የቋንቋና ስነ ጽሑፍ ምሁራን በተሰበሰቡበት ሁሉ አንድ ተደጋግሞ የሚነሳ ቅሬታ አለ። ይሄውም የአገር ውስጥ ቋንቋ ትኩረት እንደተነፈገው ነው። ይሄ ጉዳይ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ አይደለም። እያንዳንዳችን በቀላሉ የምናስተውለው ችግር ነው። የ11ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ልብ ማለት እንችላለን። 12ኛ ክፍል አማርኛም ሆነ ሌላ የአገር ውስጥ ቋንቋ ለብሄራዊ ፈተና አይሰጥም። ይህን ታሳቢ በማድረግ የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የአማርኛ ክፍለ ጊዜ ክፍል ውስጥ አይገቡም።
ይህ የሚሆነው በአማርኛ ቋንቋ አፋቸውን ባልፈቱ ተማሪዎች ሊመስል ይችላል፤ ግን አይደለም። በአማርኛ አፋቸውን የፈቱ ተማሪዎች ናቸው ይህን የሚያደርጉት። ሌላ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉ አፋቸውን በኦሮምኛ የፈቱ ተማሪዎች 11ኛና 12ኛ ክፍል ሲደርሱ በኦሮምኛን ክፍለ ጊዜ አይገቡም።
እነዚህ ተማሪዎች እንደ ምክንያት የሚያደርጉት አገር አቀፍ ፈተና ላይ የማይመጣ ነገር ለምን እናነባለን ነው። በመሰረቱ ግን ቋንቋ ለፈተና የሚነበብ አይደለም፤ ቋንቋ ለየትኛውም ትምህርት መግባቢያ የሚሆን የመጀመሪያው መሳሪያ ነው። አካባቢን ማወቅ የሚቻለው በራስ ቋንቋ ነው።
ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ብንመለስ ችግሩ እንዳለ ነው። ከስርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ ትኩረት የሚሰጠው ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው። የሒሳብና የእንግሊዝኛ ቋንቋ በሳምንቱ ሁሉም ቀናት የሚሰጥ ሲሆን የአገር ውስጥ ቋንቋ ግን ሁለት ወይም ሦስት ቀን ነው።
ይህ ደግሞ ተማሪዎች ለቋንቋ ትምህርት ግድለሽ እንዲሆኑ አደረጋቸው። ለዚህም ነው አሁን አሁን ብዙ የታሪክና የባህል መዛባት እያጋጠመ ያለው። የራሳችን የሆኑ አባባሎች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ እንቆቅልሾች እያሉን የውጭ አድናቂ የሆንን ነው። መገናኛ ብዙኃን ላይ እንኳን የምንሰማውና የምናነበው የውጭ አገራት አባባሎችን ነው።
ስለ ምሳሌያዊ አነጋገር እና ፈሊጣዊ አነጋገር ማብራሪያዎችን ለማወቅ ወደ በይነ መረቡ ዓለም ብንገባ አናገኝም፤ በአንጻሩ በእንግሊዝኛ Idiom ወይም Proverb ብለን ብንፈልግ ለማንበብ እስከሚያታክተን ድረስ እናገኛለን። ምንነታቸውንም በምሳሌ ያስረዳናል።
ወደ አገር ውስጥ ቋንቋ ስንመጣ ግን ይህ የለም። በዚህም ምክንያት ምሳሌያዊ አነጋገሮች ላይ አሁን አሁን ያለትርጉማቸው መጠቀም እየታየ ነው። አንዳንዶቹንም ትርጉማቸውን ባለማወቅ ‹‹ስህተት ናቸውና ይውደቁ›› የማለት ክርክር ላይ ሁሉ ደርሰናል። ነገር ግን የሚገቡበትን ዓውድ አለመረዳት እንጂ በስህተት የተነገረ ምሳሌያዊ አነጋገር የለም። ምሳሌያዊ አነጋገር ስሙ እንደሚያመለክተው አንድን ሀሳብ ሊመሳሰለው በሚችል ነገር መጠቀም ነው። ምሳሌያዊ አነጋገር ዓውድ አለው።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጽሑፍና ፎክሎር መምህር ዶክተር ለማ ንጋቱ ‹‹ምሳሌያዊ አነጋገሮች የንግግር ማጣፈጫ ቅመሞች ናቸው›› ሲሉ ሰምቻለሁ። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ስለተረትና ምሳሌዎች ሀሳብ ሲሰጥም ሰምቼ ነበር። እርሳቸው እንደሚሉት ምሳሌያዊ አነጋገሮች ብዙ ሀሳብ ከማዝረክረክ በአጭሩ ግልጽ አድርገው የሚያስቀምጡ ናቸው። በውስጣቸው ቅኔን የያዙ ናቸው፤ ጣፋጭ ይዘት ያላቸው ናቸው፤ ሥዕላዊ ገላጭ ናቸው። ለምሳሌ ‹‹ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል›› ይባላል። የችኮላ ሥራ ጥሩ እንዳልሆነና ቶሎ እንደሚበላሽ፤ ነገሮችን በጥንቃቄ መሥራት እንደሚያስፈልግ ብዙ ማብራሪያ ከማብዛት ይልቅ ይህ አባባል ውስጣችን የመግባት ኃይል አለው።
ምሳሌያዊ አነጋገር እንደ አስፈላጊነቱ በዓውድ የምንጠቀመው ነው። ይህንን ባለማወቅ ግን ልክ አይደሉም ተብለው የሚወገዙ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ሁሉ አሉ፤ ግን ልክ ናቸው። እንደ ምሳሌም ‹‹ዝምታ ወርቅ ነው›› የሚለውን ያነሳሉ። ‹‹ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል›› የሚለው አባባል መናገርን ስለሚያበረታታ ይደገፋል፤ ‹‹ዝምታ ወርቅ ነው›› የሚለው ደግሞ አለመናገርን ስለሚያበረታታ ይወገዛል። ግን አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜም አለ። ዝምታ ወርቅ የሚሆንበት ጊዜም አለ። አንዳንድ ጊዜ እኮ ‹‹ምነው ባልተናገርኩ፣ ምነው ባልተናገረ›› የሚባልበት አጋጣሚ አለ። በማናውቀውና ባልተዘጋጀንበት ነገር ላይ ከመናገር ዝምታ የተሻለ ይሆናል። ይህ ብቻም ሳይሆን አግባብ ያልሆነን ነገር ከመናገርም ዝምታ የተሻለ ሊሆን ይችላል።
በምሳሌያዊ አነጋገር ውስጥ የትኛው አባባል ለየትኛው ጊዜና ቦታ ይሆናል የሚለውን መምረጥ እንጂ ሁሉም የሚገልጸው የራሱ የሆነ ሀሳብ አለ። አባቶች እነዚህን ምሳሌያዊ አነጋገሮች ያለምክንያት አይደለም የተናገሯቸው፤ በሆነ አጋጣሚ አስፈልጓቸው ነው።
በሌላ በኩል የተነገሩበት ዘመንም የወቅቱን ሁኔታ የሚገልጽ ነበር። ለምሳሌ በፊውዳሉ ሥርዓት ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የተባለው በወቅቱ የነበረ ሹመኛ መብላት ስለነበረበት ነው። እዚህ አባባል ላይ ሌላም አከራካሪ ነገር ይኖራል።
‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› ማለት አንድ ሹመኛ በኋላ ይቆጨዋልና በሥልጣን ላይ እያለ ይብላ ለማለት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ከሙስና የጸዳ ልብ ከሌለው ‹‹ምነው በልቼ በነበረ ኖሮ›› ብሎ ይጸጸታል ማለት ነው። ስለዚህ ይህ አባባል የሚገልጸው በሥልጣን ላይ እያሉ ሙስና መብላት የሚፈልጉትን ነው ማለት ነው። እንዲህ አይነት ሰዎች ከሥልጣን ወርደው እንኳን ይቆጫቸዋል ማለት ነው። ሥልጣን ላይ ሲቆዩም ዛሬ ነገ እያሉ ነው የቆዩት ማለት ነው። ድንገት ከሥልጣን ሲወርዱ ግን መጸጸት ይመጣል።
ዳሩ ግን በአጠቃቀማችን ይህን አባባል በግድ ሙስናን የሚያበረታታ ትርጉም ሰጥተነዋል። ምናልባትም አበው የተጠቀሙት ሲሾም ያልበላ ሰው በኋላ መጸጸቱን እንደ መጥፎ ነገር ቆጥረውት ይሆናል። መጸጸቱን እየፈረዱበት ይሆናል። ስለዚህ ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር በሁለት ምክንያት መወገዝ የለበትም ማለት ነው። በትክክልም ሙስናን ለማበረታታት ከሆነ ይህ ያኔ በነበረው አገዛዝ የተባለ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ እውነትም ሲሾም ባለመብላቱ መጸጸቱን እየፈረዱበት ቢሆንስ?
ለቋንቋ ትምህርት ትኩረት አለመሰጠቱ የምሳሌያዊ አነጋገሮች ትርጉም ከባድ እንዲመስልም አድርጎታል። ምሳሌያዊ አነጋገር የቅኔነትም ባህሪ አላቸው፤ ውስጠ ወይራ የሆነ ትርጉም ይይዛሉ። አንዳንድ ጊዜ ቃል በቃል ብቻ በመተርጎም መልዕክታቸው አልገባን ይላል። ወይም ግራ የሚያጋባ መልዕክት ይሆንብናል።
ለምሳሌ ‹‹ችግር ነው ጌትነት በቅቤ ያስበላል›› ይባላል። ይህን አባባል የሰማ ሰው ‹‹በቅቤ መብላት ምኑ ነው ታዲያ ችግር? እንዲያውም ጥሩ ነው እንጂ›› ይል ይሆናል። ነገሩ ግን ወዲህ ነው።
አንድ ሰው በማህበረሰቡ ውስጥ የሚሰጠው ክብር ይኖራል፤ ይህ ሁላችንም የምናውቀው ነው። እገሌ እኮ ጌታ ነው፣ ቤቱ ሙሉ ነው፣ ቤቱ ቢሄዱ የደላው ነው እየተባለ ጥሩ ስም ይሰጠዋል። ያ ሰውዬ ግን ሁሌም የተሟላለት ሊሆን አይችልም። የሚቸገርበት ጊዜም ይኖራል። ዳሩ ግን የቱንም ያህል ቢቸግረው ከቤቱ ቅቤ መጥፋት የለበትም። እንግዳ እንኳን ቢመጣ የመጣው ሰው በቅቤ ነው በልቶ መሄድ ያለበት። ስለዚህ ሰውዬው ቅቤ እየበላ ያለው ደልቶት ሳይሆን የስሙን ክብር ለማስጠበቅ ነው፤ ምናልባትም ሌላ ነገር ሊሰራ ያሰበበትን ገንዘብ ለዚህ ብቻ እያዋለው ይሆናል።
ለዚህ የሚቀራረብ ሌላ አባባል እንጥቀስ። ‹‹የሌለው በኮት ያርሳል›› ይባላል። በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ኮት የክት ልብስ ነው። ለሰርግ ወይም በሌላ ከሰው ጋር በሚደባለቁበት ጊዜ የሚለበስ ነው። ለግብርና ሥራ የሚሆነው ሌላ ቀልጠፍ ያለና ለጭቃውም ለአቧራውም ምቹ የሆነ ልብስ ነው። እንዲህ አይነት ልብስ በየዓይነቱ የሚኖረው ግን ያለው ነው። ኮት ለብቻ የሥራ ልብስ ለብቻ ነው መሆን ያለበት። ይህን ማድረግ ያልቻለ ግን ከሰው ጋር ሲቀላቀል የሚለብሰው አንድ ኮት ብቻ ሊኖረው ይችላል። ይሄ ሰውዬ አማራጭ ሲያጣ ኮት ለብሶ እርሻ ሊሄድ ይችላል ማለት ነው።
ምሳሌያዊ አነጋገሮችን ስንጠቀም በቀጥታ ለተባሉበት ሀሳብ ብቻ አይደለም፤ ለምሳሌ ‹‹የሌለው በኮት ያርሳል›› የሚለውን በኮት ለሚያርስ ሰው ብቻ አይደለም የምንጠቀመው፤ ማመሳሰያ ነው። ለምሳሌ ምሳ ሳንቋጥር ወይም ቆሎ ነገር እንኳን ሳንይዝ መንገድ ሄድን እንበል። ያለንበት አካባቢ ትልልቅ ሆቴሎች ብቻ ያሉበት ቢሆንና ርሃብ ደግሞ ቢጠነክርብን ከኪሳችን ያለችዋን ጨርሰንም ቢሆን ዋጋው ውድ የሆነ ቤት እንበላለን ማለት ነው። ከትልቅ ሆቴል ስንወጣ ያየን ሰው ‹‹እንዴት ቢደላህ ነው›› ብሎ ቢጠይቀን ‹‹የሌለው በኮት ያርሳል›› ልንል እንችላለን። ለቅንጦት ብለን ሳይሆን አማራጭ አጥተን ነው ያደረግነው ማለት ነው።
ምሳሌያዊ አነጋገርን በቀጥታ ብቻ መተርጎም የተሳሳተ ነው። ለዚህም ነው አንዳንድ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን ውግዘት እንዲደርስባቸው ያደረገው። ዶክተር ለማ ‹‹ሴት ከበዛ ጎመን ጠነዛ›› የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር እንደ ምሳሌ አንስተው ነበር። ‹‹ሴት ከበዛ ጎመን ጠነዛ›› የተባለው ለሴቶች ብቻ አይደለም። ወይም ጎመን በመክተፍና በቤት ውስጥ ሥራ ብቻ ለተወሰኑ ሴቶች አይደለም። በሽተኛ እየተጉላላ ሐኪሞች ተስብስበው እያወሩ ከሆነ ይህን አባባል መጠቀም ይቻላል። ብዙ ወንዶች ሥራ ትተው ተሰብስበው ሲያወሩ ከታየ ይህን አባባል መጠቀም ይቻላል። ‹‹ሴት ከበዛ ጎመን ጠነዛ›› የተባለው ሰዎች አንድ ላይ ከተሰባሰቡ ወሬ ብቻ እንጂ ሥራ እንደማይሰሩ ለመግለጽ ነው። ዋና ትርጉሙ ሴቶች ሥራ አይሰሩም አይደለም፤ ሰዎች ተሰብስበው ወሬ ብቻ ከሆነ ሥራው አይሰራም ለማለት ነው። አባባሉ የተቀረጸው ድሮ ሴቶች ብቻ የቤት ውስጥ ሥራ ይሰሩ በነበረበት ጊዜ ስለሆነ ነው።
ማንም ይሁን ማን ካልሰራ ሸንቆጥ ይደረጋል። ሴቶችም ቢሆን እኮ ካልሰሩ ሊነገራቸው ይገባል፤ በዚሁ መጠንም የአድናቆት ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉ። ‹‹መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት፣ ሴት የላከው ሞት አይፈራም፣ በሴት የበከረ(የጀመረ) ከእግዜር ተማከረ፣ በሴትና በውሃ የማይርስ የለም›› የሚሉ ምሳሌያዊ አነጋገሮች የሚያሳዩት የሴትን መልካምነት፣ የሴትን አሸናፊነት፣ መጀመሪያ ሴት ልጅ የወለደ ሁሉ ነገር ጥሩ እንደሚሆንለት፣ የሴት ምክር ተሰሚነት እንዳለው የሚያሳዩ ናቸው። ስለዚህ ሴቶችን ለመውቀስም ሆነ ለማመስገን እንደ አስፈላጊነቱ ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉን ማለት ነው። ምንም አይተቹ ማለት ደግሞ አይቻልም።
‹‹ሴቶችን አሳንሰው የሚያዩ ምሳሌያዊ አነጋገሮች›› በሚል ጥናቶች ይሰራሉ፣ እንዲህ አይነቶች ብቻ ይሰበሰባሉ። መሆን ያለበት ግን እንዲህ አልነበረም፤ ለምን ሴቶችን የሚያደንቁት አልተሰበሰቡም? ስለዚህ የጥናቱ ዓላማ ለማውገዝ ብቻ ነው ማለት ነው? እንደ አጠቃላይ በምሳሌያዊ አነጋገሮች ላይ ለትውልድ መሆን ያለበት ጥናት ሲሰራ አይስተዋልም። የቋንቋ ሀብታችን እንደመሆኑ መጠበቅ አለበት። ቋንቋችን ሲጠናም ቀደም እንዲህ ይባል እንደነበር መታወቅ አለበት። መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ይህን ማበረታታት አለባቸው።
የሚያሳዝነው ነገር ግን መገናኛ ብዙኃን እንኳን ይህን ሊያበረታቱ ጭራሽ የጥፋቱ አካል መሆናቸው ነው። አሁን መጽሔቶቹ ራሱ የሉም እንጂ ከዓመታት በፊት አንዳንድ መጽሔቶች ላይ ‹‹አራምባና ቆቦ›› የሚል ዓምድ ሁሉ ነበር። በዚህ ዓምድ ላይ አባባሎች እየተበላሹ የሚቀርቡበት ነው። ለምሳሌ ‹‹ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ›› የሚለውን አባባል ‹‹ላም አለኝ በሰማይ አውሮፕላን እንዳይገጭብኝ›› ብለው ያስቀምጣሉ። ይህን ያነበበ ልጅ እንዴት የሚረዳው ይመስላችኋል? ጥያቄና መልስ ላይ ቢጠየቅ እኮ ‹‹… አውሮፕላን እንዳይገጭብኝ›› ብሎ ነው የሚመልስ።
ብዙ የብሔርና የፖለቲካ መጻሕፍት እንደ አሸን ሲፈሉ በእንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ ግን የተጻፉ ብዙም አያጋጥመንም። ቋንቋችን ጉዳያችን አይደለም ማለት ነው? የቋንቋችን መጥፋትና መበረዝ አያሳስበንም ማለት ነው?
ምሳሌያዊ አነጋገሮችን በተመለከተ በአንዲት ደራሲ የተጻፈ አንድ መጽሐፍ ብቻ ነው የማውቅ፤ የኔ አለማወቅ ነው እንዳልል ደግሞ ብዙ ሰዎችን ጠይቄ የጠቆመኝ አላገኘሁም።
ምሳሌያዊ አነጋገር ‹‹የድሮ ነው›› ልንለው የሚገባ አይደለም። ዛሬም ልንጠቀመው ይገባል። ዛሬም እኮ በቋንቋ ነው እየተግባባን ያለነው። በቋንቋ እየተግባባን ደግሞ ምሳሌያዊ አነጋገር አንዱ የቋንቋ ውበት ነው። ስነ ጽሑፋዊ ለዛ ያለው ነው። ምሳሌያዊ አነጋገርም ይቀየር ይሻሻል የሚባል አይደለም። ለምሳሌ የምንግባባበት ቋንቋ የአማርኛ ቋንቋ ከሆነ ቋንቋውን ልንቀይረው ነው ወይስ እንዴት ሊሆን ነው? የአማርኛ ቋንቋ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን ከቀየርን ምኑን በዚያ ቋንቋ ተግባባነው?
ምሳሌያዊ አነጋገር የተለያየ መጠሪያ አለው። ተረትና ምሳሌ እየተባለ ይጠራል፣ አባባል እየተባለ ይጠራል። በጽሑፍ ደረጃ ያለው ስሙ ግን ‹‹ምሳሌያዊ አነጋገር›› የሚለው ነው። በእርግጥም ይህኛው ስም የተለመደ ነው። በዚያ ላይ ስያሜውም ምግባሩን የሚገልጽ ነው። ምክንያቱም ነገሮችን እያመሳሰልን የምንገልጽበት ስለሆነ ምሳሌያዊ አነጋገር የሚለው ትርጉም አለው።
ምሳሌያዊ አነጋገር በግጥም መልክ የሚባል አለ፣ በጥያቄና መልስ የሚባል አለ፣ በሐረግ መልክ አለ፣ በዓረፍተ ነገር መልክ አለ። ‹‹ሁለት ባላ ትከል፤ አንዱ ሲሰበር በአንዱ ተንጠልጠል›› የግጥም ባህሪ ያለው ነው። ‹‹መስጠትን የማያውቅ መቀበልን ማን አስተማረው?›› የሚባለው ደግሞ ለጥያቄያዊ ምሳሌ ይሆነናል። ‹‹ሲበሉ የላኩት›› ሐረግ ሲሆን ‹‹ሲሮጥ የመጣ አህያን አጥብቀህ ጫነው›› ዓረፍተ ነገር ነው።
እንዲህ የዳበረ እና የበለጸገ ቋንቋና ስነ ጽሑፍ እያለን መገናኛ ብዙኃኑ ግን ያን ያህልም ትኩረት አይሰጡትም። በማንነታችን እንኮራለን ስንል የራሳችን የሆኑ ነገሮችን በማወቅ ይሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ህዳር 8/2015