የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ በሚቀጥሉት ስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደማምረት ይሸጋገራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
ኮርፖሬሽኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በላከው መግለጫ፤ በስኳር ኮርፖሬሽንና ካምስ (CAMC) በተባለ የቻይና ኩባንያ መካከል በተፈረመ ውል የፋብሪካውን ቀሪ ግንባታና ተያያዥ ስራዎች በ95 ሚሊዮን ዶላር ለማጠናቀቅ የሚያስችል ስራ ተጀምሯል።
መንግሥት ለተጀመሩ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ በቅርቡ ከፈቀደው ከአምስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ውስጥ አብላጫው ገንዘብ ላለፉት ስድስት ዓመታት ግንባታቸው በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሲከናወን ቆይቶ ላልተጠናቀቁት የጣና በለስ ቁጥር አንድ እና የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካዎች ማስፈፀሚያ እንደሚውልም በመግለጫው ተመላክቷል።
በሌላ በኩል የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካን በተመለከተም፣ ጄጄአይኢሲ (JJIEC) የተባለ የቻይና ኩባንያ ግንባታውን ለማካሄድ ያቀረባቸው የቴክኒክና የፋይናንስ ሰነዶች በስኳር ኮርፖሬሽን በመገምገም ላይ እንደሚገኙና የቀረቡት ሰነዶችም አዋጭ ሆነው ከተገኙ በኮርፖሬሽኑና በኩባንያው መካከል ውል ተገብቶ ኩባንያው ስራ እንዲጀምር እንደሚደረግም መግለጫው ይጠቁማል።
እንደመግለጫው፤ ላለፉት ስድስት ዓመታት ግንባታቸው በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሲከናወን ቆይቶ ያልተጠ ናቀቁት የጣና በለስ ቁጥር አንድ እና የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ አፈጻጸማቸው እንደቅደም ተከተላቸው 65 ነጥብ 79 በመቶ እና 80 በመቶ ላይ ደርሷል። ግንባታቸው ተጠናቅቆ በሙሉ አቅማቸው ማም ረት ሲጀምሩ እያንዳንዳቸው በቀን ከስምንት ሺህ እስከ 10 ሺህ ኩንታል ስኳር ያመርታሉ ተብሎ ይጠበቃል። በስራ ላይ የሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች ቁጥርም ወደ 10 ከፍ እንዲል ያደርጉታል።
የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ቀሪ ስራዎች የሚያካሂደው ካምስ (CAMC) ኩባንያ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካን በመገንባት ላይ ያለ ሲሆን፤ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ቀሪ የግንባታ ስራዎች ለማጠናቀቅ ፍላጎት ያሳየው ጄጄአይኢሲ (JJIEC) ኩባንያ ደግሞ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት የስኳር ፋብሪካ ግንባታ የስራ ተቋራጭ እንደሆነም መግለጫው ያሳያል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011
በበጋዜጣው ሪፖርተር