ሃሳብ የሁሉ ነገር መነሻ ነው። አንዲት መርከብ ያለ ግዙፍ የውሃ ሃይል መንቀሳቀስ እንደማትችል ሁሉ ጥበብም ያለ ሃሳብ ባዶ ናት። የሃሳብን ሃያልነት ከደራሲያንና ከከያኒያን በላይ ማን ሊረዳ ይችላል? በዴርቶጋዳ የሃሳብ ዋሻ ገብቶ በራማቶራ አዲስ የሃሳብ ዓለም ውስጥ ሲወጣ፣ በተከርቸም ስምጥ ባህር ቀዝፎ በዣንቶዣራ ድልድይ ብቅ ሲል ይስማከ ወርቁ ከማንም በላይ ይህንን ተረድቶታል ቢባል ስህተት ይሆን?።
ቁጭ ብሎ በሃሳብ እየተሳፈረ በምናባዊ በረራ ከእሩቅና ከእይታ የተሰወሩ አለማት ውስጥ ገብቶ በብዕሩ የሚያሰፍራቸው ጉዳዮች ይህንኑ ይመሰክራሉ። በምናቡ እየተመለከተ በብዕር ቀለማት ማስፈሩ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍቶቹ በአንባቢያን ዘንድ የሚፈጥሩት የስሜት ማዕበሎች ደግሞ ከታሪኮቹ በስተጀርባ ያለውን የምናቡ ዓለም ፈጣሪ ለማወቅ ጉጉትን ያሳድራሉ።
“መሄድ ከተቻለ ሂዱ-ሌላ አስሱ-ከወዳኛው ዓለም፣
ምጠቁ ጥለቁ-ይቅናቹ ግድ የለም፤
ምጠቁ ጥለቁ-በጉም ሃሳብ ህዋ-በምርቅንቅን ዓለም፤
…………..ግን………..
ያ ክር ሲበጠስ፤
ሲከጅል መመለስ፤
ምርቃናው ሲሰበር፤
እውነት ሲበረበር፤
ማንነት ሲቀለም፤
በፍኖተ ቅዠት-በምርቅንቅን ዓለም፤
ወሳጅ መንገድ እንጂ-መላሽ መንገድ የለም”
(የወንድ ምጥ)
የእርሱ መጽሐፎች እንደ መጽሐፍ ብቻ እንደዋዛ ተነበው የሚታለፉ ሳይሆኑ ከተሳሉት ገጸ ባህሪያት ጋር አብሮ በስሜት እየነሆለሉ፣ ተራራውን ወጥተው፣ በምናብ ሜዳ ሸንተረሩን አቋርጠው በድካም ውስጥ ደክመው፣ ሃዘናቸውን እያዘኑ በደስታቸው እንዲደሰቱ ያደርጋሉ። ያላየናቸውን ዓለማት በሃሳብ እየበረርን ጓዳ ጎድጓዳቸውን ያስጎበኘናል። በዴርቶጋዳ፣ ራማቶሓራ፣ ዣንቶዣራ፣ ሜሎስ፣ የኦጋዴን ድመቶች….በእነዚህ ሁሉ ውስጥ ያልቃኘናቸው እውነታዎች ያላሰስናቸው ሚስጥራት የሉም። እነዚህንና ሌሎችንም መጽሐፍት በሚጽፍበት ጊዜ ሁሉ ይስማከን ከደራሲያኑ ለየት የሚያደርገው አንድ ነገር አለ። ድርሰት የምናብና የፈጠራ ውጤት ቢሆንም የይስማከ ድርሰቶች በምናብ ብቻ የሚወለዱ አይደሉም። መጽሐፍቶቹን ከመጻፉ በፊት የታሪኮቹ መቼት ከተሰየሙበት ስፍራ በመሄድ ገጸ-ባህሪያቱን በአካል ይገናኛቸዋል። ተገናኝቶም እያወጋ ኪናዊ ተመስጦ በተሞላበት እይታ እያጤነ የልብ ምታቸውን ያደምጠዋል። በአብዛኛው መጽሐፎቹ ውስጥ ያሉት ገጸ-ባህሪያትም ከእውኑ ዓለም ያገኛቸው ለብዙዎች የማይታዩ እውነታዎች ናቸው። በመጽሐፎቹ ላይም በብዛት ይስማከ እራሱን እንደ አንድ ገጸ-ባህሪይ አድርጎ የሚያቀርበው ለዚህ ነው። መጽሐፍቱን ለመጻፍ የሚረዳውን የገሀድ እውነታዎች ፍለጋ በሄደባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ከእስር ጀምሮ በርካታ ፈተናዎች ገጥመውታል።
የኦጋዴን ድመቶች የተሰኘውን መጽሐፉን በሚጽፍበት ወቅት ወደ ኦጋዴን በማምራት ነዳጅ ይወጣል ከተባለበት ስፍራ ለመግባት ወሰነ። ወደዚያ ስፍራ ለመግባትም የነበረው አንድ አማራጭ የጉልበት ሰራተኛ ባላገርና ከስምንተኛ ክፍል የወደቀ ስራ አጥ መሆን ነበረበት። በውቅቱ ግን ይስማከ የሁለተኛ ዲግሪውን አጠናቆ የዶክትሬት ዲግሪውን ለመማር የሚሰናዳበት ወቅት ነበር። የነዳጅ ቁፋሮ ስራው ላይ መሳተፍ የሚችለው ደግሞ የተማረና የተመራመረው ሳይሆን ከስምንተኛ ክፍል ወድቆ የቀረውን ብቻ ነው። እናም ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቅ አንድ ሰው በመቅረብ ከስምንተኛ ክፍል የወደቀ ተማሪ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ በማሰራት በጉልበት ሰራተኝነት ተቀጥሮ ከኦጋዴን የነዳጅ ማውጫ ገባ። በቁፋሮ ስራው ላይም የእውነትም ለስራው እንጂ ለመጽሐፉ ግብዓት የሚሆነውን መረጃ ለመሰለል መሄዱን የረሳው እስኪመስል ድረስ ለስራው የነበረው ትጋት አስገራሚ ነበር። የቁፋሮ ሂደቱ አስደሳችና ወደስኬት እየተጠጋ ሲመጣም ይሰማከን ጨምሮ ለአምስት ሰራተኞች ከአለቃቸው የእራት ግብዣ ጥሪ ደረሳቸው። ከአምስቱ መሃከል ከአንደኛው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መስርተው ነበርና በእራት ግብዣው ላይ ሳሉ ይስማከ ለምን ጉዳይ ኦጋዴን ላይ እንደተገኘና የእውነትም ከስምንተኛ ክፍል የወደቀ ተማሪ አለመሆኑን ሹክ ይለዋል። በመጠጡ ሞቅታው እየጋለ የመጣው ይህ ወዳጁም ገና ሰላሳ ደቂቃ እንኳን ሳይሞላው ጉዳዩን ከአለቃው ፊት አፍረጠረጠው። ወዲያውኑ በአንድ የስልክ ጥሪ ይስማከ ከእራት ግብዣ ተነስቶ ወደ እስር ቤት ወረደ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ደህንነቱ ለተሰኘው መጽሐፉ፣ ከነበረበት እስር ቤት ከወጣ በኋላ ከእስር ቤቱ እስከ ቤቱ ድረስ ያለውን እርቀት በሜትር በመለካት ላይ ሳለ ፖሊሶች ይዘውት በድጋሚ ወደ እስር ቤት መመለሱን ይናገራል። ደህነነቱ የሚለው ይህ 14ኛ መጽሐፉ ከገጸ-ባህሪያቱ ጀምሮ እስከ ታሪክ አወቃቀሩ አሁናዊውን የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር የሚያስቃኝ ሲሆን ኪነ ጥበባዊ በሆነ መንገድ አሳምሮ ጽፎታል። ለቅምሻ ያህል እስቲ ከዚህ መጽሐፍ ሁለት ሃሳቦችን እንመልከት።
“አንዲት ቅንጣት እትም ነበረች ይላል ተረቱ ሲጀምር። ከዚያም በታላቁ ፍንዳታ ባንግ ቢንግ ይህን ዩኒቨርስ ፈጠረችው። ከዚያም ዩኒቨርስ ይሄን ቅርጽ ያዘ። ከመፈንዳት የሚመጣው ሥርዓት አልበኝነት ነው እንጂ ሥርዓት አይመጣም። መፈንዳት ሥርዓት አያሰፍንም…”
…………..
ዘመን አይፈረጥጥ፣
ቀንም መሽቶ አይነጋ፣
ሰው ነው የሚጨልም፣
ሰው ነው የሚነጋ።
( ደህንነቱ)
በመከራና በብዙ ፈተና የተሞላችው ሕይወት አንዲት አጋጣሚ የፈጠረችው ክስተት በይስማከ ሕይወት ውስጥ የረዥም ጊዜ መጥፎ ጠባሳ አሳርፋበት ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊት የመጥፎ አጋጣሚ መጥፎ ትዝታ ከይስማከ ሕይወት ላይ ጥላዋን አጠላች። ነሐሴ 9 ቀን 2009 ዓ/ም ሀገር ሰላም ብሎ ብዙ የተስፋ ሃሳቦችን ከውስጡ እያሰናሰነ፤ ነገን በተስፋ እየተመለከተ የግል መኪናውን አስነስቶ ከቤቱ፣ ከዚያም ከሰፈሩ እየራቀ ሄዶ ጉዞውን ከአዲስ አበባ ወደ ሐዋሳ በማድረግ አፈተለከ። የመኪናዋ ጎማ እየተሽከረከሩ ወደፊት በገሰገሱ ቁጥር የእርሱም ተስፋ በሃሳብ ሞተር ወደ ነገ ብርሃን በመንጎድ ላይ ነበረች። ግን አንዲት አጋጣሚ፣ አንዲት ቅጽበት ከሁሉም ነገሮች ቀጥ አድርጋ አቆመችው። የእርሱ የተስፋ እሽክርክሪትና የሚኪናዋ ጎማዎችም ወደፊትም ሆነ ወደኋላ ተስኗቸው ካሉበት ብቻ ያለማቋረጥ ተሽከረከሩ። ጎማዎችዋን ወደላይ ሰቅላ ከተጨራመተችው መኪና ውስጥ ይስማከ በአንገቱ ከመሪው ጋር ቁልቁል በግንባሩ ተላትሞ ለሁለት ከተከፈለው ጭንቅላቱ ስር የሞትን ቀጭን ደወል መጠባበቅ ጀመረ። ነብሱ በቀጭን ገመድ ላይ ተንጠልጥላ ወራትን በድን ሆኖ በሕክምና ላይ ቆየ። ከጊዜያት በኋላም የይስማከ አንደበት ምንም ነገር ከመተንፈስ ተቆጠበች። ይስማከ መስማት እንጂ መናገር ተሳነው። ከብዙ የሕክምና ጥረት በኋላ ነብሱ ተመልሳ ማገገም ቢችልም አንደበቱን እንዳሻው አንቀሳቅሶ ቃላትን ማውጣት ግን የማይሆን ነገር ነበር። ከአደጋው የተነሳ መስማት እንጂ መናገር ተሳነው። ከዚያም በላይ ደግሞ የማስታወስ ችሎታውን ተነጠቀ። ከብዙ የሃሳብ ውቅያኖስ ውስጥ እየጠለቀ አዳዲስ ነገሮችን የሚያጠምደው ምናባዊ አዕምሮው እንኳንስ ያልታየውን ሊያይ ቀርቶ በእውኑ ዓለም በሕይወቱ ውስጥ የሆኑትንና እየሆኑ ያሉትን ነገሮች ማስተዋልም ሆነ ማስታወስ ተሳነው። ሌላው ይቅርና ስንቶች በአድናቆትና በክብር የሚጠሩትን ‘ይስማከ’ የሚለው የገዛ ስሙን እንኳን ከአዕምሮው ተሰወረች። ስሙን ለማስታወስ ተቸግሮ እንደነበረ ዛሬ ደህና ሆኖ እራሱ በአንደበቱ ይናገረዋል።
ይስማከ ወርቁ ከደረሰበት ከባድ የመኪና አደጋ አንጻር ዳግም በሁለት እግሩ ቆሞ፣ ከአንደበቱ ቃላትን ሲያወጣ እንሰማለን ያለ ሰው አልነበረም። እንኳንስ ሌላውና እርሱ እራሱ ያቺን ወርቃማ የጥበብ ሙዳይ የነበረችውን የቀድሞ ማንነቱን በድጋሚ አገኛታለሁ የሚል ተስፋው መንምኖ ነበር። የተስፋ ሞተሩም ባለችበት ከመሽከርከርዋም በላይ ቀጥ ብላ ቆማ ነበር። ግን ሁሉም ነገሮች እንደመጥፎ ትዝታ እያለፉና እንደ ጉም እየበነኑ፣ የተስፋውም ሞተር በቀስታ እየተነሳችና ከቀን ወደ ቀን እየጋለች ሄደች። በሕይወት ውስጥ የሚሆኑ ነገሮች ብዙ እንደመሆናቸው የማይሆኑ ነገሮች የሉም። ይስማከ የተጫነበትን ግዙፍ የሕይወት አጋጣሚ አለት ፈንቅሎ ከቀድሞው ማንነቱ ጋር ከመገናኘቱም አልፎ ለሌላ የጥበብ ድግስ መሰናዳት ጀመረ። ከዚህ ሁሉ ጭንቅ በኋላ 14ኛ ልጁ የሆነችውን ‘ደህንነቱ’ የተሰኘችውን መጽሐፍ ጽፎ የሕይወት ስጦታውን ለማበርከት ቻለ። በዚያ መጥፎ ጊዜ ውስጥ ይስማከን የተመለከተ ሰው ይህንን መጽሐፍ ሲያነብ ይህ ሰው የእወነትም ይስማከ ወይንስ ዳግማዊ ይስማከ ማለቱ የማይቀር ነው…”ተመስገን! አልሞትኩም በሕይወት አለሁ..እፎይ!…” አለ ይስማከ። ሕይወትህ እስካላለፈ በሕይወትህ መጥቶ የማያልፍ ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር ያልፋል። የዚህን አባባል እውነታ ለማስረገጥስ ከይስማከ የበለጠ ማን ሊገኝ ይችላል።
ሰውን አትጥላ ልብህን ንጹህ አድርግ፣ ቀለል ያለ ኑሮ ኑር፣ አትጨነቅ በፈጣሪህ ተመካ፣ እውቀትህን ለሌሎች አካፍል አንድ አባባል ቢሆን እንኳ፣ ብዙ በሰጠህ ቁጥር ብዙ ታገኛለህ… የይስማከ የሕይወት ፍልስፍናዎች በእነዚህ የእራሱ በሆኑ አባባሎች የተቀመሩ ናቸው። ለእራስ ከመኖር በላይ ለሌሎች ሰዎች በመኖር ውስጥ ትልቅ የደስታና የእርካታ ምንጭ እንደሚገኝ ያምናል። መጽሐፍ አይሸጥም በሚባልበትና 20 ሺህ አሳትሞ መሸጥ ብርቅ በሆነበት በዚህ ዘመን 200 ሺህ ኮፒ በመሸጥ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጽሐፍ ህትመቱን ኢንዱስትሪ መምራት የቻለው የ14 መጽሐፍት ደራሲ የሆነው ይስማከ ወርቁ ስሙን በወርቅ ብዕር የጥበብ ማህደር ላይ አስፍሯል። ከደረሰበት አደጋና ከትዳር ሕይወቱ ጋር ተያይዞ ተስፋ የሚያስቆርጡ ብዙ ውዥንብሮች ቢገጥሙትም የህይወቱ አዲስ ጅማሬ መሆኑን በሚናገርለት በሌላ ትዳርም እንደገና ተሞሽሯል። ሁሉንም በጽናት አልፎ ዛሬ ላይ ‘እግዚአብሄር ይመስገን አሁን ደህና ሆኛለሁ’ ይላል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም