ወደአዋቂነት የዕድሜ ክልል ከተሸጋገርኩበት ጊዜ ጀምሮ ሁሌም የሚያስጨንቀኝ አንድ ጥያቄ አለ። ይኸውም “ለሰው ልጅ ሕይወት መሻሻል አንዳች ነገር የማያበረክት ይባሱኑ ሰውን የሚጎዳና ችግር ውስጥ የሚከት ሃሳብ ዕውቀት ሊባል ይችላል ወይ?” የሚል ነው። የዓለምን ሁኔታ በተረዳሁበት መጠን ይህንን ጥያቄ ደግሜ ደጋግሜ ራሴን ጠይቄያለሁ። በእርግጥ ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ አረዳድ ይኖረዋል፤ እኔ የደረስኩበትን ድምዳሜ ግን በትዝብት መልክ ላካፍላችሁ። በግሌ “ለሰው ልጅ ሕይወት መሻሻል አንዳች ነገር የማያበረክት ይባሱኑ ሰውን የሚጎዳና ችግር ውስጥ የሚከት ዕውቀት ዕውቀት ሊባል ይችላል ወይ?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በርካታ ጊዜያትን ካሰብኩና ካሰላሰልኩ በኋላ “አይችልም” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ። ምክንያቴን እንደሚከተለው ላቅርብ።
በእኔ ዕይታ ዕውቀት ዕውቀት ሊባል የሚችለው አገርም አልነው ዓለም ዞሮ ዞሮ የሚኖርበት ሰው ነውና ሰውን መጥቀም የሚችል ሲሆን ነው። ሰውን የማይጠቅም ይባስ ብሎ ሰውን የሚጎዳ ዕውቀት ግን ዕውቀትም አይደለም፤ ዕውቀት ተብሎ መጠራትም የለበትም።
ይሁን እንጂ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በየዘመኑ የማይጠቅምና በተቃራኒው ሰውን የሚጎዳ “ዕውቀት” ስያሜው ሳይገባው ዕውቀት የሚል መጠሪያን አላግባብ ሲጠቀም ተስተውሏል። አሁን በእኔ ዘመን እዚህ በእኛዋ ኢትዮጵያ ደግሞ ሰውን የሚጎዳ ዕውቀት ያልሆነ ዕውቀት ከመቼውም ጊዜ በላይ የተስፋፋ ይመስላል። እንዲህ ዓይነቱ ዕውቀት ያልሆነ “ዕውቀት” በተለያዩ መቸቶች ራሱን በተለያየ መልክ የሚገልጽ ቢሆንም አሁን ላይ በእኛ አገር በስፋት እየተስተዋለ የሚገኘው ግን ብሔርንና ብሔርተኝነትን ሽፋን አድርጎ ለጥፋት የቆመው ዋነኛው ዓይነት ያላዋቂዎች ዕውቀት ነው።
እውነት ነው በሐረግ እንጂ በሃሳብ የማይሰባሰቡ አላዋቂ አዋቂዎችና ዘረኛ ብሔርተኞች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታይ አላቸው። በተከታዮቻቸው ዘንድ ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው ተደርገው ይወሰዳሉ። ይሁን እንጂ ይህ ዕውቀታቸው ዕውቀት ለመባል ጠበቃ ቆምንልህ ለሚሉት “ሕዝብ” አንዳች ፋይዳ ሊኖረው ይገባ ነበር። የሆነውና እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው። እንዴያውም በመጥቀም ፋንታ ሕዝባቸውን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዱት መሆኑ በገሃድ የሚታይ ሃቅ ሆኗል። ምክንያቱም ለዘመናት አብሮ በሰላምና በፍቅር በኖረ ሕዝብ መካከል የጥላቻን መርዝ እየረጩ “ለጥቅምህ ታገልንልህ” የሚሉትን ሕዝብ ለችግር እየዳረጉት ነው።
በዚህም ከእነርሱ ውጭ ያለን ሕዝብ በጠላትነት እየፈረጁ ራስ ወዳድነትንና ግለኝነትን ይሰብኩታል፤ ያስተምሩታል፣ ያወርሱታል። ሃቁ ግን ለአንድ ብሔር ከራሱ ከብሔሩ ዘረኛ አቀንቃኞች በቀር ሌላ ጠላት አለመኖሩ ነው። ምክንያቱም “እከሌ በመሆንህ ሆን ተብሎ በማንነትህ ጥቃት እየደረሰብህ ነው” የሚል አንድ የብሔር “ተቆርቋሪ” እዳ ካልሆነ በቀር ለዚያ ሕዝብ የሚያበረክትለት አንዳች ፋይዳ የለውምና። እነዚህ ሰዎች የሚሰብኩት ቂምን፣ ጥላቻን፣ መለያየትን ሲሆን ለሕዝባቸው የሚያተርፉት ጥቅም ደግሞ ግጭትን፣ መፈናቀልንና ስደትና ሞትን ነው።
ታዲያ ፅንፈኛ ብሔርተኞች “ሕዝባቸውን” እየጠቀሙት ወይስ እየተጠቀሙበት ነው? የዚህን ጥያቄ ምላሽ ምን እንደሆነ ለእያንዳንዳችን ልተወው። ስለሆነም ከሰሞኑ እንደምንታዘበው ሰላምን መጥላት፣ ጥላቻን መስበክና ጦርነትን መቀስቀስ በምንም መመዘኛ የዕውቀት መለኪያ ሊሆን አይችልም። እስኪ የትኛው ነው ዕውቀት? ለዘመናት በፍቅር አብሮ በኖረ ሕዝብ መካከል የጥላቻ መርዝን እየረጩ እርስ በእርስ ማባላት? በአጥንትና በደም በተከፈለ መስዋዕትነት በነጭ እብሪት ያልተንበረከከ አሸናፊ ሥነ ልቦናን ያወረሰች ታላቅ አገር አፍርሶ ታናሽ አገር ለመፍጠር መነሳት? “የኔ” እንጂ “የኛ” ማለትን የማያውቅ የጥፋት ትውልድን የሚኮተኩት የውድቀት ርዕዮተ ዓለምን ያለ እረፍት መስበክ? ይኸ ነው ዕውቀት?
እንዲህ ዓይነት ዕውቀት መቼውንም ዕውቀት ሊባል፣ እንዲህ ዓይነት “ዕውቀት” ያላቸው ሰዎችም የቱንም ያህል ቢራቀቁ አዋቂዎች ናቸው ሊባሉ አይችሉም። በዚህ ዕውቀታቸው የመጨረሻው ማማ ላይ ቢደርሱም ታላቅ አይባሉም። ዓለም ላይ ታላቅ የሚባለውን ጀብዱ ቢፈጽሙም ጀግና ሊባሉ አይችሉም። እንደዚያ ከሆነማ ሂትለርን የሚያክል ጀግና ማን ነበር። ቅሉ ሂትለር አስተሳሰቡ የክፋት ዕውቀቱ የጥፋት ነበረና ያ ሁሉ የጥፋት ጀብዱው ጀግና አላስባለውም። የናዚዝም ዕውቀቱ ከፍተኛ ነበር፣ ሆኖም ዕውቀቱ አጥፊ ነበርና ሂትለር ታዋቂ እንጂ አዋቂ መሆን አልቻለም።
ነገር ግን እላለሁ፤ ጥላቻንና መለያየትን የምትሰብኩ ፅንፈኛ ብሔርተኞች እናንተ አዋቂ ከሆናችሁ የክፋት ሁሉ ምንጭ የሆነው ሴጣንም አዋቂ ነው። እንዲህ አይነት ሰዎች ጀግና ከሆኑ በሰው ልጆች ላይ የመጨረሻውን ዘግናኝ ግፍ የፈጸመው አረመኔው ሂትለርም ጀግና ነው ማለት ነው። ዕውነታው ግን እንዲህ አይነት ሰዎችም፣ ሴጣንም፣ ሂትለርም ታዋቂ ሆነው ሊሆን ይችላል እንጂ አዋቂ አይደሉም። ጀግናም አይደሉም፤ አይሆኑምም። ዕውቀት የሚባለው በክፋትና በጥፋት ልቆ መገኘት ከሆነም ሺ ጊዜ ድንቁርና ይመረጣል።
ለዚህም ነው በአውሮፓውያኑ የካቲት 2 ቀን 2015 በቅዱስ ፒተርሰበርግ ራሽያ ተወልዳ መጋቢት 6፣ 1982 ማንሃታን ኒውዮርክ አሜሪካ ውስጥ ያረፈችው “ኦብጀክቲቪዝም” በሚባል የራሷ የፍልስፍና እሳቤ የምትታወቀው ዝነኛዋ ራሽያ-አሜሪካዊት ደራሲና ፈላስፋ አያን ራንድ “ብሔርተኝነት ተፈጥሯዊ ሳይሆን የጭፍንነትና የመንጋነት አስተሳሰብ ውጤት ነው” በማለት ዘረኝነት አላዋቂነት መሆኑን አስረግጣ የተናገረችው። የዚች ታላቅ እንስት ፍልስፍና በተለይም የዘመናችን ምሁር ነን ባዮችና ፅንፈኛ ብሔርተኞች በደንብ የሚገልጽ ሃሳብ የያዘ በመሆኑ ሰፋ አድርገን እንመልከተው።
“በፍልስፍና መነጽር ስንመለከተው ፅንፈኛ ብሔርተኝነት ክፉና በጎውን ማመዛዘን የማይችል ምክንያታዊነት የጎደለው የጭፍን አስተሳሰብና በመንጋ ማመን የፈጠረው ነው። ለዚህም ዋነኛው ምክንያቱ በቡድን ካልሆነ በቀር ግለሰቦች በራሳቸው ምንም ማድረግ አይችሉም የሚለው የዘመናዊ ፍልስፍና አስተሳሰብ ነው። ይህ አስተሳሰብ በሂደት በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ሰርፆ በመግባት ተቀባይነትን ማግኘት ሲጀምር ግለሰቦች ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ ይመጣል፤ የሚጠቅማቸውን ነገር ለመምረጥና ትክክለኛ ውሳኔ ለመወሰን የራስ መተማመን ያጣሉ” ይላል የእንስቷ እሳቤ።
“ይህም ሰዎች ምክንያታዊ ዕምነት እንዳይኖራቸው ስለሚያደርጋቸው ሰዎች በአስተሳሰብ ሳይሆን በሥጋ የሚቀርባቸውን ቡድን እንዲቀላቀሉ ያስገድዳቸዋል። ይህ በአስተሳሰብ ሳይሆን በሥጋ ዝምድና የሚመሰረት “በምክንያት ያልተመረጠ ቡድን” ነው እንግዲህ “ብሔር” የሚል ታርጋ የሚለጠፍለት። በዚህ የተነሳም ብሔርተኞች በዕውቀትና በምክንያት ላይ ተመስርተው የሃሳቡን ጥቅምና ጉዳት መዝነው ሳይሆን አጥንታቸውን ቆጥረው ለተሰባሰቡበት ግዑዛዊ ቡድን “በማንኛውም ጊዜ ያለ ቅድመ ሁኔታ ለቡድንህ ታመን” ከሚለው ከሁሉም አስበልጠው ከሚያዩት የመንጋ መርሃቸው በቀር ሌላ ህግና መርህ አያውቁም።
እናም ብሔርተኝነት ፀረ ዕውቀት፣ ፀረ ምክንያታዊነትና ፀረ ሞራል የሆነ፣ ልፋት የማይጠይቅ የደካሞችና የሰነፎች ሥራ ነው። እናም በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ጽንፈኞች ከራሳቸው ጠባብ የአጥር ክልል ውጭ ስላለው ዓለም ዴንታ የሌላቸው እንዲያውም ከእነርሱ ውጭ ያለውን ሁሉ የሚጠራጠሩና በስጋትነት የሚመለከቱ፣ በራስ ወዳድነት ታስረው የተቀመጡ ድኩማን ፍጥረቶች ናቸው። ጽንፈኞች ክፉውን ከበጎው የሚለዩበት ማመዛዘኛ ህሊና እና እውነቱን እውነት፣ ሃሰቱን ሃሰት፣ ትክክሉን ትክክል፣ ስህተቱን ስህተት የሚሉበት ሞራል የላቸውም።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2015