ዘንቦ አባርቷል..። ስስ ለጋ ፀሐይ በምሥራቅ አድማስ ላይ አቅላልታለች። እንዲህ ሲሆን ደስ ይለዋል..እንዲህ ሲሆን መኖር ያረካዋል። በዘነበ ሰማይ ላይ ያቅላላች እንቡጥ ፀሐይ ሲመለከት..በተሲያት አለም ላይ ሊዘንብ ያለ ጉሩምሩምታ ሲያደምጥ ተፈጥሮና ፈጣሪ በአንድ ላይ የወገኑ ይመስለዋል። የተፈጥሮ የሀቅ ሚዛን ፍንትው ብሎ ይታየዋል..ከሀሳቡ የጠፋው የእግዜር መለኮታዊ ኃይል ህላዊ ያገኛል። ተፈጥሮ ያስደንቀዋል..የሕይወቱ አንድና ብቸኛ እውነት ተፈጥሮ ነው። በተፈጥሮ ውስጥ ማን እንዳለ ግን አያውቅም። እግዜር ይሆን ሳይንስ፣ አዳም ይሁን ዳሪውን ዛሬም ድረስ አልደረሰበትም። እግዜር የለም ባለ ማግስት ለእሱ ጥያቄ መልስ ይመስል ልክ እንዲህ እንደአሁኑ ተፈጥሮና እውነቷ በአንድ ወግነው ሰማይ ርቃን ላይ ይታዩታል። በሚያሳምን እውነት፣ በሚገርም ልዕልና ሙልዐተ አለሙ ላይ ተስለው የፈጣሪን መኖር ይነግሩታል። ይገርመዋል የተፈጥሮ እውነት..
ቡና ይወዳል። ጠቆር መረር ያለ ቡና ነፍሱ ነው። ማለዳውን በትኩስ ቡና መጀመር ሊተወው ያልቻለ የዘወትር ልማዱ ነው። በተለይ እንዲህ እንደ አሁኑ እግዜርና ተፈጥሮን በአንድ ላይ ሲያገኛቸው.. በተለይ እንዲህ እንደ አሁኑ መኖር በሚያስናፍቅ እውነት ውስጥ ሲሆን.. በተለይ እንዲህ እንደ አሁኑ ዘንቦ ባባራ አባርቶ በፈካ ፀሐይና ዝናብ በተጋቡበት የልጅነት እውነቱ ውስጥ ሲሆን ጥቁር ትኩስ ቡና መጠጣት ልዩ ስሜትን ይሰጠዋል።
ከነጥያቄው ወደ አንድ ካፌ አመራ።
እንደ እሱ በትኩስ ቁርስና በትኩስ ቡና የሚዝናኑ ጥንድና ነጠላ ሰዎች ካፌውን ሞልተውታል። የሰው ልጅ የሚኖረው ለሆዱ ነው። ሆድ ባይኖር የሰው ልጅ ምድራዊ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን ነበር የሚለውን ለመመለስ ብዙ ለፍቶ አልተሳካለትም። የሰው ልጅ ከመብላትና ከመጠጣት የተለቀ ሌላ ትልቅ ጉዳይ እንደሌለው ሲያስብ ሰው መሆን ትርጉም ያጣበታል። እሱ ራሱ እንኳን በጠዋት የሚነሳው ትኩስ መራራ ቡና ለመጠጣት ነው። ሰውነት ከመብላትና ከመጠጣት የላቀ እውነት ቢኖረው ደስ ይለው ነበር ግን እስካሁን እዛ እውነት ላይ አልደረሰም። አካባቢውን ለመቃኘት ዕድል ሳትሰጠው አንድ ጠይም አስተናጋጅ ፊቱ ቆመች።
ትኩስ ጥቁር መራራ ቡና እንደሚፈልግ ነግሮ ከፊቱ አሸሻት።
የአስተናጋጇን ከአይኑ መሸሽ ተከትሎ ወደ ተወው ሀሳቡ ተመለሰ። ብዙ ነገር ያስገርመዋል። ብዙ ነገሮች ጥያቄ ይፈጥሩበታል። ይሄ ዓለም የማን እንደሆነ እስካሁን አልገባውም። እግዜርም ሳይንስም የየራሳቸውን እውነት ይዘው ሊያስረዱት ሞክረዋል። ዛሬም ድረስ ግን እውነቱ ላይ አልደረሰም። እግዜርና ሳይንስ ከልጅነቱ ጀምሮ ግራ ሲያጋቡት የመጡ ያልተመለሱ ጥያቄዎቹ ናቸው። በልጅነቱ የሚያውቃቸው የአባቱ ነፍስ አባት የሰው ልጅ በፈጣሪ አምሳል እንደተፈጠረ ነግረውት ነበር። የሰፈራቸው የአጥቢያ ገበዝ አባ ዳምጤ ‹በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ብለው ለሕዝቡ ሲሰብኩ አድምጧል። ትምህርት በጀመረበት ጥቂት አመት ውስጥ ዛሬም ድረስ የማይረሳው ሳይንስ አስተማሪያቸው አንገቱ ላይ ያደረገውን ትልቅ የጎለጎታ መስቀል በእጁ እየነካካ የሰው ልጅ ከዝንጀሮ ነው የመጣው ሲል አስተምሯቸው ነበር። በነጋታው እኔና እናንተ የዝንጀሮ ትውልዶች ነን..በዝግመተ ለውጥ ነው ከዝንጀሮነት ወደ ሰውነት የተቀየርነው ሲል በሰው ልጅ ህላዊ ውስጥ ከፈጣሪ ይልቅ ሳይንስ እውነት እንዳለው በልበ ሙሉነት አስረግጦ አስተምሯቸው ነበር። ያን ቀን በእየሱስ የሚያምን..አንገቱ ላይ ትልቅ የጎለጎታ መስቀል ያደረገ አንድ አስተማሪ የአባን እውነት ሻረበት። ያ መምህር መስቀሉን ለምን እንዳደረገው ግን ዛሬም ድረስ አልገባውም። ሳይንስና እግዜር የተጋጩበት ያኔ ነበር። ሳይንስን እየተማሩ እየሱስን መከተል.. ለዳሪውን እውነት እየተገዙ የፈጣሪን መኖር መመስከር እንደምን ይቻላል? ትናንትም ዛሬም ያልገባው ጥያቄው ነው። ማንም ያልመለሰለት የልጅነትና የወጣትነት ጥያቄው። ዛሬም ድረስ በዚህ ያልተመለሰ ጥያቄው ውስጥ ይኖራል። እሱ ብቻ አይደለም አጠቃላይ ዓለም በዚህ ያልተመለሰ ጥያቄ ውስጥ ትመስለዋለች። አጠቃላይ የሰው ልጅ በዚህ ዝቅታና ከፍታ ውስጥ ነው ብሎ ያምናል። ዓለም የማናት? እሱስ የማን ነው? የፈጣሪ ወይስ የተፈጣሪ?..የሳይንስ ወይስ የረቂቅ እውነት? አልገባውም። ሌላ ያልተደረሰበት እውነት ያለ ይመስለዋል። የሌለም ይመስለዋል። አልታወቀውም እንጂ የሰው ልጅ ዛሬም ድረስ ጣኦት አምላኪ ነው። ዛሬም ድረስ ለሁለት ጌታ የሚገዛ ነው። ዛሬም ድረስ ቄሳርን የሚያመልክ ነው።
ትኩስ ጥቁር መራራ ቡና መጣለት። ፈገግ አለ..አንድ መዐት ፈገግታ።
ከነፈገግታው ወደ ጠይሟ ሴት ቀና አለ። እንደ መልኳ ጠይም ቡና ታመጣልኛለች ብሎ ጠብቆ ነበር። ትዕዛዙን አንዱንም ሳታጎድል ስላመጣችለት በፈገግታ እጅ ነሳት።
ጠይሟ አስተናጋጅ ግራ መጋባት ተፈጠረባት። ማንም ሰው ቡና አዟት እንዲህ እንደእሱ ደስ ሲለው አይታ አታውቅም። ብዙዎቹ መረረ..ቀጠነ..ስኳር አነሰው..ስኳር በዛው እያሉ የሚያማርሩና የሚያመናጭቁ ምስጋና የለሽ ናቸው። በትንሽ ነገር አመስጋኝና ደስታን የሚያገኝ ሰው ብርቋ ነው። የተቀዳ ቡና ስሰጠው እንዲህ የሆነ ቡና አፍልቼ ባጠጣው ምን ሊሆን ነበር ስትል እያሰበች ከአጠገቡ ሄደች።
በዘነበ ሰማይ ባቅላላች ጀምበር ስር ሆኖ..በፈጣሪና በተፈጥሮ እውነት ውስጥ ተጠልሎ የሚወደውን ቡና ፉት አለ። ቡናው ወደ ሆዱ ሲወርድ ፍጹም በሆነ ደስታ ነበር። ይሄስ የሰውነት ደስታ የማነው? ደስታ ፈጣሪው ማነው? መነሻና መድረሻውስ? ከቡናው ጋር ሌላ ጥያቄ መጣበት።
ለምንድነው የሚጠይቀው? ለምንድነው ጠይቆ መልስ የማያገኘው? ያልደረሰበት የእውነት ስፍራ ያለ ይመስለዋል። ወይም ደግሞ ከእውነቱ ጋር እየኖረ ሆድና ጀርባ ሆኖ እንዲህም ይመስለዋል።
ከቡናው ፉት አለ..የቡናውን ስኒ ጠረጴዛው ላይ ከማስቀመጡ ሰማይ ማጉረምረም ጀመረ። ወደ እውነቱ እየተጠጋ መሰለው። በዘነበ ሰማይ ርቃን ላይ ፍንትው ያለችው ለጋ ፀሐይ በዳመና ድባቅ ተመታ ብኩርናዋን አጣች። ፀሐይ ገብታ ካፊያ መጣ። ሌላ ሰማይና ምድር ተፈጠረ። ተፈጥሮ ከፈጣሪዋ ጋር በትልቅ ሰማይ ላይ ተስለው አየ። ይሄ እውነት የማነው?
ለመጨረሻ ጊዜ የቡናውን ስኒ ወደ አፉ አለ….ቡናው ወደ ሆዱ ሲወርድ ጥያቄዎቹን እየመለሰለት ነበር።
በፀሐይ ላይ ዝናብ..በዝናብ ላይ ፀሐይ። እውነቱ ጥጋ ጋ ደረሰ። ከሚፈልገው..ከሚያስፈልገውም ሀቅ ጋር ተገናኘ። ፈጣሪ ከሚለው እውነት ጋር።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም