ኢትዮጵያ የምትገኘው ከቀይ ባህር በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ እንደሆነ ይታወቃል:: ይሁንና ከዚህ ተፈጥሯዊ ሀብት ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ አልተቻላትም:: ከዚህም የተነሳ በአፍሪካ የባህር በር ከሌላቸው 17 ሀገራት መካከል አንዷ ለመሆን ተገድዳለች::
በርግጥ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት የራሷ የሆነ ወደብ የነበራት ሀገር ናት:: ነገር ግን ያ ሁሉ ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ የወደብ አገልግሎት ለማግኘት ስትል ጥገኛ ሆና ኖራለች:: በእነዚያ ዓመታት ውስጥ በርካታ እንግልትንም አስተናግዳለች:: እንደ ራስ መሆን አይቻልምና በኢኮኖሚው ሆነ በሌላ ሌላ ጉዳይ የልቧን ለማድረግ ተስኗት ቆይታለች::
ባሳለፈቻቸው ሶስት አስር ዓመታት ውስጥ ማንም ስለ ወደብ እንዳያነሳ የተባለ ይመስል ዝም ጭጭ በመባሉ ስለ ወደብም ሆነ የባህር በር ጉዳዩ ላይከፈት የተዘጋ ይመስል ተከርችሞ መቆየቱ የሚታወቅ ነው:: በእነዚያ ዓመታት ስለ ወደብ ይገባኛል ጥያቄ ማንሳት ቀርቶ ስለጉዳዩ መነጋገርም ሆነ መወያየት እንደነውር የሚቆጠርባቸው ጊዜያት ሆነው ዘልቀዋል::
ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ወደብ አልባ እንደሆኑ በራሳቸው አሳምነው ተቀምጠዋል:: እስካለፈው መስከረም ወር ድረስም ስለ ወደብ ጉዳይም አንስቶ ለመወያየትም ሆነ አጀንዳ ለማድረግ ድፍረቱ አልነበራቸውም:: ያኛውን ወይም ይሄኛውን ወደብ በታሪካዊም ሆነ በተፈጥሯዊ መንገድ የመጠቀም መብት አለኝ በሚል ጉዳዩን ማንሳትም በራሱ የሰው እንደመቀላወጥ ሲቆጠር ከርሟል::
ከሰሞኑን ግን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ‹‹ከጠብታ ውሃ እስከ ቀይ ባህር ውሃ›› በሚል መሪ ሐሳብ ኢትዮጵያ እና ቀይ ባህር ያላቸውን ታሪካዊ ትስስርን ጨምሮ ስለወደብ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል::
በዚህ ገለጻቸው በዋናነት ሊያሰርጹ የፈለጉት መልዕክት ስለ ቀይ ባህር እና ስለወደብ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን በተለይም ደግሞ የፓርላማ አባላት አጀንዳ አድርገው እንዲወያዩበት መሆኑ እሙን ነው:: አባላቱ፣ ከተያዙበት የፍርሃት ቆፈን ተላቅቀው በባህር በር ጉዳይ መነጋገር እንዲሁም አማራጭ ሃሳቦች ላይ መምከር ተገቢነቱን አስረድተዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የኢትዮጵያ ሕልውና እና ልዕልና የተሳሰረው ከቀይ ባህር ጋር ነው ሲሉም በወቅቱ ገልጸዋል:: በቀይ ባህር ጉዳይ፣ በዓባይ ግድብ ላይ እንዳለው መደራደር እንደሚቻልም አመልክተው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የመሆን ታሪክ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚ ጭምር መሆኑን ተናግረዋል::
ለመሆኑ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ለዚህስ ስኬት ከወዲሁ ምን እየተሰራ ነው? ስንል እኛም የዘርፉን ተመራማሪዎች አነጋረናቸዋል:: ካነጋገርናቸው ተመራማሪዎች አንዱ የሆኑት በውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት መሪ ተመራማሪና የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አማረ ቀናው ናቸው:: ዶክተሩ፣ አንድ ሀገር የባህር በር እንደሚያስፈልገው ይታወቃል ይላሉ:: የባህር በር ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም ለደህንነትም ጭምር አስፈላጊ እንደመሆኑ እነዚህን ለማስጠበቅ የሚጠቅም እንደሆነም ያመለክታሉ::
