሆነ፣ አይነት ፕሮፓጋንዳዎች በስፋት ይነገሩ ነበር። እንደዛሬ ሶሻል ሚዲያ የለም እንደ ዛሬ በቀለለ መንገድ መረጃ ስለማይገኝ ሰዎቹ ይህን ያምኑም ነበር። ኢትዮጵያ ግን እንደዛ አይደለችም።

አሁን ያለው እውነት እንደሚያሳየው ስለ ክርስትና የሚነገር የሚጨበጥ የሚዳሰስ ታሪክ ያላት፤ ስለ እስልምናም እንደዚሁ በብዙ አገራት የማይገኝ ታሪክ ያላት፣ ሁሉን አቅፋ ከሁሉ ጋር መኖር የምትችል አገር መሆኗን ያመላክታል። እናም ጃስ የሚሏቸው ሃይሎች በየጊዜው እንደዚህ አይነት ጉዳይ እየፈጠሩ ኢትዮጵያን ባልተገባ መንገድ በዓለም ፊት እንድትታይ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የኛዎቹ ሀይሎች ግን የሚዋጉበት ዓላማ ራሱ መዋጋት ካልሆነ በስተቀር፣ የሚዋጉበት ዓላማ አንድ ነገር ማሳካት ከሆነ፣ በክላሽ መንግሥታትን መጣል በዚህ ዘመን በዓለም ሁሉ የማይቻል፣ በኢትዮጵያ ደግሞ በፍፁም የማይሆን ነው። ካልተቻለ ከምንገዳደል ተቀምጠን መወያየት ይመረጣል፤ ወደዚያ መሄድ ነው። እስኪርቢቶም ክላሽም አንድ ጊዜ ይዞ በአንድ እጅ ውይይት በአንድ እጅ ጦርነት አስቸጋሪ ነው።

ክላሽ የያዙ ሰዎች ቀን ቀን ለውይይት ቢቀመጡ፣ ማታ ሲወጡ ከእነርሱ ሁለት ሶስቱ ሰው መተኮሱ አይቀርም:: ሲተኩስ በማግስቱ ያለው ውይይት ቀድሞ የነበረው አጀንዳ መሆኑ ይቀርና ማታ የተኮሰው ማነው፣ የት ተተኮሰ የሚል ይሆናል፤ አጀንዳው ይቀየራል።

ክላሻችንን እናስቀምጥ፣ እስኪሪብቶ እንያዝ፤ ሀሳብ እንያዝ፣ እንወያይ ለሰላም ለብልፅግና ምቹ የሆነች አገር እንፍጠር፤ ይሄ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባዋል። ይሄ ጉዳይ ግለሰቦች ላይ፣ አንድ ፓርቲ ላይ የሚተው አይደለም። ሁሉም ሰው ሀላፊነት ወስዶ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን መፍትሄ አፈላላጊ፣ ያን አምጡ ይሄን መልሱ ብቻ ሳይሆን፣ ለመልሱም የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ ቢሆን ይመረጣል። ያ ነው ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው።

ሚዲያን በሚመለከት፤ ሚዲያ እፍ እንደማለት ነው። ለማጥፋትም፣ ለመለኮስም እፍ እንደሚባለው ፤ሚዲያም እንደ እሱ ነው። አጥፊም ነው፤ አልሚም ነው። ማን ለምን ዓላማ አዋለው የሚለው ጉዳይ በጣም ወሳኝ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሚዲያ ልምምድ ጀማሪም ስለሆንን የግል ሚዲያ በስፋት ያለበት ጊዜም አሁን ስለሆነ ገመና አልባ ነው። የሚነገርና የማይነገር፤ የሚደበቅና የማይደበቅ ያልለየ ገመናን በሙሉ የሚያዝረከርክ የሚዲያ ሁኔታ ይታያል። የአገርና የህዝብ ጥቅምን የማያስከብር ይሆናል።

ለምሳሌ ሰሞኑን በሚድል ኢስት /በመካከለኛው ምስራቅ/ ባለው ችግር ብዙ አሳዛኝ ጉዳዮች ያሉ ቢሆኑም ፣ የምንማርባቸው በጣም በርካታ ጉዳዮች አሉ:: በአንድ አገር ውስጥ ሊተያዩ የማይፈልጉ፣ በከፍተኛ ጥላቻና ፀብ ውስጥ የነበሩ ፓርቲዎች ‹አይ በዚህ ጊዜ እኛ ውስጥ ጉዳያችንን ለሚዲያ አንናገርም፤በጋራ እንቆማለን› ሲሉ ይሰማሉ:: ኢትዮጵያውያን ግን በተገኘው አጋጣሚ በተለይም በሚዲያ ያን የሚቃረን ነገር እናደርጋለን::

ይሄ ወደፊት ለልጆቻችን የሚያሳፍር እንደሚሆን እገምታለሁ:: እንደ ባለፈው አይደለም፤የዛሬ 100 ዓመት የነበረው ነገር ‹ተባለ፣ ሚስተር ኤክስ /እገሌ/ ፃፉት› ነው:: አሁን ያለው አብዛኛው ነገር በቪዲዮ ስላለ፣ ልጆቻችን ያዩታል:: ፎቷችንን እያዩ፣ ድምፃችንን ስለሚሰሙት ለእኛም እንደ አባት እንደ እናት አሳፋሪ ነገር እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል::

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ 154 ገደማ ሚዲያዎች አሉ:: 20 የሚጠጉ የህዝብ ሚዲያዎች፣ 35 ገደማ የንግድ ሚዲያዎች፣ 37 የማኅበረሰብ ሚዲያዎች፣ 48 ገደማ ደግሞ የተመዘገቡ በይነ መረብ ላይ የሚሰሩ ሚዲያዎች አሉ:: ከእነዚህ ውጭ በርካታ ያልተመዘገቡ ሚዲዎች ይኖራሉ:: እነዚህ ሚዲያዎች ዘንድ ያለው ችግር የሚና መደበላለቅ ነው:: በሐይማኖት ስም ሚዲያ ከከፈቱ በኋላ ፖለቲካ ሊሰሩበት የሚሞክሩ ሰዎች አሉ:: በንግድ ስም ካወጡ በኋላ ሃይማኖታዊ ተግባር ሊፈፅሙበት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ:: ሚና ይደበላለቃል፤ለዚህ ሕግ ወጥቷል፤ደረጃ በደረጃ ሕጉን እየተገበርን እንሄዳለን::

አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን ችግሩ የሁሉም አገር መሆኑ ነው:: አደጉ በምንላቸው አገራትም ጭምር አሁን ያለው ልቅ የሚዲያ ስርዓት በጣም በከፍተኛ ደረጃ እየፈተናቸው ይገኛል:: አብዛኛው ሰው ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ በገዛ ስልኩ ነው መርዝ ከቁርሱ በፊት የሚበላው፤ ቁርስ ሳይበላ ክፉ ዜና ይበላል፤ያን እያሰበ ነው ምግብ የሚበላው:: ቀኑን ሙሉ ጠዋት ያያትንና የሰማትን ያልተገባች ዜና እያብሰለሰለ ይውላል:: አብዛኛውን ሰው ጭንቅላቱን የያዘው እንደዚያ ዓይነት የውሸት ዜና መሆኑን እናንተም ታውቁታላችሁ::

ምሳሌ ጫካ ብላችኋል:: ጫካ ከቦሌ ኤርፖርት ቪአይፒ ተርሚናል እስከ ገርጂ የሚሄድ ፕሮጀክት ነው:: ጫካ እስካሁን እንኳን ወደ 50 ኪሎ ሜትር ገደማ መንገድ በከፍተኛ ጥራት እየተሰራ ያለ፣ ቢያንስ ቢያንስ 100 ኪሎ ሜትር ገደማ መንገድ የሚሰራበት ፕሮጀክት ነው:: ጫካ አሁን ያለችውን አዲስ አበባ ግማሽ የሚያህል ከተማ የሚፈጥር ነው:: ምን ሲባል እንደነበር ታውቃላችሁ፤ ምን እንዳመናችሁም ታውቃላችሁ::

እስካሁን ያልታየበት ዋናው ምክንያት፣ ቀስ እያለ እየተተገበረ ማሳየት ስለሚሻልና ገና ሃሳብ ብቻ ብንነጋገር ብዙም ስለማንግባባ የቆየ ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም ቃል ገብቼላችኋላሁ:: አንደኛ ሳተላይት ከተማ ነው የምንገነባው፤ ሁለተኛ ታዩታላችሁ፤ሦስተኛ ማንም አያቆመውም ብያችኋለሁ:: አሁንም ማንም አያቆመውም፣ እንጨርሰዋለን፤የጀመርነውን ነገር እንጨርሰዋለን:: እናንተ ግን ስታዩ የምትረኩበት፣ የምትወዱትና ለልጆቻችሁ የምትመኙት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም:: በእርግጠኝነት መናገር የምፈልገው የኢትዮጵያን ገጽታ በእጅጉ ይቀይራል::

ታስታውሱ ከሆነ የዛሬ ሁለት/ሦስት ዓመት ‹አዲስ አበባን እንደስሟ አበባ እናደርጋታለን› ብለን ነበር:: ብዙ ሙከራዎች አርገናል:: እዚህ ጋ ይልጎበኛችሁት የሪቨር ሳይድ /የወንዝ ዳርቻ/ ፕሮጀከት አለ፤ ሦስት ዓመት ያለቀስንበት:: የሪቨር ሳይዱን ሪያላይዝ ለማድረግ /የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቱን ለማሳካት/ ትንሹም ትልቁም በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በምናምን ስም ሲያሰቃየን የኖረበት፤ አሁን ጀምረነዋል፣ ጊዜ ቢወስድም::

እኔ በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ሚዲያም ምንም ቢል የዛሬ አምስት/ሰባት/አስር ዓመት ማንም ነጋሪ ሳያስፈልገን፣ የትም አገር ዜጋ አዲስ አበባ ውስጥ ሲመጣ አዲስ አበባ አፍሪካ ውስጥ ምርጥ ከሚባሉ በጣት ከሚቆጠሩ ከተሞች አንዷ እንደሆነች ማንም ሰው እንዲያምን አድርገን እንሰራታለን፤ምንም ጥርጥር የለውም::

እየተሰራ ያለው በዚያ መንገድ ነው፤በእርግጥ አሁን ሁሉም ሰው ዐይቶ ሊገነዘበው አይችልም:: ምክንያቱም እዚያ ጋ የሚፈርስ ነገር አለ፣ እዚህ ጋ የሚቆፈር፣ እዚያ ጋ የሚጠፈጠፍ ነገር አለ:: ተያይዞ ቅርፅና መልክ አልያዘም::

አዲስ አበባ ፍሬንድ ሽፕ /የወዳጅነት/ አደባባይ ብቻ አይደለም፤ አዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክ ብቻ አይደለም:: ከገርጂ እስከ አቃቂ፣ ከሲኤምሲ እስከ ቡራዩ ባለው ውስጥ በኢንፍራስትራክቸር /በመሰረተ ልማት/ የተሞላ፣ ያመረ፣ ለኑሮ የሚመች፣ መልካም አየር ያለው፣ ግሪነሪ  /አረንጓዴ/ የትም ቦታ የሚታይበት ጽዱ ከተማ ለማድረግ እየለፋንና እየተጋን እንገኛለን:: ከህዝባችን ጋር ሆነን ደግሞ የሚሳካ ጉዳይ ይሆናል::

ሚዲያ ግን ለወደፊትም ሕግም ቢወጣ መገንዘብ ያለብን ነገር፣ መሳሪያ የሚያመርቱ ኩባንያዎችና ቡድኖች መሳሪያ ከማምረት ጎን ለጎን እንዴት ጦርነት እንደሚነሳ ይሰራሉ:: ምክንያቱም ገበያቸው ጦርነት ሲኖር ነው፤እንጂ የሚያመርቱት እንድናየው አይደለም፤ገዝተን እንድንዋጋበት ነው:: መድኃኒት የሚያመርቱ ኩባንያዎችም እንዲሁ በሽታ ያመርታሉ፣ ገበያ ነው::

ሚዲያ ላይ የሚሰሩ ኃይሎች ደግሞ ለመደመጥ ውሸትና ሴራ ያመርታሉ:: መልካም ነገር መስማት ላይ ሰው ብዙም ስላልሆነ በሴራና በውሸት የሰው ጆሮ ይዘው ገንዘብ ይሰበስባሉ:: መንቃት ያለበት ሰሚው ነው:: ‹በሽታ፣ አልባሌ ነገር ማድመጥ የለብኝም› ብሎ ማሰብ ያለበት ራሱ ሰሚው ነው:: እነሱም በሕግ እንዲገሩ ለማድረግ ይሞከራል::

ዋናው ነገር መልካም ነገር እናስብ፣ ለመልካም ነገር እንትጋ፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ መታየቱ አይቀርም:: እውነት እያደር መታየቷና መጉላቷ አይቀርም፤በውሸት የሚሸነፍ ነገር ስለማይኖር በዚያ አግባብ በመሄድ ሚዲያዎች ቢገሩ መልካም ይሆናል:: በከፍተኛ ትጋት የሚሰሩ ሚዲያዎችም እንዳሉ መዘንጋት የለበትም:: የሚጥሩ ሚዲያዎች አሉ፣ የሚያበላሹ ሚዲያዎች አሉ:: ሁሉንም ጊዜ እያጠራውና ህግ እያስተካከለው እንደሚሄድ ተስፋ ይደረጋል::

የምክክር ኮሚሽንን በሚመለከት፣

ተጠሪነቱ ለእናንተ /ለምክር ቤቱ/ ነው:: እናንተ ናችሁ ስለምክክር ኮሚሽኑ ይበልጥ መናገር የምትችሉት:: እኛ ግን እንደካቢኔ በቅርቡ ገለፃ አቅርበውልን ነበር፣ ባቀረቡልን ገለፃ የታዘብነው ነገር በከፍተኛ ትጋትና ጥራት ለመስራት ሙከራ እያደረጉ እንደሆነ፣ ጊዜ የወሰደባቸውም መሰረት ያለው፣ ታማኝ የሆነ፣ ብዙዎችን ያሳተፈ ስራ ለመስራት እንደሆነ ፣በጣም በርካታ የማኅበረሰብ ክፍል ጋር እየተገናኙ እንደሆነ፣ በሚቀጥሉት ጊዜያት የተሻለ ውጤት እንደምናይበት ተስፋ ያደረገ ገለፃ አቅርበውልናል::

የእናንተን ገለጻ አላውቅም፤ ለእኛ ያቀረቡት ጥሩ ገለፃ እንደሆነ፣ ከተደገፉና ከታገዙ የተሻለ ውጤት ሊመጣ እንደሚችል የሚያመላክት ሆኖ ነው ያገኘነው:: ሁላችንም ባለን አቅም ማገዝ ይኖርብናል::

የምናግዘው ሁሉም ለራሱ ብሎ ነው፤እያንዳንዱ ግለሰብ ለራሱ ሲል ነው የሚያግዘው ፤ ያመለጠ እድል አደገኛ ነው:: በ1953 ዓ.ም እድል ነበር ፤እነመንግሥት ነዋይና ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ የሞከሩት ሙከራ የኢትዮጵያን የጉዞ መንገድ ሊቀይር ይችል ነበር፤ሳንጠቀምበት ቀረን፤ ተበላሸ::

በ1966 ዓ.ም ሌላ እድል መጣ፤መጠቀም አልቻልንም:: በየከተማው ወረቀት ስንበትን፣ ስንሰዳደብ ቆየን፤ ስንባላ ቆየን፤አመለጠን:: በ1983 ዓ.ም ሌላ እድል መጣ፤አመለጠን::

የእኔ ልመናና ምክር ይህኛውም እንዳያመልጠን ነው:: ኢንክሉሲቭ ናሽናል ዳያሎግ /አካታች ብሔራዊ ምክክሩ/ ከመንግሥት ጫና ነፃ ወጥቶ፣ የሕዝብን ስሜት አድምጦ ብዙኃንን አወያይቶ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ነገር ውጤት እንዲያመጣ ሁላችንም ብናግዝና ይህን እድል ባናስመልጥ ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ::

አንድ ሊቅ ለምክንያት ስትል እድል አታባክን፤ምክንያት ሁልጊዜም አለ፤እድል ግን ሁልጊዜም አይገኝም:: ምክንያት አልቦ ሽንፈትም የለም:: ሰው ሁልጊዜም ሲሸነፍ ምክንያት አለው:: ለምሳሌ ፈተና ከወደቀ የእሱ አለመበርታት ሳይሆን የፈተናው ችግር እንደሆነ ምክንያት አለው፤ በሃብትም ካልተሳካለት የባንክ ብድር ችግር ነው፤ፖለቲካም ካልተሳካለት የመንግሥት ችግር ነው:: ምክንያት ሞልቷል፤ እድል ግን ሁልጊዜ የለም::

የተገኘን እድል መጠቀም በጣም ጠቃሚ ነው:: ይህ የናሽናል ዳያሎግ /የብሔራዊ ምክክር/ እድል ለኢትዮጵያ መባከን የሌለበትና ካበከንነውም ሌላ ረጅም ጊዜ የሚጠይቀን ጉዳይ ስለሆነ የምንቃወመውም፣ የምንቃረንም የምንፎካከርም፣ የምንታገልም ሁላችንም በሰከነ አዕምሮ ይህን እድል ለመጠቀም መሞከር ይኖርብናል::

ላለፉት 30 ዓመታት ይህ ኮሚሽን እንዲቋቋም ያልለመነ ተቃዋሚ የለም:: ‹ወይይት ይደረግ፣ ምክክር ይደረግ፣ ንግግር ይደረግ› ሲባል ነበር:: ‹እሺ፣ ይደረግ› ሲባል እንዳናባክነው ብንጠቀምበት መልካም ነው የሚል ምክር ነው ያለኝ:: አንድ ጎረምሳ አንድ አዛውንት ዘንድ ሄዶ ልጅዎን ይስጡኝ፤ ልጅዎን እወዳለሁ ተንከባክቤ አገባለሁ ይስጡኝ ብሎ ይጠይቃል:: አባት በሳል ሰው ናቸውና እንዲሁ እምቢ አላሉትም፤ ምንም ችግር የለም፤ አንድ ፈተና አለ:: ፈተናውን ካለፍክ ልጄን እድርልሃለሁ ይሉታል::

ፈተናው ምንድን ነው ይላል:: ሶስት በር ይከፈታል:: ሶስት ዕድል ይሰጥሃል፤ ሶስት ጊዜ ለመሞከር የሚያስችል ሁኔታም ይፈጠርልሃል፤ ከሶስቱ በአንዱ የምልህን ካደረግክ ልጄን ትወስዳለህ ይሉታል::

ፈተናው ከእያንዳንዱ በር በሬ ይወጣል:: ከበሬው ኋላ ሮጦ ሄዶ የበሬውን ጭራ ከያዘ ልጅቷን ማግባት ይችላል:: ስምምነቱ ይህ ነው::

አንደኛው በር ተከፈተ፤ የሰማይ ስባሪ የሚያህል፣ በጣም ትልቅ በሬ ወጣ:: ልጁ አየና አይ ይሄን መሞከር ጥሩ አይደለም፤ የሚቀጥለውን ዕድል ልሞክር ብሎ አንደኛውን ተወው:: ዝም ብሎ አልተወውም፤ ሰበብ አለው፤ የሰማይ ስባሪ የሚያህል ትልቅ ነው ብሎ ተወው::

ሁለተኛው በር ሲከፈት በጣም ረጅምና ቀንዱ በጣም ረጃጅም የሆነ ወጣ:: አይ ይሄም አያዋጣም፤ ዞር ካለ ገንጥሎ ይጥለኛል ብሎ ሶስተኛውን በሬ ልሞክር ብሎ አሳለፈው፤ አሁንም ሰበብ አለው::ሰበቡ ቀንዱ ረጅም ነው፤ አልችለውም የሚል ነው::

ሶስተኛው በር ሲከፈት አጋጣሚ ሆኖ ኮሳሳ ድቅቅ ያለ በሬ ወጣ:: አሁን አገኘሁ ብሎ ሲሄድ አጋጣሚ ሆኖ በሬው ጭራ የለውም:: መሞከር ባለበት ጊዜ እያሳበበ ስላሳለፈ ልጅቱን ማግባት አልቻለም ማለት ነው:: አሁን በብዙ ሰበብ በብዙ ሙከራ አይሆንም::

እናም አሁን ያለውን ዕድል መጠቀም አለብን:: ናሽናል ዲያሎጉ /ብሔራዊ ምክክሩ/ ለሁላችንም ጠቃሚ ነው:: ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዲመለሱ፤ ስርዓተ መንግሥቱ በብዙሃን ቅቡልነት ያለው እንዲሆን፤ በምርጫ፣ በፓርላማ፤ በመንግሥት አስተዳደር ያሉብንን አንዳንድ ጥያቄዎች ለመመለስ ዕድል ሰጪ ስለሆነ ለመጠቀም ሙከራ ብናደርግ ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ:: ይህም እንዲሳካ ምኛቴ ከፍ ያለ ነው::

ትምህርትን በሚመለከት

ትምህርትን በሚመለከት የተነሳው ጥያቄ ሰሞኑን ከሚሰሙ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ ዘርፈ ብዙ ስብራት የሚመለከት ነው :: ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት የትምህርት ጥራት መውደቅ በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጵያን እየጎዳ ነው ብለን ከለውጡ በፊትም፣ ለውጥ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ዋነኛ አጀንዳችን አድርገነዋል :: ስብራቱም በብዙ መንገድ ተንጸባርቋል::

የተከበረው ምክርቤት መገንዘብ ያለበት የሥርዓተ ትምህርቱን ለማዳከም በጣም ጥቂት ጊዜና ስንፍና በቂ ናቸው:: ለማዳከም ብዙ ገንዘብ አያስፈልገንም፤ መስነፍና ጥቂት ጊዜ ከተጨመረበት ይበላሻል:: ለማቃናት ግን እንደዛ ቀላል አይደለም:: በጣም ብዙ ድካም፣ ብዙ ለውጥ ይፈልጋል::

ለዚህም በለውጡ ማግስት “ሮድማፕ “ሲሠራ እናንተም ተወያይታችሁበታል፤ ያልተወያየበት የሕዝብ ክፍል የለም:: ቢያንስ ሰባት ዋና ዋና ጉዳዮችን “ሮድማፑ “ይይዛል:: አንደኛው ሥርዓተ ትምህርት /ካሪኩለም/ መቀየር፣ ሁለተኛው የመምህራንን አቅም መገንባት ፣ማሠልጠን ማሻሻል፤ ሶሥተኛው የትምህርት አስተዳደር ሥርዓትን ማሻሻል መቀየር ፤ አራተኛው በጣም ሰፊ የትምህርት መሠረተ ልማትን ማስፋፋት፤ በተለይም ታች ያለውን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ፣ መዋዕለ ህጻናት በስፋት ስላልነበረ ይህንን ማስፋት::

አምስተኛው የፈተና ሥርዓቱን ማሻሻል፤ ችግር አለበት፤ አንድ ትምህርት ቤት ያለ ተፈታኝ በሙሉ 100 ሊያመጣ ይችላል:: የፈተና ሥርዓት እንቀይር የሚል ነው:: ስድስተኛው የተማሪዎች ምገባ መጀመር ነው:: ባለመመገብ የሚደክሙ ተማሪዎች አሉ:: ለዚህም ምገባ ካልተጀመረ በስተቀር የደሃ ልጆች እኩል የትምህርት ዕድል ቢያገኙም በምግብ እጥረት ምክንያት እኩል ለመማር ይቸገራሉ:: ሰባተኛው ከፍተኛ ትምህርት ላይ ማስፋቱን አቁመን፣ ጥራቱ ላይ እንሥራ የሚል ነው:: ቲቤቲ / ቴክኒክና ሙያ/ ን እናስፋፋ እነዚህ ሁሉ ሮድ ማፑ ላይ አሉ::

ለአብነትም ባለፉት አምስት ዓመታት አንድም ዩኒቨርሲቲ አንድም ቅርንጫፍ አልከፈትንም፤ ይህም የዚህ ሮድማፕ አካል ነው:: ያሉንን እናጽና፣ እናስተካክል እንጂ አዲስ መክፈት አያስፈልጉንም አልን:: ነገር ግን መዋዕለ ህጻናት ቢያንስ ቢያንስ በሕዝባችን ተሳትፎ 18 እና 19 ሺ አካባቢ ተገንብተዋል::

ኢትዮጵያ ውስጥ ባልነበረ ልክ በጣም በስፋት መዋዕለ ህጻናት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምርት ቤቶች ተስፋፍተዋል:: ለምን መሠረቱን ካልሠራን ከላይ የምናደርገው ኢንቨስትመንት ውጤታማ አያደርገንም የሚል ዕምነት ስለነበርን ነው::

ቲቤቲ /ቴክኒክና ሙያ/ ላይ ዛሬ 1400 የሚደርሱ ኮሌጆች አሉን:: ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱን በተሟላ መንገድ ካላስተካከልነው በስተቀር በአንድ ሲንጉላር የሪፎርም /ነጠላ/ አጀንዳ ልንቀይረው አንችልም የሚል ዕምነት ስለነበረ ነው::

አሁን ፈተና ላይ ያለው ውጤት ከሞላ ጎደል የሚጠበቅ ነው:: የፈተና ሥርዓቱ የምንፈትንበት መንገድ ተቀየረ እንጂ ፈተናውም ጊዜውም ያው ነው:: ትንሽ ቁጥጥር በዛበት፤ ዓላማችን ሰው ባለበት “ኦቶሜት” ማድረግ ነው:: ኮሮና መጣና ያሰብነውን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር አይፓድ በቀላሉ ማግኘት አልተቻለም:: ለጊዜው በሚል በየዩኒቨርሲቲዎች ሰብስበን መፈተን ጀምረናል:: በዚህ ምክንያት ውጤት ዝቅ አለ::

ውጤት ላይ ሁለት ነገር ታሳቢ መደረግ አለበት:: አንደኛው በቅርቡ ቻይና በነበርኩበት ጊዜ አንድ የማውቃቸው ሰው አግኝቼ ነበር፤ እኚህ ሰው ከዚህ ቀደም ለመምጣት አስበው ስለቀሩ ለምን ቀሩ ስል ጠየቅሁዋቸው፤ የልጄ ፈተና ስለነበረ ለዚያ ነው የቀረሁት አሉኝ::

ምን ማለት ነው ብዬ ስጠይቃቸው፤ ቻይና ውስጥ ፈተና ሲደርስ ቤተሰብ ፈቃድ ጠይቆ ወጥቶ ከፈተና በፊትና በኋላ ልጆቹን በከፍተኛ ደረጃ ያግዛል:: ፈተናው በጣም ጠንካራ ስለሆነ ቤተሰብ ፈቃድ ወስዶ ካላገዛቸው አንዳንድ ልጆች ለጉዳት ይዳረጋሉ:: አስጨናቂ ነው:: ተፈታኙ ሳይሆን ፋሚሊ /ቤተሰብ/ ይጨነቅበታል:: ይህ እንደዋዛ የነገሩኝ ነገር ለእኔ ትልቅ ትምህርት ነበር:: እኛጋ ፈተና እንዴት ነው የምናየው ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል::

የፈተና ውጤትን በሚመለከት አዲሱ ቋንቋ ከ50 በላይ ያመጡ ተማሪዎች በቀጥታ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ይማራሉ አለ እንጂ፤ አምናም ዘንድሮም በ50 አልቆምንም፤ 30 አካባቢ ወርደን በርካታውን ሰው ወስደን የማዘጋጃ የአንድ ዓመት ሥልጠና ሰጥተን ትምህርቱ እንዲቀጥል ለማድረግ ነው ሙከራ የተደረገው እንጂ ከ50 በታች ያላችሁ በሙሉ ቅሩ አልተባለም:: ለምን ይጠበቃል::

ቢያንስ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በየዓመቱ ቶሎ ከዚህ ጉዳይ እንደማይወጡ እናውቀዋለን፤ ቢያስ ዘጠነኛ ክፍል ያሉ 10፣ 11 እና 12 እያለ በየደረጃው እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል እንጂ በአንድ ጊዜ ውጤቱ እንደምንፈልገው አይሆንም:: አሁን በርካታ ቤተሰቦች አዝነዋል፤ የልጆቻቸው ፌት/የወደፊት ሁኔታ/ አሳስቧቸዋል:: ተገቢ ነው፤ ይሄ ልጅ አስተምሮ ለፍቶ የማይጨነቅ ቤተሰብ የለም:: ወደቀብኝ የሚለውን መቀበል የሚፈልግ ቤተሰብም የለም:: ሁላችንም ልጆች አሉን የምንፈልገው እንዲሳካላቸው ነው::

የፈተና ውጤት በሚመለከት አዲሱ ቋንቋ ከ50 በላይ ያመጡ ተማሪዎች በቀጥታ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ይማራሉ አለ እንጂ ፣አምናም ዘንድሮም በ50 አልቆምን 30 ገደማ ወርደን በርካታውን ሰው ወስደን የማዘጋጃ የአንድ ዓመት ሥልጠና ሰጥተን ትምህርት እንዲቀጥል ለማድረግ ነው ሙከራ የተደረገው ፤ ከ50 በታች የሆናችሁ ሁላችሁም ቅሩ አልተባለም:: ለምን? ይጠበቃል፤ ቢያንስ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በየዓመቱ ቶሎ ከዚህ ጉዳይ እንደማይወጣ እናውቀዋለን:: ዘጠኝ ያሉ፣ አሥር ፣ አስራአንድ፣ አስራሁለት በየደረጃው እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል እንጂ በአንድ ጊዜ ውጤቱ እንደምንፈልገው አይሆንም::

አሁን በርካታ ቤተሰቦች አዝነዋል:: የልጆቻቸው የወደፊት ሁኔታ አሳስቧቸዋል:: ይሄ ተገቢ ነው:: ልጅ አስተምሮ ለፍቶ የማይጨነቅ ቤተሰብ የለም:: ወደቀብኝ የሚለውንም መቀበል የሚፈልግ ቤተሰብ የለም:: ሁላችንም ልጆች አሉን:: የምንፈልገውም እንዲሳካላቸው ነው::

እንደሀገር ግን የነበረውን ነገር ብናስቀጥል ስብራቱ ከባድ ነው:: እኔ ያለኝ ምክር ልጆቻችን በሕይወት ፈተና ከሚወድቁ በአንድ ዘመን ፈተና ቢወድቁ ይሻላል:: በሕይወት ዘመን ፈተና ከመውደቅ የአንድ ወቅት ፈተና ምናልባት አስተማሪ መወንጨፊያም ሊሆን ይቻላል:: አሁን የወደቁ ልጆች ወድቀው ቀሩ ማለት ነው እንዴ? አይደለም::

በነገራችን ላይ ልጆቹ የተሰጣቸውን ጥያቄ ያልመለሱ ይሆናሉ እንጂ በጣም ብዙዎቹ ጥቂት ቢሰራባቸው ሀገር ለዋጭ ሃሳብ ያላቸው (ብሪሊያንት ጭንቅላት ያላቸው) እንደሆኑ ጥያቄ የለውም:: የአሁን ልጆች በጣም ጭንቅላታቸው ፈጣን ነው:: ቁጭ ብለው ለማጥናት ፣ ለመማር ያላቸው ነገር ስለሚለያይ ውጤቱ ይነስ እንጂ በጭንቅላት ደረጃ በእርግጠኝነት እኔ ልጆቼ አሁን ያላቸውን እንደርስታንድ (መረዳት) እኔ በእነርሱ እድሜ አልነበረኝም:: እና ወደቁ ፈተና ማለት ጠፉ ማለት አይደለም::

