አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መስራችና የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ተደርጋ ብትቆጠርም የህብረቱን ሰንደቅ አላማ ከራሷ ሰንደቅ አላማ እኩል እንደማታውለበልብና ብሄራዊ መዝሙሯንም ከህብረቱ መዝሙር ጎን ለጎን እንደማታዘምር ተጠቆመ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል የአፍሪካ ህብረትን ሰንደቅ አላማ እና መዝሙር አዋጅ ለማስተዋወቅ ትናንት ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ እንደገለፁት፤ በሃምሳኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ አባል ሀገራት የህብረቱን ሰንደቅ አላማ እንዲያውለበልቡና መዝሙሩንም እንዲያዘምሩ በአዋጅ ደንግጓል፡፡
ይሁንና ከናሚቢያ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከማላዊ በስተቀር ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት የህብረቱን ሰንደቅ ዓላማ አያውለበልቡም፤ መዝሙሩንም አያዘምሩም፡፡ በተለይም ኢትዮጵያን የመሰሉና ለህብረቱ ምስረታ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ፤ ብሎም የህብረቱ ልዩ ልዩ ጽህፈት ቤቶች መቀመጫ የሆኑ አባል ሀገራት አርአያ የመሆን ድርብ ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም ይህን እየፈፀሙ አይደለም፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፃ፤ የህብረቱ ዋና መቀመጫና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ይህን መፈፀም አለመቻሏ ያስቆጫል፡፡ይሁንና አሁን በተያዘው አቅጣጫ መሰረት በኢትዮጵያ ድንጋጌውን ተግባራዊ ለማድረግ የህግ ማእቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ ህጉ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል እየታየ ይገኛል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታየ በኋላ ባለው አሰራር መሰረት በተያዘው ዓመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት የሀገሪቱ ህዝቦችና ተማሪዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ለዚህም የሀገሪቱን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያካተቱ የተለያዩ ስራዎች ይሰራሉ፡፡
በቀጣይም በአዳማ፣ በሃዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በባህርዳርና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች በመዘዋወር አዋጁን የማስተዋወቅና ዓላማውን የማስገንዘብ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011
በአስናቀ ፀጋዬ