አያቴ ጥቁር ቀለም አትወድም..ጠይም መሆኔ በጀኝ እንጂ እኔንም ልጄ አይደለም ብላ ልትክደኝ ትሞክር ነበር። ከቤታችን ውስጥ ለጥቁር የቀረብኩት ጠይሙ እኔ ነኝ..አብሬያት ስሆን ሌላ ወሬ የላትም ‹እንዳው በማን ወጥተህ ነው እንዲህ የጀበና ቂጥ የመሰልከው? በዘራችን እንዳንተም የለ! ትለኛለች። አይኗን፣ ቀልቧን ፊቴ ላይ በጥርጣሬ ጥላ ማንም ባላስተዋለኝ አይነት እያስተዋለችኝ። አያቴ የእርጅናዋን ግማሹን ያሳለፈችው በእኔ መልከ ልውጥነት ስትፈላሰፍ ነው። የልጅ ልጇ መሆኔን አምና ለመቀበል ብዙ ጊዜ ፈጅቶባታል። ይሄን ሁሉ ዘመን አብሬያት እየኖርኩ እንኳን ከሌላ የተወለድኩ እንጂ ከእሷ ዘር የመጣሁ አይመስላትም። አሁንም እንኳን ሳታምነኝ አብሬያት የሆንኩ ያህል ነው የሚሰማኝ።
አያቴ ለምን ጥቁር ሰው እንደምትጠላ ለማወቅ ብዙ ለፍቼ አልተሳካልኝም። ከሁሉም የከበደኝ ግን ጥቁር መልክ ያላትን፣ በጣም የማፈቅራትን ፍቅረኛዬን አያቴ ፊት ማቅረብና ፍቅረኛዬ ናት ተዋወቂያት ማለት ነበር። የእኔ ጠይምነት ኩርፊያ ሆኗት ጠዋትና ማታ ለምትነጫነጨው አያቴ፣ በመልኬ ብቻ የልጅ ልጄ አይደለም ብላ ልትክደኝ ላመል ለቀራት ሴት፣ የእኔን ጠይምነት አምና ሳትቀበል ሌላ ጥቁር ሴት ይዤባት ብሄድ የምትሆነውን መሆን ሳስበው ፈራሁኝ። ምን አለፋችሁ ፍቅረኛዬን ለአያቴ ለማስተዋወቅ የተቸገርኩትን መቸገር አጠይቁኝ። ጥቁሯን ፍቅረኛዬን ትዝታን ጎኔ አስቀምጨ በግራ መጋባት ተቀምጫለው..ጠረጴዛውን በጣቴ እየጠበጠብኩ።
ከትዝታ ጋር ሳንጣላ የዋልንበት ቀን የለም..የመጣላታችን ዋናው ምክንያት ደግሞ አያቴ ናት። እሷ መቼ ነው ቆይ አያትህን የምታስተዋውቀኝ? ትለኛለች።
‹ዛሬ ትንሽ አመም ስላደረጋት ሲሻላት የዛሬ ሳምንት አስተዋውቅሻለው እላታለው። መልሷ ሁሌም እሺ ነው። እኔ ብያት እንቢ ብላኝና ተቃውማኝ አታውቅም። አያቴን ታማ አታውቅም..ትዝታ ፊት በግድ የማሳምማት እኔ ነኝ። በንግግሬ ውስጥ ውስጡን ፍርሃት ይይዘኛል..የዛሬ ሳምንት ሲሻልሽ አስተዋውቅሻለው ማለቴ ያስቃል..የዛሬ ሳምንት እንደሚሻላት በምን አወክ ብትለኝ እኮ የምመልስላት የለኝም። ከነውሸቴ..ከነነውሬ ትዝታ ዝም ትለኛለች። የዛሬ ሳምንት ይረድስና ‹ዛሬ እኮ አያትህን የምታስተዋውቀኝ ቀን ነው..ረሳኸው እንዴ? ትለኛለች ተንዘላዝዬ ምንም ዝግጁነትን ስታጣብኝ።
