የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ዳዊት አንዳር ጋቸው ባዮ ሜዲካል ኢንጀነር ሲሆኑ፣ የባህርዳር ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ውስጥ ማሽኖቹን የመቆጣጠርና ለትግበራ እንዲውሉ በተጨማሪም ሥርጭቶቹን የመምራት ሥራዎችን ሠልጥነዋል።
‹‹ማዕከሉ ገና መጀመሩ ነው፤ ሆስፒታል ላይ ለሁለት ዓመት ያህል ሠርቻለሁ›› የሚሉት አቶ ዳዊት፣ ‹‹ወደ ህክምና ኦክስጅን ማምረቻ እና ማከፋፈያ ማዕከል ሥራ ላይ ከገባን ሦስት ወር ሆኖናል፤ ከኔ ጋር 17 ሠልጣኞች ማሽኖቹን እንዲቆጣጠሩ፣ እንዲተገበሩና ችግሮች ካሉም እንዲጠግኑ የሚያስችል ሥራ ሠልጥነዋል።›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ያሰለጠኗቸው የአማራ ክልል ጤና ቢሮና አሲስት ኢንተርናሽናል ሲሆኑ፣ ሌሎችም ድርጅቶች ተባረዋል፡፡ እርሳው የሚሠሩት የደሴ ሳይት ላይ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ደግሞ እየሠሩ የሚገኙት ገና ወደ ሥራ ከገባ ትንሽ ጊዜ ባስቆጠረው ማዕከል ውስጥ ነው፡፡
አቶ ዳዊት፣ሥራቸውን በተመለከተ ሲናገሩ ‹‹በዋናነትም በጄኔራል ኤሌክትሪክ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ማሽኑን በማምጣት ለኛ ሥልጠና በየሩብ ዓመቱ በመስጠት ጥገና የሚያስፈልጋቸው ማሽኖች ካሉ ማየትና ችግሩን መፍታት እንዲሁም መቆጣጠር ነው።›› በማለት ይገልፃሉ፡፡
አቶ ይበልጣል ዓይናለም በባህር ዳር ህክምና ኦክስጂን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል ይሠራሉ። ‹‹ወደ ማዕከሉ ከገባሁ ሦስት ወር ሆኖኛል›› የሚሉት አቶ ይበልጣል፣ ‹‹ባህር ዳርና ደሴ በሚገኘው ኦክስጅን ማዕከል ሥልጠና እንሰጣለን ተብሎ ጥሪ ተደረገልን። በዚያ መሰረት ስልጠናውን ከወሰድን በኋላ ጤና ቢሮ ለሁለት ሳምንት አስተምሮ ውድድር አካሂዶ አዘዋወረን፡፡ የእኛ ሥራ እያንዳንዱ ማሽን እንዲሠራ ማድረግ ነው። በሰለጠነው መሰረት ጥገና ማድረግ ነው።
ወደፊት ደግሞ ለሆስፒታሎች በተጓዳኝ ወርክሾፕ ላይ ግንዛቤ ለመስጠት ትሠራላችሁ ብለውናል›› በማለት አብራርተዋል፡፡ አክለውም፤ ‹‹አሁን ማሽኑ ላይ እየሠራን ያለነው በቀን 12 ሰዓት ነው፤ ወደፊት 24 ሰዓት ይሠራል ተብሎ መታሰቡን ነግረውናል›› በለዋል።
‹‹ህክምና ላይ ስለቆየሁ ችግሩን በደንብ አውቀዋለሁ›› የሚሉት የባዮ ሜዲካል ኢንጅነሩ አቶ ይበልጣል፣ ማዕከሉ ለሞት የተጋለጡና ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎችን ችግር እንደሚቀርፍ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ህሙማኑ ለተጨማሪ ህክምና ‹ሪፈር› ተብለው ባህርዳር ሲላኩ ኦክስጅን ላይኖር ይችላል፡፡ ችግሩን ስለማቀው በተቻለ መጠን ኦክስጅን በማምረት የህመምተኛውን ችግር እንፈታለን ብዬ አስባለሁ›› ሲሉ ሕይወትን ለመታደግ ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል የህክምና ኦክስጅን ማምረቻ እና ማከፋፈያ ማዕከል በባህር ዳር ከተማ ሰሞኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መርቀው የከፈቱ ሲሆኑ፣ የተመረቀውን ጨምሮ በክልሉ ሁለት የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከላት መኖራቸው ይታወቃል፡፡ አንደኛው በደሴ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ነው፡፡
የባህርዳር ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ትብብር 3 ሚሊዮን ዶላር የተቋቋመው ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ የክልሉ ጤና ቢሮ 10 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል። የህክምና ኦክስጅን ማዕከሉን በፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ተገኝተው የመረቁት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ የታካሚ ዜጎችን ሞት ለመታደግ የሚያስችል ለክልሉ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮዽያውያን ሁሉ ኩራት የሆነ ነው። የኦክስጅን ማምረቻ እና ማከፋፈያ ማዕከሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሞት የሚቀንስ በተለይ ደግሞ በኦክስጅን እጥረት ተጨማሪ ዕድሜ መኖር ለሚችሉ የተሻለ ዕድል ነው፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
የኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል የባህር ዳሩን ጨምሮ በደሴ ከተማ ያለውም ተመሳሳይ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። የአማራ ክልል ኦክስጅን ማዕከል የተገነባው በጄኔራል ኤሌክትሪክ ፋውንዴሽን፣ በግራንድ ቻሌንጅስ ካናዳ፣ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ እንዲሁም በፈለገ ሕይወትና ደሴ ሪፈራል ሆስፒታሎች አስተዋፅዖ ከፍተኛ ድጋፍ ነው።
በኢትዮጵያ በህክምና ቦታዎች የተሟላ የኦክስጅን አቅርቦት ካለ ይሞታሉ ተብሎ የሚገመተውን ህይወት የሚታደግ እንደሆነ ፕሬዚዳንቷ ጠቅሰው፤ በዚህም ምክንያት በወሊድ እና በእርግዝና ምክንያት 11 ሺ ሴቶችን፣ በተወለዱ በአንድ ወራቸው 60 ሺ ሕፃናትን ማዳን እንደሚቻል ፕሬዚዳንት አስረድተዋል፡፡ የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር በዘርፉ እየሠራ ያለው የሚያበረታታ ተግባር መሆኑንና ከዚህም መካከል የብሔራዊ የህክምና ኦክስጅን ፍኖተ ካርታ አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚን አማን፣ በሆስፒታሎች ለታካሚዎች የሚያስፈልግ የኦክስጅን አቅርቦት ችግር ለመፍታት እስከ 2017 ዓ.ም በሀገሪቱ 13 የኦክስጅን ማዕከል ለመክፈት መታሰቡን አስታውቀዋል። ሚኒስትሩ፣ የባህር ዳሩ ስድስተኛው መሆኑን ገልጸዋል።
የጄኔራል ኤሌክትሪክ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዴቪድ ባራሽ፣ የአማራ ክልል ኦክስጅን ማዕከል መመረቅ ብዙ ድርጅቶች ላለፉት ሦስት ዓመታት በትብብር ሲያደርጉ የነበረው ሥራና ጥረት መደምደሚያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረት ታላቅ ስኬት ከመሆኑም ባሻገር የተለያዩ አጋሮች በመተባበር ቢሠሩ ሊያሳኩት የሚችሉትን ውጤት ማሳያ ምሳሌ ነው በሚልም ማዕከሉን ገልጸውታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በ ኃይለማርያም ወንድሙ