ኮለል በአሸንዳ ገነት

አሸንዳ 2015፤ አንድም ለጥበብ አንድም ለበጎ ሥራ፤ ከ30 ያህል ድምጻውያን ጋር በሚሊኒየም አዳራሽ ከታዳሚው ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ተይዟል። ባህል ከእኔነት ወጥቶ ሀገራዊ ካባን ሲደርብ ሁሉም ዜጋ የውበቱ መጎናጸፊያ ጥለት ይሆናል። አሸንዳ 2015 ከያዘው ዓላማና ከተለየ ዳግም ድምቀት አንጻር “አሸንዳ ገነት” ልንለው ወደናል።

ከአራት ዓመታት በኋላ የአሸንዳ በዓል ዳግም ከነ ግርማ ሞገሱ የሚመለስበትን ትኬት ቆርጦ በዝግጅት ላይ ቆይቷል። ፊደል ላውንጅ ደግሞ የጉዞ ወኪሉ ሆኗል። አሸንዳ የትግራይ ሴቶች የውበት መጎናጸፊያ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህል ትውፊትና እሴትም ጭምር ነው። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በደማቁ እየተከበረ የነበረ ቢሆንም ባለፉት አራት ዓመታት ግን ደብዘዝ ማለቱ አልቀረም። ሁለት ዓመታትን በኮሮና ቫይረስ ሁለት ዓመታትን ደግሞ በጦርነቱ ሳቢያ ብዙም ደማቅ አልነበረም። 2015’ን በተመሳሳይ መልኩ ለማለፍ ግን አሸንዳም ሆነ የአሸንድዬ ክብረ በዓል ታዳሚዎች የሚፈቅዱት አልሆነም። ታዳሚው ከአሸንዳ፣ አሸንዳም ከታዳሚው ጋር ለመገናኘት በእጅጉ ቋምጠዋል። ለዚህም የክብረ በዓሉ አውታር የሆነው ፊደል ላውንጅ አሸንዳን ከፍ ባለ ድምቀት ለማክበር ለስድስት ወራት ያህል ደፋ ቀና ሲል ከርሞ አሁን ደግሞ ከበቂ ዝግጅት ጋር ፊቴን ወደ ታዳሚው አዙሬያለሁ ይላል። ቀጠሮውን ደግሞ ከሚሊኒየም አዳራሽ አድርጓል። በአሸንዳ 2015 የሚሊኒየም አዳራሽ በሮች ዛሬ ወለል ብለው ይከፈታሉ። አሸንዳም በሀገሬው ባህል አጊጠው የአሸንድዬን ጉንጉን ከወገባቸው ላይ በነሰነሱ ውብ ልጃገረዶችና ተጋባዦች ታጅቦ ይደምቃል።

ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም አዘጋጁ ፊደል ላውንጅ ስለ ዝግጅቱ የምንላችሁ አለና አድምጡን በማለት ለሚዲያ አካላት ጥሪ አድርጎ ነበር። እንዲህ ካለው ጥሪ አይቀርምና ጠሪ አክባሪ ሚዲያዎችም በተባለው ቀንና ሰዓት ቦሌ ከሚገኘው ፊደል ላውንጅ በመድረስ መግለጫውን ተከታትለዋል። እኛም ከእነዚሁ መካከል ነንና የሰማነውን ለእናንተ ለውድ የዘመን ጥበብ አንባቢያን አካፍለን፤ ለማወራረጃ ትሆነን ዘንድም ከክብረ በዓሉ ማሰሮ ላይ ጨለፍ አድርገን ልናቀርብላችሁ ወደናል።

አሸንዳ ኢትዮጵያ ሀገራችን ካሏት ግዙፍ የማይዳሰሱ እሴቶቿ መካከል አንደኛው ነው፤ በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት የፊደል ላውንጅ ስራ አስኪያጅና የአሸንዳ ክብረ በዓል ዋና አስተባባሪ አቶ ኤፍሬም ዮናስ፤ የአሸንዳ ዝግጅትን በተመለከተ የሚከተለውን ብለውናል፤ “ቀደም ሲል ማህበረሰባችን በሁለት ብርቱ ምክንያቶች የስነ ልቦና ጫና ደርሶበታል። የመጀመሪያው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ ወረርሺኝ ሲሆን ሁለተኛውም ደግሞ በጦርነት ነው። ይህን ክብረ በዓል ሰፋ ባለ መልኩ በሚሊኒየም አዳራሽ እንዲካሄድ ስናስብ እኛም ሦስት ታላላቅ አላማዎችን በማንገብ ነው። አንደኛውና የመጀመሪያው ዓላማችን የአሸንዳን በዓል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ለሚካሄደው ጥረት የጀርባ አጥንት ይሆን ዘንድ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ነው። ሁለተኛው ዓላማችን ደግሞ በዚሁ እለት ከዝግጅቱ ጎን ለጎን በጦርነቱ ወቅት ለተጎዱ ተማሪዎች የሚሆን የደብተርና እስክሪፕቶ ድጋፍ፣ ለትምህርት ቤቶች ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን፣ እንዲሁም በተጨማሪ ለአንዳንድ የማህበረሰቡ ክፍል የሚውል እርዳታ ለማሰባሰብ የተቻለንን ጥረት እናደርጋለን። ከዚህ በተጨማሪም ከትኬት ሽያጭና ከመሳሰሉት ከሚገኘው ገቢም የተወሰነው ለወገኖች ድጋፍ የሚውል ይሆናል። ሦስተኛውና ሌላኛው ግባችን በተለያዩ ምክንያቶች የኮሰሰውን የማህበረሰባችንን ስነ ልቦና በኪነ ጥበቡ በማከም ሀገራዊ ሰላምና አንድነትን ለማምጣት በማሰብም ጭምር ነው። የሁላችንም የጋራ በሆነችው በመዲናችን የሚሊኒየም አዳራሽ መከበሩ አሸንዳ የአንዲት ክልል እሴት ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ባህላዊ ትውፊት መሆኑን ያንጸባርቃል።” በማለት ተናግረዋል።

ስራ አስኪያጁ አክለውም፤ ብዙ ሃሳቦችን አንስተዋል። ‹‹በሌላ ወገን ደግሞ የምትጠይቁት ካለ ሲሉ እድሉን ለጋዜጠኞቹ ሰጥተዋል።

አሸንዳን የአንዲት ክልል ጉዳይ በማድረግ የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ በእለቱም ሆነ በዙሪያው ጣል ለማድረግ የሚፈልጉ የሉም ለማለት ይከብዳል። ነገር ግን በዚህ መንገድ ጫና ለማድረግ ወደ አዘጋጆቹ የመጣ ጉዳይ እንዳለና ምን አይነት ዝግጅት እንደተደረገ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦ ነበር። አቶ ኤፍሬም ምላሽ ሲሰጡ “ትግራይ የኢትዮጵያ የአብራክ ክፋይ ናት። ይህ እንዳይሆን የሚቃወምና የራሱን ዓላማ ለመጫን የሚሞክር ካለ የሚክደው መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብንና ኢትዮጵያዊነቱን ነው። ከትግራይ ክልልም ሆነ ከአዲስ አበባ መስተዳድር እንዲሁም ከሌሎች አካላት የተሰጠን ምላሽ አንጀት የሚያርስና የሚያስደስት ነበር። ዝግጅቱ በእንዲህ መልኩ መደረጉ የሁሉም ፈቃድ ነው።”

ዝግጅቱ ቀደም ሲል በነሐሴ 16 በትግራይ ክልል ለማክበር ታቅዶ የነበረ ሲሆን የኋላ ኃላ ግን እነዚህን ዓላማዎች በማንገብ ስኬታማ የሆነ የአሸንዳ ዝግጅት ለማካሄድና ሁለንተናዊ ለውጥን ለማምጣት ሲታሰብ ሚሊኒየም አዳራሽ በስተመጨረሻ ቀዳሚው ምርጫ ሆነ። ነሐሴ 16 በመቀሌ ከተማ ከተከበረ በኋላ የድግሱ ጽዋ በነሐሴ 18 በተራው ወደ አዲስ አበባ ይዞራል። ቀድሞ በነሐሴ 16 በመቀሌ ከተማ ብቻ ለማክበር የታሰበ በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ አምጥቶ በነሐሴ 18 የማክበሩ ሀሳብ የተከሰተው ዘግየት ብሎ ከአንድ ወር በፊት በመሆኑ ይህን እውን ለማድረግ አዘጋጆቹን መፈተኑ አልቀረም ነበር። ለ16 የተዘጋጁና ያለቀላቸው ልዩ ልዩ የህትመት ስራዎች ወደ 18 መቀየሩ ሌላ ተጨማሪ የጊዜ፣ ገንዘብና የጉልበት ጫና ነበረው። ነገር ግን ዓላማችን ለትርፍና ገንዘብ ለመሰብሰብ አይደለምና ስናደርገውም በደስታ ነው ይላሉ አዘጋጆቹ። ትልቁና ዋነኛው ግብ አሸንዳን በባህል ዙፋን ላይ አንግሶ፣ ኪነ ጥበባዊ ትውፊትንም ከሀገራዊ ስሜት ጋር ከፍ በማድረግ ወገንን መርዳት ነው።

በእለቱ ክዋክብት እንደ ጨረቃ ደምቀው ይታያሉ፣ የሚሊኒየም አዳራሽም ፈጽሞ ብርሃኑ አይደበዝዝም። ትግርኛው አይቀር አማርኛው ከላስታ እስከ ሰቆጣ፤ ከሽሬ እስከ ራያና ቆቦ አንዴ በላሌይ ጉማ አንዴ በሶራ እና ሶለል የሚሊኒየም አዳራሽ መንቀጥቀጡ አይቀርም። የትግራይ ክዋክብት ድምጻውያን ብቻም ሳይሆኑ ሌሎችም የአማርኛ ድምጻውያን አሸንዳን አካለ ውበት አልብሰው በመድረኩ ያቆሙታል። በዚሁ ዝግጅት ላይ ከ25 እስከ 30 ሺህ ታዳሚያን ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል። ሚሊኒየም አዳራሽም ቢሆን እኚህን ሁሉ ታዳሚያን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዛሬ ፈክቶ ይውላል። ለዚህም ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ላለው ሁሉ ግብዣው ቀርባል። የመግቢያ ዋጋዋም ቢሆን ከዓላማው አንጻር ቢያንስ እንጂ መቼም በዛ የምንለው አይነት አይመስልም።

በመግለጫው እለት አዘጋጆቹ በገለጹት መሰረት፣ መደበኛ የመግቢያ ዋጋ 950 ብር ሲሆን ከዚህ ላቅ ያለው ወይም የ“VIP` መግቢያ ዋጋ ደግሞ 2950 ብር መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህ ዝግጅት የታጩ 30 ያህል አርቲስቶች ከውጭና ከሀገር ውስጥ ወደ አዲስ አበባ ገብተውም በዝግጅት ላይ ቆይተው ዛሬ ወደ መድረክ ብቅ ይላሉ። አሁን አሁን በዘመን አመጣሽ ስርዓቶች ተሸብበን የኛ ነገር አልጥም አልቀመስ ላለን፤ ፍቱን መድኃኒቱ እንዲህ ያሉ ክብረ በዓላት ናቸው። ታዲያ እነዚህን ድንቅ ክዋኔዎች በየጓዳው ከመከወን ይልቅ እንደዚህ ወደ አደባባይ አውጥቶ በትልቁ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ማክበሩ ባህሉ እንዳይጠፋም ሆነ ተበርዞ እንዳይመረዝ አቅምና ጉልበት ይሆኑታል። በየትኛውም ወሰንና ድንበር ውስጥ ብንሆን እኛ የኢትዮጵያ እስከሆንን ድረስ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ባህልና ስርዓት የኛው ነው።

ስለ ዝግጅቱና አዘጋጆቹ ይህን ያህል ብለን ስለ አሸንዳ ምንነትና ስለ ክብረ በዓሉ ጥቂት ሳንል ብናልፍ ደግ አይደለምና በተራ ከአሸንዳ ጋር በአሸንድዬ ኮለል እንበል። ከዋግ ኸምራ ሻደይ፣ ከቆቦ ሶለል፣ ከላስታ አሸንድዬ፣ ከትግራይ አሸንዳ ምን ጠፍቶ፤ ከአሸንዳ ገነት ውበት ቢሉ ባህል ከክብረ በዓሉ ሰማይ ላይ ለጉድ ይዘንባል። እኛም ማሰሮዎችንን ከአሸንዳችን ላይ ደቅነን ከአሸንዳ ገነት የባህል ትውፊቷ ከጨዋታ በረከቷ እንቋደስ።

አሸንዳ የትግራይ ሴቶች በተለይ ደግሞ የልጃገረዶቹ የነጻነት አድማስ የሴትነት ወግ ብርሃን ጮራ መፈንጠቂያ ነው። ሴቶች ከዓመት ዓመት በናፍቆት እየጠበቁ በቄጠማ መሳይ የሳር አይነት ወይም በአሸንድዬ ጉንጉን ከነ ስጦታው ይቀበሉታል። አሸንዳ የሚለው ስያሜም ከዚሁ የሳር ቅጠል ላይ ተቀንጥሶ የተወሰደ ስለመሆኑ ይነገራል። ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 21 በልጃገረዶች ዘንድ ፌሽታና ደስታ፣ ጨዋታውም አሸንድዬ አሸንዳ ነው። በአሸንዳ ምድር ሴት ልጅ የት ገባሽ የት ወጣሽ አትባልም ምክንያቱም ሁሉም ቤተሰብ ለሴት ልጆቹ ነጻነትን አውጇልና። ለአሸንዳ አንዲት ሳምንት ስተቀር ሴቶቹ ሽር ጉድ እያሉ የአሸንዳን መድረስ በጉጉት ደጅ ደጁን ያያሉ። ለእጃቸው አምባር፣ ለአንገታቸው ጌጣ ጌጥ፣ የባህል አልባሳቱ ምኑ ይቀርና ሁሉንም በማዘጋጀት ይጠመዳሉ። በአሸንዳ በዓል ያገባችን ሴት ካላገባችው ለይቶ ለማወቅ ነጋሪ አያሻውም፤ የጸጉር አሰራሯን መመልከት ብቻ በቂ ነው።

በአሸንድዬ እለት ሴቶቹ በጉንጉን ጸጉራቸው ላይ ባህላዊ ቀሚሶቻቸውን ለብሰው፣ ከመቃው አንገቶቻቸው ጌጣ ጌጡን ቁልቁል ከደረቶቻቸው ለቀው፣ ከእግሮቻቸው አልቦ ከእጆቻቸው አምባሩን በማጥለቅ ሀር ጸጉር የመሰለውን የአሸንድዬን የሳር ጉንጉን ከወገባቸው ላይ አስረው ከድምጻቸው ጋር በሙዚቃው ምት ኮለል.. ሶብለል.. ዞብለል ሲሉ እንደ ማየት ያለ የባህል ውበት ከአይን አልፎ ቀልብን ይሰውራል። ከወገባቸው ላይ የታሰረውን የአሸንድዬን ዘርፋፋ የጉንጉን ዘለላዎች አንዴ ወደ ግራ አንዴ ወደቀኝ ብትን…ብትን…እያደረጉ ተሰባስበው ከመንደራቸው ሲዞሩና ዘለል ዘለል እያሉ ሲመነሸነሹማ አቤት!…አጃኢብ ያስብላል። የአዕዋፋት ዝማሬ በሚመስል መልኩ በመረዋው ድምጻቸው ላይ ዜማና ግጥሙን አክለውበት ባህላዊውን ጨዋታ ሲከውኑትማ እንዴት አያፌዝ…እንዴት አያሰምጥ ..እንዴትስ ስሜትን ከልብ ላይ አይደባልቅ…

አሸንድዬ……….ሆ

አሸንዳ ሙሴ…ሆ

እንደ ቀሚሴ……ሆ

አሸንድዬ………ሆ

አሸንዳ…….ሆ

የኔማ አባብየ………..ሆ

ውበት ያነዘዘው…..ሆ

የኔማ እማምየ………ሆ

ድልድይ ወይዘሮ….ሆ

እያሉ ሸጋ ልጃገረዶቹ በየቤቱ እየዞሩ የባህላቸውን ከነ ወጉ ያደሩታል። የቤቱ እማወራና አባወራም ለልጃገረዶቹ የሚሆን ስጦታ ከማጀታቸው አይጠፋም። የወደዱትንና ያሰቡትን ገጸ በረከት ያበረክቱላቸዋል። ከዚያ በኋላ የሴቶቹ “ሳምራ” ይቀጥላል።

ሳምራዬ……ሳምራ

ሳምራዬ……ሳምራ

ሰሸሽ…..ሳምራ

ስገባ……ሳምራ

ባጀባ……ሳምራ

ሳምራዬ……ሳምራ

ሳምራዬ…….ሳምራ

በማለት ጭፈራው ሳይቋረጥ መልካሙን እየተመኙ ይሄዳሉ።

ታዲያ ዘመን ያልሻረውን ይሄን ሁሉ የባህል ጨዋታና ጥበብ በሚሊኒየም አዳራሽ ለመመልከት እንዴት አይናፍቅም… እንዴትስ ተብሎ ይቀራል… ዛሬ ነሐሴ 18 ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ የአዳራሹ በሮች ይከፈታሉ፤ አሸንዳ ገነት ደግሞ ከቀኑ ስድስት ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት 30 ክዋክብት ድምጻውያን ነግሶ ያመሻል። እናም ስንመጣ ባህሉን መስለን፣ ሀገራዊ አንድነትን ለብሰን፣ ለወገን ድጋፍ የምትሆነዋንም ሸክፈን እንመጣ ዘንድ አደራችሁን ይላሉ አዘጋጆቹ። እኛም በአሸንዳው ዝግጅት ሀገራዊ ሰላምና ፍቅር ከእጹብ ድንቅ በረከት ጋር፤ ወርቅ አልማዝ ይፍሰስበት እያልን አበቃን!!!

አዘጋጆቹ በአንክሮ ያልዋት አንዲት ነገር ብትኖር ይቺ ናት፤ “ወደ ዝግጅታችን ስትመጡ አደራችሁን ዝግጅታችንን መስላችሁ ይሁን። የበዓሉ ዋነኛ ድምቀት እናንተው ናችሁና ክብረ በዓሉን የመሰለ አለባበሰ፣ ወግና ስርዓቱን የጠበቁ ጌጣ ጌጦች… ከጸጉር አሰራር ጀምሮ እንዳንዘነጋው በማስታወስ ለሚደረገው ድጋፍም አደራችሁን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 18/2015

Recommended For You