‹ባክሽ አልተሻላትም..! ብዬ እዋሻታለው። ራሴ በፈጠርኩት የአያቴ ህመም ፊቴን የሀዘን ጥላ አልብሼ። ብዙ ሳምንታት አለፉ..አያቴ አልዳነችም። ከዚህ በኋላ ትዝታ ‹አያትህን መጠየቅ ያለብኝ ሲድኑ ሳይሆን ታመው እያለ ነው..ደሞ ሚስትክ አይደለሁ! ላስታምማቸው ይገባል› ስትለኝ ልዋሽ የማልችልበትን ወሬ ነገረችኝ። የአያቴን የጥቁርነት ጠል ስለማውቀው..ሌላ ሰበብ ፈጥሬ አይሆንም ማለት ነበረብኝ። ግን እንቢታዬ ትዝታን አላራራትም አስቆጣት እንጂ። ለአንድ አመት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለፍነው። ዛሬም አያቴን አስተዋውቅሻለው ብያት እንደዚህ ቀደሙ ለብሳና ተውባ መጥታ ሳንገራግርባት ተኳርፈን ተቀምጠናል።
ስንገናኝ ጥቂት የፍቅር ቃላትን መለዋወጥ ግድ ነው..ከንፈሬን ወይ ጉንጨን ብቻ ለከንፈሯ የቀረባትን አንዱን ነገሬን ስማ..ክንዷን ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጋ ጎኔ አረፍ ትላለች። ትዝታ ሳትደገፈኝ ተቀምጣ አታውቅም። ስትቀመጥ እሷ ስንራመድ እኔ እንደተደገፍኳት ነው። ለትንሽ ጊዜ ፍቅራችን ያስቀና ነበር..አያቴ እስክትነሳ ድረስ። ከአያቴ በኋላ ሌላ ነን። ‹ቆይ መቼ ነው ከአያትህ ጋር የምታስተዋውቀኝ? ትለኛለች ተደግፋኝ..ወድቃብኝ..አይኔን እያየች። በነገራችሁ ላይ አይኔን ሳታይ አውርታኝ አታውቅም። ወሬዋ አስጨናቂ ሆኖብኝ ፊቴን ሳዞርባት እንኳን በእጇ አገጨን እየመለሰች አይን አይኔን እያየችኝ ነው የምታወራኝ። ለፍቅር ማን እንደ ትዝታ?
የምላት ጠፍቶኝ ዝም እላለው..ፊቴን ወደ ሌላ አቅጣጫ እያዞርኩ።
‹አትሰማም? ከአያትህ ጋር መች ነው የምታስተዋውቀኝ? ስትል ትደግምልኛለች..ወደ ሌላ የዞረ ፊቴን አገጨን በመጠምዘዝ እያስተካከለች። ሊቀየምና ሊያኮርፍ ላመል በቀረው ፊት። ከዚህ ጥያቄ በኋላ እኔና ትዝታ የሁለት ዓለም ሰዎች ነን..ተስማምተን አናውቅም። ፍቅራችን ማቅ የሚለብሰው ይሄን ጥያቄ ተከትሎ ነው። ምን መመለስ እንዳለብኝ ጠፍቶኝ ዝም እላለው።
‹ቆይ አንተ እየቀለድክብኝ ነው እንዴ? ቤተሰብ ከሌለህ ወይ የለኝም በለኝ› ትለኛለች።
‹እንደዛ አይደለም እኮ ፍቅር› እላለው ተለሳልሼ ስለ አያቴ ለመናገር ድፍረት በማጣት።
‹ታዲያ ምንድ ነው? አስተዋውቅሻለው እያልከኝ ሁለት ዓመት ሞላን›
መልስ አጥቼ ጠረጴዛውን እጠበጥባለው..ጠረጴዛውን መጠብጠቤ ያበግናታል መሰለኝ ትሸፍትብኛለች።
‹ዛሬ ካላስተዋወከኝ እመአምላክን..
