ቤተኛው ስጋ ላኪ

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር በዓለም ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደምትገኝ ይነገርላታል፡፡ ለከብት እርባታና ሥጋ ምርትም እንዲሁ የተመቸች ሀገር ስለመሆኗ የሚመሰክሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በሥጋ ምርት ተሰማርተው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙትም በእነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡ በስጋ ምርት የተሠማሩ ኩባንያዎች የሥጋ ምርታቸውን በዋናነት ወደመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ይልካሉ፡፡

በሀገሪቱ ከግብርና ምርቶች ከቡና ቀጥሎ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው የስጋ ወጪ ንግድ በወጪ ንግዱ 15 ዓመታት ዕድሜ ማስቆጠሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ታዲያ ዘርፉ ለሀገሪቷ እያስገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ካላት እምቅ የእንስሳት ሀብት አንጻር እምብዛም ተጠቃሚ እንዳልሆነችና ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ማግኘት ከቻለ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ይናገራሉ፡፡

በስጋ ምርት ከተሠማሩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መካከል አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ አንዱ ነው። ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ያላትን ዕምቅ አቅም በመረዳት ዘርፉን መቀላቀል የቻለው ድርጅቱ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የስጋ ምርትን ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል፤ ዘርፉ በብዙ ፈተናዎች ባለበት በአሁኑ ወቅትም የስጋ ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረቡን ቀጥሏል፡፡

የድርጅቱ መሥራችና ባለቤት እንዲሁም ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ ይባላሉ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ቴዎድሮስ በንግድ ሥራ ውስጥ ከተሰማራ ቤተሰብ የተገኙ በመሆናቸው ለንግድ ሥራ ቤተኛ ከመሆን ባለፈ ወላጅ አባታቸውን በንግድ ሥራ ሲያግዙ ነው ያደጉት፡፡ የትምህርት ሁኔታቸውም ከቢዝነስ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ባለው ዓለም አቀፍ ንግድ እና ሎጅስቲክስ ነው፡፡ በእነዚህ ዘርፎች ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው በመሆኑ በንግዱ ዘርፍ ለመሰማራት ብዙም አልተቸገሩም፡፡ ለንግድ ሥራ ቅርብ ሆነው በማደጋቸው እንዲሁም ባላቸው የትምህርት ዝግጅት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡

በንግድ ሥራ የረጅም ጊዜ ልምድና ዕውቀት ያላቸው አቶ ቴዎድሮስ፤ አሁን ላይ ሶስት የተለያዩ እህት ድርጅቶችን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ አንደኛውና የሥራ መነሻቸው ሼባትራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ነው፡፡ አዳማ የሚገኘው ይህ ድርጅት ጥራጥሬዎችን እንዲሁም የቅባት እህሎችን አቀነባብሮ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የተሰማራ ነው፡፡ ሁለተኛው የስጋ ምርትን ለሀገር ውስጥ ገበያ በሱፐርማርኬት ደረጃ አዘጋጅቶ የሚያቀርበው ፓዮኔር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ሲሆን፤ ሶስተኛውና በአሁኑ ወቅት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ለአቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት እንደሆነ አቶ ቴዎድሮስ ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት ሼባትራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የመጀመሪያ ድርጅታቸው ነው፡፡ ድርጅቱ የሎጅስቲክስ ሥራን ይከውናል፡፡ በመሆኑም የተለያዩ ዕቃዎችን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትና ከሀገር ውስጥ ደግሞ ለኤክስፖርት የሚሆኑ ዕቃዎችን በሀገሪቱ የጉምሩክና የመርከብ ሕግና ሥርዓት መሰረት በተለይም በጥራጥሬና የቅባት አህሎች ኤክስፖርት ንግድ ላለፉት አስር ዓመታት ሠርተዋል፡፡ የቁም እንስሳን አደልበው ለኤክስፖርት በማዘጋጀት ሥራም እንዲሁ ጥቂት ዓመታትን ካስቆጠሩ በኋላ አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራን በማቋቋም የስጋ ምርትን ወደ ውጭ ገበያ እየላኩ ይገኛሉ።

በቢሾፍቱ ከተማ 15 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የተቋቋመው አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ የተለያዩ እንስሳት ስጋን አቀነባብሮ ለውጭ ገበያ ያቀርባል። ከእነዚህም መካከል የበሬና የግመል ስጋን አቀነባብሮ መላክ የሚያስችል ማቀነባበሪያ ያለው ሲሆን፤ የበግና የፍየል ስጋንም አቀነባብሮ ለውጭ ገበያ መላክ የሚያስችል ራሱን የቻለ ማቀነባበሪያ ያለው መሆኑን አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡ የማምረት አቅሙን አስመልክቶ የኤክስፖርት ቄራዎች አቅም የሚወሰነው ምርቱን አቀነባብረው በሚያቆዩበት ማቀዝቀዣዎች አቅም እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ በቀን ከ35 እስከ 40 ቶን የስጋ ምርትን አቀነባብሮ የማቆየት ወይም ወደ ውጭ ገበያ የመላክ አቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የገበያ መዳረሻ ሀገራትን አስመልክቶ በአቅራቢ ሀገራት ሳይሆን በገዢ ሀገራት የሚወሰን መሆኑን ያነሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ገዢ ሀገራት አቅራቢ ሀገራት ጋር በመምጣት የስጋ ምርቱ በኤክስፖርት ቄራዎች ውስጥ እንዴት እንደሚያቀነባብር የሚመለከቱ እንደሆነና ከተመለከቱ በኋላ ምርቱ ወደ ሀገራቸው እንዲላክ በሚሰጡት ይሁንታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ የስጋ ምርቱን ለመላክ ብቁ ሆኖ መገኘት በመቻሉ ለአረብ ሀገራት ማለትም በሳዑዲ አረቢያ፣ በዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች፣ በባህሬን፣ በኩዌት፣ በኳታርና ኦማን ሀገራት ተቀባይነት አግኝቶ እየላከ ይገኛል፡፡

ስጋ ላኪ ድርጅቶች የስጋ ምርትን እንደፈለጉ ለውጭ ገበያ መላክ የማይችሉ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ለኤክስፖርት ዕድገቱ አንድ ማነቆ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ይሁንና አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ የስጋ ምርቱን በተወሰነ መጠን ወደ ምስራቅ አፍሪካ ለመላክ የጀመረ ቢሆንም ከዋጋ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ችግር ቀጣይነቱ ጥያቄ ውስጥ መውደቁን አስታውሰዋል፡፡ እንዲህም ሆኖ ጅማሬው የሚበረታታ እንደነበር ተናግረው የስጋ ምርት ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ያለውን ውስንነት አመላክተዋል፡፡

ሀገሪቱ በእንስሳት ሀብት ያላትን ዕምቅ አቅም በመረዳት ወደ ስጋ ኤክስፖርት እንደገቡ ያጫወቱን አቶ ቴዎድሮስ፤ ዘርፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ያልተሠራበትና ትኩረት ያላገኘ ዘርፍ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ለስጋ ኤክስፖርት እድገቱ ማነቆ ከሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል ከእንስሳት አቅርቦትና ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡ እንስሳቱን የሚያቀርበው አርብቶ አደሩ ሲሆን፤ አርብቶ አደሩ የሚያቀርበው እንስሳት ለገበያ ብሎ ያዘጋጀውን እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት፡፡

ሌሎች ሀገራት ለኤክስፖርት ቄራ ግብዓት የሚሆኑ እንስሳት በመደበኛነት የሚዘጋጁ እንደሆነና ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ እንደሌለ የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ለኤክስፖርት ቄራ የሚዘጋጁ እንስሳት የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁና ለኤክስፖርቱ በሚመጥን ደረጃ ጥራት እና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንስሳትን ማዘጋጀት እንዲሁም በሚፈለገው ልክ ማቅረብ የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ በሀገር ውስጥ አልተፈጠረም ይላሉ፡፡ ያም ቢሆን ታዲያ ኢንዱስትሪው በአርብቶ አደሩ አቅም ልክ እየቀረበ ያለውን እንስሳት በግብዓትነት እየተጠቀመ መሆኑን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፤ ይህም በጥራትና ተወዳደሪነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አንስተው በመሆኑም ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ሀብት መጠን ልክ ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻለች ነው ያስረዱት፡፡

‹‹የሀገሪቷን ሁኔታ ለተረዳና ላስተዋለ በእንስሳት ሀብት ትልቅ አቅም አላት›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ይህን እምቅ አቅም በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚቻል ነው የሚገልጹት፡፡ ለዚህም በዋነኝነት ለኤክስፖርት ቄራ ግብዓት የሚውል የእንስሳት የገበያ ማዕከላት ሊገነቡና እንስሳቱ ለኤክስፖርት በሚመጥን ደረጃ በጥራትና በብዛት ሊቀርቡ እንደሚገባ ያመላከቱት አቶ ቴዎድሮስ፤ የስጋ ወጪ ንግዱ በአርብቶ አደሩ ላይ ጥገኛ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ አሠራር በመውጣት ራሱን የቻለ ኮሜርሻል ፋርም ሊዘጋጅ ይገባል ይላሉ፡፡ ለዚህም መንግሥትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩበት ይገባል ነው ያሉት።

የቁም እንስሳው ሕገወጥ ንግድ እንዲሁም የዋጋ ንረቱ ጭምር የዘርፉ ሌላው ችግር እንደሆነ ያነሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ከኢትዮጵያ ዘግይተው ወደ ስጋ ኢንደስትሪው የገቡ ሀገራት ጭምር አሁን ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንደቻሉ ገልጸው፤ ለአብነትም ደቡብ አፍሪካን አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ ደቡብ አፍሪካ ጥራት ያለውን የስጋ ምርት ኤክስፖርት በማድረግ ተወዳዳሪ ከመሆን ባለፈ ኢትዮጵያን ከገበያ ውጭ እያደረጉ ነው፡፡ ለዚህም ኮሜርሻል ፋርም ላይ በተጠናና በተጠናከረ መንገድ መሥራት በመቻላቸው እንደሆነ አመላክተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሜርሻል ፋርም ባለመኖሩ ለኤክስፖርት ቄራ የሚቀርበው የእንስሳቱ መጠንና የጥራት ደረጃ አንድ ጊዜ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ በማለቱ ተወዳዳሪ መሆን አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

