ባለቤቴ የጉሙዝ ተወላጅ ነው። እኔ ደግሞ የኦሮሞ ተወላጅ፤ ሁለታችንም የብሄር ጉዳይ በመካከላችን ሳይኖር በትዳር ልጆች አፍርተን አብረን እንኖራለን። እኔን ከባለቤቴ ማነው የሚለየኝ፤ በማለት ሃሳባቸውን የሰጡት ወይዘሮ ድርቤ ጉማ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ይኖራሉ።
በጋብቻ፣ በጉርብትና እና በአካባቢ በማህበራዊ ኢኮኖሚ ተሳትፎ በቆየው የቤንሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሞ ተወላጆች መካከል ይህ ነው የሚባል ችግር እንዳላዩ የሚናገሩት ወይዘሮ ድርቤ፤ በቅርቡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተከሰተው ችግር እንግዳ ሆኖባቸዋል።
ኦሮሞ ሰንጋ ጥሎና ጠምቆ ከጎረቤቱ እና ከአካባቢው ጋር የሚበላ ጥሩ ባህል ያለው፤ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝብም ያለውን አካፍሎ አብሮ የሚኖር መሆኑን ምስክርነት ሰጥተዋል። በሁለቱ ህዝቦች መካከል ጣልቃ የገባውን መንግስት ለይቶ በማውጣት የህዝቡን አብሮ የመኖርና መተሳሰብ መመለስ እንዳለበት ጠይቀዋል። በተለይም ተሳስበው የሚኖሩትን ህዝቦች ለመለያየት
በማህበራዊ ድረገጽ የሚሰሩትን መታገል መንግስት ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ትናንት ለአንድ ቀን በተካሄደው የቤንሻንጉል ጉሙዝ እና የኦሮሚያ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ የጋራ መድረክ ላይ የአሶሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አልሄደር መሀመድም፤ ኦሮሞና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ተጋብተው ያፈሩት ልጅ ለሁለቱም ዳኛ ነው ይላሉ። ሁለቱ ህዝቦች የተሳሰሩ በመሆናቸው አንዱ የሌላውን ጉዳት አይፈልግም። ይልቁንም ትውልዱን ከገባበት ደባል ሱስ በማላቀቅ፤ በመልካም ስነ ምግባር በማነጽና ተተኪ መሪ በመፍጠር ላይ የሁለቱ ክልል አመራሮች እንዲረባረቡ ጠይቀዋል። የሃይማኖት አባቶችና ወላጆች የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ከምስራቅ ወለጋ ሳሲጋ ወረዳ በሬዱ ቦሎ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የተሳተፉት አርሶ አደር መልካሙ አበበ፤ በተፈጠረው ችግር አርሰው በሚበሉትና ከሞቀ መሬታቸው ለወራት ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂ መሆናቸው እንዳሳዘናቸው ይገልጻሉ። እርሳቸውም እንደሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ሁሉ በህዝቦች መካከል ችግር እንዳላዩ ይናገራሉ። በዕድሜያቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ካዩት የህዝቦች መፈናቀል፣ ሞትና የተለያየ ጉዳት ማዘናቸውን ያስረዳሉ።
በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል በተፈጠረ ዕርቅ ወደ ቀዬአቸው ሰሞኑን ከተመለሱት መካከል መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ መልካሙ፤ የቀሩትም ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ መንግስት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች ለተነሱት አስተያየቶችና ለቀረቡ ጥያቄዎች አስተያየት የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፤ ባለፉት ስድስትና ሰባት ወራት በሁለቱ ክልሎች በተፈጠረው ችግር ህዝብ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ፣ በመካከላቸው የንግድ ልውውጥ እንዳይኖር፣ እንዲሁም ለጤና እና ለማህበራዊ ችግሮች ከመጋለጥ በስተቀር ትርፍ አልተገኘም።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገና ያልተነካ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ የሚበቃ ሀብት እያለው አንዳንድ ወገኖች በተለያየ ነገር ጠብ መፍጠርና ለጉዳት መዳረግ አሳፋሪ ድርጊት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ህዝቡም ይህንን ተገንዝቦ ለልማት እና ለእድገት መነሳሳት እንዳለበት አሳስበዋል።
እንደ አቶ ለማ ገለጻ፤ ህዝቡ አንድ እንደሆነ በመድረክ የሚሰጠው አስተያየት በንግግር መቅረት የለበትም። መንግስት ትልቁን ድርሻ ይዞ በልማት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባዋል። ሁሉም ድርሻውን የመወጣት ኃላፊነትም አለበት። የኦሮሚያ ክልል በሁለቱ ህዝቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍን የተጀመረውን ጥረት በማጠናከር አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ በኩል ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል። በተለይም በልማት በመደጋገፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።
ባለፈው ዓመት ስራ የጀመረው የኦሮሚያና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሰላምና የልማት ስትራቴጂ ዕቅድ የዚሁ አካል መሆኑን አመልክተዋል። ከ2011 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው ፕሮጀክት ሰፊ ተግባሮችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሌ ሀሰን በበኩላቸው፤ የጉባኤው ተሳታፊዎች በሁለቱ ክልል ህዝቦች አምባሳደር በመሆን ለሰላም እንዲሰሩ አሳስበዋል። ክልሉ ለሁለቱ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን በክልሉ ለሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦችም በሰላምና በፍቅር የሚኖሩበት ክልል እንዲሆን ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፤ በክልሎች መካከል የተጀመረው የጎንዮሽ ግንኙነትና በልማት ለመተሳሰር እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ይገልጻሉ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው እንደሚቆም ቃል ገብተዋል። ተሞክሮው ተቀምሮ ለሌሎቹ እንደሚስፋፋም ተናግረዋል።
በክልሉ ሰላም፣ ልማትና በህዝቦች መካከል የቆየው አብሮነት እንዲጠናከር ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ ለፌዴራልና ክልል መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፤ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011
በ ለምለም መንግስቱ