የባህር በር ለማግኘት በሁለት መንገድ ሊታይ ይችላል:: አንደኛው ሙሉ በሙሉ ከባህር ጋር የሚያገናኘው ወደብ በባለቤትነት ወይም የራስ የሆነ መሬት ማግኘት ነው:: ሁለተኛው ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የባህር በር ተጠቅሞ የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ናቸው::
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ወደብ የላትም:: እየተገለገለች የምትገኘው የሌሎችን ወደብ ተከራይታ ነው:: በዚህ መልኩ መቀጠል የሚያስከፍለው መስዋዕትነት ብዙ ነው:: ከዚህም የተነሳ አሁን ጉዳዩ ተነስቷል:: ጥያቄው ቀድሞም ቢሆን ተዳፍኖ በእያንዳንዱ ልብ የተቀመጠ ነው ሲሉ ዶክተሩ ይናገራሉ::
እንደ ዶክተር አማረ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የምትችለው በቀጣናዊ ትብብር ነው:: ለዚህ ደግሞ ኮንፈረንሶችን ማዘጋጀትና በጉዳዮች ላይ መነጋገር መልካም ነው:: በተለይም ተፈጥሯዊ የሆነው ይህን ሀብት በእኩልነት እንዴት ማስተዳደር እንችላለን? የሚለውን ለማጠናከር ቀጣናዊ ትብብሮችን በአግባቡ ማጠናከር አስፈላጊ ነው::
ከዛ በመነሳት ደግሞ የትብብር ማዕቀፎችን ዲዛይን ማድረግ ያስፈልጋል:: ከዚህ ጎን ለጎን ተጠቃሚነትም መኖር አለበት:: ጉዳዩ ገና ሲነሳ ‹‹ውሃችንን ልትወስዱ ነው›› ከመባባል ባለፈ የጋራ ተጠቃሚነታችንን ጉዳይ እንዴት አድርገን ነው ማጠናከር ያለብን በሚለው ላይ መወያየት መልካም ነው:: የጋራ ተጠቃሚነት ከሌለ ግጭቶች ይኖራሉ:: ግጭት ደግሞ ከቀጣናው ውጭ ያሉትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነውና ይህንን ጉዳይ ሁሉ ለመቆጣጣር ቀጣናዊ ትብብር ወሳኝ ነው::
ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ቀጣናዊ ትብብር ብዙ ጠንካራ የሚባል አይደለም:: ስለዚህም ማጠናከር ያስፈልጋል:: ከማጠናከር አኳያ ሲታይ ደግሞ ከዚህ በፊት ጠንካራ ሚና ስትጫወት የነበረች ኢትዮጵያ እንደመሆኗ ከዚህ በኋላ ለሚደረገውም ትብብር ተነሳሽነቱን ወስዳ ልትሰራ ያስፈልጋል ሲሉ ዶክተር አማረ አስረድተዋል::
ሌላው ያነጋገርናቸው በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ እና የኢስያ ፓስፊክ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ዳርእስከዳር ታዬ ናቸው:: እርሳቸው ኢትዮጵያ እያደገ ከሚሄደው የሕዝብ ቁጥሯና ኢኮኖሚዋ ጋር ተያይዞ የባህር ባር ያስፈልጋታል ይላሉ:: ከፍ ያለ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መቀጠል እንደማትችልም ይናገራሉ::፡
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ካለፉት 30 ዓመታት ጀምሮ በአንድ ወደብ ላይ ጥገኛ ሆና ዘልቃለች:: ይህ ከነበረው የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገት አንጻር ብዙም ተጽዕኖ ሳያመጣ ዛሬ ላይ መድረስ ተችሏል:: አሁን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ጨምሯል:: ኢኮኖሚዋም በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ፊተኛውን መስመር ይዟል:: ስለዚህም አሁን ካለከውና በቀጣይ ከሚኖረውም ግዙፍ ኢኮኖሚ አንጻር አንድ ወደብ ብቻ ገቢና ወጪ ዕቃዎችን ሊያስተናግድ አይችልም::
ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል ሲባል ብዙዎች ጉዳዩን ከጦርነት ጋር ያያይዙታል የሚሉት ዶክተር ዳርእስከዳር፣ እንደዚያ ማሰቡ አግባብነት የሌለው መሆኑን ያመለክታሉ:: አማራጮቹ በርካታ መሆናቸውን በመጥቀስ ለአብነት ያህል በኪራይ ተጨማሪ ወደቦችን ማግኘት አሊያም ወደብ በጋራ ማልማት ወይም ደግሞ የአካባቢ ልውውጥ በማድረግ እንደሚቻል ያስረዳሉ::
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው ካሉ ልማቶች ውስጥ የተወሰኑትን በመስጠት እና በምትኩ ወደብ በማግኘት ማካካስ ይቻላል ሲሉም ይገልጻል:: እንዲያም ሲባል ከህዳሴ ግድብ ተርባይኖች ውስጥ የተወሰኑትን በመስጠት ወደብ በምትኩ ማግኘት ተጠቃሽ እንደሆነ ይናገራሉ::
ለአብነትም ሶማሊያ በሺዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የባህር በር አላት:: ግን ይህ ሁሉ ኪሎ ሜትር ለሶማሊያ ወደብ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል አይደለም:: ስለዚህም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች ወደብ ከኢትዮጵያ ጋር ማልማት ትችላለች:: ወይም ደግሞ ለም መሬት ወስዳ በምትኩ ወደብ ልታቀርብልን ትችላለች በሚል በርካታ አማራጮች እንዳሉ ዶክተር ዳርእስከዳር ያመለክታሉ::
ስለወደብ ጉዳይ ሲነሳ እኛም የባህር በር ሊያጋሩን የሚችሉ ሀገራትም የተቸከሉት መሬት በሚለው ላይ ጉዳይ ላይ ነው የሚሉት ዶክተር አማረ በበኩላቸው፤ በዚህ ላይ ብቻ መንጠልጠል ሳይሆን የባህር በር የሚገኝበትን አማራጭ ማስፋት ይቻላል ይላሉ::
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ከብዙ መንገዶች አንዱ በኮሪዶር መጠቀም የሚለውን ማንሳት ይቻላል:: ለኮሪዶር ደግሞ መሬት ለመስጠት ምንም ችግር የለውም:: እሱ ማለት ዓለም አቀፍ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን እንደመዘርጋት ማለት ነው፡። ኮሪዶር የሚሰራባቸው ሀገሮች አሉ:: ለምሳሌ አዛርባጃን የባህር በር የላትም:: ነገር ግን በሌላ ሀገር ላይ ኮሪዶር በመገንባት የባህር በር ተጠቃሚ የሚሆንበትን እድል ፈጥራለች::
ከዚህ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስተሩ እንዳሉት ሌላ ነገር ሰጥቶ መቀበል ይቻላል:: ይህ ግን በተለያዩ ጥናቶች የሚመለስ ነው ብዬ አስባለሁ:: በጣም ብዙ አማራጮች ስላሉ መንገዱ ዝግ አይደለም:: እንዲያው አንዱ ላይ ብቻ ከምናተኩር የተለያየ ዓይነት አማራጭ ቢኖረን እኛንም ሀገራቱንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው:: በጣም የሚያስገርመው ነገር ሌሎች ሀገራት ወደአካባቢው ሲመጡ መሬቱም ቢሆን ሲሰጣቸው ይታያል። ለምሳሌ አሜሪካ በብዙ ሺ ማይልስ ርቀት መጥታ ጂቡቲ ላይ መሬት አላት:: ጃፓንና ቻይናም እንዲሁ በብዙ ሺ የሚቆጠር ማይልስ አቋርጠው መጥተው ወይ ጂቡቲ ላይ ወይም ደግሞ ኤርትራ ላይ መሬት አላቸው::
