እኔና አያቴ ብራናና ቀለም ነን..
እሷ ትጠይቀኛለች እኔ እመለሳለሁ..‹ፀጉርህ ነው መሰለኝ ፊትህ ጭር ብሏል..ለምን አትላጨውም? አለችኝ ወደ አናቴ ሽቅብ እያስተዋለች። ‹ፀጉር ሲያድግ ምን ይሠራል? ሰውነት ነው የሚያከሳው፣ ለተባይ መራቢያ ነው የሚሆነው። ተላጭና ምች እንዳይመታህ ፀጉርህን ታጠነው› አለችኝ።
‹እንዲህ አይሻልም ብለሽ ነው? አልኳት ፀጉሬን እየደባበስኩ።
‹ራስህን በመስተዋት ባየህው መልክህን እንዴት እንዳጠፋው! ቆንጆ ነህ..ልቅም ያልክ ምን ያደርግልኛል ብለህ ነው የምታጎፍረው? አለችኝ ፍጹም በሆነ እናትነት።
ፀጉሬን መቆረጥ ስለማልወድ አንገራገርኩ። ዛሬም ድረስ ካልገቡኝ የአያቴ ምክሮች ውስጥ አንዱ ፀጉሬን ተላጭቼ ጸጉሬን የምታጠነው ነገር ነው። ምች እንዳይመታህ ተብዬ በተላጨሁ በሰከንድ ውስጥ ገል ላይ ባለ ፍም እሳት የገዛ ፀጉሬን እታጠናለሁ። ፀጉሬን እሳቱ ሲያገኘው የሚያወጣው ጭስ ጠረኑ ደስ ስለሚለኝ ካለእምቢታ ነበር የምታጠነው።
ደሞ በሌላ ቀን…በዛ በማውቀው ቀሚሷ በሩ ደጃፍ አጎዛዋ ላይ ተቀምጣ የእግሮቿን ጣቶች ስታክ (ስታክ ልበል እንጂ ስትሞዠልቅ ብል ይቀላል) አገኛታለሁ። ፊቷን በሆነ የሕመም ስሜት አጨፍግጋ ሌባ ጣቷን የእግሮቿ ጣቶች መሐል አስገብታ እንደመጋዝ ወዲያና ወዲህ እያደረገች ታካለች።
‹ምን ሆነሽ ነው? እላለሁ አጠገቧ ደርሼ እየቆምኩ።
‹ጮቅ ነው መሰለኝ ይበላኛል› አለችኝ ፊቷን ሕመም ዘርታበት።
‹ሙጃሌ እንዳይሆን?
በዓይኗ እየገላመጠችኝ ‹እኔ ሙጀሌ በዘሬም የለ› ትለኛለች ቅሬታ ባዘለ ድምጽ። የምትለውን ለመስማት እንጂ ሙጀሌ እንዳይደለ አውቄ ነበር። በነገራችን ላይ አያቴ ስትገላምጥ ደስ ትላለች። በአያቴ መገላመጥ እወዳለሁ። እንደዛ ዓይነት ውብ ግልምጫ አይቼ አላውቅም። አያቴ ስትገላምጥና በደጉ ቀን ተባረክ ስትለኝ አንድ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግልምጫዋን ናፍቄ ሆን ብዬ ላናድዳት እንዲህ እንዳሁኑ የማይሆን ነገር እላታለሁ። እነዛን ትላልቅ ዓይኖቿን አንሻፋ በግማሽ ስታ አፈርድሜ ሳይሆን አፈር ከፍሰሀ ነበር የምትቀላቅለኝ። ሙጀሌ መጥፎ ነገር እንደሆነ ያወኩት በአያቴ ግልምጫ ነው። ሁሌ ሙጀሌ ስላት አትወድም፣ ሁሌ ሙጀሌ ስላት በነዛ ውብ አይኖቿ ሳትገላምጠኝ ቀርታ አታውቅም። እኔም ግልምጫዋ ስለሚናፍቀኝ እግሮቿን ባሻሸች ቁጥር ስለሙጀሌ አነሳባታለሁ።
‹ቀልዱን ተውና ይልቅ ማማስያ አግለህ አምጣልኝ› አለችኝ ባጎነበሰችበት አይኖቿን ወደ ላይ ገልባ እያየችኝ።
‹ለምንሽ? እኔ እጠይቃለሁ።
‹ጣቶቼን እንድተኩስበት። ለጮቅ ትኩስ ነገር ጥሩ ነው። በእሱ ብተኩሰው ይሻለኛል› ብላ ወደ ማከኳ ተመለሰች።
‹የት አግኝቶ ነው የያዘሽ?
‹ክረምት አይደል! ክረምትና ጮቅ ዘመዳሞች ናቸው። ቶሎ በል..በጣም ሳይግል ለብ አድርገህ አምጣልኝ› አለችኝ ወደ ምድጃው እንድሄድ በአዓይኗ እየተማጸነችኝ።
ማማሳያ ፍለጋ ማዕድ ቤት እኳትናለሁ። ከውጪ ‹ምነው በዛው ቀረህ ጃል? የሚል ጥዝጣዜ የለወጠው የአያቴ ድምፅ ይሰማኛል።
‹ማማሰያ እየፈለኩ ነው› እኔ እመልሳለሁ።
‹አይ የአንተ ነገር! ማማስያ ፍለጋ ነው ይሄን ሁሉ ያከረመህ? ምድጃው ስር ፈልገው ካጣኸው መያዣ የሌለው ድስት ጎን ቃኘው እዛ አታጣውም›
ተናግራ ሳትጨርስ ‹አገኘሁት! አልኳት።
‹በል በጣም እንዳታፈጀው እግሬ ስስ ነው ይለበልበኛል›። ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ እንጃ ማስጠንቀቂያዋን ሰማሁት።
‹በጄ! አልኳት በሷው አማርኛ። በጄ ማለት በአያቴ አማርኛ ‹እሺ፣ ይሁን፣ ተስማምቻለሁ› ማለት ነው።
‹ክረምት ለጮቅ ምቹ ነው። ጫማ ሳታደርግ ወደ ደጅ እንዳትወጣ› ራሮት የለበሰ ድምፅዋ ተሰማኝ። ወዲያው ‹እረ ምነው ቀረህ? ማማስያ ለብ አድርጎ መምጣት ነው ይሄን ሁሉ ሰዓት የሚያቆይህ? አለችኝ መምጫዬ እንደእግዜር መምጫ ቀን ርቋት።
‹እሳት የለም..› አልኳት።
‹ኧረ ባክህ ያለው ይበቃል፣ ትንሽ ሞቅ ካለ በቂው ነው። ልትጠብሰኝ ነው እንዴ ያሰብከው? ወሬዋን ሳትጨርስ ከነማማሳያዬ ፊቷ ቆምኩ። ‹እኔ ልተኩስሽ?
‹ብትተኩሰኝ እማ ጥሩ ነበር ግን ታቃጥለኛለህ›። አለችኝ በሚያመነታ ፊት። ወዲያው ሀሳቧን ቀይራ ‹የማታቃጥለኝ ከሆነ በል ቀስ ብለህ ተኩሰኝ›። ስትል ስታከው የዋለችውን እግሯን አመቻቸችልኝ። የጋለውን ማማሰያ በጮቅ የተበላ ጣቶቿ መሐል ሳሳርፈው ‹ኡ..ኡ እረ ፈጀኸኝ! አለችኝ እግሯን ከማማሰያው እያሸሸች። ‹ጥበሰኝ እኮ አላልኩህም..! ስትል በነዛ ሲቀየሙና ሲገላምጡ በሚያምሩት ዓይኖቿ ቀልቤን ገፈፈችው።
‹እንዴ! ነካ እኮ ነው ያደረኩሽ..
‹ከቶም ነካ! ገላዬ ላይ አሳርፈኸው ነካ ነው ያደረኩሽ ትላለህ? ስትል ተቆጣችኝ.. በነዛ ዓይኖቿ፣ በነዛ ሽፋሽፍትና ቅንድቦቿ።
በተቀመጥኩበት ተመቻችቼ በድጋሚ እንዳይፈጃት እንደ ላጪ ተጠንቅቄ ቀስ እያልኩ ጣቶቿን ለመለብለብ ስሞክር ‹ኧረ ፈጀህኝ ቀስ በል! አሰማም እንዴ? የሚል ያው የቁጣ ድምፅዋን ሰማሁት። ‹እንዳውም ይቅርብኝ ራሴ እተኩሰዋለሁ› ብላ እግሯንም ማማሰያውንም አንድ ላይ ቀማችኝ።
‹ምን ይላል ይሄ! አሁን ደግ ነው እንዲህ ነፍሴ ድረስ እስኪሰማኝ ማቃጠልህ? ተቀየመችኝ። ረጅም ጊዜ የቆየ ግልምጫዋን ያን ቀን ነው እስኪበቃኝ ያየሁት። እውነትም ሳላውቅ እንዳቃጠልኳት አወኩ። ግድ የሆነ ነገር ካልገጠማት በስተቀር አያቴ ግልምጫዋን የትም የምታባክን ሴት አይደለችም።
ደሞ በሌላ ቀን..አይኖቿን ወደ ቅንድቤ ሰዳ ‹ቅንድብህ ሊጋጠም ትንሽ ነው የቀረው፣ በንጉሡ ጊዜ ቢሆን አልቆልህ ነበር› አለችኝ።
‹ለምን? አልኳት።
‹ሥልጣን ይጋፋል ይባላል› አለችኝ። እንዲህ እንዳለችኝ አፍታ ሳልወስድ አብሮኝ የኖረውን ቅንድቤን እንደ አዲስ በመስተዋት አየሁት። ‹መች ተጋጠመና ነው? ራሴን ከመስተዋቱ ላይ ሳልሰውር ጠየኳት።
‹ላመል ነው የቀረው..
በመስተዋቱ ውስጥ አተኩሬ ቅንድቤን እመረምራለሁ። አያቴ ያለችውን አይነት ቅንድብና ማንነት ማግኘት ይቸግረኛል።
‹ፀሐይዋ ከራለች ወደ ቤት ልግባ..መሸት ሲል ብወጣ ይሻላል፣ አጎዛዬን አስገባልኝ› ብላኝ ከተቀመጠችበት ለመነሳት ስትሞክር ያቅታታል። ‹ውይ መነሳትም አቅቶኛል..አይ እርጅና› እያለች እጆቿን መሬቱ ላይ ቸክላ እንደምንም ትነሳለች። አንዳንድ ጊዜ ና ያዘኝ ትለኝና ደግፌ አስነሳታለሁ። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ እንደ አሁኑ በብዙ ትግልና በብዙ የእርጅና እርግማን እንደምንም ትነሳለች። የበሩን ጉበን በእጇ ይዛ፣ መቀነቷን መሬት እየጎተተች ወደ ሳሎን ታዘግማለች። መሬት የሚጎተት መቀነቷ አደናቅፎ እንዳይጥላት ቤት ውስጥ ያለ አንድ ሰው ተሸቀዳድሞ ያነሳላታል። ትንሽ አርፋ ጀምበር ወደ ምዕራብ ስትንሸራተት፣ ዓለም ጥላ ሲይዛት ከነአጎዛዋ ደጅ አገኛታለሁ። ያኔ ሌላ ወግና ቧልት እንጀምራለን። ጥርሴን እየፋኩ አጠገቧ እቀመጣለሁ።
‹በከሰል እንጂ መፋቅ ይሄ ያነጣል ብለህ ነው?
‹ከሰል ጥሩ ነው እንዴ? ስል ጠየኳት።
‹ለጥርስ እንደ ከሰል ምን ጥሩ ነገር አለ? ሀጫ በረዶ ነው የሚያስመስልልህ። እኛ በከሰል ስንፍቅ ነው የኖርነው። ጥርሳችንን በከሰል፣ ልብሳችንን በእንዶድ እያጠብን ነው ቀን የወጣንው። እናንተ ደግ ዘመን ላይ ናችሁ..ሁሉም ተሻሽሏል›። አለችኝ።
እስኪመሽ እንዲህ ያለውን ወሬ እናወራለን። ከአያቴ ጋር..ብራናና ቀለም ነን..
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም