ወረዳው አድአ በርጋ ስፍራው ደግሞ ሞጎር በመባል ይታወቃል፡፡ በቦታው ስንድርስ የጠበቅነው ነገር ቢኖር ወደላይ እየተንቦለቦለ እና እየተጥመለመለ የሚወጣ ጥቁርም ነጭም ጢስ ነበር፡፡ ይሁንና በ137 ሄክታር መሬት ላይ ደልቀቅ ብሎ የተቀመጠው ትልቅ ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ስንገባ ግን እንኳን ጪስና አቧራ የሚስተዋልበት እንዲሁም የተለያዩ የድንጋይ ዓይነቶችን የሚፈጩ ትልልቅ ማሽኖች ያለበት ሊመስል ቀርቶ የአየር ብክለት የሌለበት አረንጓዴ አካባቢ ነው ማየት የቻልነው – በዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ፡፡
በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ 13 አገሮች ላይ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት የሚታወቅ ሲሆን፣ ዋና መስሪያ ቤቱ የሚገኘው በናይጄሪያ ሌጎስ መሆኑን በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ካንትሪ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዳኒሎ ሲ.ትራጊሎ ይናገራሉ፡፡ ዘርፈ ብዙ ቢዝነስ ላይ የተሰማራው ይህ ኩባንያ በዋናነት ሲሚንቶ፣ ሩዝ፣ ስኳር፣ ማዳበሪያና የመሳሰሉት ላይ እንደተሰማራ ነው የሚያስረዱት፡፡
ሚስተር ዳኒሎ እንደሚሉት፤ ሲሚኒቶን በተመለከተ በዓመት እስከ 46 ሚሊዮን ቶን የሚያመርቱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ የማምረት አቅማቸው እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቻቸው እነ መሰቦ፣ ደርባና የመሳሰሉት ሲሆኑ፣ እነሱም የሚያመርቱት አነስተኛ ነው፤ ዳንጎቴ ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን ወደማምረት ተጠግቷል፡፡ በቀጣይ ደግሞ ከዚህ በተሻለ ለማምረት ይሠራል፡፡
ሚስተር ዳኒሎ፣ ‹‹ከምንም በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ሠራተኛው ደህንነቱ ተጠብቆ ጤናማ የሆነ ስፍራ ላይ መሥራት እንዲችል ማድረግን ነው፡፡ የአየር ብክለት እንዳይከሰትም ፋብሪካው ከፍተኛ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ነው የሚያመርተው።
በመሆኑም ለአየር ንብረት ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ በተለይ ደግሞ ሠራተኞቻችን ሲሠሩ ጤነኞችና ደስተኞች እንዲሆኑ ቁልፉ መርሐችን ነው ይላሉ፡፡
አክለውም እንደተናገሩት፤ በኩባንያው የሚሠሩ ሠራተኞች ቁጥር 1 ሺ 822 ሲሆኑ፣ የእነዚህ ሠራተኞች ጥቅማ ጥቅም በአግባቡ የሚተገበር ነው፡፡ በተለይ የህክምና ወጪያቸው የሚሸፈን ሲሆን፣ለህክምና ወደ አዲስ አበባ በሚያቀኑበትም ወቅት የውሎ አበል የሚታሰብላቸው ይሆናል። ሠራተኛው የሚያስፈልገውን ጥቅማ ጥቅም የማሟላቱ ምስጢርም ሠራተኞቹ ለፋብሪካው አምባሳደሮች በመሆናቸውም ጭምር ነው፡፡
በፋብሪካው የሠራተኛ ጥቅማ ጥቅም ክፍል ኃላፊ አቶ መገርሳ ኢሬጋ በበኩላቸው፤ የሠራተኞችን ጥቅም የማስከበሩ ሂደት በህብረት ስምምነት የተወሰነ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ኩባንያው የተቋቋመበት ዓላማ ከግብ መድረስ የሚችለው ስርዓት ባለው ሁኔታ ሲመራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ደግሞ ግልጽ የሆነ የአሠሪና የሠራተኛ ግንኙነት ሲኖር እንደሆነም ያመለክታሉ፡፡
