• የአካባቢው የጸጥታ ችግር በቁጥጥር ስር ውሏል
• ድርጊቱ የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች አጀንዳ አይደለም
አዲስ አበባ፡- ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ አካባቢ ተከስቶ የነበረው የሰላምና ጸጥታ ችግር በቁጥጥር ስር መዋሉን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ገለጸ። ድርጊቱም የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች አጀንዳ እንዳልሆነ አስታውቋል።
በአካባቢው የተፈጠረውም ሆነ ሌሎች በአገሪቱ የሚስተዋሉ ተመሳሳይ ችግሮች መንግስት የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ስራውን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት የሚያሳይ እንደሆነም ተጠቁሟል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተና ገሩት፤ ደብረ ብርሃንን ጨምሮ በሙሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሙን ጠብቆ የኖረና የሰላም
አምባሳደር የሚባል ሰላም ወዳድ አካባቢ ነው። ይሁን እንጂ ባለፉት ሶስትና አራት ቀናት አጣዬ ላይ በተካሄደበት ወረራ ሰላሙ ተናግቷል። በተደራጀ፣ በታጠቀና በቂ ስልጠና በወሰደ ሀይል በተፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊትም በሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይም ከባድ ጉዳትም ደርሷል። ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ የጸጥታ ችግሩን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር በመቻሉ አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴው ገብቷል።
እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ፤ በቂ የመከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ በቦታው ገብቷል። የተደራጀና የታጠቀው ሃይል ውጊያ የከፈተባቸው አካባቢዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል። ህብረተሰቡን የማረጋጋት ስራም እየተከናወነ ይገኛል። በአካባቢው የተፈጠረው ችግርም የአማራም ሆነ የኦሮሞ ህዝብ አጀንዳ ሳይሆን፤ የሁለቱን ህዝቦች አንድነትና ፍቅር የማይፈልጉ አካላት ተልዕኮ መሆኑንም መገንዘብ ይገባል። ምክንያቱም የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ቀድሞም አብረው ሲኖሩ የነበሩ፤ አሁንም አብረው እየኖሩ ያሉና ወደፊትም አብረው የሚኖሩ ናቸው። ይሄን አይነት ከሰብዓዊነት የወጣ እንስሳዊ ድርጊት ከሁለቱ ህዝቦች የመነጨ አይደለም።
የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ በየቀኑ አዳዲስ ነገር እየተገኘ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተፈራ፤ የሚመለከተው አካል አካባቢውን ተቆጣጥሮ የማሰስና የማጥራት ተግባር እያከናወነ እንደመሆኑ በቀጣይ ሙሉ መረጃው የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁን ባለው መረጃ ግን የ27 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ በ27 ሰዎች ላይም የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት መድረሱንና በርካታ ንብረትም መውደሙን አብራርተዋል። ይሄን ችግር የፈጠረው ቡድንም በአግባቡ የተደራጀ፣ የደንብ ልብስ ያለው፣ ዓርማ የያዘ፣ የሰለጠነና ከግለሰብ እስከ ቡድን መሳሪያ የታጠቀ መሆኑን በመጠቆም፤ ትክክለኛ ማንነቱን በተመለከተ ግን አሁን ላይ ህዝቡን የሚያወናብድ መረጃ ከመስጠት ይልቅም ጉዳዩን የሚመለከተው የፌዴራልና የክልል አካላት የጋራ ኮሚቴ በሚያደረገው ማጣራት ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
አሁን ላይ የተከሰተውም ሆነ እስካሁን ሲከሰት የነበረው ችግር መንግስት ለህዝቦች ደህንነት ተገቢውን ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባው አመላካች መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ እስኪሆኑ ከመጠበቅና መድረስ የሚገባው አካል ቶሎ መድረስ ቢችል ኖሮ በአካባቢው ይሄን ያክል አደጋ ሊደርስ እንደማይችል ያስረዳሉ። አሁንም ህዝቡ በድርጊቱ በቁጣና ብስጭት ውስጥ መሆኑን በመጠቆምም፤ በቀጣይ መንግስት የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ስራውን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአካባቢው በደረሰ ጉዳት የተፈናቀሉና የተጎዱ ወገኖችን ከመደገፍ አኳያም ደብረ ብርሃንን ጨምሮ ሰፊ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እየተከናወነ መሆኑን በመጠቆምም፤ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ተጎጂዎችን የማቋቋም ስራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል። ህብረተሰቡም የሁለቱ ህዝቦች አንድነት ቀጣይነት እንዳለውና የጥፋት ቡድኖች ችግር ፈጥረው የሚያልፉ መሆናቸውን ተገንዝቦ ሰላምና አንድነቱን እንዲያስጠብቅ፤ መንግስትም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ በአጥፊ ቡድኑ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
የዞኑ አስተዳደር በደረሰው ሕይወትና አካል ጉዳትም የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፤ ለተጎጂ ቤተሰብም መጽናናትን ተመኝቷል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011
በወንድወሰን ሽመልስ