ሀገር ውስጥ ያለው ኮንትሮባንድ ንግድ ፈታኝ እንደሆነ ጠቅሰው፤ እንስሳቱ የሚገኙት ከጠረፍ ሞያሌና ከባሌ አካባቢ ሲሆን፤ እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ ለሶማሌና ለኬንያ ኮንትሮባንድ ንግድ ተጋላጭ በመሆናቸው እነዚህ ሀገራት የቁም እንስሳቱን ተሻምተው እንደሚገዙ የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ይህም ተወዳዳሪነት ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡ ከዋጋ አንጻርም እንዲሁ አንድ ኪሎ የበሬ ስጋ ደቡብ አፍሪካ በአምስት ዶላር ለውጭ ገበያ ስታቀርብ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አንድ ኪሎ የበሬ ስጋ ከ20 ዶላር በላይ የሚሸጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ለስጋ ወጪ ንግዱ ማነቆ ነው፡፡ ይሁንና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኤክስፖርት ቄራዎች በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ተቋቁመው የስጋ ምርትን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ወደ ዘርፉ የገባው ድርጅታቸው አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ ከዚህ ቀደም በዓመት ከሰባት እስከ አስር ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለሀገሪቷ ሲያስገባ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ግን በዘርፉ ያለው አቅምና ጥራት እየቀነሰ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ ገቢውም እየቀነሰ እስከ ሶስት ሚሊዮን ዶላር መውረዱን ነው ያመላከቱት። ምንም እንኳን ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም ችግሮቹን በመጋፈጥ ኢንዱስትሪው መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡

በዘርፉ የተጋረጡ ችግሮችን በሙሉ ተቋቁሞ መቀጠል የቻለው አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ ብቻ 220 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ በእህት ኩባንያዎችም እንዲሁ ከ200 ለሚልቁ ሠራተኞች በቋሚነት፤ በጊዜያዊነት ደግሞ 200 በድምሩ 600 ለሚደርሱ ሠራተኞች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉም አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል። ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻርም እንዲሁ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን የቻለው አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ፤ በተለይም ቢሾፍቱ አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ በሚገኝበት አካባቢ በመንገድ ሥራ፣ በትምህርት ተቋማት ግንባታ፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትና በመጠለያ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚደረግ ድጋፍ ላይ ተሳታፊ ሲሆኑ በሌሎች ሥራዎችም እንዲሁ ማህበረሰቡን እያገዙ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ መንግሥት ለሚያቀርባቸው ጥሪዎችም ምላሽ እየሰጡ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ በቀጣይ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የሚኖራቸውን አበርክቶ አጠናክረው የሚቀጥሉ እንደሆነም አጫውተውናል፡፡

በመጨረሻም የቀጣይ ዕቅዳቸውን እንደገለጹልን ከሆነ ድርጅቱ እንደ ድርጅት ሰፋ ያለ ሥራ እየሠራ ሲሆን፤ በተለይም አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ አምስት ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት የተደረገበት ትልቅ ኢንቨስትመንት ቢሆንም አሁን ላይ ሥራውን ለማስፋት እየተሠራ ነው፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት አንድ ሚሊዮን ዶላር የፈጀ የማስፋፊያ ሥራ በመሥራት አሁን ወደ ውጭ ገበያ እያደረሱ ካለው ትኩስ ስጋ በተጨማሪ ፍሮዝን የተባለውን ወይም ረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል የስጋ ምርትን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ፍሮዝን ወይም ስጋን ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ማቆየት በውጭ ገበያ ትልቅ የኤክስፖርት ድርሻ ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ስጋው በካርቶን ታሽጎ የሚላክ እንደሆነና ለዚህም፤ አቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ 90 በመቶ ያህል ዝግጅቱን ማጠናቀቅ እንደቻለ ነው የጠቀሱት፤ በቅርቡም የቀሩትን የተወሰኑ ማሽኖች በማስገባት ወደ ምርት የሚገቡ ሲሆን፤ በቀን እስከ 20 ቶን ፍሮዝን ስጋ አቀነባብረው ወደ ውጭ ገበያ መላክ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ከፍ ማድረግ የሚያስችል በመሆኑ መንግሥት አሁን ካለው ገበያ በተጨማሪ አማራጭ ገበያዎችን ማፈላለግ እንዳለበት ጠቁመው፤ የስጋ ኤክስፖርት ገበያ በግል ድርጅቶች ጥረት የሚመጣ እንዳልሆነና በሁለት ሀገሮች የጋራ ስምምነት የሚመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You