ፋብሪካው ለሠራተኞች ካመቻቸው ጥቅም መካከል ሠራተኛው ጋብቻ፣ ልጅ መዳር፣ ልደት፣ ህመም እንዲሁም ሞት በሚያጋጥመው ጊዜ አስፈላጊውና በህብረት ስምምነቱ መሰረት ተገቢው ጥቅማጥቅም እንደሚሰጠው አቶ መገርሳ ያስረዳሉ፡ ፡
‹‹ለአብነትም አንድ ቋሚ ሠራተኛ ጋብቻ ሲፈፅም ለአንድ ጊዜ ለሚቀርበው ህጋዊ የጋብቻ ሰነድ መሰረት 8 ሺ ብር ይከፈለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ልጁን ሲድርም 2 ሺ 500 ብር ‹‹እንኳን ደስ አለህ›› በማለት የሚሰጠው ይሆናል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ ከነመመዝገቢያው በሚያቀርበው ህጋዊ ደረሰኝ መሰረት በዓመት 3 ሺ ብር ድርጅቱ ድጋፍ የሚያደርግ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በፋብሪካው የጥራት ቁጥጥር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አባተ ዓሊ እንደሚናገሩት፤ ፋብሪካው የጥራት የጀርባ አጥንት በሆነው የሮሆቦቲክ ላቦራቶሪ በመታገዝ ጥራት ያለው ምርት በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ ከጥሬ ዕቃ ጀምሮ ምርቱ ተጭኖ እስከሚወጣ ድረስ የጥራት ፍተሻው በዚሁ ላቦራቶሪ የሚታገዝ ሲሆን፣ ስህተትንም በማስቀረት ትልቁን ድርሻ የሚጫወት ነው፡፡
በፋብሪካው ጥራትን በሚመለከት በዋናነት እየሠሩ ያሉት ቻይናውያን ቢሆኑም፤ በአሁኑ ሰዓት ግን የቴክኖሎጂ ዕውቀቱን እንዲያገኙ በማሰብ ኢትዮጵያውያኑን ከቻይናውያኑ ጋር በመቀናጀት እንዲሠሩም በመደረግ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይ ደግሞ ይህን የጥራት ቁጥጥሩን በሚገባ ተረድተው ቦታውን ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን ለማስያዝ ታስቦ ኢትዮጵያውያን ወደ ናይጄሪያ ለስልጠና መላካቸውን ጠቅሰዋል። ኩባንያው ሠራተኛውን ለማብቃት የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን የዘረጋ ሲሆን ጥቅማጥቅምን በተመለከተ ደግሞ እርሳቸውም የዕድሉ ተቋዳሽ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
እዛው ሞጎር አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት ከተማ ኤጀርሳ በበኩሉ በፋብሪካው የጥራት ቁጥጥር ኦፕሬተር በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከአንድ ቻይናዊ ጋር በመሆን የጥራት ቁጥጥሩ እየሠራ በመሆኑ ዕውቀት እያገኘ እንደሆነ ያብራራል፡፡ በቀጣይም ቻይናውያኑን የመተካት ዓላማ እንዳላቸው ተናግሮ በፋብሪካው የሠራተኞች ጥቅማ ጥቅም በአግባቡ እየተተገበረ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡ ፋብሪካው የሠራተኞችን መብት በማስከበሩም ረገድ ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለበት ተናግሯል፡፡
ዳንጎቴ፣ በኢትዮጵያ ፋብሪካውን ገን ብቶ ወደ ሥራ ሲገባ ከመንግሥት አንዳች ብድር ሳይወስድ ሲሆን፣ 600 ሚሊዮን ዶላር የፈጀበትን ሙሉ ወጪ ራሱ ሸፍኖ ኩባንያውን ማቋቋም መቻሉ ታውቋል፡፡ ኩባንያው ወደፊት ብዙ እቅዶችን የያዘ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ቀደም ሲል ምርቱን እየላከ ካለው እንደ ኬንያና ሌሎች አገሮች በተጨማሪ በቀጣዩ ዓመት ወደ አሥመራና ሌሎች የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ምርቱን የሚልክ መሆኑም ታውቋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በአስቴር ኤልያስ