ከአምስት ዓመት በኋላ ከሮዛ ጋር ተጋባን።ያን ወፍ ዘራሽ ወንድነቴን ባሏ አደረገችው።ያን በተለያዩ ሴቶች ያደፈ ገላዬን አቅፋው ልትተኛ ነው..ያን በብዙ ሴት የተሳመ ከንፈሬን ልትስመው ነው።
ወፍ ዘራሽ ነበርኩኝ እኮ..አብረን የሚያዩን አንዳንድ ሰዎች ወደ እኔ እየጠቆሙ ‹ይሄን ሰው ብላ አገባችው? ይሏታል።ታሪኬን የሚያውቁ አንዳንድ ጓደኞቿ ከእኔ ጋር በመጣመሯ ‹ምን አስነክቶሽ ነው ግን? ሲሉ ፊታቸውን አቀጭመው ይጠይቋታል።ለሁሉም የሚሆን መልስ አላት።
ምኔን እንደወደደችው አላውቅም።ሰው ምግባሩ ካላማረ የሚወደድ ነገር እንደሌለው ነበር የማውቀው።ከምግባርም፣ ከባህሪም፣ ከመልክም ምን የሌለኝ ሰው እዛች ልዕልት ላይ መውደቄን ሳስብ ያልነቃሁት..ወደፊት የምነቃው ህልም ያለ ይመስለኛል።
ትላንት ሌላ ነበርኩ..ዓለም ውንብድናዬን የሚገልጽ ቃል የላትም።በእየሱስ ግራና ቀኝ ከተሰቀሉት ወንበዴዎች የማልስተካከል፣ ሌንጊኖስ ብትሉ፣ አሪዮስ ብትሉ፣ ኒቼና የሞት ነጋዴው ቤልጎፌር የማይልቁኝ ምንም ነበርኩ።በዚች ሴት ፊት ባለማዕረግ ተባልኩ።
ደስታዬ ሀጢዐት ነበር። እንደ እኔ በሀጢዐት የሚደሰት ሰው አልነበረም።ስለሀጢዐት እያሰብኩ ተኝቼ ስለ ሀጢዐት እያለምኩ ከእንቅልፌ እነቃለው።ብቻዬን ተኝቼ አላውቅም..በግራና በቀኜ ሁሌም ሴቶች አሉ።ማታ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደተቀራረብኳቸው የማላስታውሳቸው ሴቶች ጠዋት ላይ ክንዴን ተንተርሰው አብረውኝ ከእንቅልፋቸው ሲነቁ አያለሁ..ይሄ ነው ጠዋቴ።ሀጢዐት እያሰቡ ከእንቅልፍ መንቃት፣ ሀጢዐት እየሰሩ መዋልና ሀጢዐት እየሰሩ ማደር..ይሄ ነው ወንድነቴ።ሮዛ ይሄን ሰው ባሏ አደረገችው..
አንድ ቀን እንደኔ ሀጢዐት በሚያረካቸው ወንድና ሴቶች ተከብቤ እየጠጣሁ በተቀመጥኩበት የቅዳሜ ማግስት አርብ ላይ ግሮሰሪው ውስጥ ከዚህ በፊት አይቻት የማላውቃትን ጠይም ሴት አየሁ።ለአይኔም ለቤቱም አዲስ እንደሆነች ስላወኩ ዛሬ ከዚች ሴት ጋር ለመጠጣትና ሀጢዐት ልሰራ አስቤ ወዳለችበት ሄድኩ።
‹ሀይ..! አልኳት ወደመስከር በተቃረበ፣ ለመንተፋተፍ ባልደረሰ ሩብ ጉዳይ ድምጽ።
ምን ሀሳብ ላይ እንደሆነች እንጃ ድንግጥ ባላ ድምጼን ወደሰማችበት ዞረች።እንዳልሰማችኝ ሳውቅ እጄን ለሰላምታ ዘረጋሁላት።
ግራ እጇን ቀኝ እጇ ላይ ጣል አድርጋ በጨዋ ደንብ ለታላቅ በሚቀርብ የሰላምታ አይነት እጄን ጨበጠችኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ በጨዋ ሴት ተጨበጥኩ።ለመጀመሪያ ቀን በእንደዚያ አይነት ሰላምታ ሰላም የተባልኩት በዛች ሴት ይመስለኛል።ማንም በእንደዚያ ባለ አክብሮትና ትህትና እጅ ነስቶኝ አያውቅም ነበር።ጨዋነቷ ምንም የማታውቅ እንደሆነች እንዳስብ አደረገኝ።ሙድ የሌላት..በቀላሉ እጄ የምትገባ መሰለችኝ።
ፍቃድ ሳልጠይቅ አጠገቧ ቁጭ አልኩኝ።በደንብ እንዳያት እድል አገኘሁ።ያልተቀባባ፣ ያልተነካካ ጠይም መልክ አላት።በዝምታ እንዲማርክ ተፈጥሮ የሆነ ነገሯን የደፋችበት የሚመስል ጠይም መልክ።
ለምን ብቻዋን፣ ለምን በዝምታ፣ ለምን በባዶ ጠረጴዛ ፊት እንደተቀመጠች ሳይገባኝ ‹ምን ይምጣልሽ? ስል ያለልማዴ ትሁት መስዬ ጠየኳት።
‹አ..አመሰግናለው› አለችኝ።
ግብዣ የምትገፋን የመጀመሪያዋን ሴት ተዋወኩ።እዛ ቤት የሚገቡ ሴቶች ሁሉ እንትና ይከፍላል እያሉ የሚጠጡ ናቸው። እኔን ተማምነው በሌለሁበት በረከት ይከፍላል እያሉ የሚጠጡ እንኳን ብዙ ናቸው።ይቺ ሴት ግን አመሰግናለው አለችኝ።የባሰ ተገረምኩባት..መቼም መጠጥ ጠጥቼ አላውቅም ትለኝና ቀን ሙሉ ስስቅ እንዳልውል እያልኩ እያሰብኩ ‹ቢራ የማይመችሽ ከሆነ ሌላ ማዘዝ ትችያለሽ..! ከማለቴ..
‹ይቅርታ መጠጥ አልጠጣም።አለችኝ..
ተመስጌን..በህይወቴ አንድ የማትጠጣ ሴት ተዋወኩ ስል ለራሴ አወራሁ። ሳወራ ሰምታኝ ኖሮ ዞራ አየችኝ።ግን ምንም አላለችኝም።የፈለገችውን ብትለኝ በወደድኩ ነበር።ለምትለኝ ለየትኛውም ነገር የተዘጋጀ ልብና አእምሮ ነበረኝ።ካላወሯት የማታወራ ነፍስ አለቻት..ዝም ካሏት እስከመቼም ዝም የምትል።ቢያንስ እዛ ቤት ለምን እንደመጣች ማወቅ ፈልጌአለው..
‹ካልጠጣሽ ለምን…ገና ሳልጨርሰው
‹ሰው እየጠበኩ ነው..› ስትል መለሰችልኝ። እንድታወራኝ ለማድረግ ያለኝ የመጨረሻ አማራጭ ያ ነበር ገና አውርቼ ሳልጨርስ ከአፌ ላይ ተቀበለችኝ። ዝም ማለት የሚያስደስታት ስለመሰለኝ ያለልማዴ ዝም ልል ተገደድኩ። ግን ዝም ማለት አልቻልኩም..ተቁነጠነጥኩ። ወዲያው የእጅ ስልኳ ጠርቶ በምልክት ቻው ብላኝ በተቀመጥኩበት ጥላኝ ሄደች።
በነጋታው ቅዳሜ ረፋድ ላይ በስሱ ነክሼ፣ ማወራረጃ ጠርሙስ ጨብጨ ቁጭ ባልኩበት አንድ ሰው ከውጪ ጠራኝ። ማንም በሙሉ ስሜ ጠርቶኝ አያውቅም። ቤካ ነው የሚሉኝ። ያን ቀን ግን ስሜን በሙሉ ሰማሁት። ስሜ በሙሉ ሲጠራ ምን እንደሚመስል ያን ቀን ነው የታዘብኩት።ማን አባቱ ነው በሙሉ ስሜ የሚጠራኝ በሚመስል አይነት እየተጣደፍኩ ወደ ውጪ ወጣሁ። ይቺው ጠይም ሴት ናት ብል ማን ያምነኛል? አዎ ራሷ ናት። ስሜን እንዴት እንዳወቀችው፣ በዛ ጠዋት እዛ ቤት ይገኛል ብላ እንዴት እንዳሰበች ለማሰብ ጊዜ አላገኘሁም። በመጠጥ የሚሰነፍጥ አፌን ይዤ ፊቷ ቆምኩ።
‹ሰላም! አለችኝ በትላንቱ አኳኋን ግራ እጇን ቀኝ እጇ ላይ አሳርፋ ከወገቧ ዝቅ በማለት።አፌ ውስጥ ያለው ጫት ትን ሊለኝ ምንም አልቀረኝ።በዛ ጨዋነት እኔን ሰላም ለማለት ማጎንበሷ ከትላንቱ የባሰ እንድደነቅባት አደረገኝ..።ሳላውቀው ተሳብኩባት..
‹ደብሮኛል..አብረኸኝ ወክ የምታደርግ ከሆነ? ስትል አይን አይኔን እያየች ጠየቀችኝ።አይናፋር መስላኝ ነበር ቅዳሜ መጥቶ..ከመሰል ወዳጆቼ ጋር ተቀምጨ ምንም የማላስበው ሰው ያን ቀን ከዛች ሴት ጋር ወክ ለማድረግ ተስማማው።ራሴን ተጠራጠርኩት..የማላውቀውን ራሴን በራሴ ውስጥ አገኘሁት።
ሁሉን አስረስታ እስከ ምሳ ሰዐት ድረስ ወክ አደረግን።ምሳ ሰዐት ላይ ጥሩ የሚባል ምግብ ጋበዘችኝ። ከሀጢዐት በቀር ምንም የማያዝናናኝ ሰው በእሷ ተዝናናሁ።ከሮዛ ጋር በእንዲያ ባለው አጋጣሚ ተዋወቅን።ከዛች ቅዳሜ ጀምሮ ብዙ ወኮችን፣ ብዙ ምሳዎችን፣ ብዙ ጊዘኤዎችን አብረን ተጋራን። እንዳላፈቅራት ስሰጋ ምኔ እንደጠለፋት አላውቅም ወዳኝ አገኘኋት። መወደዴን ሳውቅ የትም አትሄድም ብዬ ወደነበርኩበት ሀጢዐት ተመለስኩ። ጠዋት ቁርስ ልትሰራልኝ ቤቴ ስትመጣ ከሴት ጋር ተኝቼ ነው የምታገኝ። እንደዛም ሆኖ ቁርስ ሳትሰራልኝ ሄዳ አታውቅም። ማታ ሰክሬ ብዙ ነገር አደርጋታለው። ሳልሰድባትና ሳላዋርዳት ቤት ገብቼ አላውቅም። ስለ እኔ ከምተሰማው በላይ ብዙ አይታለች።ግን ልትጠላኝ አልቻለችም። ከአምስት አመት እንዲህ መሆን በኋላ ቬሎ ከለበሰ ጎኗ በሙሽርነት ቆምኩ። እንዴትና ለምን እንዳገባችኝ አላውቅም..አለ የተባለን በደል ሁሉ ነው የፈጸምኩባት። በእብለትና በውሸት የወነበድኩባት እነዛ አምስት የውንብድና አመታት እግዜር ፊት በወንጀለኝነት የሚያቆሙኝ..ገሀነምንም የሚያስፈርዱብኝ ይመስለኛል። ይሄ ካልሆነና እግዜር ስለ እሷ ካልቀጣኝ ለዳግም ህይወትም ካበቃኝ ስለ ፍቅሯ ቀሪ ዘመኔን ብዙ እሆናለው ስል ነበር። ስራዬ ነው መሰለኝ ብዙ ይቅርታ ያላትን ነፍሷን እፈራት ጀመር። ከመላዕክት ጋር እንጂ ከሴት ጋር የምጋባ አልመስለልህ አለኝ።
የሰርጋችን ቀን ብቻችንን የምንሆንበትን ጊዜ ጠብቄ ግን ለምን አገባሽኝ? ስል ጠየኳት።
‹ሁሉ ነገር ተራ እንደሆነ ሲገባህ የእኔ እንደምትሆን ስለማውቅ› አለችኝ። እንግዲህ ይቺ ጠቢብ ናት ያን ወፍ ዘራሽ ያገባችው። የማልመጥናት ሰው እኮ ነኝ..ከእንግዲህ እመጥናት ይሆናል እንጂ እስካሁን እዚህ ግባ የምባል አልነበርኩም። እውነት ነው ሁሉ ነገር ተራ እንደሆነ ስናውቅ የምንመለስበት አንድ ነገር ይኖራል። እኔም እነዛ ጓደኞቼ የእሷ ያክል ደስታ አልሰጡኝም ነበር። እንዳለችውም አለም በቃኝ ብዬ በእግዜር ፊት፣ በአለም ፊት ቃሌን እሰጣታለው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/ 2015 ዓ.ም