የሰው ልጅ በምድር ላይ ካሉ ፍጡራን ሁሉ የተለየ ባህሪ ያለው ፍጡር ለመሆኑ ከኑሮውና ከድርጊቲ መገንዘብ ይቻላል።ትንሽ እንዳትለው ከሁሉ በላይ ሆኖ በፈጣሪው አምሳል ተፈጥሯል፤ እንዳትጠላው ፈጣሪ ራሱ ከሁሉ አስበልጦ ወዶታል፤ ክፉ እንዳትለው በመልካምነታቸው ዓለምን ያዳኑ ሰዎች አሉ፤ ወንድሙን ወንድሙ ሲገድለው አይተህ አቤት የሰው ጭካኔ ስትል በውሻው ሞት ሲያለቅስ የምታገኘው አለ።እንደዚሁ ሰው የሚጠላውን ሲወድ፣ የሚረግመውን ሲመርቅ፤ የሚመሰገነውን ሲነቅፍ፣ የሚከበረውን ሲንቅ የሚስተዋልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ።ከነዚህ በተቃርኖ ቅኔ የተሞሉ የሰው ልጆች ግርንቢጥ ባህሪያት መካከል እኔም ቢገለጥ ይጠቅማል ያልኩትን ላካፍላችሁ፡፡
በሕይወት ውስጥ ራሳቸውን እንደ ሻማ እያቀለጡ ለብዙሃኑ ብርሃን የሚገልጡ፤ ለሕብረተሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት ቀዳሚ ሚና የሚጫወቱ ክብርና ምስጋና የሚገባቸው የዕውቀት ብርሃኖች፣ የሰው ሻማዎች አሉ።ሃኪሞች፣ አስተማሪዎች፣ ጸሃፊዎችና ፈላስፋዎች ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።እነዚሁ ብርኃነ ብዙሃኖች በብዙ ልፋትና ጥረት ያጠራቀሙትንና ለህዝብ ይጠቅማል ያሉትን አንዳች ሃሳብ በሚገልጹና በሚሰጡ ጊዜ “ኤጭ፤ ራሳቸው ማድረግ ያልቻሉትን ለሰው ይመክራሉ” በሚል በትችት ይብጠለጠላሉ።በምስጋናና በሽልማት ፋንታ ነቀፌታና ወቀሳን ያስተናግዳሉ።
ለዚህ በዋነኝነት እንደምክንያት የሚቀርበው ደግሞ ብዙውን ጊዜ “ምሁራኑ በዕውቀታቸው አልተጠቀሙበትም፣ ነገር ግን ራሳቸው ያልተጠቀሙበትን ዕውቅት ለሌላው ይመክራሉ፣ እነርሱ ያላደረጉትን አድርጉ ይላሉ” የሚል ነው።እንደ እኔ እንደ እኔ ግን ይህ ተገቢም ጠቃሚም አይመስለኝም።ምክንያቱም ለራስ ያላደረጉትን ለሰው ማድረግ ሊያስመሰግን እንጂ ሊያስወቅስ አይገባምና፡፡
ነገር በምሳሌ፤ ጠጅ በብርሌ ነውና እስኪ ነገሩን በምሳሌ አስደግፈን እንመልከተው።አንድ በመስኩ የጠለቀ ዕውቀት ያለውና በሙያው የተመሰገነ ነገር ግን ሲጋራ አጫሽ ዶክተር አለ እንበል።ዶክተሩ እራሱ አጫሽ ስለሆነ ከተማረውና ከሚያውቀው ተነስቶ ሲጋራ ስለሚያስከትለው ከፍተኛ የጤና ችግር ሰውን ማስተማርና መምከር የለበትም ማለት ነው? ሲጋራ ማጨስ አደገኛ የጤና ጠንቅ መሆኑን እኮ ከማንም በላይ እሱ በሳይንስ ብቻም ሳይሆን በተግባር ያውቀዋል።ስለሆነም ሲጋራ ማጨስ መጥፎ መሆኑን ከማንም በላይ መናገር የሚችለው እሱ ነው።
ሕይወቱን አደጋ ላይ ላለመጣልና ራሱን ላለመጉዳት ሲል ማጨሱን እርግፍ አድርጎ መተው እንዳለበትም ሁሌ ያስባል፣ ከዚህ አደገኛ ሱስ መላቀቅን አጥብቆ ይፈልገዋል።ግን መተው አልተቻለውም፣ አጫሽ ነው፡፡ታዲያ ዶክተሩ ማጨስ ማቆም ስላልቻለ፣ እርሱ ስላላደረገው ስለ ሲጋራ ጎጅነትና ሰዎች እንዴት ከሲጋራ ሱስ መላቀቅ እንደሚችሉ መናገርና ማስተማር የለበትም? እንግዲህ ሰዎች መናገር ወይም መጻፍ ያለባቸው የሚያደርጉትን ነገር ብቻ ከሆነ ይህ አጫሽ ዶክተርም መናገር ያለበት ስላደረገው ነገር ማለትም ሲጋራ ማጨስ ማቆም እንደማይቻል መሆን ነበረበት።ግን አላደረገውም፣ ዕውቀቱ ባያድነውም፣ ራሱን ከዚህ መጥፎ ልምድ ማውጣት ባይችልም ለሰዎች የሚያስተምረው ግን ስለ ጉዳቱ ነው።
እንዲያውም ከባዱ ነገር ይህን ማድረግ ይመስለኛል።ለራስ ማድረግ ያልቻሉትን መልካም ነገር ለሌሎች ማድረግ! ዶክተሩ በአደገኛው የሲጋራ ሱስ ውስጥ እየማቀቀ፣ ከዚህ ችግር ለመውጣት ዘወትር ፈጣሪውን እየተማጸነ ነገር ግን አልችል ብሎ ያቃተውን “እኔ አልቻልኩምና እነርሱም አይችሉም” ብሎ ተስፋ ሳይቆርጥ ለራሱ ማድረግ ያልቻለውን ሌሎች እንዲድኑ መፈለግና የበኩሉን ማድረግ።ይሄ ታዲያ ያስመሰግን ነበር እንጂ ያስወቅሳልን?።እነርሱ ሳይጠቀሙ ሌሎችን የሚጠቅሙ፣ እየሞቱ የሚያድኑ እንዲህ ዓይነቶችን የሰው ሻማዎች ልናከብራቸውና ልናደንቃቸው እንጂ ልንወቅሳቸውና ልንንቃቸው አይገባም፡፡
እንዲያውም በእኔ እምነት መተቸት ያለባቸው ለራሳቸው ያላደረጉትን ለሰው የሚመክሩ ምስኪን የሰው ቤዛዎች ሳይሆኑ “ዕውቀቱ እያላቸው ለራሴ እንኳን ያላደረኩትን ለሰው ለምን እናገራለሁ” የሚሉ ጻድቅ መሳይ ንፉጎች ናቸው።ዕውቀት ለራስ ስላልጠቀመ ብቻ ለሌሎች እንዳይተላለፍ የሚፈልጉ ከግለኝነት አጥር ያልተሻገሩ ራስ ወዳዶች ናቸው ሊተቹ የሚገባቸው።ምክንያቱም ዕውቀት የሚሰጠን ሁልጊዜ ራሳችን ብቻ እንድንጠቀምበት ላይሆን ይችላል።ዕውቀት የሚተገበረውና ጥቅም ላይ የሚውለው ግዴታ በራሳቸው በአዋቂዎች ዘንድም ላይሆን ይችላል። በእኔ ዕምነት ዋነኛው የአዋቂዎች ተግባር ዕውቀትን ለብዙሃኑ ማስተላለፍና ለሁሉም እንዲዳረስ ማድረግ ይመስለኛል።ዕውቀቱ ወደ ተግባር የሚቀየረው ግን በተደራሲው ማለትም በግለሰቡ ወይም በብዙሃኑ ህዝብ ነው፡፡
እናም አዋቂዎች ሁል ጊዜ የሚያውቁትን የሚተገብሩ ላይሆኑ ይችላሉ።ደግሞም አንድ አዋቂ ያገኘውን ዕውቀት ለራሱ ብቻ ቢተገብረው ተጠቃሚ የሚሆነውም ያው ራሱ ብቻ ይሆናል።ይህን ስል ግን አዋቂዎች ዕውቀታቸውን መተግበር የለባቸውም እያልኩ አይደለም።አዋቂው ያወቀውን ዕውቀት ተግባራዊ ማድረግ ይችላል፤ የዕውቀቱ ተግባራዊነት ግን በአዋቂው ግለሰብ ደረጃ ብቻ ከሆነ የዕውቀት ትርጉሙ ይዛባል፣ ትክክለኛ ዋጋውንም ያጣል።ምክንያቱም ዕውቀት በባህሪው ሰብዓዊና “ብዙዋዊ” በመሆኑ ነው።ሰዎች በተፈጥሯቸው ብቸኛ አይደሉም፣ ብዙ ናቸው፣ ማህበራዊ እንስሳ ናቸው።ዕውቀትም እንደዚሁ ለብቻ የሚይዙት፣ በራስ ብቻ የሚተገበር ነገር አይደለም።ከራስ ውጪ እንዳይተላለፍ የሚፈለገው በሽታ ብቻ ነው።
ዕውቀት ግን ለራስ መጥቀም ያለበት ቢሆንም እንኳን፣ በዚህ ብቻ አይረካም፤ የብዙዎች መሆን ይፈልጋል።ዋጋ የሚኖረውም ከራስ በአሻገር ለብዙዎች ሲያስተላልፉት፣ ሲካፈሉት፣ ሲሰጡት ነው።ስለዚህ የአዋቂው ሚና መሆን ያለበት ያገኘውን ዕውቀት መተግበሩ ላይ ብቻ ሳይሆን ማስተላለፉም ላይ ሊሆን ይገባል የምልበት አመክንዮም መነሻው ይኸው ነው።ስለዚህ በአንድ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ዕውቀት ያለው አንድ ምሁር እርሱ ያድርገው አያድርገው ዕውቀቱን ማስተላለፉ ግን ሊያስተቸው አይገባም ብየ አምናለሁ።ደግሞስ አዋቂው ዕውቀቱን ባይጠቀምበት የተጎዳው እርሱ ራሱ እንጂ እኛ ምን ቀረብን?
“ራሱ ያላደረገውን” በሚል አጉል ትዕቢት ተወጣጥረን ጠቃሚ የሆነውን ዕውቀት ተቀብለን ተግባራዊ ባለማድረጋችንስ የሚጎዳው ማን ነው? እርሱማ “ራሴን ሳልጠቅም እንዴት ዕውቀቴን ለሌላ አሳልፌ እሰጣለሁ” በማለት ሳይሰስት ያለውን በለጋስነት ሰጥቷል።እርሱ ባይጠቀምም ሌሎች ሰዎች እንዲጠቀሙለት ዕውቀቱን በቅንነት አካፍሏል።እናም እውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ “ለራሱ ሳይሆን” በሚል ሰዎች የአዋቂዎችን ምክርና ሃሳብ የሚነቅፉበትና የማይቀበሉበት ምክንያት ራሱ አላዋቂነት ይመስለኛል።
ነገሩን በቅጥ ሳያስተውሉ በግብዝነት ለነቀፋና ለሃሜት ከመሮጥ ይልቅ “ብልህ ጠቢባንን በመስማት ዕውቀቱን ይጨምራል” እንዲል መጽሃፉ አዋቂነት ማለት የሚተላለፈውን ዕውቀት በመስማት አዋቂዎቹ ባይተገብሩት እንኳን የእነርሱን ቃል ሰምቶ መተግበርና በዕውቀቱ መጠቀም ነው።ያኔ ዕውቀት ተግባር ላይ የሚውለው በሰጪው ሳይሆን በተቀባዩ፣ በአዋቂው ሳይሆን በብዙሃኑ መሆኑን እንገነዘባለን።ወትሮውኑም አዋቂ ጠቃሚ ነው፣ ተጠቃሚ አይደለም፤ ሰጪ እንጅ ተቀባይ አይደለም።እናም ዕውቀትና ጥበብን ይሰጣል፣ በእነርሱ አማካኝነት ለብዙዎች ይዳረሳል በዚያም ይተገበራል፡የዓለም ታሪክም ይህንኑ ይመሰክራል።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2015