ልማድ አለብኝ ክፉ ልማድ..ጥፍሬን እበላለው፣ ጸጉሬን እቆነድዳለው። እኚህ ልማዶቼ በሰው ፊት አላሳነሱኝም። አንዳንድ ጊዜ እናቴ ‹እጅህን ከራስህ ላይ አውርድ ብላ በማማሳያ ከመማታቷና ጥፍርህን ለምንድነው የምትበላው? ከማለት ባለፈ ያን ያክል ሰው አፍ ላይ አልጣለኝም። ከሁሉም የከፋው ልማዴ አስራ ስምንት ዓመት የልደት ቀኔን ተከትሎ የመጣው ልማዴ ነው። እንዴት እንደተለማመድኩት ሳላውቀው እጆቼ አፍንጫዬን አፍቅረው አገኘኋቸው። አፍንጫዬን ሳልጎረጉር፣ የደረቀና ትኩስ ንፍጥ በጣቴ ይዤ ሳልወጣና ሳላፍተለትል ቀርቼ አላውቅም። ሌባ ጣቴን አፍንጫዬ ላይ ጣል አድርጌ በአውራ ጣቴ እገዛ ከገዛ ንፍጤ ጋር እጫወታለው። በመድረቅና በመርጠብ መካከል ያለ ወፍራም ዳለቻ ንፍጥ መንግዬ በአውራ ጣቴና በሌባ ጣቴ መሀል አድርጌ አድበለብለዋለው።
ሌላው አልተው ያለኝ ልማዴ..የሰውነቴን ቆሻሻ ቦታ በጣቶቼ የመፈለግ አባዜ ነው። ህይወት የውበቷን ያክል ቆሻሻም አላት እላለው። አንዳንድ ጊዜ ሰውነት የቆሻሻ እቃ ቤት ነው..የጉድፎች መከማቻ። እስኪ ራሳችሁን ተመልከቱት..የቆሸሸና ለመንካት የሚያስነውር የሰውነት ክፍል የላችሁም? ስትነኩት የሚሰነፍጥ፣ በውሀና በሳሙና ታጥበነው የማይጸዳ ጉድፍ በሰውነታችን የሆነ ቦታ ላይ የለም? በደንብ አለ..ከዛ ነገር ጋር ነው ፍቅር የያዘኝ። በዛ ነገር ነው ፍቅር የወደኩት። የትም እንዴትም ልሁን እጆቼ አፍንጫዬን ሳይጎረጉሩ፣ ብብቴን ሳይቧጥጡ አይውሉም። አጠገቤ የተቀመጡ ሰዎች በድርጊቴ ምን ያክል እንደሚጸየፉኝ ለማሰብ ጊዜ አጥቼ ከነውሬ ጋር እነውራለው። እጆቼን ብብቴ ውስጥ አስገብቼ በላብና በጠረን የሻገተ አመዳይ ጸጉሬን አርመጠምጣለው። አርመጥምጨ አላበቃው ከገላዬ ውስጥ እጄን መዝዬ ወደ አፍንጫዬ ሰድጄ አሸተዋለው። ያኔ አጠገቤ ያለው ሰው የሚሆነው መሆን አይታሰበኝም። በቃ ለአስቀያሚ ልማዴ እጅ የሰጠሁ ነኝ። በዚህ ባበቃ ጥሩ ነበር..ግን አላበቃም..እጄ የማይሄድበት ቆሻሻ ቦታ የለም። ቦላሌዬን አልፎ፣ ቡታንታዬን አልፎ ጉድፍ ካለበት ቦታ መሄድ ያምረዋል። እዛም አደብ አይገዛም..ከሰውነቴ የቆሻሻ ገንዳ ከመቀመጫዬ ስፍራ ሲያውደለድል አገኘዋለው። ብብቴን፣ አፍንጫዬን፣ ጸጉሬን፣ ቂጤንና ጉያዬን በነካሁበት እጄ ለማዕድ እቀርባለው። ይሄን ነኝ እኔ..
እናቴ ይሄን ልማዴን ለማስተው ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። ‹ከለማበት የተጋባበት አሉ..ከየትኛው ባለጌ ወዳጅህ ጋር እየዋልክ ነው እንዲህ ነውረኛ የሆንከው? ትለኛለች..የቡና ስኒዋን እያጠበች። የቡና ስኒዋን እያጠበች ብቻ አይደለም ቡና ስትቆላም ሆነ፣ ስትቀዳ እንዲህ ሳትለኝ ቀርቼ አላውቅም። እናቴ አጠገብ ካለሁ እኔም አፍንጫዬን ከመጎርጎር እሷም እኔን ከመቆጣት አትቆጠብም። ሳላስበው እጄን አፍንጫዬ ላይ አገኘዋለሁ አፍንጫዬን እየጎረጎርኩ እንደሆነ የማውቀው በእናቴ ቁጣ ነው። ‹ባለጌን ካሳደገ የገደለ ይጸድቃል..› ትለኛለች በምሬት።
”እኔ ባለጌ ነኝ? እላታለው።
”ለዛውም የወጣለት ባለጌ ነዋ! ስትል ድምጽዋን ጫን አድርጋ ትመልስልኛለች።
”ታዲያ ለምን ገለሽኝ አትጸድቂም? ስል ለመቀለድ እሞክራለው።
”ወልጄ፣ ገድዬ እንዴት እችለዋለው? እሷው የፈረደባት ትቃጠል› ትለኛለች።
በነገር እየወጋችኝ እንደሆነ አላጣሁትም። ቀጠል አድርጋ ‹በዚህ አመልህ የትኛዋ ሴት ይሆን የምታገባህ? አለችኝ።
”ማን እኔ ነብዩ ነኝ ሴት የማጣው..ካላግበሰበስኩልሽ ምናለ ትይኛለሽ› ስል ጎራ ይነፋኛል።
”ማግበስበስ ቁም ነገር አይደለም አንዲትን ሴት ሚስት ማድረግ ነው ቁም ነገሩ› ስትል ልታርመኝ ትሞክራለች።
”አይ ሴት..! ስትል በዝምታ ትወድቃለች።
”ምነው? ስል ከሀሳቧ እመልሳታለው።
”ሴትነት ገርሞኝ ነው..› ትለኛለች።
”ለምንድነው ሴት ሆነሽ ሴትነት የሚገርምሽ?
”እንዴት አይግረመኝ! ሴት የወንድ ልጅ የጉድፉ እቃ ቤት ናት። ስንቱን ችላ፣ ስንቱን አጥርታ የምትኖር። አባትህን ሳገባው እንዳሁኑ አልነበረም። ሰካራምና ዘማዊ፣ ሀይለኛና ተደባዳቢ ነበር። እኔን ካገባ በኋላ ነው ሰው የሆነው። ነፍሴ ነች የፈጠረችው..በባዶነቱ ውስጥ ገብቼ ነው ዛሬን የሰጠሁት። በእያንዳንዷ ሴት ልብ ውስጥ ብዙ ያላለቁ ወንዶች አሉ። ወንዶች በሴት ልብ ውስጥ ነው እድገታቸውን የሚጨርሱት›። ብላ ዝም አለች። ከዚህ ንግግሯ በኋላ ዝምታዋ ተከተለ።
በአንድ ግዜ ምን ነካት እያልኩ ሳስብ ለካ ስሰማት የነበረው እጄን አፍንጫዬ ላይ ሰቅዬ ነበር።
‹ሴት የሌለችበት የወንድ ስፍራ የለም። ሴት መቼም ሙሉ ናት። ወንድ ሙሉ የሚሆነው ከሴት ጎን ሲቆም ነው› ብላኝ ትታኝ ወደ ውጪ ወጣች።
ጊዜአት ነጎዱ..እኔና አመሌ ግን አልተለያየንም። እውነት ለመናገር ልማዴን ለማሸነፍ ያላደረኩት ጥረት የለም። ግን በቃ አቅም አጣሁ..። ስራ ሳጣ መሄጃዬ ወደ ልማዴ ነው። ስተክዝ አፍንጫዬን እየጎረጎርኩ ነው። ስደሰት እጄን ብብቴ ውስጥ አስገብቼ ነው። በዚህ ልማዴ ውስጥ እያለሁ የምሰራበት መስሪያ ቤት አዲስ ከገባች ሴት ጋር ተዋወኩ። ገና እንዳየኋት ነው ስብርብር ያልኩላት። ሳናግራት እንዴት ሆኜ እንደነበር አላስታውስም..ብቻ እጄን አፍንጫዬ ላይ ሰቅዬ እንዳይሆን መድሀኒዓለምን እለምነዋለው። ያለቦታዬና ያለስራ መደቤ ወዳለችበት እየተመላለስኩ በድርቅና ተወዳጀኋት። እሷን ለማየት ስል ሳምንቱን ሙሉ ስራ ብገባ፣ ሳምንቱን ሙሉ ስራ ቢኖር ስል ተመኘሁ።
በጣም ተቀራረብን..እንዳላጣት መፍራት ጀመርኩ። በጣም ስቀርባት ምን እንደምላት እየጠፋኝ መጣ። ቤዛ ፊት ስቆም እናቴ ናት ትዝ የምትለኝ። ለእናቴ የጎረርኩት ብዙ ጉራ አለ..አመሌን ተንተርሳ ‹በዚህ ልማድህ የትኛዋ ሴት ይሆን ባል የምታደርግህ? ስትለኝ ‹ማን እኔ ነብዩ ነኝ ሚስት የማጣው?..ከፈለግሽ አግበሰብስልሻለው› ብያት አውቃለው። አሁን ላይ ያ ሁሉ ድፍረቴ ከዳኝ። ሴት ለማግበስበስ አይደለም ለቤዛ የሚሆን ወኔ እየከዳኝ መጣ። ሚስት ማግኘት እንዴት መከራ እንደሆነ በቤዛ ነው ያወኩት። በተለይ ለእንደኔ አይነቱ በብዙ ልማድ ለሚኖር ሰው ሁነኛ ሴት ማግኘት አዳጋች ነው። ሴቶቻችን ጥሩ የለበሰና እንከን አልባ ወንድ በሚፈልጉበት በዚህ ዘመን እጄን አፍንጫና ብብቴ ውስጥ እየቀረቀርኩ የትኛዋ ሴት ናት ባል የምታደርገኝ እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ። እናቴ እውነቷን ነው ወንድ ልጅ የሚጸዳው..ወንድ ልጅ የሚጠራው በሴት ነው።
ከቤዛ ጋር ልንገናኝ ተቀጣጠርን..ወኔ ከድቶኝ ፊቷ ስቀርብ እንዴት መሆን እንዳለብኝ ለማወቅ ስል ስለሴት የተጻፉ መጽሀፎችን አገላብጥ ጀመር። ሴቶች የሚጠሉት የወንድ አይነት በሚል ርዕስ ስር እንዲህ ተጽፎ አነበብኩ..‹ሴቶች ንጽህናውን የማይጠብቅ ወንድ አይወዱም› የሚል። በትንሹ እኔን የሚነካ መሰለኝ። ቀጥዬ ባነበብኩት ርዕስ ስር ግን እንዳለ ራሴን አገኘሁት። ‹ሴቶች የሚጠሉት የወንድ አይነት በሚል ሌላ ርዕስ ስር ከተጻፉ አስር ነውሮች ውስጥ ሰባቱ የኔ አመሎች ነበሩ።
ከቤዛ ጋር ተገናኘን..ያን ቀን እጄን ወደ አፍንጫዬ..ወደ ብብቴ ላለመስደድ የለፋሁትን ልፋት ለምንም ለፍቼው አላውቅም። ሚስት ማግኘት እንዴት መከራ ነው የሚል እንጉርጉሮ ሳንጎራጉር ነበር።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 7 ቀን 2015 ዓ.ም