ደብረሲና ከአዲስ አበባ በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ያለች ከተማ ናት።ከተማዋ በከፍታ ቦታ ላይ የምትገኝ እንደመሆኗ በጣም ቀዝቃዛ ናት።በዚሁ ቅዝቃዜዋ ምክንያት የከተማዋ ነዋሪዎች ጃኬቱንም፤ ሹራቡንም ፎጣውንም ደራርበው ነው የሚለብሱት።ነዋሪዎቹ ቅዝቃዜውን በልብስ ብቻ መከላከል ስለማይችሉ በጥሩ ሁኔታ እንደተዘጋጀች የሚመሰክሩላትን ካቲካላ ይጎነጫሉ።ይህች ካቲካላ ከእነርሱ ተርፋ ከተማዋን አቋርጠው ለሚያልፉ መንገደኞችም ለገበያ ትቀርባለች።ከተማዋ ከደብረብርሃን ቀጥሎ ያለች ከተማ እንደመሆኗና ወደቀጣዩ ከተማ እንደመስፈንጠሪያ ሆና ስለ ምታገለግል ሞ ቅ ያለች ናት፡፡
ከደብረሲና በቅርብ ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ሸዋሮቢት የተጓዘ ሰው አንድ ነገር ያጤናል።በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለው ርቀት 20 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው።የሚያስደንቀውና ሊስተዋል የሚገባው ጉዳይ ግን በከተሞቹ መካከል ያለው ቅርብ ርቀት አይደለም።ይልቁንም ከቅዝቃዜ እልም ወዳለ ሙቀት መግባት እንጂ።ከደብረሲና ወደ ሸዋሮቢት ሲጓዙ 20 ኪሎሜትሩን በቅጡ እንኳን ሳያጨሱ በብርድ እየተንዘፈዘፉ በቅፅበት ወደ ጋለ ሙቀት ይገባሉ።ገና ብርዱ ሳይለቅዎ በላብ ይጠመቃሉ።በቅዝቃዜ የተኮማተረው ሰውነትዎ ሳይፍታታ በሙቀት ልብዎ ቅልጥ ይላል።
ይህ ድንቅ የተፈጥሮ ክስተት ቢሆንም በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የተከሰቱትን ነገሮች ሁሉ የማያይዘው ከዚህ ተፈጥሯዊ እውነት ጋር ነው። በኢትዮጰያ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ለውጡ እንደመጣ በተለይ በመጀመሪያው ዓመት በርካታ አበረታችና ተስፋ ፈንጣቂ ስራዎች ተሰርተዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለመጀመሪያ ግዜ ፓርላማ ቀርበው ንግግር ሲያደርጉ የኢትዮጵያን ስም ደጋግመው በመጥራታቸው የብዙዎችን ልብ ማሞቅ ችለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራቸውን ‹‹ሀ›› ብለው ከጀመሩ በኋላ በቀድሞው መንግስት በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ታስረው የነበሩ እስረኞችን በመፍታታቸው፣ በውጪ ሆነው ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደአገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረጋቸው ከምንም በላይ ደግሞ ከኤርትራ ጋር የነበረውን የቆየ ቁርሾ በመፍታታቸው በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ምስጋና አግኝተዋል።በዚህም ከኖቤል ሽልማት ድርጅት በሰላም ዘርፍ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።
እነዚህን ሁሉ ተስፋ ሰጪ ተግባራትን ህዝቡ በወጉ እንኳን ሳያጣጣጥም ወዲያው ነበር እዚም እዚያም ኮሽታ መስማት የጀመረው።ልክ እንደ ደብረሲና ሸዋሮቢት ጉዞ ነበር አገሪቱ ከቅዝቃዜ ወደ በርሃ/ሙቀት/ የገባችው።በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ብሔርን መሰረት ባደረጉ ግጭቶች ብዙዎች ሞተዋል፣ በርካቶች ደግሞ ተፈናቅለዋል።የዛኑ ያህል ደግሞ በአገሪቱ ታሪክ ታይተውም ሆነው ተሰምተው የማያውቁ አሰቃቂ ግድያዎች በዜጎች ላይ ተፈፅመዋል።በተመሳሳይ ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችም ተከስተው አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ መስጂዶችም ፈርሰዋል።በዚሁ ሳቢያ ሰዎችም ለህልፈት ተዳርገዋል።
እንዲህ እያለ በፍጥነት እየተጋጋለ የመጣው የአገሪቱ ሁኔታ ይበልጥ ተባብሶ በመንግስትና በሕወሓት መካከል ወደሚደረግ ጦርነት አመራ።በዚሁ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በሁለቱም በኩል በርካታ ሰዎች አልቀዋል።ንፁሃን ዜጎች በግፍ ተጨፍጭፈዋል።ሴቶች ተደፍረዋል።ብዙሃኑም ተፈንቅሎ ለርሃብና ጥማት ተዳርጓል።ያ ሁሉ ሰው አልቆ ግን አብዛኛዎቹ ጦርነቶች በስምምነት እንደሚጠናቀቁ ሁሉ በመንግስትና በሕወሓት መካከል ለሁለት ዓመት የተደረገው ጦርነት የተቋጨው በፕሪቶሪያ ስምምነት ነበር፡፡
በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በኩል የእምነቱን ተከታዮች የልብ ትርታ ለማረጋገጥና ፖለቲካውን በእምነቱ ውስጥ ለማስገባት የተደረገው ጥረት ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ በአገሪቱ የተከሰተ ሌላኛው ትኩሳት ነው። እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነው በአምስት ዓመት ውስጥ ነው።በነዚህ አምስት ዓመታት ውስጥ ያልተደረገ ነገር የለም።ነገሩም የሆነው በላይ በላይ ነው።ልክ እንደ ደብረሲና ሸዋሮቢት መንገድ ሁሉም ነገር ከተራጋጋውና ከተቀዛቀዘው ወደ ሙቀትና ግለት ውስጥ ገብቷል።የእርሰ በርስ ንትርኩ፣ የፖለቲካው ሽኩቻ፣ ሞትና መፈናቀል አሁንም አለ። በዛ ላይ ደግሞ የኑሮ ውድነቱ አይሎ ህዝቡ ከሚሸከመው ጫንቃ በላይ ሆኗል።
በርግጥ መንግስት ሲለወጥ የሽግግር ወቅት ያስፈልጋል።ህዝቡም ይህንኑ በመረዳት ለአዲሱ መንግስት ግዜ ሰጥቷል።እንደውም ገዢው ፓርቲ ብልፅግና እንዲመራው ይሁንታውን በምርጫ አረጋግጧል።ከነገ ዛሬ ነገሮች ይሻሻላሉ ብሎ ያለውን ታጋሽነት ለመንግስት አሳይቷል።አሁንም እንዲሁ፤ ይህም ሆኖ ግን የሰላም ችግር አሁንም አገራዊ አጀንዳ ነው። ሰላም መጣ ሲባል ዳግም ይደፈርሳል።የተስፋ ጭላንጭል ታየ ሲባል መልሶ ይጨልማል።በዚህ ላይ የኑሮ ውድነቱ ተደምሮበት ሕዝቦች ችግሮች ውስጥ ይዋልላሉ።
አሁን መንግስት ለኑሮ ውድነት ቅነሳ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል። የስራ አጥ ቁጥሩም ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ በመምጣቱ በአነስተኛ ፕሮጀክቶችና በተለያዩ የስራ መስኮች ዜጎች ተቀጥረው የሚሰሩበትንና ገቢ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት።ከሁሉ በላይ ደግሞ በተለይ ወጣቶች የራሳቸውን ስራ በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከመንግስት በኩል የቦታና የገንዘብ ድጋፍ በስፋት መቅረብ ይጠበቃል፡፡
ዘላቂ ሰላም በመላ አገሪቱ እንዲመጣ ከሁሉም በላይ አቅሙን አቀናጅቶ መስራት ይጠበቅበታል። ዜጎች በሰላም ወጥተው፤ ሰርተውና ነግድው በሰላም እንዲገቡ ደህንነታቸውንና የመኖር ዋስትናቸውን ማስጠበቅ ይኖርበታል። በጥቅሉ መንግስት ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገቡ የሰላም፣ የመኖር ዋስትናና የኑሮ ውድነት ማሻሻያ ላይ ይበልጥ ትኩረት አድርጎ መስራት ይጠበቅበታል። እንዲህ ሲሆን ነው ብልፅግናን በተሻለ መልኩ ማረጋገጥ የሚቻለው!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2015