ወርቁን ያፈዘዘ፣ ድሉን ያነቀዘ

ሰውዬው በራሱ የግል ማህበራዊ ገጽ በለቀቀው ቪዲዮ እጁን ወደላይ እያመላከተ አንዳች ነገር ያሳያል። ምስሉ የሚጠቁመው የዘንድሮውን የዓለም አትሌቲክስ ሩጫን ነው፡፡ ዓይኖቼን ወደ ቪዲዮው ጥዬ በአስተውሎት መቃኘት ያዝኩ፡፡ በትክክል እያየሁት ያለው የታዋቂዎቹን የሩጫ ተወዳዳሪዎች የአንገት ለአንገት ትንቅንቅ ነበር፡፡

የመመልከቻው ስክሪን የሚሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ ያሳያል፡፡ የእኛዎቹ የ10ሺህ ሜትር ተወዳዳሪዎች ጉዳፍ ጸጋዬ፣ እጅጋየሁ ታዬና ለተሰንበት ግደይ እግር በእግር ከምትከተላቸው ሲፈን ሀሰን ጋር የሞት ሽረት ትግል ይዘዋል፡፡ ይህ አይነቱ ግብግብ ለማሸነፍ፣ ድል ለመንሳት በሚደረግ ጥረት እርስ በርስ ሳይቀር የሚፈጠር ሽኩቻ ነው፡፡

እስከ ዛሬ የበርካታ ታዋቂ አትሌቶችን መሰል እውነታዎች አስተውለናል፡፡ የአብዛኞቹ ሁኔታ ልብን ቀጥ የሚያደርግ ለአፍታ አይምሮን የሚሰውር ነው፡፡ የአሁኑን ምስል ምንነት እንዳረጋገጥኩ ጆሮዎቼ ዳግም ወደ ሰውዬው ንግግር አዘነበሉ፡፡

ተናጋሪው በአትሌቶቹ ምስል ግራና ቀኝ ታጅቦ ማውራቱን ቀጥሏል፡፡ ንግግሩን ተከትሎ የሚሰጡ አስተያየቶች አስገራሚ ናቸው፡፡ ከምስሉ በታች ያለው ጽሑፍ ደግሞ እንዲህ ሲል ይነበባል፡፡ ‹‹ ክፋት ራሱን ይገድላል››

ይህን ርዕስ ካነበብኩ በኋላ ለማወቅ ያለኝ ፍላጎት ቢጨምር የሰውዬውን ንግግር አንድ በአንድ ማድመጥ ያዝኩ፡፡ እሱ እንዲህ እያለ መዘርዘሩን ቀጥሏል፡፡

‹‹የሰው ልጅ የመጨረሻው ተንኮል እንደ ሲፈን መውደቅ መሆኑን ላሳያችሁ፣ ሲፈን በዚህ ሩጫ ላይ ተንኮልን ነበር የሰራችው፣ ደክሟት አይደለም የወደቀችው፣ ቪዲዮውን፣ ቪዲዮውን ወደኋላ ተመልከቱ››

ሰውዬው እንዳለው ለማድረግ ቪዲዮውን መልሼ በጥንቃቄ ማስተዋል ያዝኩ፡፡ ፊትና ኋላ የሚከታተሉት ሴት ሯጮች ከባድ ትንቅንቅ ላይ ናቸው፡፡ ተናጋሪው አሁንም በስሜት ማውራቱን ቀጥሏል፡፡

‹‹ሆነ ብላ እሷን ስትደበድባት ነበር ፡፡ ወደኋላ ዞራ ስትመለከት እይዋት፣ አያችኋት? እሷ ስትሮጥ የነበረው አንደኛው ‹‹መም›› ላይ ነበር፡፡ መንገድ እየዘጋች አንገት አንገቷ ላይ በክርኗ ስትመታት ነበር፡፡ እኔ እንዴት ወደቀች በሚል ስመለከት ነበርና ለምን ወደቀች? ጥላት ነው? ጠልፋት ነው? ስል ነበር፡፡ እሷን ልትጠልፍ ሄዳ ራሷ ተጠልፋ ወደቀች››

ይህን አባባሉን ተከትሎ ንግግሩን የሚደግፉ አስተያየቶች፣ ከስር መሰንዘር ጀምረዋል፡፡

‹‹እውነት ነው፣ ወንድም ፣ ደባ ራሱን ሥለት ድግሱን አይስትም ፣ እውነት ነው ክፉ ነች እግዚአብሔር አያት በድንቅ ሥራው … በጣም ስትመታት ነበር ልክ ነህ … ›› ሌሎች ሀሳቦችም እንዲሁ ያለ ተቃውሞ የሚደጋገፉ፣ የማይነቃቀፉ ነበሩ፡፡

የተናጋሪውን ሀሳብ አለፍ እያልኩ ለማዳመጥ ሞከርኩ፡፡ በድንገት ይሄኛው ቃል ይበልጥ ውስጤን ያዘው፡፡

‹‹ወደኋላ ለምን ተመለከተች አይደለም፣ ግን ተንኮሏን ተመልከቱ፣ አያችሁ እግዚአብሔርም በሕይወታችሁ እንዲሁ ነው፡፡ ጠላት ሰይጣን የሰው ሥጋን ለብሶ እንዲህ ያደርጋል፡፡ አያችሁ እቺ ራሷን አልተተናኮለችም ፣ እሷ ግን መንገዷን ዘጋች ››

የተናጋሪው ሀሳብ በዚህ ብቻ አልተቋጨም። ሌሎች ተመሳሳይ ንግግሮች በነቀፌታ ታጅበው ቀጥለዋል፡፡ የአንባብያን ተመልካቹ አስተያየት እንዲሁ፡፡ ይህን ቪዲዮ አይቼ እንደጨረስኩ የአሸናፊዎቹን ኢትዮጵያውያን አትሌቶችና ለሀገረ ኒዘርላንድ የምትሮጠው የሲፈን ሀሰን ምስል ለዓይኖቼ ደረሱ፡፡

ከሩጫው መጠናቀቅ በኋላ ሁሉም አንድ አይነት ትስስርን በሚያመላክት ስሜት ተቃቅፈው ይሳሳማሉ። የወደቀችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፈን ከመሬት ተነስታ ደስታዋን ለሀገሯ ልጆች የምትገልጸው ያለ አንዳች አስገዳጅነት መሆኑ ተሰማኝ ፡፡

የዕለቱ ሩጫ ከተጠናቀቀ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አትሌት ሲፈን ተናግረዋለች የተባለው ሀሳብ በአይምሮዬ ውል አለኝ፡፡ እሷ በሩጫው ጊዜ ‹‹አካሌን መነካት ተሰምቶኛል ›› ማለቷ ትኩረት ስቦ ሲያነጋግር ነበር፡፡ ጉዳዩ በዚህ ብቻ አልቀረም ፡፡ ይህን አስተያየቷን ተከትሎ በርካቶች የስድብና የነቀፌታ ቃላቸውን ሲያወርዱባት ከርመዋል፡፡ ከድል አፋፍ ቆማ የመውደቋ ጉዳይ ለብዙዎች ህመም አልነበረም። አጋጣሚው ከዚህ በተቃራኒ ለከፋ ወቀሳ ዳርጓታል። ንግግሯ ተንሻፎ ሲተረጎምና ሲተነተን መቆየቱም የአደባባይ ሚስጥር ነው ፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ አትሌቷ ለመገናኛ ብዙኃን የሰጠችው አስተያየት በስፋት ሲደመጥ ሰንብቷል። በእኔ ግምትም ይህ ንግግሯ በአግባቡ ከተደመጠ ሚዛን የሚደፋ ይመስለኛል፡፡ ሲፈን ጋዜጠኛው ድሉን አስመልክቶ ላቀረበላት ጥያቄ ምላሸዋ በደስታ የታጀበ ነበር፡፡ ደጋግማ በሀገሯ ልጆች የተገኘው ድል የእሷ ጭምር ስለመሆኑ ትናገራለች፡፡

ሲፈን ወደፊት በፓሪስ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ጭምር ኢትዮጵያውያን ደማቅ ድል ቢያሰመዘግቡ እወዳለሁ ትላለች፡፡ ሰዎች በማንነታቸው የሚደርስባቸውን የበታችነት የምትጸየፈው ሲፈን ለመላው ኢትዮጵያውያን ያስተላለፈችው መልዕክት ጥብቅ ነው፡፡ እየደጋጋመች፣ ስለመዋደድ፣ ስለመከባበር፣ ስለአብሮነት ትገልጻለች፡፡

