አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በ2012 መጀመሪያ ወራት ሳተላይቷን ወደ ኅዋ እንደምትልክ ተገለጸ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሩያ እንዳሉት የሳተላይት ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ ኢትዮጵያ በ2012 መጀመሪያ ወራት የራሷን ሳተለይት ወደ ህዋ ታመጥቃለች።
ሚኒስትሩ ዛሬ ሚያዚያ 1 ቀን 2011 ዓም የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን የአንድ ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከቻይና ስፔስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር እየገነባ ያለው ሳተላይት በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ በቀጣዩ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ወራት ኢትዮጵያ የራሷን ሳተላይት ወደ ኅዋ እንደምታመጥቅ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት ሳተላይቷ ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለአከባቢ ጥበቃ፣ ለማዕድን ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ ክትትል አገልግሎት የሚውል መረጃዎችን የምታሰባሰብ ናት። ሳተላይቷ 71ኪሎ ግራም የምትመዝን ስትሆን አስር ዓመታትን በኅዋ ላይ የመቆየት አቅም እንደሚኖራትም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ በራሱ አቅም ሳተላይቶችን መገንባት የሚያስችለው የሳተላይት ፋብሪካ፣ መገጣጠሚያና መፈተሻ ማዕከል ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ ተጨማሪ የሳተላይት መረጃ መቀበያ መሠረተ ልማትም በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አዲሱ ገረመው