በአዲሱ ትምህርት ፖሊሲ ካሻሻልነው አንድ ጉዳይ አንድ ተማሪ ማትሪክ ወድቆ ቲቬት ገብቶ ሌብል ዋን፣ ቱ፣ ስሪ ሄዶ ከተመረቀ በኋላ በሆነ ጊዜ ከፈለገ ወደቀለም ትምህርት መሄድ ይችላል:: ዝግ አይደለም:: አንድ በቀለም ትምህርት ዲግሪ ያመጣ ሰው ቀለም ብቻ ሳይሆን ሀንዲ /የእጅ ሙያ ያስፈልገኛል ካለ በማስተርስ ደረጃው የሙያ ትምህርት መማር ይቻላል:: የትምህርት ሥርዓቱ ይህንን የሚያስተናግድ ነው::

በቲቬት 600 መቶ ሺ ገደሞ ተማሪ የመቀበል አቅም አለን:: ግን ሰዎች ናቅ ያደርጉታል ቲቬት ሲባል:: አውሮፕላን የሠራው፣ እዚህ ቤት ውስጥ የምንናገርበትን ማይክራፎን የሠራው፣ መብራት የሠራው፣ ቲቪ የሠራው፣ የቲቬት ሙያ ያላቸው ይመረቁም አይመረቁም ሃሳብ ያላቸው ሀንዲ የሆኑ ሰዎች ናቸው:: እንጂ ዲግሪ ያለው ሰው አይደለም ይህንን ሁሉ የሠራው:: ዲግሪ አለመያዝ መጥፋት ተደርጎ መወሰድ የለበትም::

በዓለም ላይ የምናውቃቸው ዋና ዋና ተጽእኖ የፈጠሩ ሰዎች ዲግሪ ያላቸው አይደሉም:: ዲግሪ ይቅርባቸው ግን እያልኩ አይደለም:: አሁን ከ30 በላይ ሆነው ማጠናከሪያ ፈተና ወስደው መቀጠል የሚችሉት ኮሌጅ ይገባሉ:: ከእነሱ ያነሰው ደግሞ ቲቬት ገብቶ ተምሮ ከሆነ ጊዜ በኋላ ሲነቃ ተመልሶ ወደሚፈልገው የትምህርት መስክ ሊሄድ ይችላል:: ዝግ አይደለም በሩ:: በዚህኛው ቀረ ማለት ጠፋ ማለት አይደለም::

ቤተሰቦች በዚያ መንገድ መገንዘብ አለባቸው:: ልጆቹም ምናልባት ያላሰብነው ነገር የሚነቃን የሚያግዘን ነገር ሊፈጠር ይቻላል:: በዘንድሮ ፈተና ወደቅን ማለት ከሁሉ ነገር ጠፋን ማለት ስላልሆነ በቲቬት ተምረን ሌብላችንን አሻሽለን በማስተርስ ወደዚያ ማደግ እንደምንችል ማሰብ ጠቃሚ ይመስለኛል:: የመጨረሻው ተደርጎ መወሰድ የለበትም ::

ሪፎርሙን አጠናክረን ካልሠራን በስተቀር አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት አይጠገንም፤ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠልን የምናስበውን እድገትና ብልጽግና ልናመጣ እንችልም:: በሆነ ቦታ ላይ “ሰምዌር” ቆንጠጥ ብለን ጨከን ብለን ማረቅ ማሻሻል የሚሻል ይመስለኛል::

ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ አንጻር የሚታይበት ክፍተት ካለ እያየ እያሻሻለ አብዛኛውን ሰው እያቀፈ የሚሄድበት መንገድ ይከተላል:: የሚያደርጉትም እንደዚያው ነው በዚህ አግባብ ብናየው:: ለውጡ ሪፎርሙ ፈተና አይደለም:: ሆለስቲክ ነው:: ሰው ከውስጡ መዞ የሚያየው ፈተናን ብቻ ነው በዚያ መንገድ የሚያየው:: ደምረን ስናየው በጥቂት ዓመታት የትምህርት ሥርዓቱ ውጤታማ እንደሚሆን ተስፋ ይደረጋል:: ለምሳሌ አሥረኛ የነበረው አስራበሁለተኛ ሆኗል እንደምታውቁት:: ያንን ሰው አይናገርም:: እና ደምረን በማየት ብንሄድበት መልካም ይሆናል የሚል ሃሳብ አለኝ::

ጤናን በሚመለከት እውነት ነው:: ኮሌራ እና ወባ ባለፉት ጥቂት ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በ29 ሀገራት ተስፋፍተዋል:: በእርግጥ የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቀድሞ ትንበያ ሰጥቷል:: ታስታወሱ እንደሆነ እኔም በባለፈው በፓርላማ ቆይታችንን አንዱ የሚያሰጋኝ ወረርሽኝ እንደሆነ አንስቻለሁ:: እናም ይገመት ነበር:: ቢሆንም የአየር ንብረት ለውጡ በተለይም በእኛ አካባቢ ማንዱራ ትሬያንግል የሚባል ሰፈር ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሱማሊያ የሚዋሰኑበት አካባቢ ላይ የወባ በሽታ በስፋት ታይቶ ቀስ ቀስ እያለም ኮሌራ በሽታ እየተሰራጨ ሄዷል::

ይሄ አንዱ ያመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ነው:: ሁለተኛ የነበሩን መመርመሪያ ኪቶች አዲሱን የበሽታ አይነት በቀላሉ መለየት ይቸገሩ ነበር:: ለዚያም መንግሥት ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል:: ከ20 ሚሊዮን በላይ አጎበር ተሰራጭቷል:: የጸረ ወባ ኬሚካሎች ፣ውሃ ማከም እና በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው ክትባት ለመስጠት ጥረት ተደርጓል:: መድሃኒት በጣም በከፍተኛ ወጪ እንዲገባ ተደርጓል::

እንደዚህ አይነት ወረርሽኖች ተዘጋጅተን አስበን አቅደን የምንጠብቃቸው ስለማይሆኑ የሚያስከትሉት አደጋ እንዳለ ይታወቃል:: ለመከላከል የነበረው ጥረትና ውጤት ግን የሚናቅ አይደለም:: በቀጣይም ያን እያጠናከሩ መሄድ ያስፈልጋል:: በድምሩ በሰሞኑ ያያችሁት የፕሮጀክት አይነት ሥራ የጤናውን ዘርፍ እንድታዩ አደራ እላችኋለሁ::

ጤናንን በሚመለከት በአዲስ አበባም፤ ከአዲስ አበባ ውጭም በጣም በርካታ በጅምር ያሉ ሥራዎች አሉ:: ሰፋፊ የሆስፒታል ግንባታዎች አሉ:: የላብራቶሪ ግንባታዎች አሉ:: የቀደመውን ማደስና ማሻሻል ሥራዎች አሉ:: እነዚህ ተደምረው የተሞላ ውጤት የሚያመጡና ውጤቱ የሚታይበት ጊዜ ገና ቢሆንም እየተሠራ ያለው ጥረት በጣም ከፍተኛ መሆኑን ፤ የተከበረው ምክር ቤትም ጊዜ ሲኖረውና ሲመች እነዚህ ጀማሮች ሥራዎች ማየት ቢችል ጠቃሚ ይሆናል ብዬ አስባለሁ::

ከኢኮኖሚ ጉዳዮች ጋር ተያይዘው የተነሱ ጥያቄዎች የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ “የሆም ግሮውን ሪፎርም” አጀንዳ ቀርፀን  ስንሠራ ዋና ዋና ልናሳካ ካሰብናቸው አንኳር አንኳር ጉዳዮች አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታችንን ማረጋጋት ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት አለ፤ ማክሮ ኢኮኖሚ አለመጣጣም “ኢምባላንስ” አለ፤ ያንን ማረጋጋት አንዱ ሁነኛ ግባችን ነበር።

ሁለተኛው ኢንቨስትመንትና የንግድ ከባቢን ማዘመን፣ ማሻሻል ነው። ቅድም ሲነሳ የነበረው የቡና ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱን ማዘመን፣ ማሻሻል፤ የዘርፎችን ምርታማነት መጨመር፣ በግብርና እንደታየው በሁሉም ዘርፎች ምርታማነትን ማሳደግ ሌላው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ “የሆም ግሮዎን ሪፎርም ” አጀንዳ “ፒላራችን” ነበር።

ሶስተኛው የመንግሥት አቅምን ማሳደግ ነው። ተቋም መገንባት፤ የማስፈፀም አቅምን ማጎልበት፤ የሲቪል ሰርቪሱን የመከወን አቅም እያጎለበቱ መሄድ በሆም ግሮውን አጀንዳ ከያዝናቸው ፕሮግራሞች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በድምሩ ኢኮኖሚን በሚመለከት “ከግሬይ ወደ ግሪን” ኢኮኖሚ ማሳደግ ሲባል፣ ከተማ ልማት ላይ ሲሚንቶ ብቻ፣ ኮንክሪት ብቻ እንዳይሆን አረንጓዴ የሆነ ለሰው ልጅ ተስማሚ የሆነ፣ ውሃ ያለበት ዛፍ ያለበት ከተማ መፍጠር ላይ መሥራት፤ ግብርናችንም ላይ እንደዚሁ የሚባክን ውሃ፣ የሚባክን መሬት ላይ እንሥራ፤ የሰው ጉልበትን ከሥራ ጋር እናገናኝ የሚል እሳቤ በውስጡ የያዘ ነው።

ባለፉት አምስት ዓመታት እንደማንኛውም፣ በዓለም ላይ እንደሆነው ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በእኛም ሀገር ነበር ። ውጊያ ነበር፤ ኮረና ነበር፤ የዓለም የንግድ ሥርዓት መዛባት ያስከተለው ጫና ነበር። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ አቅጣጫዎችን በመከተላችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ “ጂዲፒያችን” በ5 ዓመት ውስጥ በደብል አድጓል። እኛ ወደ ቢሮ ስንመጣ የኢትዮጵያ ጂዲፒ ወደ 84 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው። አሁን ወደ 164 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ደርሷል።

ይሄ በኢትዮጵያ መንግሥት የተነገረ ዳታ ሳይሆን የአይኤምኤፍን ዳታ ነው እንዳለ ማሳየው። የሰው ነፍስ ወከፍ ገቢያችን 882 ዶላር ነበር፤ አሁን 1 ሺ549 ዶላር ደርሷል፤ እሱም ደብል አድጓል። በአፍሪካም ሆነ በዓለም የኢትዮጵያ እድገት ፈጣን እድገት መሆኑ ያው የታወቀ ሀቅ ነው። ሥራውም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኢኮኖሚ እድገቶች የእያንዳንዱን ቤተሰብ ችግር ፈትተዋል ወይ፣ የኑሮ ውድነቱን፣ ሲነሱ የነበሩ መከራዎችን ሁሉ ፈትተዋል ወይ? የምትሉ ከሆነ በእኔ እምነት የእኔና የእናንተ ዘመን ሥራ፣ እንደ ብልፅግናም የእኛ ሥራ መሠረት መጣል ይመስለኛል፣ ለሺህ ዓመት የኖረ፣ የቆየ ችግር በአስር ዓመት አንፈታም። መሠረት ነው የምንጥለው።

ከዛ ልጆቻችን እያሻሻሉ፣ እያዘመኑ ይቀጥላሉ ነው እንጂ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ድህነትና ችግር እንደዚህ በቀላሉ የሚፈታ ቢሆን ለምን እንደዚህ እስካሁን እንቸገራለን። ያለንበትን የችግር ጥልቀት፣ የድህነት ጥልቀት በወጉ መገንዘብና ረዘም ያለ አታካች ሥራ መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።

ከግብርና አንፃር ውጤት ለማየት ግብርና ሰፊ ኢንተርቬንሽን ተደርጎበታል። ባለፈው ዓመት 6 ነጥብ 3 ፐርሰንት ነው የግብርና አጠቃላይ እድገት። በተለይ የሰብል ምርት 7 ነጥብ 1 ገደማ አድጓል። እንደተባለውም ወደ 20 ሚሊዮን ሄክታር አካባቢ አርሰን ከ600 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ችለናል። በዚህ ዓመት ግን ከ22 ሚሊዮን ሄክታር በላይ እናርሳለን። ከ800 ሚሊዮን በላይ ምርት እንሰበስባለን ብለን አቅደን እየሠራን ነው። አሁን እየሠራን ያለነው የክረምት ሥራ እንደሚያሳየው ያንን ልናሳካ እንደምንችል ነው።

በመስኖ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር የበጋ ስንዴ ለመዝራት አቅደን እየሠራን ነው። አያያዛችንና አካሄዳችን የምናሳካ ይመስላል፤ ተረባርበን ማሳካት ነው። 22 ሚሊዮን ሄክታር አረስን ማለት ከዚህ በፊት የማይታረስ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ጨመርን ማለት ነው። ይህ በጣም በጣም ትልቅ ስኬት (አቺቭመንት) ነው። በኩንታል ብቻ ሳይሆን በመሬቱም።

ሥራ አጥነት ላይ፣ ኑሮ ማረጋጋት ላይ፣ በኢኮኖሚውም ላይ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጣ ስለሆነ በግብርናው ላይ ያመጣነውን አበረታች ውጤት አጠናክረን መቀጠል አለብን። ይህንን በማሰብ በዘርፉ የምንሰማራ ሰዎች ከአርሶ አደሩ ጋር በዘርፉ የምንሳተፍ ሰዎች በሙሉ በርብርብ መሥራት ይኖርብናል።

ከኢንዱስትሪ አንጻር የተመዘገበው ዕድገት ስድስት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ነበር:: በዚህ ዓመት። በተለይ የኤሌክትሪክ ዘርፍ ከፍተኛ እድገት ነበረው። ከ 12 በመቶ በላይ አድጓል። የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሰባት ነጥብ አንድ በመቶ አድጓል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም ሰባት በመቶ አድጓል።

ለእኛ በጣም አስፈላጊው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ስለሆን ኢትዮጵያ ታምርት በሚለው እንቅስቃሴ ሁላችሁም እንደምታስታውሱት የማምረት አቅማችን ያሉት ፋብሪካዎች ተደምረው የሚያመርቱት 47 ፐርሰንት ገደማ ነበር አሁን 55 ፐርሰንት ደርሷል። ስምንት ፐርሰንት ጨምሯል ማለት ነው። ይሄ አሁን መቀጠል ያለበት ቢሆንም እንደ ውጤት ግን በጣም ተስፋ ሰጪ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።

አሁን ባለው የማምረት አቅማችን ጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ 63 ፐርሰንት ደርሷል ። ቆዳ 58 ፐርሰንት ፤ የቴክኖሎጂ 35 ፐርሰንት ደርሷል። የኬሚካል ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ 68 ፐርሰንት ደርሷል። ወደ ኋላ የዘገዩት በአማካኝ “በአቨሬጅ” ሲወሰድ ግን 55 ፐርሰንት ነው።

የቀሩትን ደግፈን 60 ስድሳአምስት ብናደርስ ተጨማሪ ፋብሪካ ሳንጨምር ባሉን ፋብሪካዎች ምርታማነትን ይበልጥ ማሳደግ እንችላለን ልክ በእርሻ ክላስተር ብለን በጋና ክረምት ብለን ምርታማነት ባለው መሬት ላይ እንደጨመርነው ሁሉ ባሉ ፋብሪካዎችም አንዳንድ ችግሮችን በመቀነስ ምርታማነት መጨመር እንደሚቻል ያሳያል።

ተኪ ምርቶች ላይ አንዱ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎታችንን የሚያሳድገው ተኪ ምርት ስለሆነ ባለፉት ዓመታት በነበረው ሥራ 30 ፐርሰንት ነበር የምናመርተው ለሀገር ውስጥ ፍላጎት የሚውሉ ምርቶች አሁን 38 ደርሰናል። ለምሳሌ የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ ኢንፖርት አቁመናል። ከግብርና አንጻር የቢራ ገብስ እንዲሁ አቁመናል። እነዚህን እያሰፋን ብንሄድ ተኪ ምርቶችን ብናሳድግ በእጅጉ ኢኮኖሚያችን ላይ ኢንፓክት ሊያመጣ ይችላል።

የሰርቪስ ኢንዱስትሪው በድምር ሲታይ 7.9 ፐርሰንት ነው ያደገው በተለይ ትራንስፖርትና ኮምኒኬሽን ሰፋ ያለ እድገት አለው። 12 ፐርሰንት ገደማ አለው። የኢትዮጵያ አየር መንገድም ኢትዮ ቴሌኮምም ከፍተኛ እድገት አለው።

የሆቴል ዘርፉ ከ10 ፐርሰንት በላይ አድጓል በዚህ ዓመት ይበልጥ እንደሚያድግ ይጠበቃል። በቅርቡ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሰፋ ያለ መነቃቃት ኢትዮጵያ እንዳላት ጠቁመዋል። የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እየሰፋ ይገኛል በዚህ በድምሩ ኢኮኖሚያችን በዚህ ዓመት ባቀድነው ልክ ሊያድግ እንደሚችል ተስፋ ይደረጋል።

በርግጥ ገና የመጀመሪያው ኳርተር ስለሆነ ሦስት ሩብ ዓመቶችን በከፍተኛ ደረጃ መሥራት የሚጠበቅብን ቢሆንም ያቀድነውን እቅድ ልናሳካ እንደምንችል እስካሁን ያሉ ምልክቶች ያሳያሉ። ተግተን በታማኝነት ከሠራን ሊሳካ የሚችል ይመስለኛል።

የመንግሥት ገቢና ወጪን በሚመለከት በአሃዝ ሲታይ መሻሻሎች አሉት። አሁንም ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም። በ2011 አጠቃላይ ገቢያችን 2 መቶ ሰላሳ አምስት ቢሊዮን ነበር። ባለፈው ዓመት 4 መቶ ሰባት ቢሊዮን ገቢ አስገብተናል። የዚህ ዓመት እቅዳችን ግን 5 መቶ ሃያ ቢሊዮን ነው።

በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከ ሁለት ሰላሳ ፣ አምስት ሃያ መድረስ በፊገር ሲታይ ትልቅ ነው። ኢትዮጵያ ከምታመርተው ከኢኮኖሚው አንጻር ሲታይ ግን ከዚህ በላይ ሊሻሻል የሚገባው ሴክተር እንደሆነ ያሳያል። በቁጥር ያለው እድገት ጥሩ ቢሆንም ካለው አጠቃላይ አቅም አንጻር ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል።

በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ገብቷል። ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር 12 ፐርሰንት ገደማ እድገት አለው። ይሄን እድገት ማሻሻል እና በገቢ ያለብንን ውስንነትና አቅም ማነስ መሙላት ይኖርብናል። ወጪን በሚመለከት 141 ቢሊዮን ብር ነው ባለፉት ሦስት ወራት ያወጣነው። ይሄም ከዓምናው ወደ 20 ፐርሰንት እድገት አለው። አሁንም ገቢያችንና ወጪያችን ላይ ተጨማሪ ሥራ የሚያስፈልግ መሆኑን ያሳያል።

ከፋይናንስ ዘርፍ አንጻር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ከመቶ በላይ የፋይናንስ ሰርቪስ የሚሰጡ ተቋማት አሉ። ቁጥራቸው በጣም እየበዛ ሄዷል። 31 ገደማ የንግድ ባንኮች አሉ። 48 ገደማ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት አሉ። ስድስት የክፍያ ሰርቪስ የሚሰጡ ኩባንያዎች አሉ። ስድስት የካፒታል እቃዎች ገቢ ላይ የሚሠሩ ኩባንያዎች አሉ። ሰባት ገደማ የሞባይል ዋሌት ሰርቪስ የሚሰጡ ተቋማት አሉ።

እንግዲህ ናሽናል ባንክን በተመለከተ ድሮ የነበረው አይነት ውስን ቁጥር ሳይሆን ሰፋ ያለ የፋይናንስ ሴክተር ላይ የሚሠሩ ተቋማትን ወደ መቆጣጠር እያደገ መጥቷል ማለት ነው:: ያም ሆኖ ብሔራዊ ባንክን በሚመለከት ሪፎርም ያስፈልጋል:: ማጠናከር አለብን በሚል እሳቤ አዳዲስ አመራሮች እና አሠራሮች ለማሻሻል ሙከራ ተደርጓል:: ውጤት እንደሚያመጡም ተስፋ ይደረጋል::

አጠቃላይ ፋይናንሺያል ሴክተር እያደገ ሲሄድ በዛ ልክ የቁጥጥር አቅማችን እያደገ መሄድ እንደሚጠይቅ ይታወቃል:: እየተሠራ ያለው ሥራም ይህን ያመላክታል:: ባለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ በአማካኝ “በአቭሬጅ” 20 ፐርሰንት እያደገ መጥቷል የፋይናንስ ሴክተር:: 20 ፐርሰንት እድገት ገቨርን ማድረግ ደግሞ በዛው ልክ ያደገ የቁጥጥር አቅም ይጠይቃል ማለት ነው::

ብድርን በሚመለከት በሁለት መንገድ ከፍሎ ማየት ጥሩ ነው:: በአንድ በኩል የብድር መጠን በከፍተኛ ደረጃ አድጓል:: በባለፈው ዓመት 547 ቢሊዮን ብር ለብድር ውሏል:: ይሄ በጣም በጣም ትልቅ ነው ከቁጥር አንጻር:: ከዚህ ውስጥ 86 ፐርሰንቱ ደግሞ ለግል ሴክተር ነው የተሰጠው:: ከዚህ ቀደም የነበረው አብዛኛውን ብድር የሚወስደው የመንግሥት ኩባንያ የነበረው ቀርቶ የግል ሴክተሩ ሰፋ ያለ ገንዘብ እንዲያገኝ ሆኗል::

ከዚህ ውስጥ የአርሶ አደሮች ባለፈው የተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ወደ 15 ፐርሰንት ዕድገት አለው:: በቂ ነው ወይ? ያላችሁ እንደሆነ የለም በቂ አይደለም:: የኢትዮጵያ ብድር የኢትዮጵያ ባንኮች ባለፈውም አንስቻለሁ ተደምሮ እስካሁን ለግማሽ ሚሊዮን ሰው አላበደሩም:: ከነዚህም ውስጥ ዋና ዋና ተበዳሪ የሚባሉት በጣም ጥቂት ሺ ሰዎች ናቸው:: ለዚህ ነው ነባር ነጋዴዎች እየጠፉ አዳዲሶች የሚባለው:: ገንዘቡ በስፋት ሲሄድ ነባሮች ብቻችንን መጠቀም አለብን የሚል ዕምነት ስላላቸውም ጭምር ነው::

ሀብቱ የጋራ ነው በጋራ መሥራት አለበት ሳይሆን እንደተለመደው ጥቂቶች የሚበደሩት ጥቂቶች መኪናም ቤትም የሚያስፋፋበት አብዛኛው ያንን የሚከተልበት አካሄድ ነው ፍላጎቱ ያንን አናደርግም:: አናደርግም:: በሂደት እያስፋፋን እንሄዳለን:: ሁሉ ሰው ለማልማት በፈለገው ልክ ለመበደር በፈለገው ልክ ብር የሚገኝበት ሀገር አይደለም ኢትዮጵያ:: እንደዛ አይደለም:: ግለሰብ ሳይሆን መንግሥትም ሊሠራ ባቀደው ልክ ፋይናንስ አያገኝም የገንዘብ የካፒታል እጥረት አለብን:: ባለን ካፒታል ውስጥ ነው የምንሠራው:: ያ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን የብድር መጠን አድጓል:: የቀነሰበት የለም::

ሁለተኛ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ከዚህ ቀደም መቶ ሚሊዮን ፣ ሁለት መቶ ሚሊዮን ሲበደር የነበረ ሰው እንደ ትልቅ ድል ቢያየውም አሁን ቢሊዮን ቢበደርም በቂ አይደለም:: በቂ አይደለም ሰፊ ሥራ ስላለ ብዙ ብር ይፈልጋል::

የተከበረው ምክርቤት ግን ማወቅ ያለበት የዛሬ ሁለት ሦስት ዓመት ገዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሚሠራው በአብዛኛው በመንግሥት ነው:: አሁን ግን ግለሰቦች ኢዱስትሪያል ፓርክ ይሠራሉ:: ማየት አለባችሁ:: እንኳን ኢንዱስትሪያል ፓርክ የአንድ ፋብሪካ ባለቤት መሆን በስፋት የማይታይበት ሀገር ውስጥ አሁን አስር፤ አስራ አምስት ፋብሪካ በአንድ ጊቢ ውስጥ የሚሠሩ ግለሰቦች እየተፈጠሩ ሄደዋል::

የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ብቻውን ቢወሰድ እኮ ብቻውን በጣም በጣም ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው:: ኢትዮጵያ እስካሁን ያላትን ምርት ደምሮ ግማሽ ያክል የሚያመርት ፋብሪካ ነው:: ይሄ በከፍተኛ ድጋፍ ጭምር የሚሠራ ነው:: ግለሰቦች አሁን ለቦሌ ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ መቶ ሁለት መቶ ሚሊዮን ዶላር ማበደር በቂ አይደለም:: በጣም ትልቅ ኢንቨስትመንት ስለሆነ:: መቶ ሚሊዮን ዶላር መስጠት ግን ድሮ በዋዛ የሚቻል አልነበረም::

እያደግን ስንሄድ ፍላጎታችን እያደገ በዚያ ልክ እርካታ እያጣን እንደምንሄድ መታሰብ አለበት:: ከማዳረስ አንጻር ግን ሞባይል መኒን ብንወስድ ሰባት ቢሊዮን ብር ፤ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተበድረዋል:: ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ ብድር ያገኘው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሞባይል መኒ ነው:: ባንኮች ተደምረው የዚህን አንድ አምስተኛ ፤ስድስተኛ እንኳን አያበድሩም:: ይሄ መቀየር አለበት:: መሻሻል አለበት በጊዜ ብዛት:: ሰውም እየለመደ መበደር አለበት:: በቀላሉ ፋይናንስ የሚገኝበት ሥርዓት ማበጀት ያስፈልጋል::

ቁጠባ እንዲሁ እያደገ ነው፣ 17 ነጥብ ስምንት ነው አምና የነበረው ባለፈው ዓመት በዚህ ዓመት ወደ ሁለት ነጥብ ስድስት ትሪሊዮን ለመድረስ እየተሠራ ነው:: እንደሚሳካ ተስፋ ይደረጋል ፤ብርም ሰብሰብ እያደረግን ስለሆነ:: ብር በዋዛ ማግኘት ተቸግረናል ያሉትም የተከበሩ የምክር ቤት አባል አዎ ብር በዋዛ በሚገኝበት ሰዓት ለቁጥጥር የማይመቹ ጉዳዮች ስላሉ ትንሽ ብር የመያዝ ሁኔታ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል:: ያ ችግር አጋጠመ ያሉት እርሶ እሱ ከኢንፊሌሽን አንጻር ትርጉም ስላለው በሌላ በሥራ መስክ የሚቸግር ነገር ካለ እየፈተሽን እያረምን ለመሄድ እንሞክራለን::

እዳን በሚመለከት የሰብ-ሰሃራ ሀገራት እዳ አጠቃላይ 55 ፐርሰንት ገደማ ደርሷል:: የሰብ-ሰሃራ የውጭ እዳ 25 ፐርሰንት ደርሷል:: ታስታውሳላችሁ ከተረከብናቸው አንዱ ትልቁ ነገር እዳ ነው:: ዓለም ላይ ዞረን እባካችሁን እዳችሁን አሸጋሽጉ ብለን እምንለምነው እኛ የተበደርነው እዳ አይደለም:: የቀደመው መንግሥት የተበደረው በትክክል ምን ላይ እንዳዋለው የማናውቀውን የገንዘብ እዳ እኛ ልክ እንደፖለቲካል እዳ መክፈል ስላለብን፤ የተረከብን መንግሥት ስለሆን ነው የምንደራደረው::

ባለፉት ዓምስት ዓመታት በነበረው ሰፊ ሥራ አሁን የኢትዮጵያ አጠቃላይ እዳ 31 ፐርሰንት ገደማ ነው:: የሀገር ውስጡን ጨምሮ የውጭ ሀገር እዳችን ግን ወደ 14 ነጥብ ስምንት ፐርሰንት አድጓል:: ከሃያ ምናምን ፐርሰንት 14 አስገብተነዋል፤ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ይሄ ቁጥር እየቀነሰ ከአስር በታች እንደሚሆን ይጠበቃል:: ከአስር በታች ሲሆን በጣም በጣም ጠቃሚና በቀላሉ የምንወጣው ስለሚሆን።

የውጭ ምንዛሬን በሚመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ችግር ያልሆነበት ዘመን ያለ አይመስለኝም:: በቂ ዶላር አምርተን አናውቅም:: እንደዚህ እንደዛሬ በጣም ሜጋ ሜጋ ፕሮጀክቶች ባሉበት ጊዜ ሳይሆን፤ ሰፊ ሥራ ባልነበረበት ጊዜም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው አንዱ የፖለቲካል ችግር እኮ የነዳጅ ዋጋ ከፍ ማለትና የዶላር ማነስ ነው:: የንጉሡን መንግሥት ነቀነቀ ከሚባለው ጉዳይ አንዱ የነዳጅ ዋጋ ከፍ ማለት ነው:: ሁሌም ችግር ነበር ማለት ነው:: በቂ አምርተን በቂ ሸጠን አናውቅም፤ በኤክስፖርትና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ግን በ2014 የነበረንን ግኝት በታሪካችን አግኝተን አናውቅም::

በቂ አይደለም ነው ያልነው እንጂ ከነበረው ያንሳል ማለት አይደለም:: የውጭ ምንዛሬ ኢንፍሎውንም ስንመለከት በሰርቪስ ወደ ሰባት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር አግኝተናል:: በሀዋላ ስድስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ገደማ አግኝተናል:: በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሦስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ገደማ አግኝተናል:: ከሌሎች ደግሞ ብድር ርዳታና ከሌሎች ምንጮች ወደ ሦስት ቢሊዮን ገደማ አግኝተናል:: በድምሩ በ2013 21 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ነው ያገኘነው፤ በ2014 ደግሞ ባለፈው ዓመት 23 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ነው ያገኘነው::

በሁለቱ መካከል ስምንት ነጥብ ሁለት ፐርሰንት እድገት አለ:: ከአቻምናው ዓምና የነበረው እድገት ስምንት ነጥብ ሁለት ፐርሰንት እድገት አለው፤ የውጭ ምንዛሬ ኢንፍሎው ዘንድሮ ደግሞ 25 ቢሊዮን ለማድረስ ነው እየሠራን ያለነው:: በቂ ነው? አይደለም:: ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ አቅም ፍላጎት አንጻር በቂ አይደለም:: እድገቱን ግን በፊገር ደረጃ ዲናይ ማድረግ አያስፈልግም::

የውጭ ምንዛሬ ኢንፍሎው እያደገ የእኛ ፍላጎት በጣም እየሰፋ ስለሆነ በቂ የሚባል ደረጃ አልደረሰም:: በተለይ የኤክስፖርት ውጤታችን ሰፊ ሥራ ያስፈልገዋል የሚለውን መውሰድ ጠቃሚ ይሆናል:: የእኛ ዋናው ችግር ወጪያችን ነው:: ነዳጅ ባለፉት አምስት ዓመታት እንኳን የምናወጣው ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፤ ማዳበሪያ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል:: የእዳ ክፍያ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፤ በብዙ ምክንያት ወለድም የራሱ ችግር አለበት በብዙ ምክንያት፤ መድሃኒት ቅድም እንዳነሳችሁት ወጪ አብዝቷል::

የእኛ ደግሞ ወርቃችን፣ ቡናችን በዚያ ልክ ማደግ ስላልቻለ የውጭ ምንዛሬ እጥረቶች አሉ:: ከቡና ንግድ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ አጠቃላይ የቡና ንግድ ያው ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ማቹር ያደረገ የገበያ ሥርዓት ካለን የቡና ንግድ ነው:: ልክ እንደቡና ስንዴም እንደቡና ወርቅም እንደቡና በቆሎም ሩዝም ቢደርስ በጣም ጥሩ ነበር:: የተሻለ የሚባለው የገበያ ዋጋ ትመና የማንቸገርበት ኤርያ ቡና ነው:: ቡና ጋር ያለው ችግር የንግድ ሰንሰለቱን የተቆጣጠሩ ኃይሎች የሚፈጥሩት ችግር ነው::

ዓለም ዋጋ በሚወድቅበት ሰዓት በመንግሥት ብድር እንኳን ሰፊ ቡና የገዙ ኃይሎች ቡናቸውን ያስቀምጣሉ ኤክስፖርት አያደርጉም:: ይሄ ችግር ፈጥሯል፤ ለዚህ ደግሞ ማስተካከያ የተደረገው አንደኛው ለምሳሌ የጌድኦ አርሶአደሮች ጨምሮ በቀጥታ ኤክስፖርት ማድረግ እንዲችሉ /በማህበር/ በአዲሱ አሠራር ይፈቅዳል:: ይሄ የሆነበት ምክንያት አምራቾች መሃል ባሉ ነጋዴዎች ምክንያት ምርታቸውን ሳይሸጡ እንዳይቀሩ ለማገዝ ነው:: በዚህም ደግሞ በጣም ሰፊ ገበያ ያገኙ አርሶ አደሮች አሉ:: እኔ ራሴ አንድ ሚሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ያደረገ አርሶአደር አግኝቻለሁ በቅርቡ:: ከዚህ ቀደም የማያደርግ አሁን ቡናውን ቀጥታ ሸጦ ገንዘብ ያገኘ ሰው አግኝቼ አናግሬያለሁ::

ይሄ አሠራር መስፋት አለበት ጌዴኦ በጣም በቡና ምርት የታደለ አካባቢ ነው:: በጣም ጣዕም ያለው ቡና የሚያመርት አካባቢ ነው:: በገበያ ምክንያት እንዳበላሽ ተረባርበን ሁላችንም መሥራት ይኖርብናል:: ቡና በጣም አስፈላጊ የገቢ ምንጫችን ስለሆነ አርሶ አደሩም በደንብ የተላመደው ምርት ስለሆነ በዓለም ገበያ ሥርዓት ውስጥም በቀላሉ የተላመድነው ምርት ስለሆነ በቀላሉ እንዲበላሽ መደረግ የለበትም::

ፈተናዎች ግን አሉበት በዚያ አግባብ ቢታይ ጥሩ ነው፤ ለምሳሌ ዘንድሮ የሩዝ ምርት በክረምቱም በበጋውም በስፋት ተሠርቷል:: አንድ ሚሊዮን ሄክታር ገደማ ሩዝ አርሰናል:: ከአርባ ሚሊዮን በላይ ኩንታል   ሩዝ እንጠብቃለን:: የዛሬ ሁለት ዓመት ችግራችን ሩዝ ማምረት ነበረ፤ ዘንድሮ ሩዝ ካመረትን በኋላ ችግር የሆነብን መፈልፈያው ነው:: ለካ ሩዝ ይፈለፈላል እንደ ስንዴ አይደለም እኛ ያለን መፈልፈያ ያመረትነውን ሩዝ ያህል አይሆንም::

አርሶ አደሩ ድፍን ሩዝ ነው የያዘው አሁን፤ በፍጥነት ማሽን አምጥተን ካልፈለፈልን በቀር አይበላም አይሸጥም:: አዲስ ቻሌንጅ ነው፤ ያ ደግሞ ሲመጣ ገበያው ችግር ይሆናል:: ገበያው ደግሞ ሲፈታ ሁሌ አዳዲስ ፈተና እያየን እየፈታን መሄድ ነው ያለው አማራጭ:: በቡናም የነበረውን ነገር እንዲሁ እያሻሻሉ መሄድ ያስፈልጋል:: ትኩረት ያስፈልገዋል፤ ቡና:: ቡና የኢትዮጵያ ኤክስፖርት የጀርባ አጥንት ነው:: ቡና ከተመታ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ይመታል:: ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፣ ሥራ ያስፈልገዋል ችግሩን እያየን መፍታት ይኖርብናል:: በዚህ አግባብ መመልከት ጥሩ ይመስለኛል::

ግሽበትን በሚመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ ውድነት አለ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በኑሮ ውድነት ምክንያት ለመመገብ ይቸገራሉ:: ምንም ጥያቄ የለውም ይሄ እውነት ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን እዚሁ ከእኛ ቢሮ በመቶ ሜትር ሰዎች ይቸገራሉ:: ሩቅ መሄድ አያስፈልጋችሁም፤ ምክንያቱም እንደ አይኤምኤፍ ዘገባ አሁን ዓለም ላይ ያለው የግሽበት ሬት ባለፉት አርባ ዓመታት አልታየም:: ባለፉት አርባ ዓመታት ያልታየ የዋጋ ግሽበት ነው ዓለም ላይ ያለው:: ግን የኢትዮጵያ ችግር ብቻ ሳይሆን የዓለም ችግር ነው:: የኢትዮጵያን ያባባሰው የዋጋ ግሽበቱ የገቢ አቅማችን ዝቅተኛ በሆነበት ሁኔታና ላለፉት በርካታ ዓመታት ወደ 20 ዓመት ሳቋረጥ እያደገ ስለመጣ የሰው ገቢና ግሽበት እድገት ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ ኑሮ ላይ ጫና አምጥቷል::

ምንም የሚካድ ነገር አይደለም፤ ታስታውሱ ከሆነ አምና ዋናው ችግራችን ልንሠራበት የሚገባው አንዱ ግሽበት ነው ብዬ ነበር:: ግን ግሽበት ማለት ምን ማለት ነው፣ አንዳንዴ ግሽበትንና የኑሮ ውድነትን አንድና ያው አድርገን እናያለን:: ያው አይደለም፤ ተመጋጋቢ ነው::

የዋጋ ግሽበት ማለት የሸቀጥ ወይም የአገልግሎት የዋጋ እድገት ምጣኔ ማለት ነው:: በአንድ አገልግሎት ላይ በአንድ ምርት ላይ ያለው የዋጋ ምጣኔ ነው የዋጋ ግሽበት የሚባለው:: የኑሮ ውድደነትን የሚያባብስ አንድ ነገር እንጂ በድምሩ ኑሮ ውድነት የሚፈጠረው በግሽበት አይደለም:: ግሽበት እያለ ኑሮ ውድ ላይሆን ይችላል:: በቂ ገቢ ላላቸው ግለሰቦች እና ሀገራት::

የእኛ ችግር የሆነው ገቢያችን በዚያ ልክ እያደገ ስለማይሄድ ነው:: ዘንድሮ ያለው ሁኔታ ግን የዓለም አጠቃላይ ዋጋ ሁኔታ መረጋጋት እያሳየ፣ መረጋጋት ማሳየቱ እንደሚቀጥል ነው የሚተነበየው:: በፋይናንሻል ተቋማት የሚነገረው ይረጋጋል የሚለው ነው:: እኛንም ብትወስዱ ዓምና ስንነጋገር 37 ከመቶ ነበር አሁን ዘንድሮ መስከረም 28 ከመቶ ወርዷል:: ይሄ ማለት ኑሮ ውድነት አይደለም ይሄ ማለት የዋጋ ተመን አይደለም:: የዋጋ እድገት ምጣኔ ነው:: የሚያድግበት ሬት ከ37 ከመቶ ወደ 28 ዝቅ ብሏል ዘንድሮ፤ ይሄን ማጠናከር ያስፈልጋል::

በዚህ ዓመትና ምናልባት በሚቀጥለው ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ይወርዳል ተብሎ ይታሰባል:: ይህ ጉዳይ ያወሳሰበው ነገር የኛ የተደመረ ችግር ብቻ ሳይሆን ያደጉ ሀገራት የወሰዱት እርምጃ ጭምር ነው:: እነሱ ኢንፍሌሽን ሲመጣባቸው የኢንተርስት ሬታቸውን በማሳደጋቸው እኛ የዕዳ ክፍያችንም እንዲያድግ ፤ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችንም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጎዳ ሆኗል፤ ብዙዎቻችን ማለት ነው:: ብዙ ደሃ የምንባል ሀገራት፤ በነገራችን ላይ በዚህ ኢንፍሌሽን ምክንያት የውጭ ምንዛሬ ብቻ ሳይሆን ኤክስፖርትን ያገዱ ሀገራት አሉ::

ሩዝ፣ ስንዴ እንዳይሸጥ ያሉ ሀገራት አሉ:: ባለፉት ዓመታት ያልነበረ በዚህ ችግር ምክንያት ያጋጠመ ሁኔታ ነው የተፈጠረው ኮሮና፣ ጦርነቶች የንግድ ሥርዓት መዛባት የዓለም ኦርደር በጣም መፈተኑ እንደኛ ለማደግ በምንፍጨረጨር ሀገር ላይ ከፍተኛ ጫና አምጥቷል:: እንግዲህ ፈተናን አናስቀረውም፣ ፈተና አንፈልግህምና አትምጣ አንለውም፣ ግን ፈተና ሁሌ መልኩ ስለሚለያይ መልኩ የተለያየውን ፈተና እንደ አግባቡ ተገንዘቦ መወጣት ብቻ ነው ያለው መፍትሔ::

ዳዊት ወይም ዳውድ የሚባለው የእስራኤል ንጉሥ በእረኝነት ዘመኑ የነበረበት ፈተና እና በጎሊያድ ጦርነት የነበረው ፈተና አንድ አይደለም፤ ይለያያል:: በእረኝነት ቢበዛ በአንበሳ መበላት ነው፣ ቢበዛ አልቅሶ አባት እናቱ ጋር መሄድ ነው:: ጎልያድ ጋር ሲፋለም መልኩ ተቀይሯል:: ጎልያድን ካሸነፈ በኋላም ከሳኦል ጋር ያለው ጨዋታ እንደዚሁ መልኩ የተቀየረ ነው፤ አንድ አይደለም::

ለዘመኑ ፈተና እራስን ማዘጋጀት እንጂ ፈተና አልፎ ጉዞ የለም:: እንፈተናለን ለዛ ፍቺ እያዘጋጀን እያለፍን እያሸነፍን የምንሄድበት መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል:: ከኛ አንጻር ምን አደረግን ያላቹ እንደሆነ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎቻችን እጅ አጠር ዜጎቻችን እንዳይጎዱ አንደኛ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ሀብት በከፍተኛ ደረጃ ለመያዝ ሞከርን ቅድም እንደ ተገለጸው:: ለምሳሌ የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ፣ የቦንድ ሽያጭ በከፍተኛ ደረጃ ገንዘብ ሳክ ለማድረግ አግዟል::

ምርታማነትን ማሳደግ መቼም ኢትዮጵያ በስንዴ፣ በሩዝ፣ በቡና፣ በሻይ በፍሩት ያለውን ምርታማነት እድገት የማይገነዘብ ማንም ሰው አለ ብዬ አላስብም:: ምንም እኮ ነጋሪ አያስፈልገውም መንዳት ነው:: ከአዲስ አበባ ስትወጡ በግራ በቀኝ ይታያል:: በቂ ነው አይደለም ገና ሰፊ ሥራ ያስፈልገናል:: ግን እድገቱ አለ ያ እድገት በተወሰነ ደረጃ አግዟል ለምሳሌ የዛሬ 2003 ዓ.ም 700፣ 800 ሚሊዮን ዶላር ስንዴ እናመጣ ነበር:: ዘንድሮስ ብናመጣ እንችል ነበር ስንዴውስ አለ ወይ ሁለተኛ ልናመጣ የሚያስችል ገንዘቡስ አለ ወይ የሚለው ጉዳይ ከፍተኛ ፈተና ነው::

አሁን ምርቱ አለ ምርቱና ገበያው አይጣጣምም ፤ አንድም በዋጋ ሁለትም በተደራሽነት። በዋጋ ያለው ችግር ስንዴን ማምረት ቻልን እንጂ ፓምፕ ማምረት አልቻልንም፣ ትራክተር ማምረት አልቻልንም፣ ማዳበርያ ማምረት አልቻልንም:: ገበሬው ለማምረት የሚያስፈልገው የዋጋ ቁለላን ካልተከላከልን በስተቀር ምርቱ ሲመረት ውድ ከሆነ ገበያ ሲወጣ እንደዚሁ ዋጋው እንደዚሁ ውድ ይሆናል:: ተጨማሪ ሥራዎችን ይጠይቃል ማለት ነው::

ድጎማን በሚመለከት ማዳበርያ ላይ፣ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ለመንግሥት ግብር አይከፍልም እንዳትረሱ፤ ግብር የማይከፍል አርሶ አደር ድጎማ የሚሰጥበት ዋና ምክንያት ምርትና ምርታማነት ካደገ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ኑሮ ይደጉማል በተዘዋዋሪ በሚል እሳቤ ነው:: ግን ማዳበርያ እንደጉማለን፣ ነዳጅ እንደጉማለን ስኳር እንደጉማለን ፣ ዘይት እንደጉማለን ቢሊየንስ ይወጣል ለዚህ:: አንዱ መደጎሚያ መንገዳችን ይሄ ነው::

አቅመ ደካሞች ምገባ ብለን አይታችሁ ሊሆን ይችላል አዲሰ አበባ ላይ የጀመርናቸው አሉ፤ የተማሪዎች ምገባ አለ፤ የቤት እድሳት አለ ፤ ይሄ ሁሉ እጅ አጠር የሆኑ ዜጎችን የሚደግፍ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ የሸማቾች ሪቮልቪንግ ፈንድ በርከት ያለ ገንዘብ በዛ በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር ውስጥ እንዲሽከረከር መንግሥት ወስኗል::

የሰንደይ ማርኬት የተባለው በብዙ መቶዎች ያደገው በተጨባጭ ዋጋ ላይ ፖዘቲቭ ኢንፓክት ያመጣው እንደተጠበቀ ሆኖ በዛ እዳያበቃ አዲስ አበባ ውስጥ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ መሸጥ እንዲችሉ የገበያ ማዕከላት እየተገነቡ ይገኛሉ እንደምታውቁት፤ በቅርቡ ኮልፌ ተመርቋል፣ ምን ማለት ነው? ሰንደይ ማርኬት ያልነው ተቸግረን ነው እንጂ ፀሐይ ላይ የዋለ ፍሩት ረሃብ ቢያስታግስም ውሎ አድሮ በሽታ ያመጣብናል። ፀሐይ የማይመታው፤ ከአቧራ የራቀ ቦታ ማዘጋጀት አለብን። መብላት ብቻ ሳይሆን ንጹህ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፤ የሚል እሳቤ በውስጡ አለ። ለዚህ ነው ቦታ ተገንብቶ አርሶ አደሮች በቀጥታ በዋጋም፤ ለጤና ተስማሚ በሆነ መንገድም፤ እንዲያቀርቡት እየተሠራ ያለው። ከዚህ አንጻር አዲስ አበባ ላይ የማየው የቤቶች ሽያጭ (የፎቅ፣ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ) ዋጋ በጣም ቀንሷል። ታውቃላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ባለፈው በጣም እየወጣ ነበር ቀንሷል አሁን። አንዳንድ ዋጋም መያዝ ተችሏል።

አንዱ አዲስ አበባ ላይ ሥራ የሚያስፈልገው ጉዳይ የቤት ኪራይ ነው። የቤት ኪራይ በትክክል ሕግ አውጥተን የማንገራው ከሆነ፤ ሰው በየቀኑ የቤት ኪራይ እየጨመረ፣ በየወሩ የቤት ኪራይ እየጨመረ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ላይ ችግር እያመጣ ነው። እሱን ማስተካከል ይኖርብናል። በቅርቡም መፍትሄ እንደሚያገኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን በዓላት ሲደርሱ፣ ዘመን መለወጫ ላይ እኮ መንግሥት ልክ ውጊያ እንደሚመራው ነው ከየ ክፍለ ሀገሩ ምርት በተለያየ መንገድ በመንግሥት ተገዝተው መጥተው እዚህ ዋጋ እንዲያረጋጉ የሚሠራው ሥራ ኦፕሬሽን እኮ ነው። ለገበያ መተው የሚገባ ቢሆንም አልተውነውም። ምክንያቱም በጣም ብዙ ቤተሰብ ስለሚጎዳ። በምግብ ማጋራትም እንደዚሁ ነው። ምግብ ስናጋራ በጣም ብዙ ሰዎች ይጠቀማሉ። እሱን ታሳቢ አድርገን በኑሮ ውድነት ያለውን ውጤት ማስቀጠል አለብን። ምርታማነት ማሳደግ አለብን፤ ሕዝባችን ያለበትን መከራ ደረጃ በደረጃ መቀነስ አለብን።

እኔ ግን ለእናንተ መንገር የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚቀጥሉት አምስትና አስር ዓመታት ከእንደዚህ አይነት ቋንቋዎች ሊወጣ አይችልም። ዶላር ያንሰናል፣ ኑሮ ውድነት ይፈትነናል፣ ምርታማነት ጥያቄ ይኖረናል፣ ተረባርበን ልጆቻችን መልሰው ይህንን ጥያቄ እንዳይጠይቁ እንሥራ እንጂ በኛ ዘመን በቀላሉ የሚፈታ አድርገን አናስበው። ለውጡ ግን የሚታይ የሚጨበጥ ነው። እድገቱም ዓለም የመሰከረው ስለሆነ ያንን ባላንስ አድርጎ ማየት ያስፈልጋል ብየ አስባለሁ።

ከሥራ ዕድል ጋር ተያይዞ ባለፈው እንዳነሳሁት አንደኛ ተቋሙን ማጠናከር ነው፣ ኦቶሜሽን ማስፋት ነው። በጣም በጣም ጥሩ ጅምር ሥራዎች እየሠሩ ነው። ዘንድሮ ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ገደማ ሰው ሥራ ለማስያዝ አቅደዋል። ይሄ እስካሁን በዚህ ደረጃ እቅድ አውጥተን አናውቅም። ባለፉት ወራት እስካሁን ባለው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰው ሥራ አስይዘዋል። በውጭ ሀገር ብቻ 100 ሺህ ሰው በሕጋዊ መንገድ የሥራ ስምሪት ሠርተዋል። ይሄ ከፍተኛ እድገት ነው። በዚህ ደረጃ አድገን አናውቅም። ይህን ነገር እያስፋፋን እያሳደግን መሄድ ያስፈልጋል። በከተማም በገጠር ያለው ምጣኔም በሰርቪስ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ ያለውን ምጣኔ አሻሽለን በርከት ያሉ ሰዎች ሥራ እንዲያገኙ ማድረግ አለብን። ያው በጉብኝታችሁ እንዳያችሁት በጣም በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን ቀንና ማታ ሥራ የሚያገኙባቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ተፈጥረዋል። መስፋት አለባቸው። ብዙ ሕዝብ ስላለን፣ ብዙ ሥራ ካልፈጠርን በስተቀር የሥራ አጥነቱ ጉዳይ ውዝፍ፤ ዕዳ የሚቀጥል ዕዳ ስለሆነ በስፋት መረባረብ ያስፈልጋል የሚባለውን በዛ ማየት ጥሩ ነው።

ማዳበሪያ በሚመለከት ዓምና የነበረው ችግር፤ የኛ ችግር ብቻ አይደለም። የንግድ ሥርዓቱ ችግር ነው። ልክ እንደ ስንዴው፣ እንደ ሩዙ ማዳበሪያውን ማግኘት በጣም ከባድ ነበር። ድርድር የሚጠይቅ ነበር። ዘንድሮ ያ ችግር እንዳያጋጥም በጊዜ ግዥ ተፈጽሟል። ኦረዲ ወደ ጅቡቲ ወደብም መጫን ተጀምሯል። እንደ ዓምናው አይነት ፈተና አይገጥመንም የሚል እምነት ነው ያለው።

ፕሮጀክት በሚመለከት አንዳንድ ቦታ ላይ የፕሮጀክት መጓተቶች፣ አለመሠራቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። አጠቃላይ ግን የሪፎርሙ ውጤት የሚያሳየው ከምንጊዜውም በላይ የፕሮጀክት አፈጻጸማችን ለውጥ እንዳለው ነው። እንዳያችሁትም በጣም በርካታ ሥራዎቻችን ሕዳሴን ጨምሮ በከፍተኛ ቁጥጥርና የአመራር ሥርዓት ለውጥ አለ። ግን የማይፈጸሙ ሥራዎች ይኖራሉ። በየወረዳው፣ በየዞኑ መንገድን ጨምሮ የማይሠሩ ሥራዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ የተከበሩ እንዳነሱት በጉራጌ በአንድ ወረዳ ውስጥ የመንገድ ጥያቄ ተጠይቆ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ ሊሆን ይችላል። በሁላችሁም ወረዳ ይሄ ጥያቄ እንዳለ ታውቃላችሁ። ነገር ግን “መቼ ይሠራል?” ላሉኝ እሳቸው ያው ፓርላማው በጀት የፈቀደ ቀን እንሠራዋለን ነው መልሱ። እዚህ መጥቶ ስለሚፈቀድ እኔ እዛው የምፈቅደው ጉዳይ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ ብየ ነው። ግን ጥያቄው ሁሉ ቦታ አለ። በጉራጌም አለ፣ በስልጤም አለ፣ በሀድያም አለ፣ በከንባታም አለ፣ እዛ አካባቢ የልማት ጥያቄ ሰፊ ነው። በተቻለ መጠን ገንዘብ ስናገኝ ለፓርላማው እያቀርብን መሠራት አለበት። መሠረታዊ ጥያቄ የለም። አሁን ከተባለ ግን አንችልም። ዛሬ ኢትዮጵያ 24 ሺህ ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ትሠራለች። አዲስ አበባ ብቻ ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ አስፋልት ይሠራል። አይታችኋል አቃቂ እኮ፣ አቃቂ አምና “ለምን አላለቀም?” ያላችሁኝ መንገድ አሁን ማለቅ ብቻ ሳይሆን እንዴት ተውቦ እንዳለቀ አይታችሁታል። ከ30 ኪሎ ሜትር ያላነሰ ሀይዌይ ተገንብቷል አቃቂ ላይ። ጉራጌም እንደዛው ነው። ድሮ ከወልቂጤ ወደጉብሬ ከጥቂት ዓመታት በፊት መንገድ አልነበረም። ጥቂት ዓመታት! አሁን ምዕራቡንና ምስራቁን የሚያገናኝ አስፓልት አለ። ከኔ በላይ እሳቸው ያውቁታል። ድሮ ወርበጪ ለመሄድ በጣም እንቸገር ነበር። አሁን ግን መንገዱ ቀሏል።

ይህ በቂ ነው ከሆነ አይበቃም:: ከዚህ በላይ መንገድ ማስፋት አለብን:: የፍጥነት መንገድ ማስፋት አለብን:: ይህ ሲሆን ነው ልማት የሚመጣው:: የእራሳቸው ወረዳም የሌሎች ወረዳም ይህ ጥያቄ እንዳለ መገንዘብ ጥሩ ነው :: እኔም አጋሮ ባለፈው ሄጄ እንደሰማችሁት የእኛ መንገድ አልተሰራም የሚል ጥያቄ ቀርቦልኛል:: በሻሻ እስካሁን አስፋልት የለም:: እንደተወካይ ሲታይ እኔም ቢሠራ ባይ ነኝ:: ፓርላማው በሚቀጥለው በጀት ፈቅዶልን እነዚህን ጉዳዮች ምላሽ እየሰጠን እንደምንሄድ ተስፋ አድርገዋል:: በአንድ ጊዜ ግን አንችልም:: ደረጃ በደረጃ እየፈታን እንደምንሄድ ታሳቢ ቢደረግ ጥሩ ይመስለኛል::

ሌብነት ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ደሃ ሀገር ሌብነት ሲንሰራፋ በተለይ ሕዝብ አገልግላለሁ ያሉ ሰዎች ሲሰርቁ እድገት ከባድ ነው:: ሌብነት ማለት ተቋም የሚያፈርስ ምስጥ ማለት ነው:: የሚቦረቡር:: ሌብነት ማለት አሳቢያን ማሰብ እንዳይችሉ ሃሳብ የሚሰርቅ ካንሰር ማለት ነው::

በልበ ሙሉነት መናገር፣ መሥራትና ሕዝብ ጋር መገናኘት የማያስችል ሽባ የሚያደርግ ነገር ነው:: በተደጋጋሚ ብዬዋለሁ:: ሌብነት ግን ውስብስብ ነው:: በቀላሉ ታግለን የምንወጣው ጉዳይ አይመስለኝም:: በመንግሥት ደረጃ በመዋቅር ደረጃ ሰፊ ሥራ ሠርተናል ብዙ ቁጥጥር እያደረግን ነው:: ፕሮጀክቶችን በቀጥታ ስለምናየው ለውጦች አሉ:: ይሁንና በጣም ሰፊ የሆነ የባህል ትግል ፣ የሕግ እና አሠራር ትግል ፣ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ማሻሻያውን በደንብ መተግበር ኦቶሜሽን ማስፋት ካልቻልን በስተቀር በጣም ከባድ ፈተና ነው:: ብዙዎች ይታሠራሉ:: ከቦታቸው ይነሳሉ:: በየግምገማው በየሥልጠናው ይነገራል:: በቀላል የምናልፈው ፈተና አልሆነም::

ለነገሩ አሁን አሁን ስመለከት ሌብነት የዓለም ችግር ነው:: ለዛም ነው ብዙ መከራ እና ጣጣ እየመጣብን ያለው:: በእኛ ሁኔታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት 190 በላይ ሰርቪሶች ኦቶሜት ተደርገዋል:: ገቢን ጨምሮ ጥቂት ቢሊዮን የሰበሰብነው በዚህ ዓመት በሞባይል መኒ ነው:: የትራፊክ ፖሊስ ቅጣት ሊሆን ይችላል ንግድ ፈቃድ ሊሆን ይችላል በጣም በርካታ ሰርቪሶች ኦቶሜት አድርገናል:: ይህን እናስፋፋዋለን:: የሰውን ንክኪ እየቀነስን ስንሄድ ተገልጋይና አገልጋይ በቀጥታ የማይገናኙበት መንገድ ሲፈጥር ሊቀንስ እንደሚችል ይታሰባል::

ከዚህ ጋር ተያይዞ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ ፤ የመጀመሪያው ነገር ነገርየውን መገንዘብ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ሲጀመር ትክክል ነው ተብሎ የሚያውቅ ነገር የለም:: ታውቃላችሁ ፊልም ቤት ሲጀመር የሰይጣን ቤት ተብሏል:: የሰይጣን ቤት መባሉ ግን ፊልም አላቆመም:: አሳደገው::

መኪናም ሲጀመር፤ ሆቴልም ሲጀመር ፤ ለሁሉም ነገር ስም አለን እኛ:: ላላመቀበል ስም እንሰጣለን:: ይህ ከእኛ ጋር የኖረ ነው:: አዲስ ነገር አይደለም:: ነገር ግን መማር ያለብን ነገር ቻይናዎች 1949 የኮሚንታንግን መንግሥት ወደ ታይዋን አባረው መንግሥት ከሆኑ በኋላ በጣም ከፍተኛ ችግር እና ረሃብ ባለበት ሁኔታ በ1951 እና 52 ስለ ስፔስ ሳይንስ ኒውክሌር ቦምብን ስለመፍጠር ይነጋገሩ ይሠሩ ነበር:: ያኔ ለቻይና ቅንጦት ነው:: ዛሬ ግን የክብር መገለጫ ነው:: ህንዶች ፓኪስታኖች የዛሬ 50 እና 60 ዓመታት እነዚህን ነገሮች ሠርተዋል::

እኛ ሁል ጊዜ የሠራውን እያደነቅን ለመሥራት ስናስብ ደግሞ እያንቋሸሽን ከሄድን አናድግም:: ስንዴ ሲሠራ ስንዴ ምን ያደርጋል? አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሲሠራ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ምን ያደርጋል? መንገድ ሲሠራ መንገድ ምን ያደርጋል? ክላሽና ሚሳኤል ስናሳይ ሚሳኤል ምን ያደርጋል? በምን ያደርጋል የተሞላ ሃይል ነው::

ይሁንና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በጣም አስፈላጊ ነው:: ወደድንም ጠላንም የዓለምን ሁኔታ ይወስናል:: እኛ አሁን ባለን አቅም ባለን ገንዘብ ዓለምን የሚወስን ነገር በእጃችን እናስገባለን ባንልም ለነገሩ ባዳ እና እንግዳ እንዳንሆን ግን ሥራ ያስፈልጋል:: እንዴት ነው የምትሠሩት ላላችሁት በጣም በርካታ ሰዎች በተለያየ ዓለም እያስተማርን ነው:: ተቋም ገንብተናል:: ሥራ እየሠራን ነው:: ቢያንስ ቢያንስ እንደ ኒውክሌርና እንደ ስፔስ እንግዳ እንደማንሆን ጥርጥር የለውም:: በዚህ አግባብ እየሰፋ ይሄዳል:: ልጆቻችን ደግሞ ከእኛ በተሻለ ጭንቅላታቸው በጣም ስማርት ስለሆነ የተሻለ ውጤት ያመጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ:: ለዚህ ነው ትውልድ ላይ አበክረን የምንሠራው:: ታዳጊዎች የምንዘጋጀው በእነርሱ ጊዜ የሚፈጠር ስለሆነ ጥፋቱንም ልማቱንም አስተካክለው መጠቀም እንዲችሉ ነው:: ኒውክለር እንደማንኛውም ቴክኖሎጂ፤ አንዳንዴም ከቴክኖሎጂዎች ሁሉ በላይ ጥፋት አለው:: ኒውክሌር ቦምብም ነው፤ ኢነርጂም ነው:: አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እንደዛው ነው:: ቦምብም ነው ኢነርጂም ነው:: ኢነርጂና ቦምብ መሆኑን መጠቀም ሳይሆን ለመለየት ግን ማወቅ ያስፈልገናል:: ለእርሱ እንደሚሠራው ውጤታማ እንደምንሆን ተስፋ አደርጋለሁ:: በጣም በርካታ ስታርት አፕስ እየተደገፉ ነው:: በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም ሆነ በሳይንስና ቴክኖሎጂ አዳዲስ ፈጠራ ያላቸው ልጆች እየወጡ ነው::

በቅርቡ በነበረው ውድድር አይታችሁ ሊሆን ይችላል። ይሄ ነገር እየሰፋ ሄዶ ለውጥ እናመጣለን ብዬ አስባለሁ ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ማጭበርበርን በሚመለከት ፋይዳ የተሰኘው የዲጂታል አይዲ ብዙ ጉዳይ ይፈታል ተብሎ ይታሰባል ። ሥራው በጥሩ ሁኔታ ተጀምሯል ገና ብዙ ሩቅ ነው ያለው ። በትብብር እንሥራው አንድ ሰው 10 መታወቂያ 10 ካርታ … ከሚይዝ ፤ አንድ ሰው አንድ እንዲይዝ እና ከሌላው አንድ ሰው ጋር እኩል እንዲሆን ፤ እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ ስለሆነ እነዚህን ማስፋት ያስፈልጋል ። በቅርቡ ሥራ የሚጀምር የእናንተን ድጋፍ የሚፈልግ፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ የሚደግፈው ጉዳይ ግን ስቶክ ማርኬት ነው። ስቶክ ማርኬት በጣም ብዙ ሰው ሃሳብ አለው፤ ገንዘብ የለውም:: ጥቂት ሰዎች ገንዘብ አላቸው፤ ሃሳብ የላቸውም ። ጥቂቶች ደግሞ ገንዘብ አላቸው ሃሳብም ገብቷቸዋል ነገር ግን ተቋም የላቸውም ። ስቶክ ማርኬት ማለት ገንዘብ ያለውን፣ ሃሳብ ያለውን እና ተቋም የሚያገናኝ ምርጥ ሃሳብ ማለት ነው ።

ለምሳሌ በአረብ ሀገራት የሚገኙ እህቶቻችን ፤ስቶክ ማርኬት  ውስጥ ሼር ገዝተው እዛ እየሠሩ ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ ። አርሶ አደሮች እያረሱ ከስቶክ ማርኬት ሼር ገዝተው እያረሱ ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ :: ዳያስፖራዎቻችን መቼም ውሎ አድሮ አንድ ቀን መመለሳቸው ስለማይቀር ፤ ሲመጡ ምንም የሌላቸው እንዳይሆን ከወዲሁ ዋና ዋና ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ ። ለምሳሌ ቴሌኮሙኒኬሽን በቅርቡ የተወሰነ ፐርሰንት ለሕዝቡ ይሸጣል። ቀስ ቀስ እያልን ቴሌ ኮሙኒኬሽንን የሕዝብ ተቋም ማድረግ አለብን። አየር መንገድን የሕዝብ ተቋም ማድረግ አለብን ። እኛ ሂልተንንም ጊዮንንም አየር መንገድን ቴሌኮምን ይዘን አንዘልቀውም። እነዚህን ኩባንያዎች ብዙዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉበት ካደረግን የተሻለ አመራር የተሻለ ኢኮኖሚ ሊያመጡ ስለሚችሉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ያግዛል ተብሎ ይታሰባል። የእናንተን ድጋፍ በእጅጉ ይጠይቃል። በድምሩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ፣ የኑሮ ሁኔታችንን ለመቀየር ያለው መፍትሄ አንደኛ ትጋት ነው። ሁለተኛ ዲሲፕሊን ነው ፤ ዲሲፕሊን ማለት ጠዋት መትጋት ማታ መተኛት ሳይሆን ፤ቀጣይነት ያለው የማይናወጥ ኮንቪክሽን ማለት ነው ። ሁሌም የምንሠራው ። ሦስተኛው ነገር ለልማት ፣ለቀና ነገር ሀገር ለሚጠቅም ነገር ሁላችንም በጋራ መቆም ነው ።

ያን ማድረግ ስንችል ስንደጋገፍ ስንተባበር ብዙ ሀብት አለን:: ብዙ ሰው አለን:: ልናድግ ልንቀየር እንችላለን ። ጅማሯችን ተስፋ ሰጪ ነው በዚህ ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ። በመጨረሻ ዲፕሎማሲ እና ወደብ በሚመለከት የተነሱ ነገሮች አሉ ፤ ከእነሱ በፊት ፕሪቶሪያን በሚመለከት ፕሪቶሪያ ለትግራይ እናቶች ለኢትዮጵያ እናቶች ቢያንስ ቢያንስ እፎይታ ሰጥቷል ። ቢያንስ ቢያንስ ተጨማሪ ሰዎች እነዳይሞቱ አድርጓል ። ከዚያ ባሻገር በገባነው ስምምነት መሠረት ሰርቪስ የሚባሉትን ኤሌክትሪክ ስልክ ትራንስፖርት ፣ ባንክን ጨምሮ በስፋት እንዲጀመር አድርገናል። የክልሉ መንግሥት ተቋቁሟል ፣ በጀት ተፈቅዷል የፈረሱ ተቋማት ላይ ሰፊ ርብርብ ተደርጓል ። በጣም በርካታ ነገሮች መስመር ይዘዋል ፤የቀሩ ሥራዎች አሉ። እነዚያ የቀሩ ሥራዎች በትግራይ በኩልም ፣ በአማራ በኩል ፣ በፌዴራል በኩልም በትብብርና ሰላምን በማስቀደም ፤ በትብብርና ወደድንም ጠላንም አብረን ነዋሪ መሆናችንን አምነን በመቀበል በውይይት እየተፈቱ ይሄዳሉ ብዬ አስባለሁ። ቀሪ ሥራ ስላለ ካልተዋጋን ፣ ቀሪ ሥራ ስላለ ወደ ነበረው ካልተመለስን ካልን ግን ጥፋት ነው። የነበርነው ከሁሉ የከፋ ነው። አሁን አብዛኛውን ሠርተን የቀረ ጉዳይ ደግሞ ካለ በውይይት በምክክር እየፈታን መሄድ ያስፈልጋል።

እናም ፕሪቶሪያ ቢያንስ እፎይታ የሰጠ እንደሆነ መገንዘብ ጠቃሚ ይመስለኛል። ዲፕሎማሲን በሚመለከት የእኛ ዲፕሎማሲ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን እንደተመላከተው ግልጽ ነው። ዋናው መስፈሪያው ሚዛኑ የኛ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ከሌሎች ጋር በሚኖር ትብብርና ስምምነት የሚፈጸም መሆኑን የሚያመላክት ነው አብዛኛው የፖሊሲያችን መነሾዎች። አንደኛ ብሄራዊ ጥቅም ሁለተኛ ሉዓላዊነት ሦስተኛ መልካምድራዊ ታሪካዊ ኢኮኖሚያዊ ቱሩፋቶች ፣ በዚህ ውስጥ ደግሞ ጎረቤት ላይ ቅድሚያ የሰጠ፤ ጎረቤትን ያቀፈ ወደፊት የሚፈጠርን ኢንቲግሬሽን ታሳቢ ያደረገ ፖሊሲ እንከተላለን። አሁንም የምንከተለው ይሄንኑ ነው። ሰሞኑን ብሪክስን ከገባን በኋላ አንዳንድ ነገሮች ይደመጣሉ ። ብሪክስ የገባነው አንደኛውን ወገን ትተን ሌላኛውን ወገን ደግፈን እንደሆነ ተደርጎ ይነገራል። አንደኛ ብሪክስ የሳውዝሳውዝ ኮኦፕሬሽን ተቋም ነው። ለምሳሌ እኛ የአፍሪካ ህብረት መሥራች ነን። በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ቻይና አባል መሆን አልቻለችም። ቻይናን ለመጉዳት አይደለም አባል ያላደረግናት። አፍሪካ ህብረት የአፍሪካውያን ስለሆነ እንጂ የአፍሪካ ህብረት ውስጥ ቻይና አባል ባለመሆን ቻይና እንድትጎዳ ወይም ሌላ ሀገር አየርላንድ አባል ባለመሆን አየርላንድ እንድትጎዳ አይደለም ። የአፍሪካ ህብረት ዋና መሠረቱ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ያሉ ሀገራት የፈጠሩት ህብረት ነው። ሌላ ለመጉዳት ሳይሆን እነሱ ለመልማት ለማደግ ብለው ነው።

ሊጎፍ ኔሽን ስንገባ፤ ዩኤን ስንገባ ሁሉ አሁን ላይ ያለ ሀገር ዩኤን እኮ አልነበረም:: ሊጎፍ ኔሽን እኮ አፍሪካውያን አልነበሩም ብቻንን እኮ ነበርን :: ያኔ እዛ የነበርነው ሌላውን ልንጎዳ አይደለም:: እኩል ድምጽ፣ እኩል ንግግር ፣ እኩል ሥርዓት እንዲፈጠር ነው የገባነው::

አሁንም ብሪክስ የገባነው የሳውዝ ሳውዝ ኮርፖሬሽ ስለሆነ በሳውዝ ሳውዝ ኮርፖሬሽ ውስጥ ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ሀገር ስለሆነች ብንገባ ለብሪክስም ለኛም ጠቃሚ ነው በሚል እሳቤ ነው:: ኢትዮጵያን ያገለለ ህብረት ብዙ ጥቅም የለውም በሚል ብዙ ሀገራት ጥያቄ አቅርበው እኛም እንደተባለው ጠይቀን በነሱ መልካም ፈቃድ ገብተናል፤ ብዙ ጥቀሜታ እንደሚኖረው ተስፋ ይደረጋል::

ብሪክስ ስንገባ ሌላውን ጠልተን ፤ ሌላውን ተቃውመን ግን አይደለም:: ኢትዮጵያ ከምእራቡም ከምስራቁም ከመካከለኛ ምስራቁም ከቅርቡም ከሩቁም ተስማምታ ተጋግዛ ማደግን የምታስቀድም ሀገር ስለሆነች ፖሊሲያችን ባስቀመጠው መሠረት ጉዳዩ መታየት ያለበት በዛው በአግባቡ ነው:: ለምሳሌ ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ አባል አይደለችም::

የአረብ ሊግ አባል ሳትሆን የአረብ ሊግ ሰብስቦ ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ይመካከራል፣ ውሳኔ ይሰጣል፣ መግለጫ ያወጣል በውሳኔያቸው ተጠቃሚ ሳንሆን ተጎጂ ነን:: እኛ ሳንደመጥ ሳንናገር ባልተገኘንበት ቦታ ላይ ስለኛ ጉዳይ መምከር አይጠቅመንም:: ቢቻል አባል ሆነን የለም ህዳሴ ሁላችንም ይጠቅማል ብለን መናገር ነበረብን:: ግን የለንበትም:: ወይ ደግሞ ሴኩሪቲ ካውንስል አባል አይደለንም:: ምንም ባልረባ ነገር 13 ጊዜ ሴኩሪቲ ካውንስል ኢትጵያን አስቀምጦ ያነጋገረው እንደሌላው ጠንከር ያለ ድምጽ ቢኖራት ኖሮ ባልሆነ ነበር:: አባል ያለመሆናችን ጎድቶናል::

ጥያቄያችን መሆን የነበረበት እዴት ብሪክስ ገባን? አይደለም:: እንዴት ሴኩሪቲ ካውንስል እንገባለን? አረብ ሊግ እንዴት እንገባለን? ሌሎችም እንደዚህ ጉሩፖች ያሉበት ቦታ ካለ እንዴት ተገኝተን ድምጻችንን እናሰማለን? ጥቅማችንን እናስከብራለን? የሚል ቢሆን ጥሩ ነው::

ብሪክስ እኛ ካልገባን ትልቅ ፤ እኛ ስንገባ ትንሽ፣ እኛ ካልገባን ጠቃሚ ፤ እኛ ስንገባን ጎጂ፤ ሊሆን አይችልም:: ትላልቅ ሀገራት አሉበት በርካታ ጠቀሜታ አለው:: የጥቅሙ ምንጭ እና ግብ ግን ሌሎችን መጉዳት አይደለም:: መሆንም የለበትም:: ኢትዮጵያም ለጥቅሟ ብላ ሌሎችን መጉዳትን አታምንም አትከተልም::

እኛ ስንጠቀም ሌሎችም በአግባቡ እንዲጠቀሙ ብቻ ነው እንጂ የምናስበው ሌላውን በሚጎዳ አይን አናይም::

ወደብን በሚመለከት ብዙ አይነት ንግግሮች፣ ትንበያዎች፣ ሴራዎች፣ ትንተናዎች፣ ተደርገዋል:: የተከበረው ምክር ቤት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፣ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ሀገራት፣ የአፍሪካ ወንድሞቻችን፣ የምእራቡና የምስራቁ የዓለም ክፍል ያሉ ሀገሮች እንዲገነዘቡ የምፈልገው የኛን እውነተኛ ፍላጎት እና የእኛን ችግር ነው:: እንዲህ አስቦ ነው፤ እንትን ቦታ እንትን ብለዋል፤ ሳይሆን የኛ ፍላጎት ይኸው አሁን ዛሬ የምናገረው ነው:: በዚህ ጉዳይ ሁሉም በቀና ልብ ተባባሪ እንዲሆን አደራ ማለት እፈልጋለሁ::

አንደኛ የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ የሁለት ወደብ ባለቤት ነበረች:: የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ ሁለት ወደብ በነበራት ጊዜ 46 እና 47 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ነበራት:: ኢትዮጵያ በዚያን ጊዜ 10፣ 12፣ 13 ቢሊዮን ዶላር ጂዲፒ ነበራት:: አሁን ያለንበትን በኋላ እመጣበታለሁ:: ከ30 ዓመት በኋላ ከ ሁለት ወደብ ባለቤትነት ሁለት ወደብ በንግድ ሕግ መጠቀም ወደምትችልበት ደረጃ ዝቅ አለች:: ቢያንስ አሰብን እና ጅቡቲን በገንዘቧ ፣ በንግድ ሕግ ፣ በስምምነት መጠቀም ወደምትችልበት ዝቅ አለች:: ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ግጭት ሲያጋጥም አንደኛው ቀረና ወደ አንደኛው ወደብ ዝቅ አልን፤ ወደ ጅቡቲ:: ጅቡቲን በሚመለከት የጅቡቲ መንግሥት እና ሕዝብ ለኢትዮጵያ እድገት ያደረገው አስተዋጽኦ ብቻ ሳይሆን ወደቡን ባሻን መንገድ እንድንጠቀም የጅቡቲ ሕዝብና መንግሥት ያደረገውን ድጋፍ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እውቅና ይሰጣል::

ከጅቡቲ መንግሥት እና ሕዝብ ምንም አይነት ጥርጣሬም ስጋትም የለንም:: ነገር ግን የኛን ፍራቻ ጅቡቲዎችም ሌሎችም እንዲገነዘቡት እንፈልጋለን:: የዚህ አካባቢ ጂኦ ፖለቲክስ ተበላሸ:: ለምሳሌ ትላልቆቹ ሀገራት አንዳንዴ ሲጨቃጨቁ በሚዲያ ሲጣሉ እኛ እንደነግጣለን:: ኬንያ እንደኛ ላትደነግጥ ትችላለች:: ታንዛኒያ ላትደነግጥ ትችላለች:: ደቡብ አፍሪካ ላትደነግጥ ትችላለች:: እኛን የሚስደነግጠን አንድ ወደብ ነው ያለን:: የጅቡቲ መንግሥት እና ሕዝብ ወንድማችን ነው ችግር የለም:: ግን ትላልቆቹ ቢጣሉ ጅቡቲ ላይ ካምፕ ስላላቸው ድንገት ቢታኮሱ የእኛ ቦቴዎች ነዳጅ ሊያመጡ አይችሉም:: የጅቡቲ መንግሥት እየፈቀደ የጅቡቲ ሕዝብ እየፈቀደ ፤ እኛም ፍላጎት እያለን ፤ በሌሎች ግጭት ምክንያት ለአንድ ሳምንት ነዳጅ ባይኖር አስቡት፤ ማዳበሪያ ካልገባ አስቡት ፤ በሌሎች ግጭት ምክንያት ለአንድ ሳምንት ነዳጅ ባይኖር፣ ማዳበሪያ ካልገባ አስቡት:: ሰሞኑን ሰምታችኋል ‹‹ከየመን ሚሳኤል ይተኮሳል እንትን ይተኮሳል›› ይባላል:: በየመንና ጅቡቲ መካከል ያለው ርቀት 28፣ 29፣ 30 ኪሎ ሜትር ነው:: በጣም ቅርብ ነው:: እዛ ያሉ ሃይሎች ወደዚህ ካምፖች ፍለጋ ቢተኩሱ እኛ ወደቡን መጠቀም /አክሰስ ማድረግ/ አንችልም:: ይሄ ይሄ የጅቡቲ መንግሥትና ሕዝብ የሚያደርግብን ጫና ሳይሆን የጂኦ ፖለቲክሱ መሳከርና አንዳንድ ሃይሎች በርቀት መተኮስ፤ በርቀት መግደል አቅም ስለፈጠሩ ነው:: ያ ነገር ቢፈጠር 120 ሚሊዮን ሕዝብ ምን እናደርገዋለን ነው ጭንቀታችን:: ምርጫ የለንም:: ያለን አማራጭ አንድ ነው:: ይህንን ቸል ማለት ጥሩ አይደለም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ አልሸባብ ሶማሊያን አስቸግሯል፣ አፍርሷል ብሎ ልጆቹን ልኮ እየሞተ ነው::

ኢትዮጵያ ተቸግሬያለሁ ስትል ወንድም ጎረቤቶች ደግሞ ችግርሽ ምንድ ነው? ብሎ ማድመጥ መወያየት ጠቃሚ ይመስለኛል:: ለምን? ያላችሁ እንደሆነ ባለፉት 20 ዓመታት ኢትዮጵያ የምታስገባው /ኢንፖርት/ የምትልከው /ኤክስፖርት/ በ20 እጥፍ እሴት አድጓል:: የሕዝብ ብዛት 120 ሚሊዮን ገብቷል፤ ኢኮኖሚያችን ከ 17 ቢሊዮን 160 ቢሊዮን አልፏል:: ኢኮኖሚ እያደገ የሕዝብ ቁጥር እያደገ በዚያው ልክ ደግሞ ወሳኝ የኢኮኖሚ አውድ የሆነው ነገር እያነሰ ከሄደ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ችግር ያመጣብናል ነው:: እና እንወያይበት፣ እንመካከርበትና በቢዝነስ ሕግ እንሥራው ነው:: በነገራችን ላይ ‹‹ቀይ ባህር ያስፈልገናል፣ ጠቃሚ ነው›› የማይል ዓለም አለ እንዴ ከምስራቅ ጫፍ ከምዕራፍ ጫፍ ያስፈልጋል ያሉኮ አሉ እዚሁ ሰፈራችን:: ምነው እኛ ስንፈልገው ነውር ሆነ?

ያስፈልገኛል ብሎ የማይረባረብ ዓለም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ደሃ ናችሁና አይመለከታችሁም ካልሆነ በስተቀር ‹‹ቀይ በህር ያስፈልጋል›› ብሎ የማይጠብቅ፤ ‹‹የባህር ላይ ውንብድና አለ›› ብሎ የማይጠብቅ ዓለም የለም:: እኛ ደግሞ ብቸኛ መተንፈሻችን ነው:: ይሄን ጉዳይ አዲስ ጥያቄ አድርገው የሚያወሩ ሰዎችም አሉ:: አሁን ነው? አጀንዳ ነው? እያሉ:: ሳስበው የባህር ሃይል ስንገነባ ሰዎቹ አልነበሩም መሰለኝ ወይም ዩቲዩብ አልነበራቸውም:: የባህር ሃይል ስንገነባ ሌላ አጀንዳ የለንም:: የባህር ሃይል እንፈልጋለን ነው:: አጀንዳው ግልፅ ነው:: ያኔ ዩቲዩብ ያለነበረው ሁሉ አሁን ዩቲዩብ ፈጥሮ የጊዜው አጀንዳ ነው ምናምን ቢል ትክክል አይደለም::

ሁለተኛ ደግሞ የኤርትራን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ነው የሚሉም አሉ:: እኛ የህዳሴን ግድብ የሠራነው የሱዳንን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ነው እንዴ? እንደዛ ይታመናል? እኛ ህዳሴን ያለማነው ኢነርጂ ለማምረት፣ ውሃውን ለወንድሞቻችን ለክተን ዓመቱን ሙሉ ለመላክ ነው:: ህዳሴ ለግብፅም፣ ለሱዳንም ለኢትዮጵያም ሲሳይ እንዲሆን ነው የምንፈልገው እንጂ እነሱ እንዲጎዱ አንፈልግም:: ቀይ ባህርም እንደዚሁ ማለት ነው:: የማንንም ሉዓላዊነት የመንካት ፍላጎት የለንም፤ ማንንም የመውረር ፍላጎት የለንም:: በቢዝነስ ሕግ ግን የማያወላዳ ምርጫ እንፈልጋለን::

ይሄ ከኛ በላይ መጨነቅ ያለባቸው ወንድሞቻችን ናቸው:: ለምን? ባለፉት ጥቂት ወራት ከሳውዲ አረቢያ 130 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ መንገድ የሄዱ መልሰናል:: ሰምታቹሃል:: ሳውዲ መጨነቅ አለባት:: ይህ ጉዳይ ካልተፈታ ግማሽ ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል:: በጣም ብዙ ሕዝብ ነው ያለን:: ከታንዛኒያ በሺህ የሚቆጠሩ እስረኞች ተፈትተው መጥተዋል:: ታንዛኒያ መጨነቅ አለባት:: ይሄ ጉዳይ ካልተፈታ በሺህ ሳይሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሰው ሊሄድ ይችላል:: ደቡብ አፍሪካ መጨነቅ አለባት:: ሕገወጥ ሰዎች ይመጡብኛል እያለች ነው:: ይሄ ጉዳይ ካልተፈታ በሚሊዮን ሊሄድ ይችላል::

ይሄ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ነው:: ከቸገረው፣ ከራበው፣ ነዳጅ ከሌለው አይሞት መቼም ይሞክራል:: ለምሳሌ አምስት ሚሊዮን ኤርትራ፤ አምስት ሚሊዮች ጅቡቲ፤ አምስት ሚሊዮን ሶማሊያ ቢሄድ መሸከም ይቻላል? ቀላል ነው ይሄ ነገር? አይቻልም:: እና ወንድሞቻችን በከፋ መንገድ ከማየት ቁጭ ብሎ አጀንዳውን መነጋገር፤ በቢዝነስ ሕግ ማየት ጥሩ ነው:: እኛ ግጭት አላልንም:: ግጭት እንዳይመጣ እንነጋገር ነው ያልነው:: ረሃብማ የማያመጣው ጉድ አለ እንዴ? ሰው ከተራበ መጥፎ ነው ራሱን ይበላል:: የተራበ እንዳይኖር ወደ ችግር እንዳንሄድ ተረዱን ነው ያልነው::

የዓለም መንግሥታት፣ የአሜሪካ መንግሥት፣ የቻይና መንግሥት፣ የአውሮፓ መንግሥታት፣ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መንግሥታት፣ የአረብ ሀገራት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ሀገራት መንግሥታት፤ ኢትዮጵያ ያልተገባ ጥያቄ ከሕግ ውጪ፣ ከቢዝነስ ውጪ፣ እናም ሰላም ከሚያረጋግጥ ነገር ውጪ ጠይቃ ከሆነ ያነጋግሩንና እረፉ ይበሉን እንተወዋለን:: ነገር ግን እንወያይ ነው ያልነው:: እንወያይ፣ እንነጋገር በ2030 ኢትዮጵያ 150 ሚሊዮን ትገባለች፤ ሰው እያደገ ነው የሚሄደው፤ ኢኮኖሚ እያደገ ነው የሚሄደው፤ ጣጣ እንዳያመጣና ልጆቻችንን እንዳይባሉ አሁን መፍትሄ እናበጅለት ነው ያልነው::

ይሄ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን አንድ ቆንጆ ትምህርት አለ:: በንጉሡ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የኤርትራና የኢትዮጵያ ስምምነት ኮንፌዴሬሽን ነበር:: እና ንጉሱ ያኔ በነበረው እምነትና እሳቤ ያኔ የነበረው መንግሥት ኮንፌዴሬሽን አያስፈልግም እኛ እንሻላለን፤ እኛ ጠንካራ ነን ብሎ ፌዴሬሽኑን ቀደደው፤ ያኔ ጠንካራና ኃያል የነበረው መንግሥት ወድቆ የተቀደደበት ኃይል ደግሞ ዘመናት ቢፈጅም የለም ብሎ ታግሎ ኤርትራ ሀገር ሆነች:: ይህ የትናንት ማስታወሻችን ነው::

አሁን እንወያይበት ስንል ናቅ የሚያደርግ ሰው ካለ ልክ እንደ ኮንፌዴሬሽኑ የሚያጋጥመውን ነገር አላውቅም:: በውይይት ካልተፈታ፣ በንግግር ካልተፈታ ፣ በቢዝነስ ካልተፈታ ነገ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል መገመት አይቻልም:: ግን ኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ፣ ወደ ሱማሌ፣ ወደ ጂቡቲ ወደ ኬንያ ወይም ወደ ሌሎች ጎረቤቶቻችን አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የላትም:: በሉዓላዊነታቸው ጥያቄ የላትም:: እያልን ያለነው በአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ አለን፤ እሱን እንጋራና ውሃ አጋሩን፤ በአፍሪካ አንደኛውን ግድብ ገንብተናል ፤ እሱን እንጋራና አጋሩን፤ እናንተም እኛም የኢኮኖሚ ችግር አለብን ተያይዘን እንደግ ነው ያልነው::

አየርመንገድን እንጋራ ማለት እንዴት ጦርነት ሊሆን ይችላል? ህዳሴ ግድብ እኮ ስሙ እራሱ ኩራት ነው እንኳን ልትጋራው ቀርቶ ፤ በስንት መከራ የገነባነው ግድብ ነው:: እርሱንም ቢሆን እንጋራ ግድ የለም፤ ፍሬሽ ውሃ እንጋራ ነው እየተባለ ያለው:: ይህን ጉዳይ በሰከነ መንገድ በሰላማዊ መንግድ መወያየት ጥሩ ነው:: ደግሞም የሚገርመው ሁላችንም በዚህ አካባቢ የምንኖር ሀገራት ደሃዎች ነን:: በትክክል ምግብ ልናመርት አልቻልንም:: ተረባርበን እንደግ ሲባል ያልቻልን፤ ጦርነት ሲባል የምንችል ልንሆን አንችልም::

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ በጦርነት ስጋት የለባትም፤ ከጎረቤቶቻችን የሆነ ኃይል ተነስቶ ኢትዮጵያን ሊመታ ይችላል የሚል ሥጋት የለብንም:: ኢትዮጵያን የመታደግ ከበቂ በላይ አቅም አለን:: ግን እኔ የምፈልገው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚፈልገው፣ አናንተ የምትፈልጉት ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን ሱማሊያም ሰላም እንዲሆን ነው:: ለዚያ ነው ሰው ሀገር ሄደን የምንሞተው ፤ ኬንያ ሰላም፣ ሶማሊያ ሰላም፣ ጂቡቲ ሰላም፣ ሁሉ ሰላም ሲሆን ነው የእኛ ሰላም የሚረጋገጠው::

ወደብን በሚመለከት ኤርትራ በነበረኝ ጉዞ ፤ ምጽዋን ጎብኝቻለሁ፤ አሰብን ጎብኝቻለሁ:: ኬንያ በነበረኝ ጉዞ እንደምታስታውሱት ላሙን ጎብኝቻለሁ:: ጂቡቲ ላይ በነበረኝ ጉዞ እንደዚሁ የጂቡቲን ወደብ ጎብኝቻለሁ:: ያልጎበኘሁበት፤ ያልተነጋገርኩበት፤ ያልጠየኩበት ጊዜ የለም:: አዲስ አጀንዳ እንዳይመስላችሁ:: ይህ ጉዳይ ሁሌ ያስጨንቀኛል:: አንድ ቀን የሆነ ነገር ተፈጥሮ ልጆቻችን መድሃኒት አጥተው አይናችን እያየ አንዳይሞቱብን እንሰጋለን:: መድሃኒት ለምነን እና ገዝተን የምናመጣ፣ ነዳጅ ለምነንና ገዝተን የምናመጣ ሀገር ችግር ካጋጠመ ከወዲሁ ተወያይተን መፍትሄ እናብጅ ሲባል ጉዳዩ ከጦርነት፣ ከግጭት፣ ከወረራ፣ ከሉዓላዊነት ጋር መያያዝ የለበትም:: እኛ ማንንም አንወርርም፤ የመውረር ፍላጎት የለንም:: ረሃቡ ሳይመጣ ችግሩ ሳይመጣ ፣ መከራው ሳይመጣ፣ ተወያይተን መፍትሔ እናብጅ ነው ያልነው::

ችግሩ ከመጣስ? ያኔ ሕግ አይሰራም፤ ረሃብ ከመጣ ምን ሕግ አለ፤ እኛ ምግብ ማስገባት ቸግሮን ከራበን የሚይዘን ሕግ አይኖርም:: ያገኘነውን በልተን ሰርቫይቭ አናደርጋለን:: ይህ የሰው ልጆች ሁሉ ባሕሪ ነው:: ያ ሳይመጣ ግን ቀድሞ መነጋጋር እና ሕጋዊ መፍትሔ ማበጀት ጠቃሚ ይመስለኛል::

የዓለም መንግሥታትም ከዚህ አንጻር 120 ሚሊዮን ሕዝብ፣ በዚህ ላይ ደሃ ሀገር፤ በዚህ ምክንያት ለረሃብ ለችግር እና ለመበተን እንዳይጋለጥ ማገዝ ይኖርባቸዋል:: ትርፍ ጠይቀን ከሆነም አስተካክለው በሕግ አግባብ መፍትሔ እንድናገኝ ማገዝ አለባቸው:: ማራገብ ሳይሆን ማገዝ አለባቸው:: ያ ቢሆን ለሁሉም ይበጃል ብለን እናስባለን፤ የእኛ ፍላጎት ግን በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ያሉ ሀገራት አሁን ያለውን ሰው ሠራሽ ድንበራቸውን እየቀነሱ ወደፊት ቢያንስ የጋራ ዲፕሎማሲ፣ የጋራ ሠራዊት ቢገነቡ ይመረጣል:: የየግል ባንዲራ ቢኖረንም የየግል ወታር አያስፈልገንም:: የሱማሊያ፣ የኢትዮጵያ፣ የጂቡቲ፣ የኤርትራ፣ ወታደሮች መቀመጥ ያለባቸው በሕንድ ውቅያኖስ እና በቀይ ባህር ዳርቻ ነው:: መሀል ላይ ፖሊስ እንዲበቃ ብናደርግ ነው የምናድገው:: ለዚህም ትብብር፣ አብሮ ማደግ፣ መዘጋጀት፣ ማሰብ፣ መምከር፣ ለሁላችንም የሚያስፈልግ ይሆናል:: ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ ለጊዜው ይመስለናል እንጂ አያዋጣንም::

እኛ የምንፈልገው ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና፣ የጋራ ውይይት ነው:: ይህንን የምታምኑ ወንድሞቻችን በማንኛውም ቦታና ጊዜ በዚህ አጀንዳ ለመነጋገር ዝግጁ ከሆናችሁ በእኛ በኩል ፍላጎታችን ከፍተኛ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ልገልጽ እፈልጋለሁ፤ የተከበረው ምክር ቤት ባለፈው እንደተመካከርነው ነው ደግሜ የማነሳው :: የምንወረው የለም፤ የምንወጋው የለም፤ በጥያቄው ግን አናፍርም፤ ምክንያቱም የልጆቻችንን ሕይወት መታደግ አለብን:: ለዚያ ነው የብልጽግና የ 10 ዓመት የ20 ዓመት እቅድ የምንለው:: ይህን ጥያቄ ማንሳት እንደወንጀል የሚያስቡ ሰዎች ቢያስቡበት ጥሩ ነው:: ሁለተኛ ጉዳይ ከወደብ ጋር ተያይዞ ወደብ፣ ጦርነት፣ ምናምን እያሉ ሴራ የሚተነትኑ ሰዎች ከተቻለ በጽሑፍ ያድርጉት:: ምክንያቱም በቪዲዮ እንዲዚህ አውርተው አውርተው በኋላ ነገሩ ሲሳካ በልጆቻቸው ፊት ማፈሪያ እንዳይሆኑ እሰጋለሁ አመሰግናለሁ::

አዲስ ዘመን   ኅዳር 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You