ሲፈን ከሀገሯ የወጣችው በልጅነቷ ነው፡፡ ከድል በኋላ የምትሮጥበትን የኒዘርላንድ ባንዲራ ማውለብለብ ግድ ቢላትም ከዚሁ ጎን የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ ማየቱ በእጅጉ ያኮራታል፡፡

እሷ እንደምትለው አንዳንዴ የአንዳንድ ሰዎች ክፉ ንግግር እያስከፋት ነው፡፡ ከባንዲራ ጋር ተያይዞ የሚሰጠን ያልተገባ አስተያየት ደግሞ መቼም ቢሆን አትቀበልም፡፡ አትሌቷ ኢትዮጵያ የተወለደችባት፣ ዕትብቷ የተቀበረባት ምድር መሆኗን የምትናገረው በኩራት ነው፡፡ ዘንድሮ የተገኘው ድል የእሷም ነውና ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ›› የምትለው በተለየ ስሜት ሆኗል።

አስቀድሜ በማስረጃ ካሳየኋችሁ እውነታ መለስ ባልኩ ጊዜ የአንዳንድ ሰዎችን አሁናዊ ስሜት ለማየት ሞከርኩ፡፡ እነሱ እንደሚሉት በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፈን ሀሰን ላይ የተሰጠው አስተያየት ተገቢ አልነበረም፡፡ ለሌላ ሀገር ተሰልፎ መሮጥ በእሷ የተጀመረ አይደለምና፡፡

ሩጫን ጨምሮ በእግር ኳስና በሌሎች የስፖርት ዘርፎች በተለመደው አነጋገር ‹‹ ተሸጦ›› መሄድ ብርቅ ሆኖ አያውቅም፡፡ ከሰሞኑ ሩጫ ተያይዞ የሚሰነዘረው አጉል ሃሳብ ግን በክፉ ስሜት የታሸ ውል አልባ ጉዳይን ሰንቋል፡፡

በእነሱ ዕምነት ማንም ቢሆን ለውድድር ሲቀርብ የራሱን አሸናፊነትና አይበገሬ ድል በማስቀደም ነው። የሀገርንና የግል ስምን አድሞቆ ለማውጣት ደግሞ ሁሌም እስከ መውደቅ፣ መላላጥ የሚደርስ ፉክክር ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ይህ እውነታ ባለበት አንዷን ክር ብቻ መዞ ስም ማጥፋቱ ለሀገርም፣ ለወገንም አይበጅም፡፡

የሁሉንም አስተያየትና ስሜት በእኩል አስቀምጬ ጉዳዩን በወጉ ልለየው ሞከርኩ፡፡ ያኖርኩት ሚዛን ወዲያው ለአንዱ ወገን አጋደለ፡፡ የተባለው እንዳለ ሆኖ በራስ ግምት በመነሳት ብቻ የሰው ስም ማጥፋቱ ለእኔ ልክ ያለመሆኑ ገባኝ፡፡ ሁሌም ከምርቱ ግርዱ ሲቀድም ከእጅ የገባ ፍሬ ይወድቃል፡፡ ከክምሩ ይልቅ ትቢያ አፈሩ ይገኛል፡፡

ከሰሞኑ የሆነውም እንዲሁ ነው፡፡ በወቅቱ በእጃችን የገባን ድልና አሸናፊነት ከማድነቅ በላይ ጎዶሎ ፍለጋን ባዝነናል፡፡ ድላችንን አሳስተን በአጉል መንገድ ተጉዘናል፡፡ ይህ ባይሆን፣ ባይታሰብ መልካም ነበር፡፡ እንዲህ መሞከሩ ደማቁን ወርቅ አፍዝዞ፣ ታላቁን ድል እንዳያነቅዝ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡

ወደፊት ገና ብዙ ሩጫዎች፣ ብዙ ድሎች ይጠብቁናል። እኛ ሁሌም መውደቃችንን ትተን መነሳታችን እናስብ። ክፉውን ስሜት ስንረግጠው መልካም አጋጣሚው ከጎናችን ይሆናልና፡፡ ‹‹አበቃሁ!››

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 20/2015

Recommended For You