ታዲያ የአፍሪካ ሲሆን ልዩነቱ ምንድን ነው? ሲሉ የሚጠይቁት ዶክተር አማረ፣ ቢሆን የተባለው እንኳ በሊዝ፣ በኮሪዶርና መሰል ነገሮች ነው ሲሉ ያስረዳሉ:: ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን ቀጣናዊ የሆነ ትብብር ሲኖር ነው:: ለምሳሌ መሬቱ ለኢትዮጵያ በተለያየ መንገድ ቢሰጥ የሚለው ሃሳብ አልተገዛም:: ለአሜሪካኖቹ አሊያም ለሌሎቹ ሀገራት እንደሚሰጠው ሁሉ ለኢትዮጵያ እንስጥ የሚለው ሃሳብ በሌላውም ዘንድ አልተገዛም:: እኛም እስካሁን አልገዛነውም:: ይህ በጥናት መደገፍ አለበት ይላሉ::
ዘይላ ሶማሊያ እንደሀገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባህር በር ነው የሚሉት ዶክተር ዳርእስከዳር፣ ደግሞ ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም መኖሯን ያስታውሳሉ:: ስለዚህ ለኢትዮጵያ ቅርበት ያለው ዘይላ ከሞቃዲሾ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚርቅ ስለሆነ ሶማሊያ ልትጠቀምበት እንደማትችል ጠቅሰው፤ ስለዚህም መነጋገር ከተቻለ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የዘይላን ወደብ ኢትዮጵያ ብትጠቀምበትና ሶማሊያም በምትኩ ጥቅም ብታገኝ ሁለቱም ሀገራት አሸናፊ መሆን ይችላሉ ሲሉ አስረድተዋል::
እንደ እርሳቸው አባባል፤ በተመሳሳይም ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው መልካም የሰላም አጋጣሚ የአሰብን ወደብ በሰላማዊ አማራጭ ለመጠቀም ውይይት ማድረግ ይቻላል:: በምትኩ ደግሞ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የምትፈልጋቸው አቅርቦቶች ይኖራሉ፤ እነሱን በመስጠት አሰብን መጠቀም ይቻላል:: በሌላ በኩል የሶማሌ ላንድ ሌላኛው ተጠቃሽ ሲሆን፣ የበርበራ ወደብን በጋራ ማልማትና መጠቀም የሚቻል ነው::
የኢትዮጵያ ማደግ ለጎረቤት ሀገራት ዕድል ይዞ የሚመጣ እንደሆነ የሚያብራሩት ዶክተር ዳርእስከዳር፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ሲመጣ ተጨማሪ ወደቦች ያስፈልጓታል:: ጎረቤት ሀገራትም ወደቦችን በማከራየት፣ በጋራ በማልማት ወይም ከኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን በማግኘት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ ብለዋል::
ለምሳሌ ሲዊዘርላንድን ብትመለከት የባህር በር የሌላት ሀገር ነች:: ነገር ግን የአካባቢው ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት የሚያምን ስለሆኑ በገበያ ዋጋ ለስዊዘርላንድ ወደባቸውን በቀላሉ እያከራዩ እየተጠቀሙ ነው:: ለእነሱ የወደብ ጉዳይ ብዙም አወዛጋቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል::
ታዲያ ወደ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሲመጣ ችግሩ ምንድን ነው የሚሉት ዶክተሩ፣ ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ያስረዳሉ:: በቀጣናው ከመተባበርና በጋራ ከመሥራት ይልቅ የመከላከልና ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚደረግ ነገር እንዳለ አመልክተው ይህ ግን ወደ ትብብር ቢቀየር ሁሉንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ:: ከትብብር ይልቅ የመገፋፋት ባህሪን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያመለክታሉ::
በቀጣናው ያሉ ሀገራት ሁሉ ማደግ ይፈልጋሉ:: ስለዚህም አጓጊ ከሆነው የኢትዮጵያ እድገት ለመሻማት እራሳቸውን ማዘጋጀታቸው አይቀርም:: ስለዚህም አሁን ያለውን በመንግሥታት ደረጃ ያለውን ግንኙነት ተቋማዊ ማድረግ ከተቻለና የበለጠ መተማመን ከተፈጠረ የአሰብን ወደብ በጋራ የምንጠቀምበት ሁኔታ አይኖርም ብዬ አላስብም ይላሉ:: ሁሉም ሊያስተሳስረው እና ትብብር ሊፈጥርበት የሚችለው ነገር እንዳለውም ያስረዳሉ:: ከአካባቢው ሀገራት ጋር መነጋገር እና ፍላጎትን ማጣጣም ከተቻለ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ አማራጮችም እንዳሉም ይናገራሉ::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይም፣ ስለቀይ ባህር እና ወደብ ጉዳይ ለፓርላማ አባላት በገለጹበት ወቅት፤ የባሕር በር ጥያቄ ኤርትራ፣ ጂቡቲ እና ሶማሌላንድ አማራጮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ዘርዝረዋል:: ኢትዮጵያ ካሏት የወደብ አማራጮች መካከል በተለይም በቀዳሚነት ያስቀመጡት ዘይላን ሲሆን፣ ዘይላ ወደብ በሶማሌ ላንድ ግዛት በምዕራባዊ አውደል ግዛት ውስጥ የሚገኝ እና የኤደን ባሕረ ሰላጤን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል:: በሁለተኛ አማራጭ ነው ያሉት የጂቡቲ ወደብ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራ የሚገኘው የአዱሊስ ወደብንም ጠቅሰዋል::
በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸውንና የሚያመቻትን የወደብ አማራጮችን ብቻ አልዘረዘሩም:: በምትኩ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደብን ለማግኘት በምላሹ ከሕዳሴ ግድብ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ከኢትዮ-ቴሌኮም ድርሻ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላትም አብራርተዋል::
መሪ ተመራማሪዎቹ በየበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል:: ወደብ ለማግኘትም በርካታ አማራጮች አሏት:: በእነዚህ አማራጮች ላይ ግን መነጋገር፣ መወያየትና መግባባት ያስፈልጋል:: መፍትሔው ቀጣናዊ ትብብር ነው:: እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን በእኩልነት እንዴት ማስተዳደር እንችላለን? የሚለውን ለማጠናከር ትብብርን በአግባቡ ማጠናከር አስፈላጊ ነው::
በተለይም ዶክተር አማረ እንደሚሉት፤ የትብብር ማዕቀፎችን ዲዛይን ማድረግ ያስፈልጋል:: ተጠቃሚነትም መኖር አለበት:: ጉዳዩ ገና ሲነሳ ‹‹ውሃችንን ልትወስዱ ነው›› ከመባባል ባለፈ የጋራ ተጠቃሚነታችንን ጉዳይ እንዴት አድርገን ማጠናከር አለብን በሚለው ላይ መወያየት መልካም ነው::
የጋራ ተጠቃሚነት ከሌለ ግጭቶች ይኖራሉ:: ይህ ደግሞ ከቀጣናው ውጭ ያሉትን አካላት ተጠቃሚ ያደርጋል:: በውክልናም በመግባት መንግሥት እስከመመስረት ያደርሳል። ስለሆነም ይህንን ጉዳይ ሁሉ ለመቆጣጣር ቀጣናዊ ትብብር ወሳኝ ነው:: ከማጠናከር አኳያ ሲታይ ደግሞ ከዚህ በፊት ጠንካራ ሚና ስትጫወት የነበረች ኢትዮጵያ ተነሳሽነቱን ወስዳ ቀጣናዊ ትስስሩ እንዲጎለብት የማድረግ ብቃት ያላት ናት ይላሉ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2016