ሴተኛ አዳሪዎችን አነፍንፎ አድኖ የከንፈር ወዳጅ ከማድረግ አልፎ፣ የትዳር አጋር ማድረግ ይቀናዋል። የከንፈር ወዳጆቹ አለፍ ሲልም የትዳር አጋሮቹ በሴተኛ አዳሪነት ሲሠሩ አድረው ያገኙትን ገንዘብ መጀመሪያ የሚያስረክቡት ለእሱ ነው። የትም ከመሄዳቸው በፊት ለእሱ የእጅ መንሻ መቅረብ ግዴታቸው ነው።
ይህ ሰው ያለምንም ሐፍረት እነዚህ ምስኪን ሴቶች ገላቸውን ቸርችረው ባመጡት ገንዘብ ያማረውን በልቶና ጠጥቶ ዘና፣ ፈታ ብሎ ይኖራል። የምግብ፤ የቤት ኪራይና ዕለታዊ ወጪው ጭምር ከእነዚህ ምስኪን ሴቶች በሚገኝ ገንዘብ የሚሸፈን ነው። ይህ ሰው ገቢውንም ለማስፋት በሚል በርካታ ሴተኛ አዳሪዎችን በጓደኝነት የመያዝ ልምድ አለው።
ይህ ሰው ወጣት ደጉ በቀለ ይባላል። መልከመልካምና የደስደስ ያለው ወጣት ነው። ጨዋታውም አይጠገብም። ይህ ተክለ ቁመናውና ጨዋታ አዋቂነቱ ብዙዎችን አፍዞና በፍቅር አደንግዞ በደጉ እቅፍ ውስጥ አኑሯቸዋል።
ወጣት ደጉ የሴተኛ አዳሪ ሥራ እየሠራች እያለ ከተዋወቃት ደስታ ፀሐይ ጋር የፍቅር ጓደኝነት ጀምሯል። ጥንዶቹም በፍቅር ዓለም አብረው ክፉና ደጉን አሳልፈዋል። ሆኖም ደስታ ማታ ማታ አዳር ሴተኛ አዳሪነት ስትሠራ አድራ ጠዋት 2፡00 ገደማ ሁሌ ወደ ቤቷ ትገባለች። ጠዋት ወደ ቤቷ ስትገባ ወጣት ደጉ እግር በእግር ተከታትሏት ይገባና ገላዋን ሽጣ ያገኘችውን ገንዘብ ይቀበላታል። በዚህም ሁሌም ጠዋት ጠዋት ሥራ አድራ ወደቤት ስትገባ ተከታትሏት ገብቶ ገንዘብ “አምጪ” በሚል ሲጨቃጨቁ ጎረቤት ይሰማል። ይሁን እንጂ በመካከላቸው ፍቅር ስላለ እንዲህ እየተፋጩ፣ እየተጋጩ ዘለግ ላለ ጊዜ በፍቅር ግንኙነት አሳልፈዋል።
እንደ ሁልጊዜው ሁሉ የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ማታ 12፡00 ሰዓት ገደማ፤ ደስታ ኩሏን ተኳኩላ፣ በሜካፕ ተውባ፣ አጭር ልብሷን ለብሳ ሴተኛ አዳሪነት ወደምትሠራበት ሳሪስ ንግድ ባንክ አካባቢ አመራች። በአንጻሩ በዚሁ ቀን ፍቅረኛዋ ደጉ ከአንድ ሞቲ ከተባለ ጓደኛው ጋር አደይ አበባ ዘንባባ አካባቢ አንድ ሁለት ሲሉ አምሽተው ሞቅ ብሏቸዋል። እንዲህ አንድ ሁለት እያሉ ሳያስቡት ሰዓቱ ነጉዷል። ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት ገደማ ሆኗል። በዚህ ሰዓት ተከራይቶ የሚኖር ሰው በር ቆርቁሮ ክፈቱልኝ ማለት ይከብዳል። ያለው አማራጭ አልጋ ይዘው ማደር ነው። ይሁን እንጂ ጓደኛማቾቹ አልጋ ለመያዝ የሚበቃ ገንዘብ እጃቸው ላይ አልነበረም።
best find more info provided here are crafted following the original ones.satisfy the sleep and needs most of them. people today on earth may possibly be the quest for high quality https://wilsonsflooringdirect.co.uk.swiss discover more here online for sale at cheap price.ይሄኔ ደጉ ጓደኛውን አስከትሎ ፍቅረኛው ሴተኛ አዳሪነት ወደምትሠራበት ሳሪስ ንግድ ባንክ አካባቢ አቀኑ። በዚያም ፍቅረኛው ደስታ ብርድና ነፋሱን ችላ፣ የአልፎ ሂያጅ ሰካራም መንገደኛውን ስድብ ተቋቁማ፣ “ሌቦች አሁን ከአሁን ማጅራቴን አሉኝ” በሚል አካላቷ እያለቀ አስፓልት ዳር ቆማ ሥራ እየጠበቀች ያገኛታል። ፍቅረኛውን ሲያገኛት ጊዜው ምሽት 5 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ገደማ ነበር።
ደጉ ከፍቅረኛው ጋር ሰላምታ ከተለዋወጠ በኋላ “ገንዘብ ስጪኝ አልጋ ይዤ ልደር” ብሎ ይጠይቃታል። እሷም “ሥራ አልቀናኝም፣ አልሰጥህም” ትለዋለች። “ስጪኝ፣ አልሰጥህም” በሚል ፍቅረኛማቾቹ አንድ ሁለት ሲነጋገሩ፤ የደጉ ጓደኛ ሞቲ መሀላቸው ገብቶ “አንተም ተው! አንቺም ተይ! ብዙ አሳልፋችኋል” ብሎ ያስማማቸዋል።
ከዚያም ወቅታዊ አለመግባባቱ ተፈትቶ ፍቅረኛማቾቹ ደጉና ደስታ እንዲሁም ሞቲ ሆነው ተያይዘው በዚያ ደረቅ ሌሊት አልጋ ለመያዝ ወደ ላፍቶ ድልድይ አስፓልቱን ይዘው በእግራቸው ያመራሉ። እንዲህ ሦስቱም አብረው አንድ ላይ እየተጨዋወቱ እየሄዱ እያለ ጫካ ያለበት አካባቢ ሲደርሱ፤ በመሀል ደጉ “ቅድም ለምንድነው ያመናጨቅሽኝ” በሚል ይደነፋባታል። ። እሷም “እዚህ ያመጣኸኝ ልትመታኝ ነው እንዴ?” ብላ መልስ ከመስጠት አልፋ “አንተ … እንትን” በሚል እላፊ ቃል ትሰነዝራለች።
ይሄኔ ደጉ ተበሳጭቶ ሊመታት ዞር ሲል፤ ደስታ ሮጣ ልታመልጥ ስትል (በሰዓቱ ደስታ አንገቷ ላይ እስካርፕ አድርጋና ኮፍያ ያለው ሹራብ ጃኬት ለብሳ ስለነበር) ደጉ እስካርፗን አፈፍ አድርጎ ይይዛታል። ከያዛት በኋላም አንድ ጊዜ በቦክስ ሆዷ ላይ ሲመታት “ዋይ!” ብላ መሬት ላይ ኩርምት ብላ ተቀመጠች። መሬት ላይ ቁጭ ስትል ግብረአበሩ ሞቲ አፏን በቀኝ እጁ አፍኖ ይይዛታል። ይሄኔ ስምና ምግባሩ ለየቅል የሆነው ደጉ፤ ደስታ ለብሳው በነበረው የሹራቧ ገመድ አንገቷን አንቆ ሲይዛት፤ እራሷን ስታ አይኗ ነጩ ተገልብጦ አረፋ እየደፈቀች መሬት ላይ ተዘርግታ ወደቀች።
ግብረአበሩ ሞቲም ሞታለች በማለት አፍና አፍንጫዋን በስካርፗና በፎጣ አፍኖ ጠቀለላት። ከዚያም ደጉ ሕይወቷ እንዳለፈ ሲረዳ በቀኝ በኩል የታፋ ኪሷ ውስጥ የነበረውን 950 (ዘጠኝ መቶ ሃምሳ) ብር አውጥቶ ኪሱ ውስጥ አደረገ።
ይህንን የወንጀል ድርጊት ጓደኛማቾቹ ከፈጸሙ በኋላ ደጉ ከወደኋላ በኩል የሟችን አስከሬን ደረቷ አካባቢ በሁለት እጁ ሲይዝ፤ ግብረአበሩ ሞቲ ደግሞ ሁለት እግሮቿን ይዞ እየጎተቱ በን/ስ/ላ/ክ/ ከተማ ወረዳ 12 ክልል ልዩ ቦታው ላፍቶ ድልድይ በሚባል አካባቢ በሚገኝ የመስኖ ውሃ መውረጃ ቦይ ውስጥ አስከሬኑን በመጨመር ከአካባቢው ይሰወራሉ።
ደጉ በነገታው ማለትም በ17/06/2013 ዓ.ም ጠዋት 3፡00 ሰዓት ገደማ ሟች ተከራይታ ወደምትኖርበት ቤት አቀና። እሱም በእጁ የቤቱ ቁልፍ ስለነበረው ከፍቶ ገብቶ የሟች የሞባይል ቀፎ ቡና ረከቦት (የስኒ መደርደሪያ) ውስጥ ከተቀመጠበት አውጥቶ ይወስዳል። ልብሱንም ቀይሮ ይወጣል። የሟችንም ስልክ ለጉታ ታደሰ ለተባለ ግለሰብ በ300 (ሦስት መቶ) ብር ይሸጥለታል።
እንዲሁም የሟች የቤት አከራይ “ኧረ ደስታ ቤቷ ከቀረች ሰነባብታለች፤ እዚህ ሄጃለሁም አላለችኝም፤ አይተሀታል ወይ?” ብላ ደጋግማ ደጉን ትጠይቀዋለች። እሱም ደጋግሞ “አላየኋትም” የሚል ምላሽ ይሰጣታል። አከራይም “ለምንድነው ልጅቱን የማትፈልጋት” ትለዋለች። እሱም በምላሹ ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ “ደስታ ፀሐይ የተባለችው ፍቅረኛዬ ጠፍታብኛለች” ብሎ እንዳመለከተ እና የአፋልጉኝ ማስታወቂያ በየአደባባዩና ቤተእምነቱ እንደለጠፈ ይገልጽላታል።
ይሁን እንጂ ደስታ “ለሥራ” ብላ ከቤቷ እንደወጣች ቀናቶች ነጉደዋል። ለስድስት ወር ያህል ተከራይታ ወደ ኖረችበት ቤቷም ዳግም አልተመለሰችም። ‹‹እዚህ ቦታ አየናት›› የሚል ሰውም አልተገኝም። በመጨረሻም ለፖሊስ በደረሰ ጥቆማ ከሞተች ከ10 ቀን በኋላ ማለትም በ25/06/2013 ዓ.ም ከቀኑ 6:00 ሰዓት ገደማ ከላይ በተገለጸው ቦታ የሟች አስከሬን ወድቆ ይገኛል። ፖሊስም የሟችን አስከሬን አስመርምሮ ሟች በሰው እጅ እንደተገደለች ከተረዳ በኋላ፤ ገዳዩ ማን እንደሆነ አነፍንፎ በመድረስ ለፍርድ ለማቅረብ የወንጀል ምርመራ ሥራውን ጀመረ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ የሟችን ስልክ ማን ይዞ እየተገለገለበት እንደሚገኝ ባደረገው ሙያዊ ክትትል፤ አቶ ጉታ ታደሰ የተባለ ግለሰብ የሟችን ስልክ ይዞ እየተገለገለ እንደሚገኝ ይደርስበታል። ፖሊስም ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አውሎ “ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ስትል ሟችን ገድለሃል” በሚል ክስ ያቀርብበታል። አቶ ጉታ በምላሹ ስልኩን ያገኘው ወንጀል ሰርቶ ሳይሆን ገዝቶ እንደሆነ ለፖሊስ ጠቁሞ፤ ስልኩን እንዴት እና ከማን እንደገዛ እንደሚከተለው ያስረዳል። አቶ ጉታ ሥራ ቦታው ላይ እያለ ደጉ በቀለ የተባለ ግለሰብ (ከዚህ ቀደም ሠፈራ አካባቢ ዓለም ግሮሠሪ ባር ማን ይሠራ የነበረና በዚህ ግሮሰሪ ሲዝናና የሚያውቀው ሰው) ቼሪ የሚል ማርክ ያለው ሞባይል ይዞ መጥቶ ስልኩን ያዝና ብር አበድረኝ እንዳለው ይናገራል። እሱም “ገንዘብ የለኝም” ሲለው፤ ደጉም የቤት ኪራይ ደርሶብኝ ነው፣ ሞባይል የሚገዛኝ ሰው ፈልግልኝ ይለዋል።
ይህን ባለው በሁለተኛው ቀን ደጉ ተመልሶ ወደ አቶ ጉታ ሥራ ቦታ በመሄድ፤ ከዚህ ቀደም ያሳየውን ስልክ “ግዛኝ፣ ቤት ኪራይ አልፎብኛል፣ የምበላውም የለኝም” ይለዋል። አቶ ጉታም “ብር የለኝም፣ አሁን ያለኝ 300 (ሦስት መቶ) ብር ነው” ይለዋል። ደጉም “ሌላ ጊዜ ትጨምራለህ፣ ውሰደው” ብሎ ስልኩ ውስጥ ያለውን ሲም ካርዱን አውጥቶ ሞባይል ቀፎውን ይሰጠዋል። ጉታም 300 ብሩን ሰጥቶ ስልኩን ይቀበላል።
ደጉም ሌላ ጊዜ መጥቶ ጉታን “ብር ጨምረኝ” ሲለው፤ “ከፈለግህ ብሩን መልስና ስልክህን ውሰድ” ብሎ ጉታ መልስ ይሰጠዋል። ከዛ በኋላ ተጠርጣሪው ግለሰብ መጥቶ እንዳልጠየቀውና ስልኩን ሟችን ገሎ ሳይሆን በገንዘቡ እንደገዛው ጉታ ለፖሊስ ያስረዳል። በተጨማሪም ተጠርጣሪው ግለሰብ ስልኩን በሸጠለት በነገታው ይኖርበት ከነበረው ሠፈራ አካባቢ “ሰው ጋር ተጣልቻለሁ” በሚል መልቀቁንና የመኖሪያ ቤት እቃውን ጭኖ ከባለቤቱ ጋር ወደ ሰበታ እንደሄዱ ጉታ ለፖሊስ ጥቆማ ይሰጣል።
ሴተኛ አዳሪዎችን እያደነ የሚያገባው ደጉ፤ በተመሳሳይ ጫልቱ ጉዲሳ የተባለች ሴተኛ አዳሪ አግብቶ እንደ ንጹህ ሰው በሰበታ ከተማ ኑሮ መስርቷል። በዚያም ማንም እንደማያውቀውና የሠራውን ወንጀል እንደማይገልጥበት እርግጠኛ ነበር። ይሁን እንጂ ተጠርጣሪው በሰበታ ከተማ ከ27 ቀን በላይ ከፖሊስ ተሰውሮና ከሕግ አምልጦ መቀመጥ አልቻለም። ፖሊስ ባደረገው ክትትል በ24/07/2013 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት 2፡00 ሰዓት ገደማ ጀሞ አካባቢ የተጠርጣሪውን ባለቤት ጫልቱን በቁጥጥር ሥር አዋለ።
ተጠርጣሪ ደጉ በቀለ የት እንዳለ መርታ እንድታሳይ በፖሊስ ተጠይቃ፤ ፖሊሶችን እየመራች ሰበታ ተከራይተው ወደ ሚኖሩበት ቤት ያቀናሉ። ሆኖም ጫልቱ ከፖሊሶች ጋር የመኖሪያ ቤቷ ስትደርስ ባለቤቷ ደጉ ልብሱን ይዞ ከቤት ወጥቷል። የፖሊስ አባላትም ተጠርጣሪው ከአካባቢው እርቆ ሂዶ ዳግም ሳይሰወር እግር በእግር ተከታትለው ሰበታ መናኸሪያ ውስጥ በቁጥጥር ያውሉታል። ተጠርጣሪውም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ከላይ የወንጀል ታሪኩ በተገለጸው መሠረት የወንጀል ድርጊቱን መፈጸሙን አምኖ ለፖሊስ ተናግሯል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ተጠርጣሪውን ከ27/07/2013 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ሥር አውሎ፤ የተጠርጣሪዋን የእምነት ክህደት ቃል፣ የምስክሮችን የምስክርነት ቃል፣ የሟች አስከሬን የሕክምና ውጤትና የአማሟት ሁኔታ የሚያሳይ ምስሎችና መረጃዎች አደራጅቶ ዐቃቢ ሕግ በተጠርጣሪው ላይ ክስ እንዲመሰርትበት መረጃውን አቅርቧል።
የሚስት የምስክርነት ቃል
ከሦስት ዓመት በላይ በሴተኛ አዳሪነት እንደሠራች የምትናገረው ጫልቱ ጉዲሳ፤ ይህን ሥራ እየሠራች እያለ ከተጠርጣሪው ባለቤቷ ደጉ ጋር ይተዋወቃሉ። ትውውቃቸው ጠንክሮ ወደ ፍቅር ግንኙነት አደገ። ፍቅራቸውንም በአንድ ጣሪያ ሥር ለመኮምኮም በመወሰናቸው ተጠርጣሪው ደጉ፣ ጫልቱ ወደ ተከራየችው ቤት ገብቶ በአንድ ላይ ጋብቻ መስርተው መኖር ይጀምራሉ።
ይሁን እንጂ ጫልቱ ባል አገባሁ ብላ ሴተኛ አዳሪነቱን መሥራት እንዳላቆመችና ባለቤቷም ይህን ሥራ እንድታቆም ግፊት አለማድረጉን ጠቁማ፤ እሷም ማታ ማታ ከቤት እየወጣች ሴተኛ አዳሪነት ስትሠራ አድራ ጠዋት ወደ ቤት ትመለሳለች። ጠዋት ጠዋት ባለቤቷ ደጉ ቤት ጠብቋት ከሠራችው ገንዘብ መቶ ብር ብቻ አስቀርቶ ሌላውን ይዞበት እንደሚሄድ ትናገራለች። እንዲሁም እሷ ማታ ለሥራ ስትወጣ ባለቤቷ ደጉ ደግሞ ማታ ማታ የሌብነት ወንጀል እንደሚፈጽም ጠቁማለች።
እንዲህ ለሁለት ዓመት ያህል በን/ስ/ላ/ክ ከተማ ሐና ማሪያም ሠፈራ በመባል የሚታወቀው አካባቢ ባልና ሚስቱ ቤት ተከራይተው አብረው ከቆዩ በኋላ፤ ባለቤቷ ደጉ “ከሰው ጋር ተጣልቼ ሰው መትቻለሁ፤ ስለዚህ መኖሪያ ቤታችንን መቀየር አለብን” ብሎ ባለቤቱ ጫልቱን አሳምኖ በ27/06/2013 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት 2፡00 ሰዓት ሲሆን፣ እቃቸውን በተሽከርካሪ ጭነው ወደ ሰበታ አቅንተው ቤት ተከራይተው በዚያ መኖር ይጀምራሉ። ለ27 ቀናት ባልና ሚስቱ በሰበታ ከተማ አብረው ከኖሩ በኋላ በ24/07/2013 ዓ.ም ጫልቱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሏን ትናገራለች።
በአጠቃላይ ተጠርጣሪው ሴተኛ አዳሪዎችን በፍቅር ጓደኝነት እንደሚይዝ፤ በሴተኛ አዳሪነት ሠርታ ያገኘችውን ገንዘብ እንደሚወስድባት፤ በሴተኛ አዳሪነት ስትሠራ በተመሳሳይ በዚህ ሥራ ላይ ሟች ደስታ ፀሐይ ስትሠራ እንደምታውቃት እንዲሁም ተጠርጣሪው ደጉ በቀለ በፖሊስ እስከተያዘበት ቀን ድረስ ባልና ሚስት ሆነው አብረው ሲኖሩ ይህን ወንጀል መፈጸሙን እንደማታውቅ ለፖሊስ ገልጻለች።
ዐቃቤ ሕግ
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 671/2/ ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሽ የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ቀኑና ሰዓቱ በትክክል በማይታወቅበት በ16/06/2013 እስከ 20/06/2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከላይ በተጠቀሰው ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ ሟች ደስታ ፀሐይ የተባለችውን ግለሰብ ተከሳሽ ሆዷ ላይ በቦክስ ሲመታት መሬት ላይ ቁጭ ስትል፤ ያልተያዘው ግብረአበሩ አፏን በእጁ አፍኖ ሲይዛት፤ ተከሳሽ ሟች ለብሳው በነበረው የሹራቧ ገመድ አንገቷን አንቆ በመያዙ አረፋ እየደፈቀች ስትወድቅ፤ ያልተያዘው ግብረአበሩ ሞታለች በማለት አፍና አፍንጫዋን በስካርፕና በፎጣ ሲሸፍናት፤ ተከሳሽ ከሟች ኪስ ውስጥ 950 (ዘጠኝ መቶ ሃምሳ) ብር በመውሰድ ተከሳሽ ደረቷን፣ ያልተያዘው ግብረአበሩ ደግሞ ሁለት እግሯን በመያዝ ወደ ውሃ መውረጃ ቦይ ጥለዋታል።
ከዚህ በኋላም ተከሳሽ ሟች መኖሪያ ቤት በመሄድ ንብረትነቱ የራሷ የሆነ ቼሪ የተሰኘ ሞባይል ወስዷል። በመሆኑም ተከሳሽ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀመው ከባድ የውንብድና ወንጀል ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አደራጅቶ ክስ መስርቶበታል።
ውሳኔ
መጋቢት 09 ቀን 2014 ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ደጉ በቀለ በ15 (በአሥራ አምስት) ዓመት ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም