
አዳማ፡– የህብረት ሥራ ማህበራት በወቅቱ ኦዲት አለመደረጋቸው ማህበራቱን ለችግር እየዳረገ መሆኑ ተገለጸ።
የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ በአዳማ ከተማ የበጀት ዓመቱን የስምንት ወራት አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት እንደተገለጸው የማህበራቱ በወቅቱ ኦዲት አለመደረግ የማህበራቱን እንቅስቃሴ ከማዳከም ባለፈ ለሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በር ከፍቷል።
በኤጀንሲው የኦዲት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳሪቡ ቡሴር እንደተናገሩት፣ አንድ የህብረት ሥራ ማህበር በዓመት አንድ ጊዜ ኦዲት መደረግ ያለበት ቢሆንም አምስት ዓመት ድረስ ያልተደረጉ በርካታ ማህበራት አሉ። ይህም በመሆኑ ማህበራቱ ገቢና ወጪያቸውን እንዲሁም ትርፋቸውን ለማወቅ ስለማይችሉ ለትርፍ ክፍፍልና ከባንኮች ብድር ለማግኘት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል።
በተጨማሪም የኦዲት ክፍተት በማህበራቱ ላይ እምነት ስለሚያሳጣ የአባላትን ቁጥር ለማሳደግ የሚሠሩ ሥራዎችን እየገደበ ይገኛል። የቆዩ ሰነዶችን ኦዲት ማድረግ ያስቸግራል ያሉት ዳይሬክተሩ ማህበራቱ በወቅቱ ኦዲት ባለመደረጋቸው ለሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በር እንደሚከፍትም ተናግረዋል።
በማህበራቱ የሚቀጠሩ የሂሳብ ባለሙያዎች የሚያገኙት ክፍያ ዝቅተኛ በመሆኑ ኦዲተሮች ልምድ ለመያዝ ብቻ ገብተው ይለቃሉ ያሉት ዳይሬ ክተሩ፣ይህንንም ለመቅረፍ ለኦዲት ሠራተኞች ጥቅማ ጥቅምና ደመወዝ እንዲስተካከል እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአንዳንድ ማህበራት የሚሠሩ ባለሙያዎችም የክህሎት ክፍተት እንዳለባቸው በመጠቆም ስልጠና ለመስጠትና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን ለመቃኝት ከዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎችና ከሞያ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር ለመሥራት በዝግጅት ላይ መሆመናቸውን ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል የህብረት ሥራ ኤጀንሲ የልማት፤ እቅድና ክትትል ዳይሬክተር አቶ መብራህቶም እምባየ በበኩላቸው፣ የኦዲት በወቅቱ አለመደረግ ለኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና በር እየከፈተ እንደሆነ ይናገራሉ። ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት በተደረገ ቁጥጥር በወቅቱ ኦዲት ባለመደረጉ በተለያዩ ጊዜያት 20 ሚሊየን ብር መጥፋቱ ታውቋል። የማጣራት ሥራ እየተሠራ ቢሆንም መዝገቦቹ የቆዩ በመሆናቸው ክፍተቱ ያለበትን ለመለየት አስቸጋሪ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በክልሉ 120 ኦዲተር የሚያስፈለግ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ያሉት 73 ብቻ መሆናቸውን በመጠቆም ፣ በዚህም የተነሳ ማህበራቱ የብድር አገልግሎትም ሆነ ሌሎች አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ መቸገራቸውን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሺፈራው በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኦዲት ሊደረግ ከታሰበው 51 በመቶ ብቻ መከናወኑን በማስታወስ ማህበራቱ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል። የኦዲት ሥራ ለማህበራቱ ዋስትና ነው ያሉት ኃላፊው፣ እንደ ክልል እያንዳንዱን ማህበራት የሚመለከት ውሳኔ ለማስተላለፍ መቸገራቸውን ጠቁመዋል።
ችግሩ ለዓመታት የዘለቀ እንደሆነ በመግለት በቂ ነው ባይባልም ከዓመት ዓመት መሻሻሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። በየዓመቱ በርካታ ተቀጣሪዎች ቢኖሩም ቶሎ እንደሚለቁ በመጠቆም ችግሩ ሀገራዊ በመሆኑ ከፌዴራል ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመሆን ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም ኃላፊው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