በተቀመጥኩበት ውሀ ሆንኩ። ልቤ በአፌ ልትሾልክ ቃተትኩ። ትዝታ ከማለች ቀልድ አታውቅም..በተለይ በእናቷ..በተለይ በእማአምላክ..። እማምላክን ብላ ውሸት ሆና አታውቅም..መሀላዋ ለዘላለም ሊያቆራርጠን እንደሚችል ሳስብ አየር አጠረኝ። ጉሮሮዬ ለትንፋሼ ጠበበው..። ደግነቱ እመአምላክን ብላ አልቀጠለችም..ዝም ነው ያለችው። ዝምታዋ ግን ረፍት ነሳኝ..እመአምላክን ብላ ዝም ከምትል ያሰበችውን ብትነግረኝ ይሻለኝ ነበር..። የሆነ ክፉ ነገር እንዳሰበች ተረዳሁ። በቃ ልትለየኝ ነው ስል ብዙ ስጋት ሰጋሁ። አፌ አያቴን ሊረግም አሞጠሞጠ..ግን በአያቴ ላይ አልደፈረም።
ከዚህ ንግግር በኋላ ለሶስት ቀን አናወራም..አንነጋገርም። በጣም ስለማፈቅራት ሁሌ የምለማመጣት እኔ ነኝ። ትዝታን አጥቼ መኖር አይደለም መሰንበት የምችል አይመስለኝም። ለዛም ነው የተኮራረፍንባት ሶስት ቀን ዝንታለም የምትሆንብኝ። ህይወቴን በውብ ቀለም ቀልማ አምሬ እንድታይ ያደረገችኝ እሷ ናት። ፍቅሯ አሸክታቤ ነው..እሷ ደግሞ ጥቁር መላዕኬ። አያቴን ባስተዋውቃት ከእሷ ይልቅ እኔ ነበርኩ የምደሰተው ግን አያቴን ፈራኋት..ጥቁር መልክ አትወድም። ጥቁር ሰው አይሆነንም፣ ጥቁር ሰው ገፊያችን ነው እያለች ነው ያሳደገችኝ። ያ ሲያየኝ ጭራውን እየቆለ እግሬ ላይ የሚንደባለለውን የጎረቤታችንን ጥቁር ውሻ እንኳን ብዙ ጊዜ ወርውራ ስታው እንዳላየው ስትል በመርዝ ያስገደለችው እሷ ናት። ጥቁር ስለሆኑ ብቻ ከብዙ የልጅነት ጓደኞቼ ተቆራርጫለው። ትዝታ ደግሞ ጥቁር ናት..ድብን ያለች ጥቁር። ይቺን ሴት አያቴ ፊት ባቀርባት አያቴ ምን ልትሆን እንደምትችል ሳስብ እሰቃያለው። አያቴ ስትናገር ሰው ይከፋዋል አትልም፣ የመጣላትን ነው የምትተፋው። ኋላ አስቀይማት ስል እሰጋለው..
ትዝታ እንደእስከዛሬው በቀላሉ አልታረቀችኝም..መሀላዋን የምፈራው ለዚህ ነው። ‹ውሸታምና ቃለአባይ ሰው ፍቅረኛዬ እንዲሆን አልፈቅድም። ከእንግዲህ ከአንተ ጋር ነገ አይኖረኝም። ለሁሉም ነገር አንድ ሳምንት እሰጥሀለው። ስትል በአፏ ልትነግረኝ ተጸይፋኝ በማውቀው ጠማማ የእጅ ጽሁፏ ወረቀት ላይ ጽፋ ጠረጴዛው ላይ ትታልኝ እብስ አለች። ትዝታ እንዴት መውደድ እንደሚቻል የማወቋን ያክል እንዴት እንደሚጠላም ታውቃለች።
ምንም ሳልሰራበት የሰጠችኝ የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ አራት ቀን ቀረው። ሶስቱን ቀን ጥቁር አምልኮዋን ከተወች ብዬ አያቴ ፊት አሳዛኝ ፊቴን ይዤ ስንጎራደድ ሰነበትኩ። እሷ ግን ምንም ያው ናት። በቴሌቪዥን ያየችውን ጥቁር ሰው እየተጸየፈች ‹ኧረ ዝጋው ወዲያ! ምኑን ነው የሚያሳየኝ..የሰው ዲያቢሎስ› ትለኛለች። ፊቷን በቴሌቪዥን ከሚታያት ጥቁር ሰው እያሸሸች። አያቴ ፊት ስለትዝታ ለማንሳት አቅም አጣሁ። ሳምንቱ አለቀ። ነፍሴን ያራቆቱ ሰባት ቀናቶችን ተጋፈጥኩ። ትዝታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ረሳችኝ። ሳምንቱ ለወር ሲቀርብ..ብቻዬን ማውራት ጀመርኩ። በፍቅሯ ላብድ ትንሽ በቀረኝ አንድ ማለዳ ላይ አያቴን ‹የምትወጂኝ ከሆነ ወደ አንድ ቦታ አብረሽኝ እንድትሄጂ እፈልጋለው..እንቢ የምትይኝ ከሆነ ግን ተመልሼ ቤትሽ አልመጣም› አልኳት። እግዜር ይስጣት እሺ አለችኝ..አያቴን የክቷን አልብሼ ጥቁሯ ፍቅረኛዬ ትዝታ ፊት ሳቆማት የሆነችውን መሆን መቼም አልረሳውም።
ከትዝታ በኋላ አያቴ ከጥቁር ውጪ የምትወደው ቀለም ጠፋ። ትዝታ የአያቴን የአጉል እምነት አይነጥላ ገፋ ለእኔ ሚስት ለአያቴ ደግሞ የማትተካ ምራት ሆነች።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2015